>
1:20 pm - Thursday December 8, 2022

ሃኪሞቻችንም ተረጋጉ ፤ አቢቹም መፍትሄ ስጣቸው!!!  (ዘመድኩን በቀለ)

ሃኪሞቻችንም ተረጋጉ ፤ አቢቹም መፍትሄ ስጣቸው!!! 

ዘመድኩን በቀለ

★ አቢቹ ሆይ ግድ የለም ሃኪሞቹን አድምጣቸው። ሃኪሞቹ ዐማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ ወዘተም አይደሉም። ቅንጅትም፣ ቅንብቢትም አይደሉም። ቦለጢቃውን ጥዩፍ ናቸው። እናም ግድየለህም ጮጋ ብለህ ስማቸው።
★ መምህራንም አኩርፈዋልና ኩርፊያው ወደ ተማሪዎች ሳይሻገር አቅም የፈቀደ መፍትሄህም በቶሎ ስጣቸው።
* እናንት ደግሞ በማያገባችሁ እየገባችሁ ነገር የምታጋቡ እወደድ ባይ ተካ ካድሬዎችም አድበ። በሃኪሞቹ ማኩረፍ አቢቹም ሆነ ተካ ካድሬው አይጎዳም። ተጎጂው ያው መከረኛ ምስኪን ህዝብ ነውና ተካዎች ሆይ ቤንዚን አታርከፍክፉ።
★ እኔ ሃኪም አደለሁም። ችግራቸው ግን ይሰማኛል። ከአቅም በላይ ለማሠራትም ቢሆን እኮ እያባበሉና እየሸነገሉ እንጂ እንደ ባርያ እየሰደቡዋቸውና እየደበደቧቸው መሆን የለበትም። ይሄንን አጥብቄ እቃወማለሁ። መሃይምና ፍልጥ ጥርብ ካድሬ ተዘፍዝፎ በሀብት ቁንጣን እየተሰቃየ በሚኖርባት ኢትዮጵያ ሃኪሞችን ክብራቸውን እየነኩ ከሙያው ማራቅ ይሄ ሌላ ክፉ ሴራ ነው። የተደበቀ ክፉ ሴራ።
• ለእኔ ጠሚዶኮ ዐቢይ ዐህመድ በቅርቡ ኢትዮጵያውያን የህክምና ባለሙያዎችን ባነጋገሩ ጊዜ ልክ ኦቦይ ስብሃት ነጋን መስለው ነው የታዩኝ። የዛሬው ጦማሬ ገፊ ምክንያትም ይኸው ነው። ጠቅላዩ በሃኪሞቹ ጥያቄ ለምን ተበሳጩ? ለምንስ ተቆጡ? ክብረ ነክ ቃላትንስ ለምን ተጠቀሙ? በራሴ ገጽ የራሴን ሃሳብ እሰጣለሁ።
•••
ጠሚዶኮ ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ኮርቻው ላይ  ከተፈናጠጡ በኋላ  ሽምጥ እየጋለቡ በየክልሉ በመሄድ ዜጎችን ሰብስበው ማነጋገራቸው፣ ማወያየታቸው ይታወሳል። አሁን ቃል በቃል ባላስታውስም በወቅቱ ትግራይን ሞተር፣  ዐማራን የሆነ ነገር፣ ኦሮሞንም እንዲሁ፣ ሶማሌና አፋርን፣ ጋምቤላን፣ ደቡብን፣ ቤኒሻንጉልን ዞሮው የየሃገሩን የሰላምታ ቃል አጥንተው መልሰው በማቅረብ ህዝቡን ጮቤ አስረግጠዋል። በዚያ ጉዞአቸው ጉራጌን ብቻ ነበር ለእናንተ ክልል አያስፈልጋችሁም። ገና መቋድሾ ሄዳችሁ ትሠራላችሁ ብለው ክልል አልባ መሆናቸውን በይፋ ያረዱአቸው።
•••
ከሙያ ማኅበራት ጋርም ተነጋግረዋል፣ ተመካክረዋል፣ ሥልጠናም ሰጥተዋል፣ የተለመደውን ምርጥ ምርጥ ፎቶም ከአርቲስቶቻችን ጋር ተቃቅፈው ተነስተዋል። በዚህም የተነሳ አርቲስቱ በድራማና በቲያትር መሃል ስማቸውን እያስገባ ከፍ አድርጎ አንስቷቸዋል። ምንም እንኳን በወቅቱ ሃጫሉ ቢያኮርፍ አስቴር በዳኔም ድፍረት ድፍረት ተጫውታ ለማስቀየም ብትሞክርም የተቀረው ግን ደስብሎት ውሎ ደስ ብሎት አድሯል። አዝማሪውም መሲህ አድርጎ ግጥምና ዜማ አዘጋጅቶ አወድሷቸዋል። እሳቸውም አርቲስቲን በፀባይ ነው የያዙት፤ ምሳ አብልተውም የሸኙትም።
•••
ጠሚዶኮ ፖሊሶችን፣ ወታደሮችን፣ ጄኔራሎችን ሳይቀር ሰብስበው የወታደራዊ ሳይንስ ሥልጠናም ሰጥተዋል። አባብለው፣ አሳስቀው፣ አሞጋግሰው ያው እንደተለመደው ወታደር የሚፈልገውን ያውቃሉና ምሳ አብልተው አብረውት እቅፍ አድርገው ፎቶም ተነስተው በጠባይ ሸኝተውታል። ወዳጄ ድሮስ ማን ከወታደር ጋር ይሳፈጣል?
•••
ተማሪውን ቢሆን ከኬጂ እስከ ዩኒቨርስቲ የሚማሩትን በየ ምክንያቱ ቤተመንግሥት ጠርተው አነጋግረዋል። ለህጻናቱ ቦርሳና ደብተር ሰጥተው፣ ከትልልቆቹ ጋርም ለኢንስታግራምና ለፌስቡክ የሚሆን ሰለፊ ፎቶ ተነስተው እንደተለመደው ሁሉንም አሞካሽተውና አወድሰው ምሳም አብልተው ሸኝተዋል።
•••
መምህራንንም እንዲሁ አነጋግረዋል። እንዲያውም ለመምህራን ብዙ ነገር ቃል ሁላ ገብተውላቸው ሆዳቸውን በተስፋም፣ በምግብም ሞልተው ቁዝር አድርገው አባብለው ሸኝተዋቸዋል ነው የሚባለው።
•••
መጀመሪያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ዋጋ ከፍለው ከሁለት ወደ አንድ መልሰዋል። አሜሪካ ድረስ ሄደውም የተከፈለውንና ለብቻው ተጎምዶ በውጭ የቀረውን ሲኖዶስ በጫንቃቸው ተሸክመው አምጥተው በመንበሩ አስቀምጠዋል። እዚህ ላይ ዳንኤል ክብረትን ያለማመስገን ንፉግነት ነው። የሲኖዶሱ ዕርቅ የዳንኤል ራዕይ ውጤት ነው። የሆነውም የተፈጸመውም እሱ ነው።
•••
 በመጨረሻም የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን በቀደም ዕለት በሸራተን ሰብስበው እንዳስታረቁ ፎቶውንም አይተናል፣ ቪድዮውንም ተመልክተናል፣ ዜናውንም ሰምተናል አንብበናልም። ይሄም ይበል የሚያሰኝ ነው። ፕሮቴስታንቶቹን ግን ያው እዚያው ቸርች ስለሚያገኟቸው ሰበሰቡ፣ አስታረቁ፣ ሲባል አልሰማሁም። ደግሞስ ኢዩ ጩፋን ከማን ያስታርቁታል? ለራሱ የጦር ሠራዊት ያለውን ፓስተር እኔ ሰፈር ካለው ከምስኪኑ ፓስተር ከአቡሻ ጋር ምን ብለው ያስታርቁታል?
•••
ታዲያ ይሄን ሁሉ ማድረጋቸው መልካም ነው። አያስከፋምም። በእነዚህ መልካም የሚመስሉ ነገር ግን ያን ካላደረጉ ስልጣናቸውን ከሚያሳጣቸው ተግባር መሃል በወቅቱ ሃኪሞችን ዘንግተዋል ተብሎም ክፉኛ ይታሙ ነበር። እውነት ነው ሁለቱን ሲኖዶስ ማስታረቃቸው ለአቢቹ በአሜሪካ ዋነኛውን የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ ኃይል ነው ጎምደውና ገንድሰው የጣሉት። ኢሳት ነሽ ታማኝ ተረረም ተደርገው የተቀነጠሱት በዚያ ወቅት ነው። ያን ማድረጋቸው ነው ዛሬ 3 ሚሊየን ህዝብ ተፈናቅሎ፣ ዜጎች እየሞቱም ሼም ኦን ዩ ብሎ ድምጹን የሚያሰማ ሰው የጠፋው።
•••
ሲያልቅ አያምር እንዲሉ ክፉ ዕድል ሆኖ ሃኪሞችም እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ጠሚዶኮ ሊያነጋግሩን ይገባል በማለት በመጨረሻ በሙጣጩ ሰዓት ጥያቄ በማቅረባቸው ጠሚዶኮው እንደተለመደው ሃኪሞቻችንን ድግስ ደግሰው፣ እንደቀደሙቱ ሁሉ ዶክተሮቹን ሰብስበው አነጋግረዋል። ስለ ንጽህና አጠባበቅ፣ ስለ ሀገር መውደድ፣ ስለ የሥራ ሰዓት አከባበር፣ ወዘተም አስተምረው፣ ባልተለመደ መልኩም ከፍ ዝቅ አድርገው በነገርም በምላስም ሸንቆጥ አድርገው ሸኝተዋቸዋል።
•••
ጠሚዶኮ ዐቢይ ሌላ ጊዜ እንደሚያደርጉት ከስብሰባው በኋላ ከሃኪሞች ጋር ተቃቅፈው የተነሱት ፎቶ እስከአሁን አልታየም። ከሌሎቹ ጋር እንደሚያደርጉት እየተጎራረሱ የተነሱት ፎቶም አልታየም። በትከሻቸው ላይ ተንጠልጥለው ለከንፈር የቀረበ መሳም የሚስሟቸው ቆንጅዬዎቹ ነርሶችም ሆኑ ውብ ዶክተሮች ፎቶም አልታየም። እናም ሃኪሞቹ በስብሰባው ተበሳጭተዋል ማለት ነው። ለምን ግን ሃኪሞቹን ማበሳጨት አስፈለገ? እኔ ሦስት ምክንያቶች ይታዩኛል።
•••
አንደኛ፦ ጠሚዶኮ ስብሰባም፣ ዲስኩርም የሰለቻቸው ይመስላል። ደግሞም እውነታቸውን ነው። ከነ ተረቱስ “ነገር ቢበዛ በአህያ አይጫንም” አይደል የሚባለው። እናም አንድ ዓመት ሙሉ ሃገር ምድሩን ዞረው ሰብከው ጠብ የሚል ነገር ሲጠፋ ስብሰባና ዲስኩር ቢሰለቻቸው አይፈረድባቸውም።
•••
ሁለተኛ፦ ጥሩ ሙድ ላይ አልነበሩም። ወይም ደግሞ ቀድመው እንደሌላው ጊዜ አልተዘጋጁበትም። ወይም ደግሞ የሆነ ክፉ ሰው ክፉ ሃሜት አውርቶላቸው በዚያ በስጭተው ሳይመጡ አይቀሩም። ወይም ደግሞ የተስብሳቢዎቹ ሃኪሞች ጥያቄ ናላቸውን አዙሮት “ እንዴ ምን ዓይነት ጉድ ነው? ምንድነው እንዲህ እኔን ማጨናነቅ ” ብለው ጠያቂዎቹን በቁጣና በማሸማቀቅ ጥያቄዎቹን ደግሞ በሀገር መሪነት ሥልጣናቸው ተጠቅመው አፈር ከድሜ አብልተው ለማለፍ ሳይከጅሉ አልቀረም። የሆነው ሆኖ ግን ሁለቱም ተደባብረዋል።
•••
ሦስተኛ፦ ይሄኛው ግን የእኔ የግል ሃሳብ ነው። በይሆናል የገመትኩት ነው። ይኸውም ምንድነው ያላችሁኝ እንደሆነ እኔ ዝም ብዬ ሳስበው በኢትዮጵያ ውስጥ የሆነ ዝም ብሎ ባልተጻፈ ሕግ የሕዝብ ቅነሳ እየተደረገ ያለ ይመስለኛል። ማፈናቀል፣ ግድያው፣ ረሃቡ ወዘተ በጠሚዶኮ ዘመን በአስደንጋጭ መልኩ መካሄዱን ሳስበው የሆነ ነገር ትከሻዬን ይሸክከኛል። እናም ለዚህ ሥራ ደግሞ ዶክተሮቹን ማበሳጨትን እንደ ጥሩ ዘዴ የተጠቀሙበት ይመስለኛል።
•••
ቆይ ማነህ አትቸኩል ልመጣልህ ነው። የማቀርበው የራሴን ሃሳብ ነው። የምን ቀደም ቀደም ነው። የምን መበሳጨት ነው። መጀመሪያ የጀመርኩትን ልጨርስ ከዚያ አንተ ደግሞ እስኪሰለችህ ድረስ በኮመንት መስጫ ሳጥኑ ላይ ሃሳብህን ትሰጣለህ። አታቋርጠኝ። ሃይ ምንድነው ሳ።
•••
ይኸውልህ ነፍሴ ጠሚዶኮ ዐቢይ ከሃኪሞቹ በፊት ያናገሯቸውን ሁሉ ብትመለከት አባብለው፣ ሸንግለው ካልያዟቸው ለሥልጣናቸው አስጊዎች ናቸው። እና ሥልጣን ደግሞ ጣፋጭ ናት። በስስት ካልጠበቋት እንደ ኢህአዴግ መሰባበር ይመጣልና ያን ስለሚያውቁ አባብለው ይዘዋቸዋል። ወታደሩ ቢከፋው የሚያስወግደው ራሳቸውን እንደሆነ ስለሚያውቁ ወታደሩን በሆዱም፣ በደሞዙም፣ በሥልጣንም ቀፍድደው ይዘውታል። ተማሪም አስተማሪም ቢከፋው የሚጮኸው የእሳቸው መንግሥት ላይ ነውና አባብለው ይዘውታል። አርቲስቱም ከከፋው 17 መርፌ እያለ ያሳብዳቸዋልና እሱንም አባብለው ይዘውታል። ነጋዴውንም እንደዚያው።
•••
ሃኪሞቹ ግን ቢያኮርፉና ሥራ ቢያቆሙ ጠሚዶኮዬ ምንም አይሆኑም። የሚጎዳው፣ እንደ ቅጠል የሚረግፈው ያው መጀመሪያም በደማከሴ ሲፈወስ የከረመው ምስኪኑ ህዝብ ነውና ሥልጣናቸው እንደማይነካ ስለሚያውቁ ለህዝብ ቅነሳው ሲባል ሃኪሞቹን ማበሳጨት አስፈላጊ መስሎ ያገኙት ይመስለኛል።
•••
እንኳን ዘንቦብሽ እንዲያውም እንዲያው ነሽ፣ ጤዛም ነሽ እንዲሉ አቢቹ ሆን ብሎ ሃኪሞቹን በስጩ እንዲነቅሉ አስደርጓቸዋል። እንጂ የኢትዮጵያ ሃኪም በጸሎት እንደሚያክም ጠፍቶት አይደለም። ተራ ካድሬ አስመጪና ላኪ ሲሆን ህይወትን በጨበጣ ያለመድኃኒት በምክርና ምፅ እያለ ከንፈር በመምጠጥ ለሚያክመው የኢትዮጵያ ሃኪም የሚከፈለው ደሞዝ ፌር እንዳልሆነም ጠፍቶት አይደለም።
•••
የኢትዮጵያ ሃኪሞች ያለ መብራት በስልክ ባትሪ ኦፕራሲዮን የሚሠሩ፣ ድስት ጥደው መርፌ የሚቀቅሉ፣ በሽተኛ ኮሪደርና ዛፍ ስር አስተኝተው የሚያክሙ፣ ማርያም ማርያም እያሉ ያለመርፌ የሚያዋልዱ፣ በህክምና ቁሳቁስ አቅርቦት እጥረት ምክንያት ሚልዮኖችን ከሞት ለማዳን መከራቸውን የሚበሉ፣ ከተካሚ ጋር አብረው እያለቀሱ፣ የቋጠሩትን ምሳ እያበሉ፣ ከደሞዛቸው ላይ ቆንጥረው ምስኪን ታካሚዎች እየረዱ ህይወታቸውን የሚገፉ የህክምና ባለሙያዎች ያሉባት ምድር መሆኑም ጠፍቷቸው አይደለም።
•••
በቃ እኔ ሲመስለኝ ሆን ብለው፣ ተዘጋጅተውበት፣ አቅደብውበት ይመስለኛል። እንጂ እንደሌሎቹ እንደከዚህ ቀደሙ ተሰብሳቢዎች አባብለው፣ አሳስቀው፣ አሻሽተው፣ ምሳም አጉርሰው በተስፋ ሆዳቸውን ነፍተው መሸኘት አቅቷቸው አይደለም። ሆን ብለው ይመስለኛል።
•••
የኤልፓ ሠራተኞች ቢያኮርፉ የሚጎዳው መንግሥትም ህዝብም ነው። ውኃ ክፍሎች ቢያኮርፉ የሚጎዳው መንግሥትም ህዝብም ነው። የመንግሥት ጉዳቱ ውኃ ጥሙ የበረታበት ህዝብ ራሱኑ መንግሥትን ስለሚጠጣው ነው ጉዳቱ እንጂ ዋናው ተጎጂማ ህዝብ ነው። የሃኪሞች ማኩረፍ ግን የሚጎዳው ህዝብ ነው። መንግሥትማ የት ይጎዳል? እንኳን ራሱን ውሽሞቹን ጭምር ባንኮክ እየላከ በደሃው ህዝብ ግብር የሚያሳክም ባለሥልጣን በሞላበት ሃገር መንግሥቱ የት ተገኝቶ ይጎዳል? ለጉንፋን ዱባይ፣ ለጨጓራ ደቡብ አፍሪቃ፣ ለቃር አውሮፓ፣ ለስትራፖ ባንኮክ ሄዶ የሚታከም ባለሥልጣን ከኢትዮጵያ ሃኪሞች ጋር ምን ቀረኝ ብሎ ያዝንላቸዋል? ደግሞስ ለጥቁር አንበሳና ለሚኒልክ ሆስፒታል ሃኪም አዘነ አላዘነ እሱ ምን ተእዳው? መርፌ አይወጉት፣ ኪኒን አይሰጡት። ደግሞስ ከየት አምጥተው ይሰጡታል። ሃኪሙ እኮ ለታካሚው የሚያቀርበው መንግሥት ያቀረበለትን ነው። መንግሥቱ ለሃኪሙ መድሃኒት እንዳላቀረበ ስለሚያውቅ እሱ ሲታመም ወደ ባንኮክ ይነካዋል። ምስኪኑ ህዝብ ግን ይሄን ሳያውቅ ሆስፒታልና ሃኪም ሲያማርር፣ ሲረግምም ይውላል።
•••
የእኔን ገጠመኝ ላንሳ፤ ሆዴን ክፉኛ ያመኝ ነበር። ምግብ አልበላም። ሆዴ ተቀብትቶ ሊፈነዳ የደረሰ ይመስላል። እናም በብዙ ሆስፒታሎች ታየሁ፣ ተመረመርኩ ወፍ የለም። በመጨረሻም ዶኒ አቦ ጠበል ሄድኩ። እዚያ በነፃ በአቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ጠበል ከህመሜ ተገላገልኩ።
•••
ደግሞም እግሬ ላይ እብጠት ወጣብኝ። ያውም መሃል እግሬ ላይ። መራመድ አቃተኝ። ሃኪሙም ትሄ ህክምና እዚህ ሀገር የለም አለኝ። አረርቲ ማርያም ምንጃር ለጉባኤ ሄጄ መራመድ እንዳቃተኝ ያየ አንድ ሰው አባቱ ጋር ወሰደኝ። የሆነ አርጩሜ የመሰሉ እንጨቶች ቆርጠው አመጡ። ከሰል አቀጣጠሉ፣ እንጨቶቹን አጋሉና በፍሙ እግሬ መሃል ያበጡትን እባጮች ተኮሷቸው። እባጩ ፈረጠ። እኔም ዳንኩኝ።
•••
ግንባሬ ላይ የሆነች እባጭ ነበረች። የአዲስ አበባው ሃኪሜ ብንነካካው ጥሩ አይደለም። እንዲሁ አስታመው። የተሟላ መድሃኒት ስለሌለ ጥሩ አይደለም አለኝ። እኔም ተውኩት። ኋላ ግን አውሮጳ ጀርመን መጣሁ። ግንባሬ አካባቢ ያበጠችውን ነገር ሃገር ቤት በአቅርቦት ምክንያት ማከም አንችልም ያሉትን ለጀርመኖቹ አሳየኋቸው። በ5 ደቂቃ ውስጥ ድራሽ አባቱን አጥፍተው ገላገሉኝ። ይኸው እስከዛሬ ምልክቱም የለም። እናም ምን ለማለት ፈልጌ መሰላችሁ እኛ ሃኪም ሳይሆን ያጣነው ለሃኪሞቻችን ምቹ ሜዳ የሚፈጥር መንግሥት ነው ያጣነው። የኢትዮጵያ ሃኪም ህመሙን ከነ መፍትሄው ያውቀዋል። ታዲያ በምኑ ያክምህ?በህዋው ውስጥ ያሉትን ፕላኔቶች በአካል ሳይጎበኛቸው በቃሉ እንደሚተነትንልህ እንደ አስትሮኖመሩ ህጻን ሮቤል እሱም በሽታህ ይሄ ነበር። መድኃኒቱና የማከሚያ መሣሪያው ስለሌለ ግን ጠበል ሞክር የሚልህን ደግ አማኝ ሃኪም ባናስቀይም መልካም ነው። ለኩላቲት ጠጠር የየካ ሚካኤልና የሚጣቅ አማኑኤል ጠበል ቀስ ብለው የሚያዙ ሃኪም አውቅ ነበር።
•••
ወዳጄ እኛ አሞን ሃኪሙ ጋር ቀርበን መዳን የምንጀምረው ሃኪሙ እህ ብሎ ችግራችን በፀጥታ፣ በትህትና ሲያዳምጠን ነው። ሃኪሙ ማከም የሚጀምረው መጀመሪያ እኛ የነገርነውን ኢንፎርሜሽን ሰብስቦ ነው። ምን ይሰማሃል? መቼ ጀመረህ? እንዴት ያደርግሃል?  ብሎ ጠይቆ ነው ወደ ሥራው የሚገባው። እናም ዛሬ ደግሞ ሃኪሙ በተራው አሞኛል አድምጡኝ ሲል ያለማድመጥ ነውር ነው።
•••
ሰሞኑን አንዳንድ ተካ ካድሬዎች በኢትዮጵያ ሃኪሞች ላይ ሲያላግጡ ሳይ ለእነሱ እኔ አፈርኩ። ከምር የኢትዮጵያ ሃኪሞች የሚሰደቡ አይደሉም። የሚንሀጓጠጡም አይደሉም። አይሳሳቱም እያልኩ ግን አይደለም። አያጠፉም እያልኩ ግን አይደለም። የህክምና ስህተር ተፈጥሮአዊም ዓለምአቀፋዊም ነው። ይሄ ለግርዛት ገብቶ የሬሳ ማድረቂያ፣ ለምጥ ገብታ የሬሳ ማድረቂያ፣ ለጨጓራ የኩላሊት መርፌ ወጉ የሚባለው ከሚልየን መልካም ነገር አንዷን ስህተት አውጥቶ ሃኪሞቹ ላነሱት ጥያቄ እንደ ማሸማቀቂያ መጠቀም ከካድሬዎቹ የማይጠበቅ ነውር የሆነ ተግባር ነው።
•••
መፍትሄው ሃኪሞቹን ማድመጥ ነው። ችግር ቢኖር እንኳ ችግሩን ቀርቦ በትህትና መንገር እንጂ በሩቁ ማሸማቀቅ ለማናቸውም አይበጅም። ከፍ ከፍ ያሉና የተሳካላቸውን ጥቂት ነጋዴ ኢንቨስተር ሃኪሞች የተደላደለ ኑሮ እያየን በመከራ ውስጥ ሆነው። በአስማትም በተአምራትም ህዝባቸውን ከፓስተርና ከቄስም በላይ እያገለገሉ ያሉትን ምስኪን የህክምና ባለሙያዎች አታበሳጩዋቸው።
•••
ሃኪሞችም ታገሱን። ብዙዎቻችን ጨርቃችንን ጥለን አማኑኤል ያለመግባታችን ነው እንጂ በብዙ ነገር ያበድን እብዶች መሆናችንን ልትረዱልን ይገባል። ልብስ ለብሰን ስንሄድ ጤነኛ መስለናችሁ እንዳትሸወዱ። እናም 100% አትበሳጩ። ብስጭቱን 50% ወይም ቢበዛ 60% አድርጉት። ለእናንተም ለእኛም ጥሩ አይደለም። ጥያቄያችሁ መልስ እስኪያገኝ ግፉበት። ታዲያ እያስፈራራችሁም ቢሆን በሽተኞችን መጎብኘታችሁን አታቋርጡ።
•••
በመጨረሻም ለአቢቹ መልካሙን ሁሉ እመኝለታለሁ። እንደ አጀማመርህ መሮጥ አልቻልክምና አስብበት። ፍጻሜህንም ያሳምርልህ። መጀመሪያ እንደ ንጉሥ ያዩህና የቆጠሩህ ዐማሮች ዛሬ ተከፍተውብሃል። በመጨረሻ ያናገርካቸው ሃኪሞች ደግሞ የበለጠ ክፉኛ ተከፍተውብሃልና መፍትሄ ካለ ጀባ በላቸው። መቼም ከሃኪም ጋር ተቀያይመው  በቃልቻ፣ በአዳል ሞቲ፣ በአርሲዋ እመቤት፣ በታዬ ከራማና በአተቴ ጊሚቢ፣ በጠቋር ሃኪሞቹን አትተካቸው። እናም ሃኪሞቹን ልብያድምጧቸው። ተካ ካድሬዎችንም አትስማ አንተን ያስደሰቱህ መስሎአቸው በሃኪሞቻችን ላይ የሚያወርዱትን ወርጅብኝ ብዙም አትውደደደው። ለማንኛውም መውጫውን ያዘጋጅልህ።
ከራየን ወንዝ ዳር።
Filed in: Amharic