>
5:13 pm - Sunday April 19, 0133

የአገዛዙን ሸፍጥ ልብ ብላቹህ እየተከታተላቹህት ነው??? (አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

የአገዛዙን ሸፍጥ ልብ ብላቹህ እየተከታተላቹህት ነው???
አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
* ዐቢይና ለማ ምን እያሉ ሿሿ እንደሠሯቹህና በኋላ ላይ እነማን ሆነው እንደተገኙ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነውና የምትረሱት አይመስለኝም፡፡ 
አስገራሚው ነገር እስከ አሁኗ ዕለት ድረስ ዐቢይ እና ለማ ሕዝብን ባጃጃሉበት መንገድ በተደጋጋሚ እየተጃጃልን መገኘታችን ነው፡፡
ለወትሮው “ሞኝን ሁለት ጊዜ እባብ ይነድፈዋል የመጀመሪያውን ሳያይ ሁለተኛውን ሲያሳይ!” ይባል ነበር፡፡ የሀገሬ ሕዝብ ግን ሁለት ጊዜ ብቻ ሳይሆን እልፍ ጊዜ በተመሳሳይ ዘዴ እየተጃጃለ መገኘቱ ትንግርት ሆኖብኛል፡፡ ትናንንትና መሬት በማይረግጥ ሽንገላ እንደተታለለ እያየ ዛሬም በሽንገላ ይጃጃላል፡፡ ምን አለፋቹህ ሕዝቡ ባዶ የአገዛዙን ሽንገላ ቀለቡ አድርጎታል፡፡
ሌላው ቢቀር እንኳ “ትናንትና እንዲያ ብላቹህን ተግባራዊ ሳታደርጉ ቀርታቹሃልና ወይም ሌላ ነገር አምጥታቹሃልና አሁን ልናምናቹህ አንችልም! እንድናምናቹህ ከፈለጋቹህ የማይመስል ሰበብ አስባብ ሳትደረድሩ ተግባራዊ አድርጋቹህ አሳዩን? ከዚያ ውጭ ባዶ ወሬ አንፈልግም!” የሚል ሰው ጠፍቷል፡፡ አገዛዙም ምን ገዶት ባዶ ሽንገላውን እያጣፈጠ ያዘንብለታል፡፡
ዐቢይና ለማ ከተናገሩት ተቃራኒ የሆኑ ነገሮች እየተደረጉ ሲመጡ ተደማሪ ልኂቃን ሿሿ እንደተሠራ ሲነቃና እንደነቃም አገዛዙ ሲያውቅ ልኂቃኑ የአጸፋ እርምጃ መውሰድ ከመጀመሩ በፊት ባለፈው ጊዜ በጠቅላይ ምኒስትሩ የደኅንነት አማካሪ በኩል “የአለመረጋጋቱና የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ቀውስ ወይም ችግር መንስኤው ሀገሪቱ እየተከተለችው ያለችው ቋንቋንና ዘርን መሠረት ያደረገው የፌዴራሊዝም ሥርዓት እንደሆነ ደርሰንበታል!” የሚል ጆሮገብ ወሬ እንዲነዛ በማድረግ ተደማሪ ልኂቃኑ “ችግሩ ይሄ መሆኑን ከደረሱበትና ካመኑ በቃ ከዚህ ከፋፋይና ጠንቀኛ የአሥተዳደር ሥርዓት እንድንወጣ ይወስናሉ ማለት ነው!” ብሎ ትናንትና በባዶ ሽንገላ ከመጃጃሉ ሳይማር መልሶ ተኛ፡፡
ከዚያ በኋላ ግን አገዛዙ የሚሠራውና በተግባር እያደረገው የሚገኘው ነገር የጎሳ ፌዴራሊዝሙን የሚያጠናክር ሆኖ ሲገኝና “ለምን?” በሚሉ ጥያቄዎች ሲያፍር ጊዜ በቀደምለት ባደረገው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ቀደም ሲል በጠቅላይ ምኒስትሩ የደኅንነት አማካሪ በኩል ሆን ብሎ ለማታለል ዓላማው “የአለመረጋጋቱና የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ቀውስ ወይም ችግር መንስኤው ሀገሪቱ እየተከተለችው ያለችው ቋንቋንና ዘርን መሠረት ያደረገው የፌዴራሊዝም ሥርዓት እንደሆነ ደርሰንበታል!” ሲል ነዝቶት የነበረውን መረጃ ቅርጫት ውስጥ በመጣል “የአለመረጋጋቱና የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ቀውስ ወይም ችግር መንስኤው ጽንፈኛ ብሔርተኝነት ነው!” ብሎ መግለጫ በማውጣት በጉዳዩ ላይ አደረኩት ያለውን ስብሰባ ቋጭቷል፡፡
ወዲያውም ትናንትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ በኢሲኤ በተደረጉ ሀገሪቱ እየተመራችበት ባለችውና ልትመራበት በሚገባው የአሥተዳደር ሥርዓት ዓይነት በተደረጉ ውይይቶች እንደ እነ አቶ ልደቱ አያሌውና ዶ/ር ሰሚር አሚን ያሉ ቅጥረኞቹን በማሰማራትና የተናገሩትንም በብዙኃን መገናኛዎቹ የዜና ሽፋን ላይ በመናኘት የጎሳ ፌዴራሊዝምን በሕግ ማገድ ወይም መከልከል አግባብ እንዳልሆነ ጮኾ እንዲሰማ በማድረግ ከጎሳ ፌዴራሊዝም ለመውጣት ፈቃደኛና ዝግጁ አለመሆኑን አረጋገጠ፡፡ ቀድሞም ቢሆን እንዲያው በከንቱ ተጃጃሉ ሲላቹህ ነው እንጅ የችግሩ አካል የሆነ ክፍል መልሶ እንደገና የመፍትሔ አካል ሊሆን እንደማይችል የታወቀ ነበር፡፡
የቅጥረኞቹ አቶ ልደቱ አያሌውና የዶ/ር ሰሚር አሚን እንዲያ ለማለታቸው ያቀረቡት የመከራከሪያ ነጥብ “የጎሳ ፌዴራሊዝሙን አጥብቀው የሚፈልጉትና ለድርድር የማያቀርቡ ክፍሎች አሉና!” የሚል ነው፡፡
እንደ እነሱ አስተሳሰብ ናዚዝምንና ፋሺዝምምን አጥብቀው የሚፈልጉትና ለድርድር የማያቀርቡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ስላሉ ጀርመንና ጣሊያን ናዚዝምንና ፋሺዝምን በሕግ መከላከል አልነበረባቸውም ማለታቸው እንደሆነ አልገባቸውም፡፡ የመከራከሪያ ነጥባቸው ምን ያህል ብላሽ እንደሆነ ልብ በሉ፡፡
የመከራከሪያ ነጥባቸውን ይበልጥ ብላሽና የደነቆረ የሚያደርገው ደግሞ በሠለጠነው ዓለምም ሆነ በየትኛውም ሀገር ይህ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ዓይነት ሉዓላዊ ሥልጣንን ለጎሳዎችና ብሔረሰቦች የሰጠና ጎሳ ተኮር የፖለቲካ እንቅስቃሴን የሚያስተናግድ የፌዴራሊዝም (የራስገዝ) የአሥተዳደር ሥርዓት ዓይነት ጨርሶ የሌለና በሕግም በጥብቅ የተከለከለ መሆኑ ነው፡፡
ልደቱና ሰሚር፦
* በሠለጠነው የዓለማችን ክፍልም ሆነ በሌሎችም ሀገራት የተለያዩ ብሔረሰቦችና ጎሳዎች ስለሌሉ ይመስላቹሀል ወይ ጎሳ ተኮር ፖለቲካና የጎሳ ፌዴራሊዝም በሕግና በጋራ መግባባት የተከለከለ የሆነው???
* በሠለጠነው የዓለማችን ክፍልም ሆነ በሌሎችም ሀገራት የተለያዩ ብሔረሰቦችና ጎሳዎችም እንዳሉ ካወቃቹህስ ፍላጎቱ ጨርሶ ስለሌለ ይመስላቹሀል ወይ ጎሳ ተኮር ፖለቲካና የጎሳ ፌዴራሊዝም በሕግና በጋራ መግባባት የተከለከለ ሊደረግ የቻለው???
* ሀገራቱ በሕግ በከለከሉበት ጊዜስ የተከፉ ወይም የሚከፉ የማኅበረሰቦቻቸው ክፍሎች ስለሌሉ ይመስላቹሀል ወይ በሕግ የከለከሉት???
* ሀገራቱ ይሄንን የአሥተዳደር ሥርዓት ዓይነት እስከ መከልከል ድረስ ያደረሳቸውስ ምን ይመስላቹሀል???
* ለዚህ ጎሳ ተኮር ፖለቲካና የጎሳ ፌዴራሊዝም ጊዜ መስጠት ወይም ተጨማሪ ዕድሜ እንዲያገኝ መፍቀድ ከውጭ የገቡትና ከውስጥም የነበሩት ጽንፈኞቹ ጠንቀኛውን ጽንፈኛ አስተሳሰብ እንዳይነቀል አድርገው እንዲተክሉትና ሀገሪቱንም ይሄ ጠንቀኛ የአሥተዳደር ሥርዓት በሚያመጣው ቀውስ ዘለዓለሟን ስትታመስ እንድትኖር ማመቻቸት እንደሆነ እንዴት ፊደል የቆጠራቹህ ሆናቹህ ሳላቹህ መገንዘብ ተሳናቹህ??? ነው ወይስ ሀገሪቱን የማፍረስ የተደበቀ ዓላማ አንግባቹሃል???
* እራስን በራስ ማስተዳደርና በራስ ቋንቋ መማር፣ መዳኘት፣ መተዳደር ከጎሳ ፌዴራሊዝም ውጭ በሆነው ፌዴራሊዝምና በዲሞክራሲያዊ አሐዳዊ ሥርዓት ጭምርም ማስተናገድ ማካተት ማድረግ እንደሚቻል እየታወቀ እነኝህን መብቶች ለምን ከጎሳ ፌዴራሊዝም ጋር አስተሳስራቹህ ማየት ፈለጋቹህ???
ለልደቱ እንኳን ቅጥረኝነት የኖረበትና የሚሞትበትም ቃል ኪዳኑ ወይም ልክፍቱ ነው፡፡ ዶክተር ተብየው ሰሚር ግን እንዴት በዚህ ደረጃ አገዛዙን ለመደገፍ በማሰብ ብቻ ኢሳይንሳዊ የሆነ ትንታኔ በመስጠት እራሱን ትዝብት ላይ ሊጥል ቻለ??? ለጎሳየ ብቸኛው አለኝታ ወያኔ/ኢሕአዴግ ነው ብሎ በማሰቡ ወይስ ለጥቅም??? ሰውየው ይሄ ተግባር ሲበዛ ርካሽነትና ወራዳነት እንደሆነ እንዴት በዚህ ደረጃ የተማርኩ ነኝ እያለ መረዳት ይሳነዋል??? ከአገዛዙ ምን ዓይነት ጥቅም ቢፈልግስ ነው እራሱን በዚህ ደረጃ ለትዝብት ዳርጎ አገዛዙን ሊያገለግል የቻለው??? የወያኔ/ኢሕአዴግ ጀምበር እንደጠለቀች እያየ ለጎሳው አለኝታ ወያኔ/ኢሕአዴግ ብቻ እንደሆነ አምኖ ወያኔ/ኢሕአዴግን ከውድቀት ለመታደግ ሳይንሳዊ ትንታኔ የሚሰጥ በመምሰል በየመድረኩ መንደፋደፉ የሚያሳዝን ሆኖ ነው ያገኘሁት ፡፡
እንግዲህ ወያኔ/ኢሕአዴግ እንዲህ እያጃጃለ እዚህ ደርሷል፡፡ ከዚህ በኋላ ደግሞ እነኝሁ ዘገምተኛ ተደማሪ ልኂቃን ምን ተስፋ አድርገው ሊጃጃሉ እንደሚችሉ ደግሞ በሚቀጥሉት ጊዜያት የምናየው ይሆናል፡፡ መጨረሻው እግዚአብሔር ይወቀው፡፡
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic