>
9:21 am - Wednesday December 7, 2022

ሃይ ባይ ያጡት ደላሎች!! (አሸናፊ በሪሁን)

ሃይ ባይ ያጡት ደላሎች!!

 

(አሸናፊ በሪሁን ከ seefar)

 

የካናዳ መንግስት በቅርቡ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን እንደሚቀበል ካስታወቀ ወዲህ ለደላሎች አዲስ የማጭበርበሪያ ሥራ ተከፍቶላችዋል። ቢቢሲ በአማረኛ ደረ-ገፁ ላይ በቅርቡ እንዳስነባበን ይህንን የሰማችው ኑአሚን የዛሬ ዓመት ገደማ ነበር ወደ ካናዳ እንወስድሻለን ያሉ ሰዎች በኩል እንቅስቃሴ የጀመረችው፡፡ ጓደኛዋ ሆኑ ኑአሚን ወደ ካናዳ እንወስዳለን ብለው የሚሉትን ሰዎች በአካል አያውቆቸውም። ትውውቃቸው ከስልክ የዘለለ አልነበረም:: በሰላሳዎቹ መጀመሪያ የዕድሜ ክልል ውሰጥ የምትገኘው ኑአሚን መኩሪያ የካናዳ ጉዞ ሂደቱን የጀመረችላት ካናዳ የምትኖር የቅርብ ጓደኛዋ ነች። ኑአሚን በተለያዩ ጊዜያትን ለሂደቱም ማስፈፀሚያ በሚል ወደ ካናዳ እንልክሻለን ላሎት ደላሎች ከ30ሺህ ዶላር በላይ ከፍላለች፡፡ ሰላሳ ሺህ ዶላሩ የተከፈለው በተለያየ አገር ውስጥ እና ውጪ ሀገራት ባሉ የባንክ ሂሳቦች ነው። ኑአሚን አራት ሺህ ዶላር (በብር መንዝራ) ሃገር ውስጥ ባለ የባንክ ሂሳብ ስታስገባ ጓደኛዋ ደግሞ ካናዳ፣ ጣልያን፣ ዱባይና ኬንያ በሚገኙ የባንክ ሂሳቦች ቀሪውን ገንዘብ ለደላሎች አስተላልፋለች። ይሄ ሁሉ ብር ፈሶም ደላሎች በዚህ አልረኩም ወጪዎችን ከላይ ከላይ እየቆለሉ መጠየቁን ቀጠሉበት እንጅ ፡፡ ይሄኔ ነው እነ ኑሀሚን መተማመኛ ነገር ሲያጡ እና ሂደቱም ለውጥ እንደሌለው ሲያውቁ ቆም ብለው ማሰብ የጀመሩት ፡፡ በሆላምሂደቱ ገና ነው አላለቀም እሉ ሲያጭበርበሩ በነበሩት ደላሎች መጭበርበራቸውን አውቀው ገንዘብ ላለመጨመር አሻፈረኝ ብለው ሂደቱን ያቆረጡት፡፡

የኑአሚን ታሪክ በዳላሎች እየተጭበርበሩ ያሉ የበርካታ ኢትዮጵያውያንም ታሪክ ነው ። ዛሬም ወደ አውሮፓ ሀገራት ለስራ እንልካለን በሚሉ ደላሎች እና ሰራተኛ እና አሰሪ አገኛኝ ድርጅቶች እየተጭበረበሩ ያሉትን ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ በቅርቡም ትልቅ ክፍያ የሚያስገኝ ስራ እናስቀጥራችኋለን በሚሉ አጭበርባሪ ደላሎች ተታለው ወደ ፖላንድ ያቀኑ ኢዮጵያውያን ለከፋ ችግር እየተጋለጡ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቆል ፡፡እነዚሁ ስደተኞችም በተለያዩ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ቅስቅሳ ተገፋፍተው ከ8 ሺህ ዶላር እስክ 300 ሺ ብር የከፈሉት በፖላንድ ርዕሰ መዲና ዋርሶ የተሻለ ስራ ታገኛላቹ ተብለው ነበር ፡፡ ፖላንድ ከደረሱ በሆላ ግን ወፍ የለም ፡፡ እናም ዛሬ ያሰቡት ሳይሆን ቀርቶ መግቢያ እና መድረሻ አጥተውሜዳ ላይ ወድቀው ስቃይ ላይ ናቸው፡፡ ለዜጎችዋ ስራ መፍጠር እየከበዳት ያለችው ፖላንድ አዲስ ስደተኛ ልትቀበል ቀርቶ የአውሮፓ ህብረት የስደተኞች ፖሊሲ ሳይቀር በመቃወም ስደተኞችን በኮታ የመቀበልን ጥያቄ ውድቅ ያደረገች ሀገር ነች ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ወደ አረብ ሃገራት እንዲልኩ ህጋዊ ፈቃድ የተሰጣቸው ሰራተኛ እና አሰሪ አገኛኝ ድርጅቶች ከተሰጣቸው ፈቃድ ውጭ ወደ አውሮፓ ፣ እስያ እና ሌሎችም ውጭ ሀገራት እንልካለን የሚሉ አማላይ ማስታወቂያዎችን በድረ ገፆቻቸው ላይ በመለጠፍ ማጭበርበራቸውን እንደቀጠሉበት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሰዎችን ወደ ተለያዩ የአውሮፓ እና እስያ ሀገራት ለመላክ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፈቃድ እንዳገኘ ሲያስተቀዋውቅ የነበረው እና በቅርቡ መግለጫ የተሰጠበት ኢትዮጵያ ሰራተኛ እና አሰሪ አገኛኝ የተባለው ደርጅት አንዱ ነው፡፡ ድርጅት ወደ ተለያዩ አገራት ለስራ እና ለጉብኝት ለመላክ ህጋዊ ዕውቅና እንደተሰጠው በመግለጽና ለዚህም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የድጋፍ ደብደቤ እንደጻፈለት በማስመሰል ደረ ገፁ ላይ በመለጠፍ ብዙዎችን ሲያጭበረብር ቆይቶል፡፡ ዕውቅና ተሰጠም ባለው ደብዳቤ ላይም ደርጅቱ ወደ ካናዳ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን ፣ ስዊዲን፣ ኖርወይ፣ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ ፣ ሰፔን እንዲሁም ከእስያ ሀገራት መካከል ደግሞ ወደ ቻይና ፣ ጃፓን ፣ ኮሪያ ፣ ሲንጋፖር እና ወደ ሌሎችም ውጭ ሀገራት በህጋዊነት እንደሚልክ ይገልፃል ፡፡ ይሁን እንጅ በቅርቡ ውጭ ጉዳይ ሚኒሰቴር መስሪያ ቤት ለድርጅቱ ምንም አይነት ደብዳቤ እንዳልፃፈና ዜጎችም በዚህ የሃሰት ደብዳቤ ተገፋፍተው ችግር ላይ እንዳይወድቁ የሚያስጠነቅቅ ምላሽ ሰጥቶል፡፡ ሚኒስቴሩ በድርጅቱ እና ይህን መሰል ወንጀል በሚፈጽሙ መሰል ተቋማትን ተከታትሎ ለህግ እንደሚያቀርብም አስታውቆል ።

በካናዳ ፣ አውሮፓ እና ሌሎችን ሀገራት ለመሄድ በማሰብ የተጭበረበረ ቪዛ እና የመኖሪያ ፍቃድ ለማግኘት ሲባል ሐሰተኛ ማስረጃዎችን መጠቀም እንደ ከፍተኛ ወንጀል ይቆጠራል። ሀገራቱ ሐሰተኛ ማስረጃ መጠቀማቸው ያረጋገጡባቸውን ስደተኞችም በወንጀል ከመክሰስ ባለፈ ዕድሜ ልካቸውን ወደ ሃገራቸው እንዳይገቡ ዕገዳ ሊጣሉባቸው ይችላል።
ማንኛውም ሰው የተሻለ ኑሮ የመኖር ፍላጎት ቢኖረውም ይህን ፍላጎቱን ለማሳከት ግን ትክክለኛው እና ህጋዊ የሆነውን መንገድ መከተል ይኖርበታል፡፡ ስደተኞችም የስራ ዕድል ተገኝቷል፣ ነጻ የትምህርት ዕድል ይሰጣችዋል ስለተባለ ብቻ የጉዞ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተው ረብጣ ገንዘባቸውን በከንቱ ከማፍሳሳቸው በፊት የመረጃው ትክክለኛነት ከሚመለከታቸው ተቋማት ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል ፡፡ ይህ ለአጭበርባሪ ደላሎች የሚከፈለው ገንዘብም ሃገር ውስጥ ያሉ ሌሎች ስራ የሚፈጠርባቸውን አማራጮችን ለመጠቀም ከበቂ በላይ ው ፡፡ በመሆኑም ስደትን አስበን እንቅስቃሴ ውስጥ ስንገባ እንደነ ነአሚን ልንጭበረበር የምንችልባቸውን ዕድሎቸ ሰፊ መሆናቸውን በማሰብ ልናስብበት እና ህጋዊ መንገዶችን ልንጠቀምባቸው ይገባል ፡፡ ሰዎችን ወደ ተለያዩ ውጭ ሃገራት እንልካለን በሚል የሚያጭበረብሩትን ደላሎች እና ድርጅቶችም ሃይ ባይ የሚላቸው ያጡ ይመስልም፡፡ ዛሬም ስም እና አድራሻቸውን እየቀያየሩ ብዙዎችን ለከፋ ነገር እየዳረጉ ነው፡፡ መንግስትም ሰዎችን በህገወጥ መንገድ በመላክ ፣ ለእንግልት ለስቃይ ብሎም ለሞት እየዳረጉ ያሉ ግለሰቦችን እና ድርጅቶች ላይ የማያዳግም ዕርምጃ በመውሰድ ዜጎችን ሊታደግ ይገባል እንላለን ፡፡

Filed in: Amharic