>
9:40 am - Saturday November 26, 2022

በደም የተገነባች በአጥንት የቆመች አገር!!! (ደረጄ በላይነህ)

በደም የተገነባች በአጥንት የቆመች አገር!!!
ደረጄ በላይነህ

“–ኢትዮጵያን ለማፍረስ ማሰብ ራሱ የአባቶቻችንን ሥጋና አካል ማፍረስና መቀንጠስ ነው፡፡ በጣልያን ቦንብ ተደብድቦ የተበተነውን አካላቸውን እንደ ጅብ መጋጥ ነው፡፡ እርም መብላት ነው፡፡ ክህደትም ነው፡፡ ኢትዮጵያ የነፃ ስጦታ ሳትሆን በመስዋዕትነት የተሠራች፣ የደም ዋጋ ናት፡፡ ቢሮ ውስጥ ቁጭ ብለን ከድረ ገፆች ላይ የምናወርዳት ፊልምና ታሪክ ሳትሆን፣ በፈረሰ የጀግኖች ሥጋ፣ በውድ የሰው ልጅ ደም የተገኘች ብርቅ አገር ናት!–”

ኢትዮጵያ፤ ዛሬ ሁሉም ወዳሻው አቅጣጫ እንደ ኳስ ሊጠልዛት ቢሽቀዳደምም፣ የትናንት መሠረቷና የታሪኳ ቀለም ግን እንዲህ በዋዛ የተገኘ አይደለም:: የሺህ ዓመታት ታሪክ ያላትና በኋላም በመሳፍንት እጅ ወድቃ እንባ ያጥለቀለቃት ኢትዮጵያ፤ ቴዎድሮስ ሊታደጋት ሲመጣም ብዙ ዋጋና መራር መስዋዕትነት ተከፍሎባታል፡፡ የቀጣዩዋን ኢትዮጵያ ህልም ያረገዘው አፄ ቴዎድሮስ፤ ህልሙ  የረገፈው በውጭ ጠላት ብቻ አይደለም፣ በሀገር ውስጥ ክህደትም ጭምር ነው፡፡ የብዙ ጀግኖቻችን ፍልሚያ እንደ ቅጠል የረገፈው በጠላት ብቻ አይደለም፤ በራሳችን ስግብግቦችና ሆዳሞች፣ ሲያልፍም ስማቸውን ከሀገራቸው አብልጠው በሚሻሙ ቂሎችም ጭምር ነው፡፡
አዎ፤ ጀግኖቻችን በአድዋ ጦርነት ያስመዘገቡት ድል ደምቆ በርቶ፣ በዓለም የክብር መዝገብ ላይ ቢሰፍርም፣  የ1928 ዓ.ም ጦርነትም፣ የኢትዮጵያ ጀግኖች ታላቅ ተጋድሎ አድርገው፣ በርካታ ድሎችን የተቀዳጁበት ነው፡፡ ይህንን ጦርነት በቁዘማና በቀዘቀዘ መንፈስ ብናስታውሰውም፣ በውስጡ ችቦ ሆነው የነደዱ አያቶቻችን ግን የሚያኮራ ገድል ፈጽመውበታል፡፡ ታንክ በጐራዴ ማናፈጥ፣ አውሮፕላን በቆመህ ጠብቀኝ ባፍጢሙ መድፋት፣ መትረየሱን ላንቃውን መዝጋት በየትኛውም ዓለም ቢተረክ እጅን በአፍ የሚያስጭን የጀግንነት ታሪክ ነው፡፡
ይህንን ታሪክ ከማንም በተሻለ ሁኔታ የጻፈው የቼክ ተወላጁ አዶልፍ ፓርላስክ፤ “የሀበሻ ጀብዱ” በተሰኘው መጽሐፉ በዝርዝር ተረኮታል፡፡ ደራሲው የየዕለት ክንውኖችን በጥልቀትና በስፋት ከማስፈሩም ባሻገር በታሪኩ ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ በመሆን፣ የሰሜኑ ጦር አዛዥ የነበሩትን ራስ ካሳን በማማከር አገልግሏል፡፡
መጽሐፉን ለኢትዮጵያውያን በሚስማማ ሁኔታ የተረጐመው ተጫነ ጀብሬ መኮንንም፣ ይህን ማድረጉ እንደ ባለውለታ ሊያስቆጥረው ይችላል፡፡ በተለይ አሁን ባለንበት ጊዜ መጽሐፉን ገልጠን ባየን ቁጥር የሚሰማን ልዩ ስሜት አለ፡፡ “ኢትዮጵያ” የምትባለው ሀገር በምን ዐይነት ውድ ዋጋ፣ በስንት ሺህዎች ደም የተሠራችና የቆየች መሆንዋን ይመሰክርልናል፡፡ ዛሬ በየሠፈሩ የተነሳ ጋጠወጥ እንደ ዳቦ ሊቆርሳትና እንደ ቆሎ ሊበትናት ሲያስካካ ሥናይ፣ ትናንት ከየአቅጣጫው ተምሞ ረሀብና ጥማት እየደፋው፣ እጅና እግሩ ተቆርጦ፣ በመርዝ ጢስ እየተደበደበ፣ ለሀገሩ መከራ የተቀበለው ያለፈው ትውልድ ስቃይ ቁብ እንዳልሰጠው ወይም እንደ ቂጣ ባንድ ቀን ተጠፍጥፋ የተሠራችና የማንም ዕዳና ደም የሌለባት እንዲመስል ያደረገው አለማወቅ እንዳለ ይጠቁመናል፡፡
ይህንን ለማወቅ የፈረንጁን መጽሐፍ ሁሉ ማጣቀስ ባይቻልም፤ አንዳንድ የሚያሳምሙ፣ የሚያሰቅቁና የሚያስለቅሱ ሁነቶችንና ገጠመኞችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ታዲያ ይህንን ታሪክና በታሪኩ ውስጥ ያሉትን ድርጊቶች ስናይ፣ ኢትዮጵያ ከሰሜን፣ ከደቡብ ከምሥራቅና ከመሀል ሀገር በተውጣጡ ጀግኖች መስዋዕትነት የተሠራችና የኖረች ሀገር እንደሆነች እንገነዘባለን፡፡ አያቶቻችን ሞት ብቻ ሳይሆን ከባድ ረሀብና ስቃይ፣ በሽታና ጉሥቁልና አሳልፈዋል፡፡ ውሃ ጥም አቃጥሏቸው በየጥሻው ወድቀዋል፡፡ ልብሳቸው በላያቸው አልቆ፣ ሰውነታቸው ሸትቷል፡፡ በአውሮፓ የቅንጦት ኑሮ የለመዱ ኢትዮጵያውያን ሳይቀሩ በዚያ ጉሥቁልናና ህመም ውስጥ አልፈዋል፡፡ ይህ ሁሉ መስዋዕትነት የተከፈለው ግን ከርሥ ለመሙላት ሳይሆን ለሀገር ክብርና ለህዝብ ነፃነት ነው፡፡
አንዳንዶቹ በዐድዋ ድል ተሰልፈው በጀግንነት ያገራቸውን ስም ያስጠሩት ሳይበቃ፣ ከአርባ ዓመታት በኋላም በእርጅናቸው ዕድሜ፣ ለሀገራቸው ልዕልና፣ በሀገራቸው ምድር ላይ መስዋዕት ሆነው አልፈዋል:: አዶልፍ ፓርላስክ፤ደጃዝማች ወንድይራድ የተባሉ አዛውንት ገድልን እንዲህ አስፍሮታል፡-
“–ሽማግሌው ደጃዝማች ወንድይራድ ከዛሬ አርባ ዓመት በፊት ከእምዬ ምኒልክ ጦር ጋር በአድዋ የጣልያንን ጦር ድል የመቱ ጀግና፣ ለሁለተኛ ጊዜ ተመሳሳይ ጠላትን በማይጨው ገጥመው፣ በጐራዴያቸው አንገት ቀንጥሰው፣ በጦራቸው የጠላት ደረት በስተው ቢወድቁም፣ ከዚህ በላይ አስደሳች ሞት የለምና ጀግናው አዛውንት ደጃዝማች ወንድይራድ የጀግና ሞት ሞተዋል፡፡–”
ኢትዮጵያ አንዴ ብቻ ሳይሆን ሁለቴ እሳት ውስጥ ገብተው፣ እንደ ሻማ የሚነድዱላት ጀግና ልጆች የነበሯት፣ በውድ መስዋዕትነት የኖረች ሀገር ናት:: ዘልለው ሞት ጉሮሮ ላይ እንደ አጥንት እየተሰኩ፣ ነፃነታቸውን ያስተፉ የጀግኖች እናት ናት፡፡ ለምሳሌ ጀግናው የከንባታ ጦር መሪ ደጃዝማች መሸሻና አቢቹ የተባለው የሰላሌው ልጅ፣ ደመቅ ያለ ታሪክ እንዳላቸው እንረዳለን፡፡ ይህ ጦርነት ሽማግሌውን ደጃች ወንድይራድንና የ16 ዓመቱን አቢቹን የያዘ የኢትዮጵያውያን ቅይጥ መሆኑን ያሳየናል፡፡
የከንባታው ደጃዝማች መሸሻ በተደጋጋሚ በመጽሐፉ ውስጥ የሚጠቀሰው “ጀግናውና ደፋሩ” በሚል ቅጽል ነው፡፡ አቢቹ ደግሞ ወጣት ተወርዋሪ ጦሩን ይዞ፣ በኋላም ከኤርትራ፣ ከትግራይ በአራት ጀኔራሎች የሚታዘዝ ሠራዊት መሪ ሆኖ፣ ጣልያንንና የትግራይን ሽፍቶች ቀሚስ ሲገልብ ነው፡፡ አቢቹ፤ የሰላሌው ጦር መሪ፣ የደጃዝማች አበራ ጦር አባል ነው፡፡ ለጊዜው የጀግናው የደጃዝማች መሸሻን የጦርነት ገድል፣ በተደጋጋሚ የጠቀሰውን የቼኩ ፀሐፊን ብዙ ትረካ መጥቀስ አልፈለኩም፡፡ ይልቅስ መስዋዕትነቱንና ለሀገሩ ሲል የጠጣትን የሞት ጽዋ ከመጽሐፉ ለማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡
“…ክፉኛ የቆሰለው የከንባታ ልጆች ጦር መሪ ደጃዝማች መሸሻ፣ የራስ ካሳ ጦር ከተንቤን የብረት አጥር ሰብሮ እንዲወጣ ሽፋን ሲሰጥ የነበረው፤ የራስ ካሳ ጦር የብረት አጥሩን ሰብሮ ከወጣ በኋላ ወደ ኋላ እያፈገፈገፈ ሲዋጋ፣ ጀግናው የከንባታ ልጆች መሪ ደጃዝማች መሸሻ፣ በአንድ የእጅ ቦምብ ከመመታቱም በላይ በሶስት የመትረየስ ጥይቶች ሆዱን ተመትቶ በወደቀበት ቦታ እንደሞተ ሰው ተኝቶ ውሎ ሲመሽ፣ በጨለማ እንደ እባብ እየተሳበ፣ ከዋለበትና ከቆሰለበት የጦርነት አውድማ ወጥቶ ወደ ካጫ ይገባል፡፡ ከዚያች ጫካ የትግል ጓዶቹ አንስተው የተረፈ ጦራቸው ወደሰፈረበት የጦር ሰፈር ወሰዱት::
“…የጀግኖቹ ጀግና ደጃዝማች መሸሻ፣ በከባዱ ከመቁሰሉም በላይ ያለ አንዳች የሀኪም እርዳታና ያለ አንዳች እረፍት ያደረገው ጉዞ ከፍተኛ የደም መፍሰስ ስላስከተለበት፣ ራስ ካሳ ካስነጠፉለት አልጋ ላይ ሁለት ሰዓት ያልሞላ ጊዜ ካረፈና የትግል ጓዶቹንና አለቆቹን ከተሰናበተ በኋላ ከዚያች ስቃይ ተገላገለ::–” (ገጽ 280)
እንግዲህ ሀገር የተሠራችው፣ በነፃነት የቆየችው እንዲህ ነው፡፡ ዛሬ እኛ በየቤታችንና በየቢሯችን ኮምፒውተር ላይ ተጥደን፣ ሻይና ቡና አሊያም መጠጣችን እየተጐነጨን፣ “ትፍረስ ትበተን” እያልን እንደምንዘብተው አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ደም ፈስሶላታል፤ ስቃይና አበሳ ተከፍሎላታል፡፡ የአሞራ ሲሳይ፣ የጅብ ራት ተሆኖላታል፡፡ በደም እንጂ በመርፌ የተጠቃቀመች ጨርቅ አይደለችም፡፡ ውድ ልጆች የሞቱላት፣ ውድ ሀገር ናት፡፡ በጦርነት እሣት መንደድ ደግሞ ዝም ብሎ እንደ ማውራት ዘበት  አይደለም፡፡
“የሀበሻ ጀብዱ” ፀሐፊ ገጽ 266 ላይ ያሰፈረው የአንድ ኢትዮጵያዊ ቁስለኛ ታሪክ፣ ሀገር የምታስከፍለውን ውድ ዋጋ የሚገልጽ ይመስለኛል፡፡
“…የዋይታ ድምጽ ወደምሰማበት አቅጣጫ መራመድ እንደጀመርኩ፣ አንድ ቁጥርጥር ፀጉር ያለው በጣም ጥቁር ልጅ ካንዲት ድንጋይ ስር ብቅ ሲል አየሁና፣ እርምጃዬን ገትቼ ስቆም፣ ከዚያች እንደ ከለላ ከቆመች ትልቅ ድንጋይ ስር አንድ በደረቱ የሚሳብ ወጣት የሀበሻ ወታደር አየሁ፡፡ ያ ቆፍጣና ወታደር፣ በደረቱ እየተሳበ፣ እኔ ወደ ቆምኩበት ቦታ መጣ፡፡ ይኼ ጀግና ልጅ ማለዳ ላይ ሰማዩን እየዳሰሰች የቦምብ ዝናብ ታወርድ የነበረችው አውሮፕላን የጣለችው ቦምብ፣ አንድ እጁን እጅጌው ድረስና አንድ እግሩን ከጉልበቱ በላይ፣ ሞኝ የጨፈጨፈው ዛፍ አስመስላ ቆርጣ ጥላዋለች፡፡ ከዚህ ትልቅ ዘግናኝ ቁስሉ ነፍሱ እያመለጠች ነው፡፡ ይኼ ወጣት ወታደር የቀረችውን አንዱን እጁን ወደኔና ወደ ሰማዩ ጌታ ዘርግቶ፤ “ጌታ፣ ጌታ እባክህ ስለ እግዚአብሔር ብለህ እርዳኝ፤ ጌታ እኔን የሚያስታምምና በቀረችኝ ጥቂት ጊዜ ስቃዬን የሚካፈል ጓደኛ የሌለኝ ብቸኛ ነኝና፣ ይኸው ስቃዬን ብቻዬን ተሸክሜ መሞቴ ነው፡፡ እባክህ ጌታ፣ ስለ እግዚአብሔር ብለህ፣ ውሃ አጠጣኝ፡፡ ውሃ ጥም ሞትኩ” አለኝ፡፡
አያችሁልኝ! ኢትዮጵያ በነዚህ ብርቅዬ ኢትዮጵያውያን ሰቆቃና ፍዳ የተሠራች እንጂ ከሰማይ የወረደች፣ ወይም በነፃ ተሠፍታ የተቀመጠች ሙዳይ አይደለችም፡፡ እንዲህ ተቆራርጠውላታል፤ እንዲህ ደምተውላታል፤ እንዲህ ደም ተፍተውላታል፡፡ እንዲህ የአሞራ ሲሳይ፣ የጅብ ቀለብ ሆነውላታል:: ዛሬ ማንም በምቾት እየተንደላቀቀ፣ ሊያፈርሳት የሚያላዝነው ትናንት ጀግኖች ልጆችዋ በዱር በገደሉ፣ በረሃብና ጥማት የተንከራተቱላትን ልጆችዋን ዋጋ ስለዘነጋ ነው፡፡
ኢትዮጵያን ለማፍረስ ማሰብ ራሱ የአባቶችን ሥጋና አካል ማፍረስና መቀንጠስ ነው፡፡ በጣልያን ቦንብ ተደብድቦ የተበተነውን አካላቸውን እንደ ጅብ መጋጥ ነው፡፡ እርም መብላት ነው፡፡ ክህደትም ነው፡፡ ኢትዮጵያ የነፃ ስጦታ ሳትሆን በመስዋዕትነት የተሠራች፣ የደም ዋጋ ናት፡፡ ቢሮ ውስጥ ቁጭ ብለን ከድረ ገፆች ላይ የምናወርዳት ፊልምና ታሪክ ሳትሆን፣ በፈረሰ የጀግኖች ሥጋ፣ በውድ የሰው ልጅ ደም የተገኘች ብርቅ ናት!
አዛውንቱ ደጃዝማች ወንድይራድ ብቻ ሳይሆኑ የእናቱን ጠረን ያልጠገበው የአስራ ስድስት ዓመቱ ታዳጊ አቢቹ መከራ የተቀበለላት ሀገር ናት:: ከየአካባቢው የመጣው የኢትዮጵያ የገበሬው ሰራዊት፣ የመላው ኢትዮጵያ ህብረት እንጂ ከአንድ ሰፈር የተዘገነም አልነበረም፡፡ ጦሩ፤ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ከንባታና ሌሎችም የተካተቱበት ነው፡፡ የጦሩ ተጋድሎና ጀግንነት ደግሞ “እንኳን ኢትዮጵያዊ ሆንኩ!” የሚያሰኝ እንጂ የሚያሳፍር አይደለም:: ብረት ለበሱንና ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀውን የጣልያን ጦር መተናፈሻ አሳጥቶ፣ የተለያዩ የጦር ሜዳ ድሎችን የተቀዳጀው ለነፍሱ ሳይሳሳ፣ ሬሳ እየተራመደ፣ ታንክ ላይ ዘልሎ እየወጣ ነበር፡፡
“–በጣልያን ታንኮች ጥይት ተመትቶ በወደቀ አንድ ወታደር፣ አስር ሌሎች ጀግኖች እየተተኩ፣ የወደቀ የጦር ሜዳ ወንድማቸውን እየዘለሉ ወደፊት ገሰገሱ፡፡ የጣልያን ታንኮች ያለማቋረጥ የግድያ ተግባራቸውን ቢቀጥሉም፣ በታንኮቹ ዙሪያ የወደቁት ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ሬሳ ቢከመርም፣ ይኼ ጀግኖቹን ወደ ኋላ ሳይስብ፣ ጀግኖቹ የወደቁ የጦር ሜዳ ጓዶቻቸውን እየዘለሉ ወደፊት ገፉ፡፡ አሁንም አንዳንዶቹ ወደ ታንኮቹ  ተጠግተው ቀዳዳ እየፈለጉ፣ አነጣጥረው ለመተኮስ ሲሞክሩ፣ ብረት ለበሶቹ ታንኮች በጀግኖቹ ላይ ያለ ምንም ርህራሄ እየወጡባቸው ገሰገሱ፡፡
“የተንቤን ሙቀት ታንኮቹን የላይኛውን መግቢያ በር እንዲከፍቱ አስገደዳቸው፡፡ ይኼንንም ሰፊ ቀዳዳ ጀግኖቹ ጦራቸውን ሰብቀው በመሄድ ላይ ባለው ታንክ እየቧጠጡ ወጥተው ወደ ውስጥ፣ ወደ ታንኩ ጓዳ መወርወር ጀመሩ፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የመጀመሪያዋ ታንክ ድምፅዋን አጥፍታ ቆመች፡፡ መትረየሶቿም ፀጥ ረጭ አሉ፡፡ የመጀመሪያዋን ታንክ እጣ ፈንታ ያዩት ሁለቱ ታንኮች ፊታቸውን አዙረው ወደ ጦር ሰፈራቸው ወደ ወረዶ መፈርጠጥ ጀመሩ::”  (ገጽ 176)
ስለ ኢትዮጵያውያን ጀግንነት የሚወራው ገድል ተረት አለመሆኑን የመሰከረው የቼክ ፀሐፊ፤ ብዙ ብዙ ጀግኖችን በመጽሐፉ ውስጥ ያሳየናል፡፡ ምናልባትም ኢትዮጵያዊነት በጥቁር ሰሌዳ ላይ በዳስተር የሚጠፋ ጽሑፍ ለመሰለን ሁሉ፤ በደም የተፃፈ፣ የጀግኖች ተጋድሎ ውጤት መሆኑን ያረጋግጥልናል፡፡ ይህንን መሪር መስዋዕትነት ያወቀና ያስተዋለ፣ ለሀገሩ አንድነት ህይወቱን እንደ ዘንባባ ያነጥፋል እንጂ በየሄደበት ክብሪት አይጭርም፡፡ የጀግኖች አባቶቹን ክብር እንደ እምቧይ አያፈርጥም፡፡
በተለያዩ ፀሐፍት ያነበብናቸው ኢትዮጵያዊ ታሪኮች በሙሉ የአስደማሚነታቸው ምንጩ ይኸው ስለ ሀገርና አንድነት ክብር ያላቸው፣ በዋጋ የማይተመን ፍቅር ነው፡፡ በተለይ ዛሬ ያተኮርኩበት የአዶልፍ ፓርለሳክ መጽሐፍ ወደር የማይገኝለትን ኢትዮጵያዊ ጀግንነትና ስለ ሀገር የሚከፈለውን ውድ ህይወት በከፍታ ያሳየና ሊታመን የማይችል ድንቅ ገድል ነው፡፡
ጦርነቱ ያንን ያህል ዋጋ ተከፍሎለት የተጨበጡ ድሎች ሳይቀር ወደ ኋላ የተመለሱበትንም ምክንያት ገምግሞ ትችቱን አስቀምጦልናል፡፡ ይህ ፀሐፊ ለብዙ ዓመታት የተወራውን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ሽሽት በምክንያት አስተባብሎታል፡፡ “በጦር ግንባር ገጥመው እንደ ማንኛውም ተራ ሰው ውጊያውን ተካፍለው ደም ውስጥ አልፈው፣ ልብሳቸው ደም አጥቅሶ፣ ጎራዴያቸው ጠላት ቀንጥሷል፡፡”እያለ ይሞትግላቸዋል፡፡ “የሃበሻ ጀብዱ” ፀሐፊ፤ የማይጨው ጦርነት ውጣ ውረድ ከቃላት በላይ እንደሆነ ይገልፃል፡፡
“–የሰው ልጅ ጥንካሬ የሚያስገርም ነው፡፡ በኔ ባይደርስ ባላመንኩ ነበር፡፡ ከአቢ አዲ  የካቲት 4 ቀን ተነስተን፣ ከጥቂት ሰዓታት እረፍትና እንቅልፍ በስተቀር ሳናርፍ እንደሮጥን ይኸው አሁን ከመጋቢት 5 ልንሸጋገር ነው፡፡ አንድ ወር ሙሉ የሰው ልጅ ጥቂት አርፎ፣ እፍኝ ሽምብራ ቆርጥሞ፣ ጉንጭ ውሃ ጠጥቶ፣ ተራራ ወጥቶ፣ ቁልቁለት ወርዶ፣ ገደል ቧጦ፣ መሮጥ መቻሉ ተዓምር ነው እንጂ ሌላ ምን ይባላል?–”
ከላይ እንደጠቀስኩት የ16 ዓመቱ ታዳጊ አቢቹ፤ ከስር በችግኝነት ዕድሜው ለኢጣሊያ ወራሪ ምን ያህል እሳት እንደሆነበትና ለሀገሩ ልጆች አለኝታ እንደነበር ይህ ፀሐፊ ባያሳየን ኖሮ፣ በታሪክ ገፅ ውስጥ የማናገኘውን ተዓምረኛ ልጅ አጥተን ነበር፡፡ አቢቹን ወደ ታሪክ አደባባይ ያመጣው የቼክ ሪፐብሊኩ “ፈረንጅ ኢትዮጵያዊ” እንጂ የኛ ሀገር የታሪክ ፀሐፍት አይደሉም፡፡ ይህ በራሱ እንቆቅልሽ ነው፡፡ ይሁንና አቢቹ በጣልያኖች ብቻ ሳይሆን በኛ ሀገር ራሶችና ደጃዝማቾችም ጭምር እንደ አመፀኛ የሚታይና የሚተች ነበር፡፡
ግና አቢቹ አመፀኛ የነፃነት ረሀብተኛ ነበር:: ለትምህርት የተዘጋጀ ልቡን፣ ለሀገሩ ሲል ለሞት አሳልፎ የሰጠ፡፡ ልጅነቱን በእሳትና በደም መሀል ያሳለፈ፣ የሚወዳቸውን ወንድሞቹን ለሞት ያጎረሰ፣ እያለቀሰች በሸኘችው የሰላሌዋ እናቱ ላይ ጨክኖ ወደፊት የገሰገሰና ሃገሩን ያኮራ፣ ለወገኖቹ ፈጥኖ በመድረስ ከሞት ላንቃ የተናጠቀ ብርቱ ጀግና ነበር፡፡
አቢቹ በየጊዜው ንጉሡ “ልጁን አቁሙት!” እያሉ ራሶቹን ሲልኩበትም፣ ጥርሱን ነክሶ ልጅነቱን ለኢትዮጵያ ሀገሩ ሰውቷል፡፡ ከአቢቹ ጋር የነበሩት የትግራይ፣ የኤርትራ፣ የሰላሌ፣ የአማራ ልጆች ለውዲቷ ኢትዮጵያ ዋጋ ከፍለዋል፡፡ በአምስቱ ዓመት የአርበኝነት ዘመንም፣ በዱር በገደሉ ተንከራትተው ነፃነት የሰጡን የሀገራችን ልጆች ውለታ ቀላል አይደለም!
ኢትዮጵያ የሁላችንም አባቶችና አያቶች የመስዋዕትነት ውጤት ናት የምንለው ለዚህ ነው:: “እኔ ልሙትና አንቺ ኑሪ!” ተብላ በክብር የቆየችን ሀገር፤ “አንቺን ገድዬ ሆዴን ልሙላ!” በሚል አሳፋሪ ታሪክ መቀየር የለበትም!! ኢትዮጵያ ውድ ዋጋ የተከፈለላት ውድ ሀገር ናት! እኔም አያቴን በማይጨው ጦርነት በመክፈሌ “ስለ ሀገሬ ያገባኛል” ስል ስለ አባቴ አባትም ነው፡፡ ሁላችንም ለኢትዮጵያ አዋጥተናል፡-
ይህንን ሁሉ መዋጮ የካዱና ከንቱ ያደረጉ ወገኖች ዛሬ በአደባባይ ያለ ሀፍረት ኢትዮጵያን ለማፍረስ እንደሚተጉት ሁሉ፣ ያኔም የጦርነቱን አቅጣጫና የድሉን ባለቤትነት የቀየሩ የታሪክ ነውረኞች አልጠፉም፡፡ አገራችን፤ በየዘመኑ ከሀዲዎችና ከርሣቸውን ያነገሱ ስግብግቦችን ብትወልድም፣ በዋናነት ግን ጥርሳቸውን ነክሰው በመሟገትና በመሞት፣ ታሪክ የጻፉላት ልጆችዋ የፍቅር እሳት መቼም ከልብ የማይጠፋ ነው፡፡

Filed in: Amharic