>
10:17 am - Wednesday November 30, 2022

ኢሳት የእናንተ ነው! የእኔ ነው የሚል ከመጣ እንዳትሰሙት!!! (መሳይ መኮንን)

ኢሳት የእናንተ ነው! የእኔ ነው የሚል ከመጣ እንዳትሰሙት!!!
መሳይ መኮንን
ንቅናቄው የመጨረሻውን ጥይት በጨለጠበት መድረክ የኢሳት ባለቤት ነኝ የሚል ነውር መግለጫ መስጠቱን በተመለከተ በወቅቱ በዝምታ አልፌው ነበር። አመራሮቹ በየቲቪ መስኮቱ እየወጡ ደጋግመው ሲነግሩን ግን ቢያንስ በግሌ ”የግንቦት ሰባት ጋዜጠኛ” እንዳልነበርኩ መግለጽ እንዳለብኝ ተሰምቶኛል።
ኢሳት የግንቦት ሰባት ነው የሚለው ጩኽት ጆሮ ያደነቁራል። ንቅናቄውም ሆነ አባላቱ በኢሳት ምስረታና ዘለቂታዊ ጉዞ ላይ ድርሻቸው ቀላል እንዳልሆነ አውቃለሁ። ለዚህም ክብር አለኝ። ይሁንና ባለቤት ነን የሚለው ህጋዊም ሆነ አመክንዮታዊ መሰረት የሌለው መግለጫ እየተደጋገመ ሲሰማ የዝምታን ትዕግስት ይፈታተናል። ታሪክ ነውና ተንሻፎ መቅረት የለበትም። ንቅናቄው የመጨረሻውን ጥይት በጨለጠበት መድረክ የኢሳት ባለቤት ነኝ የሚል ነውር መግለጫ መስጠቱን በተመለከተ በወቅቱ በዝምታ አልፌው ነበር። አመራሮቹ በየቲቪ መስኮቱ እየወጡ ደጋግመው ሲነግሩን ግን ቢያንስ በግሌ ”የግንቦት ሰባት ጋዜጠኛ” እንዳልነበርኩ መግለጽ እንዳለብኝ ተሰምቶኛል።
በመሰረቱ የኢሳት አፈጣጠር፡ ቅርጽና ባህሪ ለአንድ የፖለቲካም ሆነ በየትኛምው መልኩ ለተደራጀ አካል በባለቤትነት የሚሰጥ አይደለም። የኢሳት ባለቤት ህዝብ ነው። በዝርዝር ይገለጽ ከተባለም በየወሩ የሚያዋጣው ኢትዮጵያዊ፡ ከጀርባ ሆነው ኢሳትን በቋሚነት ሲረዱ የነበሩ ቆራጥ ደጋፊዎች፡ በዋናነትም ሌት ተቀን ኢሳት በፋይናንስ እንዳይጎዳ ሲሰሩ የነበሩ ቻፕተሮች ሲሆኑ ጋዜጠኞቹ ደግሞ ከፊት ለፊት ሆነው ኢሳት የህዝብ ለመሆኑ እያረጋገጡ የዘለቁ ባለድርሻ አካላት ናቸው። በዚህ ውስጥ ድርጅቶች አሉበት። ከሃይማኖት ተቋማት እስከ ሙያ ማህበራት ሚናቸው ከፍተኛ ነው። ግንቦት ሰባት የሚችለውን አድርጓል። አንድነት ፓርቲ ኢሳት ህልውና እንዲቀጥል በተለያዩ አስተዋጽኦዎች አብሮን ነበር። ሰማያዊዎች ከጎናችን ሆነው ደግፈውናል። ከሀገር ቤት በኢትዮጵያ ብር ሳይቀር በመቶሺዎች የሚልኩልን ነጋዴዎች ነበሩ። የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የጀርባ አጥንታችን ናቸው። የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ቤተክርስቲያን የኢሳት አጋር ሆና ዘልቃለች። የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች በተቋምና በግለሰብ ደረጃ ኢሳትን ሲያግዙና ሲረዱ በቅርበት እናውቃቸዋለን። ከፖለቲካው፡ ከሃይማኖቱ፡ ከምሁር እስከ ገበሬው ኢሳትን ለዚህ ያበቃው እልፍ ዜጎችን መዘርዘር የሚቻል አይደለም።
ኢሳትን የእኔ ብሎ አንድ አካል መግለጫ መስጠቱ ሃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው፡፡ የሰውን አእምሮ ያለፍቃዱ የእኔ ማለት እብደት ነው። እኔ በኢሳት ቆይታዬ የተለያዩ አካላትን እገዛ በቅርበት ስለማውቅ የአንድን አካል ”የእኔ ነው” አቋም እስከጥግ ድረስ ዘልቄ ልቃወመው እንደሚገባኝ አምናለሁ። አስተዋጽኦ ማድረግ የባለቤትነት ጸጋን አያጎናጽፍም። እንደኢሳት ያሉ የህዝብ ተቋማትን ለአንድ የፖለቲካ ስብስብ በባለቤትነት መጥራት ተቋሙን የሚገድል፡ የህዝብ ነው የሚያሰኘውን ባህሪውን የሚገፍና የተአማኒነት ገጽታውን ጥላሸት የሚቀባ አደገኛ አካሄድ ነው። የግንቦት ሰባት ሰዎች በኢሳት ጉዞ በነበራቸው አስተዋጽኦ ጥሩ ስም እንደማግኘታቸው በመክሰሚያ መድረካቸው የኢሳትን ታሪክ ከመቃብር የሚከት አቋም ማንጸባረቃቸው በእጅጉን የሚያበሳጭ ነገር ነው። ሀገር ልንመራ ተዘጋጅተናል ከሚሉ የፖለቲካ አመራሮች የማይጠበቅ ውሳኔ ነው።
በኢሳት ቆይታዬ ከግንቦት ሰባት ንቅናቄ ጋር በቅርበት ሰርቼአለሁ። በዚህም የንቅናቄው ”ጋዜጠኛ” የሚል ቅጽል ስም ላተርፍ ችዬአለሁ። በመሰረቱ በወቅቱ የነበረው የተበጣጠሰና የተበታተነ ትግል በአንድ የፖለቲካ ስብሰብ ካልተመራ ለኢትዮጵያ አይበጅም ከሚል መነሻ ምክንያት ብቻ የንቅናቄው ትግል አጋር ሆኜ ሰርቼአለሁ። ያም ለኢትዮጵያ ይበጃታል ከሚል ቀና አስተሳሰብ እንጂ ለንቅናቄው የተለየ ፍቅር ወይም ከሌላው ኢትዮጵያዊ የበለጠ ቅርበት ኖሮኝ አልነበረም። በነበረኝ አካሄድ የንቅናቄው ጋዜጠኛ ልመስል ብችል ስህተት አይደለም። እንደዚያ ያመነም ካለ አላጠፋም። እውነቱ ግን ሌላ ነው። ይህ አቋሜ ፍጹም ልክ ነው እያልኩ አይደለም። በሌላ መከራከሪያ የእኔ የ8ዓመታት አካሄድ መሞገት ይቻላል። ያን በማድረጌም የምጸጸት አይደለሁም። ለትግሉ አስተዋጽኦ ያደርጋል ከሚል እምነት እንጂ በሌላ የተለየ ምክንያት አልነበረምና። እርግጠኛ ሆኜ ለራሴ የማምነውና አምኜም የምዘልቀው ”እኔ የግንቦት ሰባት ጋዜጠኛ” እንዳልነበርኩና ልሆንም እንደማልችል ነው። ይህ የብዙዎቹ ባልደረቦቼ እምነትና አቋም እንደሆነ ይሰማኛል።
ዋናው ነገር ኢሳት የህዝብ መሆኑን፡በየትኛውም ድርጅት ባለቤትነት የሚገለጽ እንዳልሆነ የግሌን አቋም ለማሳወቅ ነው። ኢሳት የእናንተ ነው። የእኔ ነው የሚል ከመጣ እንዳትሰሙት!!!
Filed in: Amharic