>
11:43 am - Friday May 20, 2022

ጉልበት 20ን በማስመልከት የተፃፈ...   (ፍቅር ሠይድ)

በእኛ ተላላነት በኢህአዴግ እባብነት ሀገር ልትፈርስ ! 
 ፍቅር ሠይድ
ጉልበት 20ን በማስመልከት የተፃፈ ነው
***
መደብደብ ማሰር መግደል የኢህአዴግ ህጋዊ መርሆቹ ናቸው።
ስንደበደብ ስንታሰር ስንገደል በወረት መጮህ መታገል ደግሞ የእኛ መለያ ባህሪያት ናቸዉ ።
**
 አድሎአዊ እና በሴራ ተንኮል የተሞላ ኢኮኖሚ ልማት ማካሔድ ማራገብ የኢህአዴግ ህጋዊ መርሆች ናቸው።
“ኢትዮጵያዬ ሱሴ” ስለተዘመረ መሠረተድንጋይ ስለተጣለ ፋብሪካ ሊገነባነው ስለተባለ የሴራና ተንኮል ልማት ስለተሠራ በወረት ሙሴ ጀግና እያሉ ማሞገስ እስከ መመካት በጭብጨባ አብዮት መጥለቅለቅ የእኛ መለያ ባሕርያት ናቸው።
****
ላለፈው 28 ዓመት ኢህአዴግም ስህተቶችን ከዓመት ዓመት እያረመ ዴሞክራት እና ሕዝባዊ መንግስት መሆን አልቻለም ለመሆንም አልሞከረም ወደፊትም ሊሆንም አይችልም።
ላለፈው 28 ዓመት ሕዝቡ የትግል ስልቶቹን ስህተት ከዓመት ዓመት እያረመ መሔድ ባለመቻሉ የኢህአዴግን ሞት ማፋጠን አልተቻለም። ሁሌ በሆይሆይታ ሰላማዊ ሠልፍ ሁሌ በቀቢፀ ተስፋ መታለል መሸወድ። መርህ አልባ ትግሎች። ስልት አልባ ጩኸቶች። ስሜታዊ ድንፋታዎች። ግልብ ንቅናቄዎች።  የአንድ ሰሞን ትግትጎች።
***
.. . እከሌ ይፈታ ይፈታ ይፈታ። ከዛ ጭጭ። ፍትህ ለእንትና ከዛ ጭጭ። ወንጀለኞች በአስቸኳይ ለህግ ይቅረቡ ከዛ ጭጭ። መጨረሻ የሌለው ጅምር ትግል። ማሳረጊያ የሌለው ፀሎት። የነብር ጅራት ለመያዝ በስሜት በግልብ መንጦልጦል። ጅራቱን ከያዙት በኋላ ደግሞ እንደገና ማንቀላፋት። ገዥም ለምን ጅራቴን ያዛችሁ ብሎ መደብደብ ማሠር መግደል። የተያዘን ጅራት መቁረጥ ትተን ስንለቅ ኖረናል። 1987, 1991, 1992, 1993, 1997, 1998, 1999, 2002, 2003, 2006, 2007, 2008, 2009, 2010, 2011, በነዚህ ዓመታት ሁሉ ከሽፈናል። ጅራት ይዘን ለቀናል። ደጋግመን ተሸውደናል። በኢህአዴግ የውሸትና የተንኮል ፖለቲካ ስንት ጊዜ እንደተሸወድን ብናሰላው እኮ ይዘገንናል።
 ወደፊትም በዚሁ መለያዊ ባህርያት መጓዛችን እንደማይቀር ያስታውቅብናል። በስሜት በግልብ መጮህ ሰልፍ መውጣት ከፍ ካልን ለብለብ እርምጃ ወስዶ እሷን እንደ መጨረሻ ድል አጣጥሞ እፎይ ማለት። ጅራት ለቆ እንደገና መነሳት።
ቡራዮ አማራዎች ሲታረዱ አየን ነፍሰጡር ባሏፊት ስትደፈር አየን ሲፈናቀሉ አየን። ስሜታችን ተቆጣ የአውሬውን መንግስት ጅራት አፈፍ አደረግን ጩኸት ጀመርን ሰልፍ ወጣን ጨረስን። የአውሬውንም ጅራት ለቀቅን። ግንየቡራዮን አማራ መጨረሻ እስካሁን ዘወር ብለን አላየነውም ከምን እንደደረሰም አልጨነቀን። ግብአልባ ትግል። ሐዋሳ ሰው ከነነፍሱ ተቃጠለ። ሻሽመኔ ሰው ተዘቅዝቆ ተሰቀለ። ወንጀለኞች ለፍርድ ይቅረቡ አልን እንጂ  ታድነው ተይዘው ፍርድ እስኪያገኙ አልታገልንም።
በአማራነታቸው በየ ዩኒቨርስቲው ተማሪዎቻችን ሲሰቃዩ ሲገደሉ ሲባረሩ ሰልፍ ወጥተናል። አድማ መተናል። የትግሉን ዓላማ ጀምረን ትተነዋል። ተማሪዎቹ አሁን ምን ላይ ናቸው??? እየተማሩ ወይስ ከትምህርት ርቀዋል? በየሚቀርባቸው ካምፓስ ተመድበው እንዲማሩ ተደርጓል? ስነልቦና ቀውስ እንዳይገጥማቸው ምን ተሰራ?
የሟች ተማሪ ቤተሰቦችስ አስታውሰናቸዋል?
ልጃቸውን በአሶሳ ዩኒቨርስቲ በሚዘገንን ሁኔታ በመሀይም ዘረኞች በድንጋይ ተወግሮ የተገደለባቸው የኮምቦልቻው የአብዱ ሰኢድ ወላጆች እንባ በጥቂቱ እንኳ ታበሰ ወይ የተሰበረ ልባቸው በከፊል ተጠገነ ወይ?
አማራ ብሄር ተኮር የዩኒቨርስቲ ግጭቶች ሰለባ ከሆኑት አንዱ በአሶሳ ዩኒቨርስቲ የ2ኛ ዓመት ተማሪ የጎንደሩ (ደራ)መልካሙ ዋለ ሞት ያስደነገጠን ያስቆጨን ያህል የእድሜልክ ሃዘንተኛው ድሃ ቤተሰቡን አስታውሰነው እናውቃለን? የሞራል ጥገናስ አድርገናል?
የአማራም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማቆሚያ የሌለው መከራና ሰቆቃ የገሃነም ፍዳ ውስጥ የሚኖረው ግብ አልባ ትግል አላማ አልባ ተቃውሞ መነሻው እንጂ መድረሻው የማይታወቅ ጩኸት የሕዝባችንን ፍዳ ዘላለማዊ አድርጎታል።
በቅርብ ዓመታት እንኳ መለስ ብለን ራሳችንን ብንታዘብ የጀመርነውን መጨረስ አንችልበትም። ለዛ የተዘጋጀ አደረጃጀትም ሞራልም ብቃትም ዝግጁነትም አልነበረንም።
 የ2008, 2009, 2010 እነዚያ ምድር አንቀጥቅጥ ትግሎችና አመፆች ዓላማ እና ግብ ምን ነበር? የመጨረሻ እቅድ ኢህአዴግን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዳይነሳ አድርጎ መቅበር አልነበር እንዴ??? እና እቅዳችን ማን በላው? ራሱ ኢህአዴግ። ማን ቀለበሰው? ራሱ ኢህአዴግ። ማን አከሸፈው? የኢህአዴግ የማታል ምላስ። አፈር ልሶ የመነሳት ብቃቱን በእኛ ሞት ላይ ተረማምዶ ተነሳ።
እነሆ 2011 የኢህአዴግ ሕይወት ቀጥሏል። የሕዝባችንም መከራና ሰቆቃ አምናዎችን በሚያስንቅ መልኩ እጥፍ ድርብ ሆኖ ቀጥሏል።
*****
ተግዳሮቱ እና መፍትሄው
*
1ኛ:- ለሕዝብ ተቆርቋሪ ምሁራን ከዳር ተመልካችነት ተላቀው እንደየ ሙያቸው ለሕዝብ ለውጥ መታገል ለነገ የሚባል አይደለም።
2ኛ:- መደራጀት። መደራጀት። መደራጀት። ከተደራጀህ በኋላ ለመደርጀት ጥርት ያለ ዓላማና ግብ ሊኖርህ ይገባል። ለዛ ነው ለሕዝብ ተቆርቋሪ ምሁራን ተ.ቁ 1 ላይ ያደረኩልህ።
3ኛ:- ለዓላማህ እና ግብህ እስከ መጨረሻው ታማኝ መሆን። በጠላትህ ላለመበላት ብቸኛው አማራጭህ ነውና። ከአባትህ ከፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ መስዋእትነት በላይ ለዓላማ መታመን ምሣሌ የሚሆን ማስረጃ የለም። ጀግናው ፕሮፌሰር የጀመሩትን ዓላማ ለመተው ከጠላት ብዙ መልካም ዕድሎች ተሰጥቷቸው ነበር። ዝርዝሩን ስለምታውቀው ገብቶሃል።
4ኛ:- በመላው ሕዝብህ ውስጥ በፈተናዎች የማይቆራረጥ ኔትወርክህን ለመዘርጋት ተዘጋጅ። በመውደቅ መነሳት አምነህ ወደ ግብህ የሚወስዱ ስልቶችን ንደፍ። ትንንሽ ድሎች አያዘናጉህ።
5ኛ:- ጠላትህን የሚርድ አጀንዳ ፍጠር አጀንዳ ፈፅሞ አትቀበል። በጊዚያዊ የጠላት ጥቃቶች ተደናግጠህ ሕዝብ አታስደንግጥ። የሰጡህን አትጉረስ። ከጎረስክ አላምጠህ ዋጥ ወይ ትፋ።
6ኛ:- ከወገንህ ጋር ተደማመጥ አንድ ሁን ቢያጠፉ እንኳ ለጠላት አሳልፈህ አትስጣቸው። አለያ ጠላት በቀደድከው ገብቶ ይከፋፍልሃል።
7ኛ:- ከሞቱት ብቻ ሳይሆን ከህያውያንም ICON ይኑርህ። አይከኖችህን ተንከባከብ። ከሁሉም በላይ ግን አይከኖችህን ሰብስባቸውና የሆነ ድርጅት እንዲፈጥሩ አድርግ።  ስማኝ ጀግኖችህ እየባከኑ ነው። አንድቀን ጠላትህ ቀንቶት ካጠፋቸው ያንተም መጥፊያ ነው ።እንዲያውም ብልጥ ከሆንክ አንተ ከመደራጀትህ በፊት እነሱን አደራጃቸውና የሆነ ተቋም ይሁኑ።  ከግለሰብ ጀግንነት ወደ ተቋም ጀግንነት ቀይረህ ትንሳኤህን አፋጥን። ደጀናቸው ሁን። ቤተሰባቸውን ሕይወታቸውን ጠብቅ። በቅርብህ አድርጋቸው።
እነ  ቬሮኒካ መላኩ ሚኪ አምሐራ ቹቹ አለባቸው ህሊና ቀበሮ ጠቢቡ አማራ መላኩ አላምረው ጋሻው መርሻ ጋሻው አቸነፈ ቶማስ ጀንጃው ዶር ደሳለኝ ጫኔ  ረፕሮ በለጠ ሞላ ክርስቲያን ታደለ መልካሙ ተሾመ (ሌሎች የአብን አመራሮች) እነ ጄኔራል አሳምነው ፅጌ ኮረኔል ደመቀ ዘውዱ ንግስት ይርጋ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ዘመነ ካሴ እስክንድር ነጋ ወዘተ ወዘተ ሰብስበህ ተቋም አድርጋቸው። አንበሳዎችህን ሰብስበህ በኔትወርክ ጫካ ተክለህ አስፈሪ ተቋም አድርጋቸው። እንዲህ ስታደርግ ጫካው ይፈራል። ይከበራል። በአንበሶችህ ምክክር ክርክር ተወስኖ ይሰጥሃል። እሱን ትፈፅማለህ። የኢኮኖሚ መስመር የትግል ስልት የፖለቲካ ርዕዮት የሕዝብ አስተዳደር የፀጥታ ተቋማት አደረጃጀት የማህበራዊ እፎይታ ፓሊሲ ስትራቴጂ ወዘተ ወዘተ በየሙያው እየተቀረፀ ከአንበሶቹ ይሰጥሃል ትተቻለህ ትፈፅማለህ የፈፀምከውን አስተችተህ ትሰጣለህ። ዴርቶጋዳ ከደበረህ እስራኤል እንዴት ሀያል ሆነች የሚል መፅሐፍ ፈልገህ አንብብ።
8ኛ:- በሌሎች ከኔ በሚልቁ ሙህራኖች እና በተጠኑ ሰነዶች ላይ ያሉ  መፍትሔዎች ይጨመሩበት።በዚሁ እየየገዳሙ እያልን ከቀጠልን ግን ኢህአዴግ እልልል እያለ ያፈራርሰናል።
Filed in: Amharic