>

"ግንቦት 20 - "አይ ኢትዮጵያ ለካ ሰው የለሽም!" (አብርሃም በላይ)   

“ግንቦት 20 – “አይ ኢትዮጵያ ለካ ሰው የለሽም!” 
አብርሃም በላይ     
“ሰዎች መለስ ዜናዊን ከኮለኔል መንግስቱ ኃ/ማርያምና አልፎ ተርፎም ከዓጼ ኃ/ስላሴ ጋር “ኢትዮጵያዊ ዲክታቶር” ብለው በአንድ ቅርጫት ውስጥ ይከቱታል። ይህ አባባል ሀቅነት አለውን? ይነበብ!
መለስ ዜናዊ 1) ሁለት መፃህፍት ጻፈ። ሁለቱንም ተጀምረው እስኪያልቁ በ”ኢትዮጵያ ቅኝ አገዛዝ ስር ለዘመናት ስለማቀቀቸው” ስለኤርትራ ነፃነት የሚያወጉ ናቸው።
2) አንድ ሰው ህወሃትን ሲቀላቀል የመጀመሪያ የሚቀርብለት ጥያቄ በኤርትራ ነፃነት ታምናለህ ወይ የሚል ነው።
3) ማንም የህወሃት አባል በኤርትራ ላይ – ለምሳሌ ኢትዮጵያን ደግፎ ስለ ወደብ አስፈላጊነት ካነሳ – ወድያው ይታሰራል፣ ቶርቸር ይደረጋል፣ በእምነቱ ፅኑ ሆኖ ከተገኘ  ይገደላል።
4) 70ሺ የኢትዮጵያ ወጣት ተሰውቶ ያመጣውን ወታደራዊ ድል አዲስ አበባ ላይ ሆኖ፣ “ያይናቸው ቀለም ካላማረን እናባርራለን” እያለ እያጭበረበረ፣ በኢትዮጵያ ወታደር ተገርፎ ወደ ሱዳን ሲሸሽ የነበረውን የሻቢያ ወታደር አራት ኪሎ ላይ ሁኖ፣ ሬድዮ ላይ ወቶ “ጦርነቱ በ24 ሰዓት ይቆማል” ብሎ የጠላት ጦር እንዲመለስ አደረገ።
መጨረሻም ኢትዮጵያን እያዋረደ መኖር ነበር አላማውና፣ በራሱ አነሳሽነት ዘ ሔግ ፍ/ቤት እንዲቆም አስወስኖ፣ በየማነ ጃማይካ የሚመራው የኤርትራ ቡድን ከአዲስ አበባ ወደ ዘ ሔግ ተጓዘ። ሌላው ኤርትራዊው ቡድን ከአስመራ ተነስቶ ዘ ሔግ ገባ። ገለልተኛ ዳኞቹ የሁለት ኤርትራውያን ወግ መሆኑን ተገንዝበው፣ “አይ ኢትዮጵያ! ለካ ሰው የለሽም” ብለው ፋይሉን ኤርትራን በሚጠቅም መንገድ ዘጉ።
አሁን ከኢሳያስ አፈወርቂ ሺ ጊዜ ጽንፈኛ ኤርትራዊ ብሄርተኛ የነበረው፣ ማንም የህወሃት “ባለስልጣን” ትግሬ “ስልጣኑን” የመለስ ትእዛዝ ማክበር እንጂ ሌላ “ሓባ ስልጣን” እንዳልነበረው ዛሬ በሃፍረት ሻማ ተከናንቦ የሚያስታውሰውን፣ በብቸኝነት 100% ስልጣን ተቆጣጥሮ “ኦሮሚያ” የሚል እና ሌሎች ትንንሽ፣ ሲጋጩ እንዲኖሩ ተደርገው ተጠፍጥፈው የተሰሩ አገሮችን ፈጥሮ፣ የጥላቻ መርዙን ሲረጭበን የኖረው መለስ ዜናዊ የገዛበት ዘመን ምን ግራ የሚያጋባ ሆኖ ነው “የጠላት አገዛዝ ዘመን” ተብሎ በታሪክ የማይዳኘው?
ይህ ጉዳይ መለስን በጠላትነት ፈርጆ ቁጭ ለማለት ሳይሆን፣ ከተፈረጀ በኋላ መለስ ከኤርትራ እና ከሱዳን ጋር የተፈራረማቸውን ኢትዮጵያን ክፉኛ የሚጎዱ ውሎች ኢትዮጵያን ሊወክሉ እንደማይችሉ ለማስረገጥ (to make them null and void)፣ ሌሎች እንደ ዶ/ር አብይ አህመድ ከመሪ፣ እንደ ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ እንደ ዜጋ የመለስን ውሎች ለማጽደቅ የሚጣደፉትን አደብ እንዲገዙ፣ እንደ ዶ/ር ያቆብ ወ/ማርያም በፅኑ ኢትዮጵያዊነት ትግሉን እንዲመሩ ለማድረግ፣ እና እንደ ቀይ ባህር የአፋር አገርን በህጋዊ መንግድ ከነ አሰብ ወደቡ ወደ ታሪካዊት ባለቤቷ ወደ ኢትዮጵያ ለማስመለስ በሚደረገው ትግል ለቀጣዩ ትውልድ ፅኑ የህግና የታሪክ መሰረት ሆኖ ስለሚያገለግል ነው”
የኢትዮጵያ ክብር በልጆችዋ ፅኑ ተጋድሎ ይመለሳል”
Filed in: Amharic