>

«የጎባጣ አሽከር ጎንበስ ብሎ ይሄዳል፤ ምነው ቢሉት ጌታዬን ለመምሰል!!!» (አቻምየለህ ታምሩ)

«የጎባጣ አሽከር ጎንበስ ብሎ ይሄዳል፤ ምነው ቢሉት ጌታዬን ለመምሰል!!!»
አቻምየለህ ታምሩ
አምባቸው መኮንን የሚባለው የአማራ ሕዝብ ሸክም ከሰሞኑ ደብረ ታቦር ላይ ባደረገው ንግግር «አዲስ አበባ ከኦሮምያ ለምታገኘው ውኃ ልዩ ጥቅም ብትሰጥ ምናለበት?” ሲል አምቦ ላይ በሞቅታ የተናገረውን ድንቁትውን ደግሞታል። «ተሳስተሀል?! ብለው ትችት ለሰነዘሩበት የደብረ ታቦር ልጆች ትክክል ስለመሆኑ ራሱ ሲከላከል «ከሕገ መንግሥቱ የወጣ አንዳች ነገር አልተናገርሁም» በማለት መልሷል።
የአምባቸው ድንቁርና የሚመነጨው እነ በረከት ሰምዖን ድንጋይ ማምረቻ ውስጥ ከተውት በጭንቅላቱ ያጨቁበትን ቆሻሻ ለማራገፍ አለመቻሉና አለመፈለጉ ነው። አሁንም የሚያስበው እነ በረከት ካድሬ ሊያደርጉት ባስገጠሙለት ጭንቅላቱ ነው። ካድሬ የሆነ ሰው ዘመን ቢለወጥና አለም ቢቀየር ጌታ ይቀይር እንደሆነ እንጂ ተፈጥሯዊ ስሪቱ የሆነውን ካድሬነቱን አይቀይረውም። ካድሬ በአማርኛ ሎሌ ወይንም አሽከር ማለት ነው። ባገራችን «የጎባጣ አሽከር ጎንበስ ብሎ ይሄዳል፤ ምነው ቢሉት ጌታዬን ለመምሰል» እንደሚባለው አምባቸው መኮንንም ለማወቅ ሳይሆን በረከትን ለመምሰል የበረከትን በፋብሪካ የተመረቱ ቃላቶች በመሸምደድ እድሜውን የፈጀ ሽማግሌ ካድሬ ነው። በረከት በዐቢይ ሲቀየር አምባቸውም የዐቢይ ጉዳይ ፈጻሚ ሆኖ አሰላለፉን አስተካክሏል። እሱ ማሰብ ስለማይችል ዐቢይ የተናገረውን በየመድረኩ ያለ ርሕራሔ ሲደግም ይውላል።
በመሰረቱ ካድሬ መድገም እንጂ እንደ አምባቸው ቢገለምስ እንካ ማሰብና ማሰላሰል አይችልም። ካድሬነት ማነብነብ እንጂ ማንበብ ባሕሪው አይደለም። ማሰብ ሀሳብ ፍለጋ አእምሮን ከጥግ እስከ ጥግ መወርወር፣ ማሰላሰልና መቆዘም ይጠይቃል። ከሁሉ በላይ ሀሳብ ዝግጅት ይጠይቃል። መዘጋጀት ማለት ደግሞ በአብዛኛው ማንበብ ማለት ነው። አንድ ሰው «አነበበ» ማለት ሀሳብ አፍላቂ ሆነ ማለት አይደለም። አንድ ሰው «አነበበ» ማለት ለሀሳብ ማፍለቅ ሁኔታዎችን አመቻቸ ማለት ነው። ማንም ሰው ሀሳብ ይመጣለታል። ሕጻናትም ቢሆኑ ሀሳብ ይመጣላቸዋል። ግን የሀሳብን ጥሩነት ደረጃ በትክክልና በፍጥነት ለመገመት አስቀድሞው አንብቦ መዘጋጀት ያስፈልጋል።
ሀሳብ ማለት መንገድ ላይ የሚገኝ ወርቅ ማለት ነው። ወርቅን ካላወቅን ድንጋይ ብናገኝ ወርቅ ብናገኝ ልዩነት የላቸውም። ስለዚህ አንድ ሰው ሁል ጊዜ በእውቀት የታነጸ የሀሳብ ባለቤት ለመሆን ራሱን በንባብ ማዘጋጀት አለበት። እንደ አባቸው ያለ ራሱን በንባብ ያላዘጋጀ የበረከት ካድሬ ሀሳብ እንኳ ቢመጣለት ተንኖ ይጠፋበታል እንጂ ጥቅሙን ሊያውቀውና ሊያደረጀው አይችልም። አንድ ሰው ወርቅ ቢያገኝ ወርቅነቱን ካላወቀው በስተቀር ከድንጋይ ሊለለየው እንደማይችል ሁሉ ሀሳብም ያለ ንባብ ጠቀሜታ የለውም። ያላነበበ ሰው አለምን የሚለውጥ ሀሳብ እንኳ ቢያፈልቅ የሀሳቡ አለም ለዋጭነት ሊታወቀው አይችልም። ስለዚህ አንድ ሰው የሚያመነጨውን ሀሳብ ጠቀሜታ ለማወቅ አልያም እንደ ዐቢይ አይነት አፍ ነጠቆችን ዲስኩር ሳይሆን የጥራዝ ነጠቆችን እውቀት ለመቀበል በንባብ የበቃ መሆን አለበት! የሀሳብን ክብደት ማወቅ የሚቻለው በንባብ የበቃ ሰው ብቻ ነው።
አምባቸው ግን ድንቁርና ከሚሰጠው ድፍረት ውጭ በንባብ የተገነባ ሀሳብ የላትም፤ ብታገኘውም ልክ ወርቅና ድንጋዩን መለየት እንደማይችል ሰው ናት። ካድሬ መሆኑ የመድገም እንጂ የማሰብ ጸጋ አልተሰጠውም። ያነበበና የማሰብ ጸጋ ቢኖረው ኖሮ «አዲስ አበባ ከኦሮምያ ለምታገኘው ውኃ ልዩ ጥቅም ብትሰጥ ምናለበት?» ብሎ ሲናገር «ጣና በለስ፣ ግልገል በለስ፣ ተከዜ፣ ጢስ አባይ 1 እና 2፣ ጨሞጋ፣ ወዘተ. . . ለመላው ኢትዮጵያ መብራት ስለሚያቀርቡ ጣና በለስ፣ ግልገል በለስ፣ ተከዜ፣ ጢስ አባይ 1 እና 2፣ ጨሞጋ፣ ወዘተ ግልገል በለስ፣ ጢስ አባይ፣ ወዘተ የሚገኙበት የአማራ ክልልም ልዩ ጥቅም ያስፈልገዋል ማለት ነው፤ ሆኖም ግን አማራ ክልል ለሚያቀርበው መብራት ልዩ ጥቅም ስላልተሰጠው ኦሮምያ ክልል ውኃ ብቻ ስለሚያቀርብ ከሌሎች ክልሎች ተለይቶ ልዩ ጥቅም ለብቻው ሊከበርለት ይገባል የሚለው እስቤ ትክክል አይደለ» ብሎ የልዩ ጥቅምን ደንብ በመሰረተ ሀሳብ ደረጃ ውድቅ ያደርገው ነበር።
በእውነቱ ልዩ ጥቅም ያስፈልጋል ከተባለ ኦሮምያ ክልል የሚባለው ከአዲስ አበባ ይሰጠው ከሚባለው ጥቅም በላይ አማራ ክልል የሚባለው ኦሮምያ ከሚባለው ክልል የሚገባው ልዩ ጥቅም ይበልጣል። ኦሮምያ የሚባለው ክልል የሚጠቀመው መብራት የሚመጣው አማራ ክልል ከሚባለው ነው። ኦሮምያ ክልል የሚባለው የአዲስ አበባ ሕዝብ ከፍሎ ለሚጠጣው ውኃ ስላቀረበው ልዩ ጥቅም ይሰጠኝ ካለ ከውኃ በላይ ውድ የሆነውን መብራት ለሚያቀርበው የአማራ ክልል ለሚባለውም ልዩ ጥቅም መስጠት አለበት። በልዩ ጥቅም እሳቤ እንኳን ሊከፈለው ከሁሉም የወያኔ ክልሎች በላይ ከፋይ የሚሆነው ኦሮምያ የሚባለው ክልል ነው። አምባቸው መኮንን ግን የዐቢይ አሕመድ ጉዳይ ፈጻሚ እንጂ የአማራ ባለጉዳይ ስላልሆነ ይህንን ሀሳብ ሰዎች ቢያቀርቡለት እንኳ ሊገዛው አይችልም።
አምባቸው በደብረ ታቦሩ ስብሰባ «የአማራን ሕዝብ መብትና ጥቅም አሳልፎ ለመስጠት ከማንም ጋር አንደራደርም፤ በዚህ እንዳትጠራጠሩን» ሲልም ተደምጧል። ደንቄም! ይህንን የአምባቸውን ንግግር የተናገሩት ዶክተር አሰፋ ነጋሽ አልያም፣ ዶክተር ሀብታሙ ተገኜ አልያም አቶ ማሸት አማረ ቢሆኑ ኖሮ የትገባ እንጂ ጥያቄ ባልተነሳ ነበር። «የአማራን ሕዝብ መብትና ጥቅም አሳልፎ ለመስጠት ከማንም ጋር አንደራደርም፤ በዚህ እንዳትጠራጠሩን» የሚለውን ቃል የተናገረው የአማራን ሕዝብ እንደ ልጃገረድ የደፈረውን ፋሽስት ወያኔና ናዚ ኦነግ ሕገ መንግሥት የሚሉትን የቅሚያና የግድያ ደንብ እንደ ሕጋዊ ሰነድ ተቀብሎ ሊያስፈጽም አንጠልጥሎ የሚዞረው አምባቸው መኮንን መሆኑን ስናውቅ ግን ንግግሩ እጅጉን ቧልት ይሆናል።
«የአማራን ሕዝብ መብትና ጥቅም አሳልፎ ለመስጠት ከማንም ጋር አንደራደርም፤ በዚህ እንዳትጠራጠሩን» የሚለን አምባቸው አምቦ ላይ በሞቅታ የተናገረውን እምነቱን «ከሕገ መንግሥቱ የወጣ ንግግር አላደረግሁም» የሚለን ጉድ ነው። ከአማራ አንጻር የተጻፈው ሕገ አራዊት ያወጀው ልዩ ጥቅም እንዲከበር እታገላለሁ የሚለን አምባቸው ነው እንግዲህ «የአማራን ሕዝብ መብትና ጥቅም አሳልፎ ለመስጠት ከማንም ጋር አንደራደርም፤ በዚህ እንዳትጠራጠሩን» የሚለን።
ልዩ ጥቅም የሚባለው የአፓርታይድ እሳቤ መሰረቱ አማራና የተቀረውን አዲስ አበቤ የአዲስ አበባ መጤና ሰፋሪ አድርጎ በማሳነስ አገር አልባ የማድረግ ዘረኛነት ነው። «የአማራን ሕዝብ መብትና ጥቅም አሳልፎ ለመስጠት ከማንም ጋር አንደራደርም፤ በዚህ እንዳትጠራጠሩን» የሚለን አምባቸው መኮንን ኦሮምያ የሚባለው ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለው ልዩ ጥቅም ሳይሸራረፍ እንዲከበር የሚታገለውኮ አማራንና የተቀረውን አዲስ አበቤ ነው። አምባቸውና የወንጀል ባልደረቦቹ ደልቷቸውና ተዘባነው የሚኖሩት የአማራ ገበሬ በሚከፍለው ግብር ቢሆኑም አምቦ ላይ በአንደበቱ እንደተናገረውና ደብረ ታቦር ላይ በድጋሜ እንዳረጋገጠው እሱና የወንጀል ባልደረቦቹ ግን የሚታገሉት እሱ እንዳለን «የአማራን ሕዝብ መብትና ጥቅም አሳልፎ ለመስጠት ከማንም ጋር አንደራደርም፤ በዚህ እንዳትጠራጠሩን» ለአማራ ሳይሆን አማራን ነው።
አምባቸው በየ መድረኩ የሱንም ሆነ የአማራ ባለጉዳይ ያልሆነውን ድርጅቱን መንፈስና ተግባር የማይወክል ንግግር ሲያደርግ «የአማራን ሕዝብ መብትና ጥቅም አሳልፎ ለመስጠት ከማንም ጋር አንደራደርም፤ በዚህ እንዳትጠራጠሩን» የሚለው ዲስክሩ የመጀመሪያው አይደለም። ባለፈው ሰሞንም የዓድዋውን ጀግና የአንጎለላው አማራ ፊታውራሪ ገበየሁ ተክሌ ወደ አድዋ ሲዘምቱ «ጥይት በግንባሬ እንጂ በጀርባዬ ከመታኝ እንዳትቀብሩኝ» ሲል የተናገረውን ታሪካዊ ንግግር በመድገም «ጥይት በግንባሬ እንጂ በጀርባዬ ከመታኝ እንዳትቀብሩኝ ከሚል ሕዝብ ተወልደን ጥቅሙን ለጨዋታና ለቀልድ አናቀርብም» ብሎን ነበር። የታላቁ አርበኛ የፊታውራሪ ገበዬሁ ታሪካዊ ንግግር ፋሽስት ወያኔን እንደ አምላክ ተቀብሎ ለሀያ ሰባት ዓመታት ሙሉ እስኪያልበው ሲያገለግል በኖረው አምባቸው መኮንን አፍ ሲደገም ክብሩን ያጣና ቧልት ይሆናል።
እስቲ ጠይቁት?! አምባቸው መኮንን ባለፉት ሀያ ሰባት በአማራ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት እያካሄደ ታሪኩን ሲያጠፋ የኖረውን ፋሽስት ወያኔን እስኪያልበው ሲላላክና ሲያገለግል የኖረው «ጥይት በግንባሬ እንጂ በጀርባዬ ከመታኝ እንዳትቀብሩኝ» የሚል ሕዝብ ስላልፈጠረው ነው ማለት ነው? ነው «ጥይት በግንባሬ እንጂ በጀርባዬ ከመታኝ እንዳትቀብሩኝ» የሚል ሕዝብ እንደፈጠረው የተገለጠለት ከ27 ዓመታት በኋላ በዚህ ዓመት ነው?
ባጭሩ አምባቸው መኮንን ዐቢይ አሕመድ ልዩ ጥቅም ተብዮውን የአማራን ሕዝብ ወክሎ እንዲያስፈጽም የጎለተው ካድሬ እንጂ የአማራ ሕዝብ ባለጉዳይ ባለመሆኑ መሄጃውን መፈለግ ይኖርበታል። የበረከት ካድሬዎች የሆኑት ሌሎች ብአዴኖችም  ለአማራ ሕዝብ ውለታ ሊውሉለት የሚችሉት  ከአማራ ሕዝብ ጫንቃ ላይ ሲወርዱ ብቻ ነው:: በተለይ  አምባቸው  አማራ ክልል በሚባለው ላይ ተጣብቆ ገደል ሳይገባ መሄጃውን ቢፈልግ  ከሁሉ በላይ ለራሱም ይበጀዋል።  በእኔ እምነት  አምባቸው  የጎለተው የጌታው የዐቢይ አሕመድ «አደራ» ስላለበት ይህንን የሚያደርግ አይመስለኝም!  ሆኖም ግን ትናንትን ዛሬ አይደለም። ትናንት  የፋሽስት ወያኔ ባለአደራ ሆኖ ደልቶት ተዘባኖ  እንደኖረው ዛሬም የዐቢይ ባለአደራ ሆኖ መኖር አይችልም። ዛሬ ላይ እሳት የሚተፉ አማራ ልጆች ደርሰዋል። የዐቢይ አገልጋይ መሆን እሳት ከሚተፉ የአማራ ልጆች ቁጣ እንደማይድን በእርግጠኛነት መናገር ይቻላል። ይኼው ነው!
Filed in: Amharic