>
10:40 am - Friday May 20, 2022

“ሁሌም ቢሆን ከእውነትና ከመርህ ጋር እንቆማለን!!!”  ከኢሳት ዲሲ ስቱዲዮ ጋዜጠኞች የተሰጠ መግለጫ

“ሁሌም ቢሆን ከእውነትና ከመርህ ጋር እንቆማለን!!!”
 
ከኢሳት ዲሲ ስቱዲዮ ጋዜጠኞች የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴሊቭዥን እና ሬዲዮ /ኢሳት/ላለፉት 9 ዓመታት የሕዝብ ድምጽ፥ አይንና ጆሮ በመሆን ለነጻነት የሚደረገውን ትግል ሲደግፍና ለታፈነው ዜጋ ሁሉ መረጃ በመስጠት ወደር የለሽ አስተዋጽኦ ማድረጉ ይታወቃል።የዚህ እልህ አስጨራሽ ትግል ዋነኛ አላማም በየትኛውም ተቋም ወስጥ ግለሰቦችን ለስልጣን ማብቃት ሳይሆን በኢትዮጵያ ፍትህ፥ዲሞክራሲና አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ሲባል እንደነበርም አይዘነጋም ።
በዚህ የብዙዎችን መስዋዕትነት በጠየቀው የትግል ሂደት ውስጥ ሕዝቡ የከፈለው ዋጋ ከምንም ነገር ጋር የሚመጣጠን እንዳልሆነ ቢታወቅም የኢሳት ድጋፍ ኮሚቴና እና በውስጡ የምንገኝ ጋዜጠኞች ያደረግነው አስተዋጽኦና አበርክቶ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ዘንድ የሚረሳ ጉዳይ እንዳልሆነም እንገነዘባለን።
የሕዝባችንም ሆነ የኢሳት ድጋፍ ኮሚቴዎችን እገዛ በመንተራስ እና በተቋሙ ውስጥ ስንሰራ የነበርን ጋዜጠኞች የራሳችን እና የቤተሰባችን ሕይወት በመጉዳት የሀገርንና የሕዝብ ጥቅም በማስቀደም ትልቅ ዋጋ ከፍለናል ብለን እናስባለን።
በዚህ አስቸጋሪና ዋጋ የከፈልንበት ዓላማ ውስጥ ስንገባም በኢትዮጵያ የሚገኙ ቤተሰቦቻችንን ሕይወት አደጋ ላይ በመጣል ጭምር እንደነበርም ለማስታወስ እንወዳለን። ይህን ሁሉ ዋጋ ስንከፈልና እስከዛሬ ድረስ በዓላማችን ጸንተን ስንቆም ግን የእናንተ የኢሳት ቤተሰቦችና ድጋፍ ሰጭዎች እገዛ ባይጨመርበት ኖሮ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ የማንችል መሆናችንን እንደምንገነዘብም በዚህ አጋጣሚ ለማሳወቅ እንፈልጋለን ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ያደረገውን መራራ ትግል ተከትሎ በአሁኑ ጊዜ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ከመጣ በኋላ ሂደቱን በመደገፍና ችግሮች ሲኖሩም በመተቸት የሚጠበቅብንን ሙያዊ እገዛ መስጠታችንን እንደቀጠልን  ሁላችሁም የምታውቁት ጉዳይ ነው። ሁሌም ስንመኘው እንደነበረው ብዙ መስዋዕትነት ከተከፈለ በኋላ በተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ በሀገራችን ኢትዮጵያ ፍትህ፥ ዲሞክራሲና ሰላም ሰፍኖ የምናይበት ጊዜ እሩቅ እንደማይሆንም ትልቅ ተስፋን ሰንቀን መቆየታቸንም የሚታወስ ጉዳይ ነው።
በዚህ ተስፋ ውስጥ እያለን ግን በለውጥ ሂደት ውስጥ የሕዝብ መፈናቀል፥ የግጭቶች መበራከትና ይሕንኑ ተከትሎም በርካታ ወገኖቻችን መገደላቸው በመቀጠሉና ኢፍትሐዊነት እያየለ በመምጣቱ ባለብን ሙያዊ ግዴታ መሰረት ሁኔታው እንዲስተካከል ስንጠይቅ መቆየታችንም ይታወሳል።በተለይ ደግሞ በለገጣፎና በጌዲዩ እንዲሁም በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የደረሰውን የህዝብ ሰቆቃ በኢሳት የማጋለጥ ስራ ሲጀመር የአፈና ስራ ለማከሄድ በመሞከሩ የተወሰንን ለመርህ የቆምን ሰዎች ሙያዊ ግዴታችንን ለመወጣት ስንሞክር ቀሪዎቹ ከለውጥ ሀይሉ ጋር ቆመናል የሚሉ ባለደረቦቻችን ሳይቀሩ የዘገባ ስራችንን ለማፈን ሞክረዋል።
 በተለይ ደግሞ እኛ በዋሽንግተን ዲሲ የምንገኝ የኢሳት ጋዜጠኞች እነዚህ ችግሮች እንዲስተካከሉ አበክረን በመጠየቃችን ሁኔታው ያልተዋጠላቸው በቦርድ ስም የተቀመጡ የኢሳት አመራሮች   በተለይም በውጭ ሀገር ያሉትን የኢሳት ስቱዲዮዎች በእጅ አዙር የመዝጋት እርምጃ ወስጥ መግባታቸውን ለመረዳት ችለናል።ለዚህ ዓላማቸው ማስፈጸሚያም በኢሳት ባልደረቦች መካከል ክፍፍልን በመፍጠርና በተቋሙ ወስጥ የገንዘብ አቅም ተዳክሟል በሚል ሰበብ ድርጅቱን ለመዝጋት ሲንቀሳቀሱ የሕዝብን ፍላጎት እና የተቋሙን ሕልውና በማስቀደም ትግስት የተሞላበት የወስጥ ትግል በማድረግ ስንቀሳቀስ ቆይተናል።
ይህን የውስጥ ትግላችንን ወደ ሕዝብ አለመውሰዳችን እንደ ድክመት በመቁጠር ጋዜጠኞችንና መላውን ሰራተኛ ሳያማክሩ በቦርድ አባልነት ስራውን ሲመሩ የነበሩ ግለሰቦች  የኢሳትን የውጭ ስቱዲዮዎች ለመዝጋት ወስነው ሲያበቁ  ሁኔታው በእቅድ እንዲመራ የሕዝብ ጥያቄ እያየለ ቢመጣም በቸልተኝነት ወደ አዲስ አበባ በመንቀሳቀስ ድርጅቱን በሚጎዳ ተግባር ውስጥ ሲንቀሳቀሱ እንደነበርም ለመረዳት ችለናል።
ያለምንም ጥናትና ዝግጁነት ሰራተኛውን ሳያሳውቁ በአዲስ አበባ ወስጥ ስራ እንዲጀመር አድርገዋል። በዚሁም በውጭ የሚገኙ ስቱዲዮዎችን ለመዝጋት ሲሉ ጋዜጠኞችን ሲከፋፍሉ ከቆዩ በኋላ በብዙዎች ዘንድ ታቃውሞ ሲገጥማቸው ሰራተኛውን ደሞዎዝ መክፈል አንችልም በማለት የማባረር እርምጃ እንደሚወስዱ ለሰራተኞች ሲያሳወቁ ሊሎች አማራጮችን እንዲያዩ እና ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት እንዲመክሩበት እንዲሁም ኢሳት የሕዝብ ሆኖ እንዲቀጥል ቢጠይቁም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
ይባስ ብሎም ከዚህ በፊት ባልታየ ሁኔታ የጋዜጠኞችን የሙያ ነጻነት በመጻረር ፕሮግራሞች እንዳይተላለፉ ከማገድ ጀምሮ ለውጥ አደናቃፊ በሚል ሰበብ የተለያዩ እርምጃዎችንም ሲወስዱ ቆይተዋል።
በሕዝብ ስም የተቋቋመን ሚዲያ በባለቤትነት እኛ ነን የመሰረትነው የሚል መግለጫ በመስጠት ከፖለቲካ ድርጅትነት ከስመናል ያሉ አካላትም በተዘዋዋሪ መንገድ የራሳቸውን ሰዎች በመመደብ አሁንም ኢሳትን ለመቆጣጠር በመሞከራቸው ይህም ተገቢ እንዳልሆነ በዋሽንግተን ዲሲ ጋዜጠኞች በኩል ሜይ 10/2019 ዓም ይህንኑ የሚቃወም መግለጫ ማውጣታችንም ይታወሳል።
በዚህ መግለጫ ያልተደሰቱት የኢሳት ቦርድ አመራር ነን የሚሉት እነዚሁ አካላት በገቡት ቃል መሰረት ኢሳትን ለሕዝብ እንዲያስርክቡና በድርጅቱ ስም ከተለያዩ ወገኖች የተሰባሰበው በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የት እንዳደረሱት በመጠየቃችን እንዲሁም  በፋይናንስ እጥረት ስም ሰራተኞችን እንቀንሳለን ማለታቸውም ትክክል እንዳልሆነ እና ሃላፊነታቸውን ለሕዝብ እንዲያስረክቡ ባለፈው ሀሙስ ማለትም እኢአ ሜይ 28/2019 በጻፍንላቸው ደብደቤ ብንጠይቃቸውም ለዚህ ጥያቄያችንም ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በሚከተሉት የዋሽንግተን የዲሲ ኢሳት ጋዜጠኞች ላይ በስራ ላይ እያሉ ድንገት ከስራ የማሰናበትና ለፖለቲካዊ ሴራቸው ማስፈጸሚያ እንዲረዳ የመጀመሪያ ከፋፋይ  እርምጃ ስማቸው በውል ባለተገለጹ የቦርድ አካላት ተወስዶባቸዋል።እነዚሁም፦
1.ምናላቸው ስማቸው
2.ሀብታሙ አያሌው
3.እየሩሳሌም ተክለጻዲቅ
4.ጌታቸው አብዲና
5. ልዩ ጸጋየ እና ሌሎችንም ጨምሮ ነው።
ይሕ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ለማፈን የሚደረገው እርምጃ ኢሳትን በመዘጋት የሚደመደም እንደሚሆን   ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው ስምምነቶች ውሳኔ ማሰለፋቸውንም ለመረዳት ችለናል። ስለሆነም በተለያዩ ሰበቦች ኢሳትን የማፍረሱ እርምጃ ተጠናክሮ በመቀጠሉና ከበስተጀርባ የሚካሄዱ ሴራዎች መኖራቸውን ስለደረስንበት ይሕንኑም ለሕዝብ ማሳወቅ አስፈላጊ ሆኖ በማግኘታችን ከዚህ ቀደም በጻፍነው ደብዳቤና ባሳለፍነው ውሳኔ መሰረት እኛ ከዚህ በታች ስማችን የተገለጸውና ፊርማችንን በዚህ መግለጫ ላይ ያሰቀመጥን ጋዜጠኞች ምንም እንኳን ከኢሳት ተገፍተን ብንወጣም ተቋሙን ለመዝጋት የተያዘውን የፖለቲካ አቋም በመቃወም ስራችንን  በሌላ መንገድ አጠናክረን የምንቀጥል መሆናችንን  እንገልጻለን።በዚህ አጋጣሚም ለሕዝብ ያለንን ወገተኝነት እያረጋገጥን ቀጣዩን ሂደታችንን በተመለከተ ከሕዝብ ጋር ተመካክረን ውሳኔያችንን በተወካዮቻችን አማካኝነት የምናሳወቅ መሆናችንን በዚሁ አጋጣሚ እንገልጻለን።
ማስታወሻ ፦ ለኢሳት ቦርድ ከዚህ ቀደም ያቀረብነው ደብዳቤና የስም ዝርዝራችን ከዚህ መግለጫ ጋር ታያይዟል።
‘’ሁሌም ቢሆን ከእወነትና መርህ ጋር እንቆማለን’’
  በዋሽንግተን ዲሲ የኢሳት ጋዜጠኞች
1.ርዕዮት ዓለሙ
2.ምናላቸው ስማቸው
3.ኤርሚያስ ለገሰ
4.ተወልደ በየነ
5.ሐብታሙ አያሌው
6.እየሩሳሌም ተክለጻዲቅ
7.ልዩ ጸጋዬ
8.ግርማ ደገፋ
9.ብሩክ ይባስ
እና ሌሎችም……………

Filed in: Amharic