>

የማይሰበረው ፅኑው ሰው!!! (ደሴተ ኢትኦጵ)

የማይሰበረው ፅኑው ሰው!!!

.ደሴተ ኢትኦጵ
ሕወሓትን በከፈሉት መስዋእትት ገፍትረው ከጣሉትና ይህን ለውጥ አምጠው ከወለዱት ጀግና ታጋዮች መካከል እስክንድር ነጋ አንደኛው ነው ። እስክንድር ለሕወሓታውያን አገዛዝ የጎን ውጋት ሆኖ ኖሯል ። እስክንድር ነጋ  በፅናቱና ከእውነት ጋር ባለው ቁርኝት የተወዳሽ ስብእና ባለቤትም ነው ። በፈተና የማይሰበር ፣ የማይታጠፍና የማይልፈሰፈስ እንደብረትም  የጠነከረ ስለመሆኑ ወዳጆቹ ብቻ ሳይሆኑ አሳዳጆቹም ያውቃሉ ። ለዚህም ነው ” የሕወሓትን የግፍ አገዛዝ አልቀበልም ! ” ብሎ የታገለው ፤ በዚህም ነው ያንን ሁሉ  መራራ መስዋእትነት የከፈለው ።
.
ወያኔ እስክንድርን ለመስበርና ለማንበርከክ ያልፈፀመበት ግፍ የለም ። ግፉ ከሱ አልፎ መላውን በተሰቡ ጎብኝቷል ። ሰርካለም የእስክንድር ባለቤት ልጇን ናፍቆት እስክንድርን አምጣ የወለደቺው የሕወሓት ግፍ በሚቀዳበት ከርቸሌ ውስጥ ነው ። በኢትዮጵያውያን ባሕል የተከበረውን የአራስነት ወቅቷን በዚያው ከርቸሌ እንድታሳልፍ ግፈኞቹ እነመለስ ፈርደውባታል ። ይህ ሁሉ የተደረገው እስክንድርን ከእውነት መስመር ፈልቅቆ ለማውጣት ነበር ፤ ይህ ሁሉ የተፈፀመው እስክንድር ከቆመለት የእውነት መስመር አልታጠፍ በማለቱም ጭምር ነበር ።
.
እስክንድር ለዚህ ለውጥና በዚህም ለውጥ ዙፋን ላይ ለወጡት ቡድኖች ባለውለታ ነው ፤ ሕወሓት እንዲንኮታኮት እሱ በግሉ ያዋጣው አስተወፅኦ ግዙፍ ነው ። እድለቢሷ ኢትዮጵያ ዘላለሟን የገደላት አለያም ሊነጋ ሲል ብቅ ያለ ” የድል አጥቢያ አርበኛ ” አይኑን በጨው እጥቦ ፣ እጁንም አለቅልቆ  የሚበላት የድግስ ማእድ አይነት ሆና ነው እንጂ ለእስክንድር ውለታ ምላሹ ይህ አልነበረም
.
ዛሬ ወያኔ እስክንድርን በመሳሰሉ የትግሉ ፊት አውራሪዎችና የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግልና መስዋእትነት ከቤተ-መንግስት ቢባረርም አስተሳሰቡ ከዙፋኑ አካባቢ የራቀ አይመስልም ። ዛሬም ” መንገድም ፣ እውነትም እኔ ነኝ ! ” የሚል አስተሳሰብ እየገነገነ ነው ፤ ዛሬም ” ስንናገር አድምጡ እንጂ … አትናገሩ ! ” የሚል መንፈስ እየተወራጨ ነው ፤ ዛሬም የአድሎ አገዛዝ አለ ፤ ዛሬም አንዱ ልጅ ሌላኛው የእንጀራ ልጅ ፣ አንዱ አጥፍቶም የሚሞካሽበት .. ሌላው ስለእውነት በመቆሙ የሚሳደድበት ተግባር እየታየ ነው ። ይህ መሰል አገዛዝ መሬት ወርዶ በእግሩ እየተራመደ መምጣቱን የሚያስረዱ ብዙ ማስረጃዎችም እያየን ነው  ።  ከነዚህ ውስጥ የእስክንድር አፈና አንዱ ነው ። እስክንድር ….”  አትናገር ፣ አትሰብሰብ ፣ አትደራጅ (አታደራጅ ) ! ” እየተባለ ነው ።
.
ገዢዎቻችን እስክንድርን ላያቆሙት ሠንገድ እየዘጉበት ፤ ሕጋዊ ያልሆነ እንቅፋት በየመንገዱ እያስቀመጡበት ነው ። መንገድ መዝጋት ፣ አዳራሽ መከልከል ፣ እንዳትናገር ማለት ፣ አዋኪ መንጋ ማሰማራት ፣ ጋዜጣዊ መግለጫ ማገድ ፣ እስክንድርን ከአላማውና ከእውነቱ የሚያቆመው ቢሆን እነመለስ ያኔ ያስቆሙት ነበር ። ወያኔ እስክንድርን እንደማያቆመው ሲያረጋግጥ ነው 18 አመት የፈረደበት ።
.
የዛሬዎቹ ተረኛ ዙፋነኞችም እስክንድርን እነሱ በቀደዱት ቦይ በማፍሰስ ከአላማው ሊመልሱት አይችሉም ፤ ሊያስሩት ግን ይችላሉ ፤ በዚህም አላማውን ግን አያቆሙትም ። በጋጠወጦች ሊያስገድሉትም ይችላሉ ፤ ይህም የእስክንድርን የእውነት መንገድ አይገድለውም ። እስክንድር የሸከመው አላማ የሐገርና የሕዝብ ያህል ግዙፍ ነው ። የእስክንድር አጀንዳ ነፃነት ፣ እኩልነት ፣ ከሁሉም በላይ እውነት ነው ። እነዚህ ደግሞ በእስክንድር መታሰርና  መታፈን የሚወድቁ ምናምንቴዎች አይደሉም ፤ እነዚህ ለአገርና ለሕዝብ የኦክሲጂን  ያህል የሚያስፈልጉ ቁም ነገሮች ናቸው ።
Filed in: Amharic