>
5:13 pm - Friday April 19, 6993

በያቅጣጫው አፈና ከተጀመረ ማቆሚያው የት ይሆን?!? (ሉሉ ከበደ)

በያቅጣጫው አፈና ከተጀመረ ማቆሚያው የት ይሆን?!?
ሉሉ ከበደ
በእስክንድር ላይ የተከፈተው ማዋከብ ፤ ክልከላና የስነልቡና ጦርነት፤ ላዲሳባ ህዝብም ሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚያስተላልፈው ቀላል መልክት፤ ህውሀት ቦታውን ለቆ ዶክተር አብይ ከተተካ በኋላ ፤ የረጅም ጊዜ ህመማችን ማስታገሻ መርፌ አገኘ እንጂ አልዳነም ።ገዢዎች የሚሰጡን ህመም ማገርሸት ጀምቷል።
አቶ ለማ መገርሳ ያዲስ አበባን ዲሞግራፊ የመቀየር ስራ መስራት አለብን ፤ አምስት መቶ ሺህ ተፈናቃይ ኦሮሞዎችን ወደ ነበሩበት ሳይሆን አምጥተን ባዲስ አበባ ዙሪያ  እናሰፍራለን፤ ብለው የኔ ለሚሉት ወገን ሲናገሩ መሰማታቸው፤ ታከለ ኡማን አዲስ አበባ ከንቲባ ያደረግነው የኦሮሞን ጥቅም በፊንፊኔ ላይ የመጠበቁን ስራ ለማቀላጠፍ ነው መባሉ እንደተሰማ፥   ያዲስ አበባ ነዋሪ ላልሆኑ የኦሮሞ ተወላጆች መታወቂያ በገፍ ሲታደል ፤ ግዳጁን እንድትፈጽም የታዘዘችው እህት ተቃውሞ አደባባይ ሲወጣ ፥ ሌላም ሌላ አደገኛ የዘረኝነት ሴራ ምልክቶች ከኦህዴድ ውስጥ ብቅ ብቅ ማለታቸው ገሀድ ሆነ። ህውሀት በሌላ ገጽታ መከሰቱ ግልጽ ሆነ።ያዲስ አባባን ህዝብ መኖሪያ ፤ አልባ አገር አልባ ለማድረግ የተጠነሰሰው ሴራ ፍንትው ብሎ ታየ። አዲስ አበቤ እስክንድርን ከፊትለፊት አቁሞ ፤ ቢያንስ የአሁኖቹ ባለተራዎች እንዳያፈናቅሉት በማህበር ተደራጅቶ ሮሮና አቤቱታውን ሊያሰማ ባልደራስን አቋቁሞ ተንቀሳቀሰ። ባልደራስ “አዲስ አበባን የሁላችንም አድርጉልን እንጂ የአንድ ዘር ንብረት አድርጋችሁ የትንሿን ኢትዮጵያ አዲስ አበባ  መላ ህዝብ ለስቃይ እንዳትዳርጉን” ነው የሚለው።
ሆደ ሰፊ ነኝ ታጋሽ ነኝ እያለ ስንቱ በገጀራ፤ በዱላ፤ በጥይት ሲያልቅ ፤ ስር አተ አልበኛ እንደፍልፈል በየከተማው በየገጠሩ እየተርመሰመሰ ግፍ ሲፈጽም ሰምቶ እንዳልሰማ የሚሆነው  አብይ፤   እስክንድር ስለመብት ሲናገር ቴሌቪዥን ላይ ወቶ ፎከረ። ጦርነት ይሆናል ብሎ። የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፍቷል፤ ዜጎች ሰባዊ መብታቸው እውን ሆኗል፤  ያለን ሰው ነው እንግዲህ። ጃዋር በቴሌቪዥን ወቶ ቄሮ ተነስ እያለ ጦርነት ሲያውጅ አያይም አይሰማም። ኦነግ ሀያ ባንክ ሲዘረፍ አያይም አይሰማም። ያርበኞች ግንቦት ሰባት ሰዎች ቢሆኑ ኖሮ ያን ያደረጉት ምን ይፈጠር ነበር?
በዚያ ብቻ አላበቃም ባልደራስ ብዙ መሰናክል ተጋርጦበት ከተቋቋመ በኋላ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ አዲስ አበቤዎችን ሲጎበኝ በፖሊስ መታሰር፤ መዋከብ ፤በስክንድር ላይ መዛት፤ በግልጽ የሚታይ የመብት ጥሰት ሆነ።  ህውሀት ከዚህ የተለየ ምን አድርጎ ነበር? አብይ ይዞልን የመጣውን ተስፋ ወዴት አደረሰው? እንደዚያ ንቅል ብለን ደግፈነው? አጨብጭበንለት?
ሴራቸው እንደብቅህ ቢሉትም ከንግዲህ የሚሆንላቸው አልመሰለኝም። ሰናይ ቴሌቪዥንን ለመክፈት እስክንድርና አጋሮቹ ሲንቀሳቀሱ ለሁለተኛ ጊዜ ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳይሰጥ መከልከሉ  ኦህዴድ የደገሰልን ነገር መኖሩን አመላካች ክስተት ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ ከወዲሁ ነቃ ብሎ ያለውን ሁኔታ መከታተል ይጠበቅበታል። የዜግነት ፖለቲካ አራማጅ የሆነው ኢዜማ ጋሙጎፋ ውስጥ እየተዋከብኩ እየተሳደድኩ ነው ብሎ ሮሮውን በማሰማት ላይ ነው። በያቅጣጫው አፈና ከተጀመረ መቆሚያው የቱጋ ነው? የጥገናው ለውጥ ስር ነቀል ሊሆን ካልቻለ የምንመለሰው እዛው የነበርንበት ፈተና ላይ ይሆንና ፈርጀ ብዙ ትርምስ ውስጥ መግባታችን አይቀርም። ዘውጌ ፖለቲከኞች ግባቸው የሚሆነው ኢትዮጵያን አፍርሶ ሁሉም የየድርሻውን ይዞ መቀመጥ ይመስላል። ሀገር አፍርሶ በሰላም መኖር የሚቻል ከሆነ። ወያኔን ጨምሮ ያሉት የዘር ድርጅቶች ሁሉ ኢትዮጵያን አፍርሰው በሰላም የሚኖሩ የሚመስላቸው ከሆነ ቀጣዩ ምእራፍ መበታተን ይሆናል። ላለመበተን መዘጋጀት ነው።
Filed in: Amharic