>
3:23 pm - Saturday October 23, 2021

ቧ ል ት!!! (አሳዬ ደርቤ)

ቧልት!!!

አሳዬ ደርቤ
ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በማለዳ ተነስተው ለባለቤታቸው ወደ ትግራይ እንደሚሄዱ ሲነግሯቸው ቀዳማዊት-እመቤቷ ‹‹ለምን አብረን አንሄድም?›› በማለት ጠየቁ፡፡
‹‹ለልጆቻችን ስለምታስፈልጊያቸው እኔ ደርሼ እስክመለስ ድረስ አንድ ሁለት የመሰረት ድንጋዮችን እየጣልሽ ጠብቂኝ›› የሚል መልስ ሰጧትና በሩን አልፈው ከመውጣታቸው በፊት ፊታቸውን ዞር አድርገው ‹‹ካልተመለስኩ የችግኞቼን ነገር አደራ›› የሚል ኑዛዜያቸውን አስቀመጡ፡፡
*
አውሮፕላኑ እንደ ንስር አሞራ መንሳፈፍ በጀመረ ጊዜም…… ሸገርን ሳይሆን እስክንድርን ያዩ ይመስል ፊታቸውን አጨፍግገው ከስራቸው ያለችውን ዛፍ-አልባ ከተማ ሲያስተውሉ ከቆዩ በኋላ ‹‹ሰው እንዴት ችግኝ መትከል ቢያቅተው የኦነግን ባንድራ መስቀል ያቅተዋል›› ብለው አሰቡ፡፡
አውሮፕላኑ የአዲስ አበባን እና የኦሮሚያን ሰማይ አልፎ እስኪሄድ ድረስ ውጭ ውጩን ሲመለከቱ ቆዩ፡፡ ከዚያም የአማራ ምድር ሊታያቸው ሲጀምር ዐይናቸውን ወደ ውስጥ መልሰው ቁልቁል የሚጥሉት ነገር ይፈልጉ ጀመር፡፡ ሆኖም ከአውሮፕላኑ ወለል ላይ በዐይናቸው የሚፈልጉት ነገር ቦምብ ይሁን ዝናብ እርግጠኛ ለመሆን ይቸግራል፡፡
በዚህ መሃከል ታዲያ ከጉዞ መዳረሻቸው ጋር….. አቋሙን የማይገልጹት ዶክተር ደፂ፣ መልኩን የማያውቁት ጌታቸው አሰፋ፣ ጠላቶቹ የሚመስሉት አባይ ጸሐዬና አቦይ ስብሐት፣ እንደ አጠቃላይም ‹‹ህውሓቶች›› ትዝ አሏቸውና በንደት ፈንታ ስጋት ይሰማቸው ጀመር፡፡ ስለዚህም ጊዜውን ወደ ኋላ በመጠምዘዝ ‹‹የቀን ጅብ›› የሚል ንግግራቸውን ‹‹ፀረ-ጅብ›› ብለው ማስተካከልና ግንቦት ሃያን በደማቅ ሁኔታ ማክበር ፈለጉ፡፡ ይሄ እንደማይሆን ባወቁ ጊዜም አውሮፕላኑን ከፓይለቱ ነጥቀው ወደ ኋላ ማዞር አሰኛቸው፡፡
.
አክሱም ደርሰው የአውሮፕላኑ ጎማ ምድር ሲነካም…… ጌታቸው አሰፋ የፍርድ ቤት መጥሪይ ይዞ እንዳይጠብቃቸው እንጂ የአበባ ጉንጉን እንዲበረከትላቸው አልተመኙም፡፡ በየአደባባዩ “መሽረፈት” (ማራገቢያ) እያሉ ሲዘልፏቸው የነበሩት የትግራይ እናት ካድሬዎች የተቀበሏቸው እንደ ግንቦት ሃያ በከበሮና በእልልታ ነበር፡፡ ዘፈናቸው ግን በደፈናው ስለ አንድ ታላቅ መሪ የሚያቀነቅን በመሆኑ ውዳሴው ለአብይ ይሁን ለመለስ አልታወቀም፡፡
የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር ደፂ ‹‹እንኳን ወደ አገራችን በሰላም መጣህ›› ብለው ሲጨብጧቸው….ጠቅላያችን ‹‹ወደ ክልላችን›› ብለው ሊያርሙት ካሰቡ በኋላ የቆሙበት መሬት ትዝ ሲላቸው ‹‹እንኳን በሰላም ቆያችሁኝ›› ብለው የትግራዩ አቻቸውን መዳፍ በፈገግታ ወዘወዙት፡፡ በማስከተል ለህዝቡ እጃቸውን እያውለበለቡ ከፊታቸው ወዳሉ መኪኖች በማምራት ከዶክተር ደፂ ጎን ተቀምጠው ይጓዙ ጀመር፡፡
.
የመጀመሪያው መርሐ-ግብር የአክሱም ሐውልቶች ያሉበትን ሁኔታ መጎብኘት ሲሆን በዚህም መሰረት ወደ ስፍራው አምርተው ወደ ሰማይ የተቀሰሩትን ሐውልቶች ዶክተሩ ሲመለከቱ ‹‹ይሄማ ዋነኛው የኩሽ ምድር ነው›› የሚል ድምዳሜ ላይ ደረሱና ‹‹በገዳ ስርዓት ሲተዳደር የነበረው ህዝብ በአፋኝ ስርዓት እጅ መውደቁ›› እያሳዘናቸው ጉብኝታቸውን አደረጉ፡፡
በማስከተል የነበረው ፕሮግራም ደግሞ ‹‹የአክሱም ነዋሪዎችን ማነጋገር›› የሚል ሲሆን  ጉብኝቱን እንደጨረሱ ወደ ስብሰባው አዳራሽ በቀጥታ ሄዱ፡፡ በዚህም ስብሰባ ላይ የቀረቡት ጥያቄዎችና ቅሬታዎች ‹‹የከተማዋ ህዝብ ከባለፈው ሃያ ሰባት ዓመት ይልቅ በዚህ አንድ ዓመት ከመጠን በላይ መማረሩን›› የሚያመላክቱ ነበሩ፡፡  እሳቸውም የቀረበላቸውን ውሃ ሲጠጡ ባይታዩም ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ግን ከፕሮፌሰር ብርሃኑ በተሻለ ሁኔታ መልስ ሊሰጡ ችለዋል፡፡
በመጨረሻም….
ጠቅላይ ሚኒስቴሩና ርዕሰ-መስተዳድሩ ረዘም ያለ ጊዜ ወስደው በጋራ እና በአማራ ጉዳዮቻቸው ላይ እንደመከሩ ከምንጮቻችን ያላገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
Filed in: Amharic