>

ሉዓላዊነትን ማስደፈርና  ጥሪት መሸጥን አጥብቀን እናወግዛለን !!! (ከኢትዮጵያዊያን ሃገር አቀፍ ንቅናቄ የተሰጠ መግለጫ)

ሉዓላዊነትን ማስደፈርና  ጥሪት መሸጥን አጥብቀን እናወግዛለን !!!
(ከኢትዮጵያዊያን ሃገር አቀፍ ንቅናቄ የተሰጠ መግለጫ)
 
ሀገራችን ኢትዮጵያ ተከታታይ ትውልዶች በከፈሉት መስዋዕትነት ሉዓላዊነቱዋንና ነፃነቷን አስከብራ የኖረች ሀገር ነበረች። ይህንን የትውልዶች ብሔራዊ ክብር በመናድ  የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ በአስቸኳይ ስብሰባ ሁለት አንኳር ጉዳዮችን በመወሰን ታሪክ ይቅር የማይለው ሀገራዊ ክህደት ፈፅሟል።
1ኛ. ከሰባ ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን የተሰውለትን የሉዓላዊነትና የዳር ድንበር ክብር ባልተጠበቀና በድንገተኛ ውሳኔ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አሳልፎ ለመስጠት ወስኗል።
2ኛ. የኢትዮጵያን ህዝብ በኑሮ ውድነት እየቆላ ባልታሰበበትና ባልተጠና ፖሊሲው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ብሎ የሃገሪቱዋን ጥሪት አሟጦ የሃገሪቱንም ብሔራዊ ዕዳ (ብድር) ወደ 25 ቢሊዮን ዶላር አሳድጎ ለሙስና መንገድ መክፈቻ የጀመራቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች እንደተጀመሩ ሜዳ ላይ ቀርተዋል። ይህም በሃገር ላይ ያደረሰው የኢኮኖሚ ቀውስ ሳይበቃው እነዚህን ሜዳ ላይ የቀሩ ፕሮጀክቶችና የሃገር ምልክት የሆነውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጭምር ለሽያጭ አቅርቦታል።
ከላይ የጠቀስናቸው ሁለት የኢህአዴግ ውሳኔዎች የሃገርና የህዝብን ጥቅም አሳልፈው የሰጡ የክህደት ውሳኔዎች መሆናቸውን እናምናለን። ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ስርዓቱም “ህገ መንግስታዊ” እንደሆነ ከተቆጠረ ኢህአዴግ የወስናቸው ውሳኔዎች በመንግስት የውሳኔ ሰጭ አካላት የተወሰኑ አይደሉም።  ይህ  ሉዓላዊነታችንን ያስደፈረ፣ አንጡራ ሀብታችንንና የሃገር ምልክት የሆኑ ተቋማትን  ለሽያጭ ያቀረበው የኢህአዴግ የክህደት ውሳኔ ኢትዮጵያ እንደ ሃገር አታውቀውም። ኢትዮጵያንም አይወክልም።
የኢትዮጵያ ህዝብ በታሪኩ እንዲህ ዓይነት ወደር የለሽ ክህደት ተፈፅሞበት ዝም ብሎ  አያውቅም። በመሆኑም  ከትውልድ ተጥያቂነት ለመዳን ይህንን ድርጊት በማውገዝ ውሳኔው እንዲቀለበስ በጋራ ተቃውሞውን እንዲገልፅ እንጠይቃለን።
 ኢትዮጵያንም እንደ ሃገር ስርዓቱንም ህገ መንግስታዊ አድርገው የሚቆጥሩ አካላትም ይህ ውሳኔ ኢትዮጵያን እንደ ሃገር የማይመለከት ስለሆነ የኢትዮጵያ አቁዋም አድርገው ከማራገብ እንዲቆጠቡ በአፅንዖት እናሳስባለን።
ለ27 ዓመታት አገዛዙ በዘራው የጥላቻና የልዩነት መርዝ ምክንያት የኢህአዴግን የክህደት ውሳኔ  አቃሎ የማየትና የምንቸገረኝ ስሜት በአንዳንድ ኢትዮጵያዊያን ላይ አስተውለናል። ይህ ዝንባሌ ለገዥዎች  ስልጣን ማራዘም የሚመች ፣ሉዓላዊነታችንን የሚያስደፍርና ለዚች ሃገር ክብርና ነፃነት ሲሉ ምንም የግል ጥቅም ሳያገኙ  ህይወታቸውን የሰጡ ተከታታይ ትውልዶችን መካድ ስለሆነ በጊዜ እንዲታረም በጥሞና እናሳስባለን።
 የፖለቲካ ቡድኖችም የሃገር ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ክብር ከቡድኖች ሽኩቻና መሸናነፍ በላይ ስለሆነ ህወሃትና ኢህአፓ ሶማሊያ ኢትዮጵያ ሃገራችንን በወረረች ጊዜ የፈፀሙትን ዓይነት ታሪካዊ  ስህተት ለመፈፀም የመዘጋጀት አዝማሚያ በታሪክ የሚያስጠይቅ መሆኑን ተገንዝባችሁ የምትወስዱትን አቋም ደጋግማችሁ እንድታስቡበት እንጠይቃለን።
በመጨረሻም ከላይ የተጠቀሱት ውጥንቅጥ ችግሮች ኢህአዴግ እንደ መንግስት መንቀሳቀስ የማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን በግልፅ ያሳያሉ። የኢትዮጵያ ህዝብ  እንዲህ ዓይነት ውሳኔ በላዩ ላይ የወሰነውን ቡድን በህዝባዊ አስተዳደር ለመተካት የመጨረሻ አማራጭ የሆነውን የነፃነትና የእኩልነት ትግሉን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በፅኑ እናምናለን። ህገ መንግስታዊ የስርዓት ለውጥ ለማድረግ የሚያመቻች የባለ አደራ መንግስት እንዲቋቋምና ሃገራችንን ከመፍረስ አደጋ ታድገን የህዝብ የስልጣን ባለቤትነት እንዲረጋገጥ የጀመረውን ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥል በድጋሜ ጥሪ እያቀረብን እኛም ትግሉ የሚጠይቀውን ሁሉ ለመፈፀም ዝግጁነታችንን እናረጋግጣለን።
ሰኔ 03 ቀን 2010 ዓ. ም
አዲስ አበባ
Filed in: Amharic