>
1:43 pm - Thursday December 8, 2022

የእኛዎቹ አክቲቪስቶች ‹‹ማይክሮ ዌቭ›› አክቲቪስ ናቸው!!! (ዮናታን አክሊሉ)

የእኛዎቹ አክቲቪስቶች ‹‹ማይክሮ ዌቭ›› አክቲቪስ ናቸው!!!
ዮናታን አክሊሉ
🔷 … ኢትዮጵያ የማትለወጥበት ምንም ምክንያት የለም ። ኢትዮጵያ የተወጋችው ማደንዘዣ ብሄርተኝነት ነው፡፡
ሰርጀሪ የተወጋ ሰው ማደንዘዣውንሲያነሱለት ይነቃል፤ አሁንም ልክ እንደዚያ ነቅተናል፡፡ ድሮም ነበርን፤ ወደፊትም እንቀጥላለን፡፡ አሁን ከተወጋንበት ማደንዘዣ ነቅተናል፡፡…
ከለመድኩት መድረክ እና ቦታ ለየት ያለ ስለሆነ ለእኔ ይህ መድረክ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ ስለዚህ ብዙም ልምድ ስለማይኖረኝ ትረዱኛላችሁ ብየ አስባለሁ፡፡ መጋቢ ሐዲስ እሸቱ ከሃይማኖት ቦታ አልፎ እንዴት ስለአገር መወራት እንዳለበት አስተምረውኛልና እርሳቸውን አመሰግናለሁ፡፡
በልምድም በዕድሜም ብዙ የምትበልጡኝ አላችሁ፤ ይሁን እንጂ የኖርኩበትን አገሬን ያስተዋልኩትንና የተማርኩትን ስለአገሬ መፍትሔ እናገራለሁ፡፡
አገር የኪሎ ሜትር ድንጋይ አይደለችም፤ ተተክላ አትቀርም፤ ትለወጣለች፡፡ በየዘመናቱ አገር የምትናወጠው በለውጥ አፍቃሪና በድሮ ሥርዓት ናፋቂ መካከል በሚደረግ እሰጥ አገባ ነው፡፡ አንድ መዝሙር ብቻ እየዘመርን እንድንሞት የሚፈልጉ አሉ፤ እሱ ግን አይቻልም፡፡ በዘመናት መካከል የማይለወጥ ነገር የለም፡፡
ሳይለወጥ ሁሉን የሚለውጥ አንድ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ እኔና ኢትዮጵያ፣ እኛና ኢትዮጵያ ብየ ሳስብ፤ የሰዓት መቁጠሪያውን ኢትዮጵያ፣ የሰዓት መያዣውን ደግሞ እኛ አድርጌ አስባለሁ፡፡ የሰዓት መያዣው ሰዓቱን ከያዘው ጥሩ፤ ካልያዘው ግን መቁጠሪያው መቁጠሩን አያቆምም፡፡
በየዘመናቱ ትውልድ አገሩን ከያዘ ጥሩ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሰዓት መቁጠሪያው ነች፡፡ በሚገባ አገርን መያዝ፣ በሚገባ መኖር መልካም ነው፡፡ ከሃይማኖት እንደመጣ ሰው ለንግግር የሚረዳኝን ሀሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ልዋስ (ሰበከ እንዳትሉኝ ሲሉ ሰምቻለሁና መጋቢ ሐዲስ እኔንም እንዳትሉኝ)
መጽሐፍ ቅዱሳችን ላይ እስራኤል በሰለሞን ዘመን እንደበለጸገችው በማንም ዘመን አልበለጸገችም፡፡ ሰለሞን በነገሰበት አርባ ዓመት አባቱ ዳዊት ተዋግቶ ያኖረውን አገር ነው ሰለሞን አውርቶ ያኖረው፡፡ ሰለሞን 300 ሚስቶችን፣ 700 እቁባቶችን እንዳገባ እና ወደ አንድ ሺፍቅረኞች እንደነበሩት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል ።
ለምንድነው ይህን ያደረገው ብየ ሳስብ ለመተኛት ካለው ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ከታሪክ መጽሐፎቻችን እንደምንረዳው በዙሪያው ካሉ ነገስታት ጋር አማች ለመሆን ነው፡፡ ሰለሞን በነበረበት ዘመን የዘበኛው ወንበር በወርቅ ነበር የተለበጠው፡፡ ዘበኛው ተነስቶ የሚፈትሸው ከወርቅ ላይ ነው፡፡ እንደዚያ የበለጸገ፤ እንደዚያ የገነነ ሀገር ሰለሞን ሲሞት የእስራኤል ሽማግሌዎች ሰለሞን ጋ መጥተው ‹‹አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር›› አሉት፡፡
እዚህ ጋ የምንረዳው የአገር እድገት ማለት መሰረተ ልማት ሳይሆን የህዝብ እርካታ እንደሆነ ነው፡፡ ባለፈው 27 ዓመት የኖርኩበት መንግስት የሳተው ነገር ቢኖር የህዝብ ደስታ አለመፍጠሩ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ የአገር እድገት ማለት የህዝብ ደስታ ማለት ከሆነ ኢትዮጵያዊ ደስታው ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡
ኮንዶሚኒየም አይደለም፤ አስፋልት አይደለም፤ ኢትዮጵያዊነት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን ለመደገፍ ያ ሁሉ ህዝብ የወጣው መልካም አስተዳደር ስለተመለሰለትና ፍትሕ ስለተሰጠው ሳይሆን አጥቶት የነበረው ኢትዮጵያዊነት ስለተወራለት የተመለሰ ስለመሰለው ነው፡፡ የእኔና የእናንተ ደስታ፤ የቀጣዩ ትውልድ ደስታ፤ ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡
ኢትዮጵያዊ ቁጣውን በዓድዋ፣ ጥበቡን በላሊበላ፣ ትዕግስቱን በአክሱም እየገለጠ የኖረ ህዝብ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ለእኔ በማተለቅ መተለቅ ነው፡፡ ሁለት የትልቅነት መንገዶች አሉ ። አንደኛው በማሳነስ መተለቅ ነው፡፡ በማኮሰስ፣ በማዋረድ መተለቅ ነው፡፡ የራስን ቤት ለመገንባት የሌላውን ቤት ማፍረስ፡፡ የራስን ክብር በሌላው ሰው ውድቀት መግዛት፡፡ ይሄ በማሳነስ መተለቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ግን በማተለቅ መተለቅ ነው ።
ሁለተኛው የትልቅነት መንገድ በማተለቅ መተለቅ ነው፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ሲያገባ የባለቤቱ ቤተሰቦች ጋ ሽማግሌ ልኮ፣ ጉልበት ስሞ፣ ያኛውን ቤት አተልቆ ነው የሚያገባው፡፡ አዋርዶ የሚተልቅ ኢትዮጵያዊ የለም፡፡ የተቀበልናቸው መልካም እሴቶች አሉ፡፡ አሁን ያለው ኢትዮጵያዊ ጉዳይ ያለማንም ደጋፊ ይፈታል፡፡ አክሱምን ያለድጋፍ ያቆመ ህዝብ የትኛውንም ችግር ያለውጭ እርዳታ ማቆም ይችላል፡፡ ኢትዮጵያዊነት በማኮሰስ፣ በማዋረድ መተለቅ አይደለም፡፡
ክፍለ ከተማ ላይ አንድ ትልቅ ሰው ካለ፤ እዚያ ክፍለ ከተማ ላይ ትልቅ ሰው ለመሆን ያ ሰውየ ካላበደ ወይም አገር ካልለቀቀ ትልቅ የምንሆን ስለማይመስለን የማሳበድ ሥራ የማስለቀቅ ሥራ መሥራት የለብንም፡፡ አንድ ቀበሌ ላይ ያስቸገረ ትልቅ ሰው ካለ እሱን አተልቀን ወደ ክፍለ ከተማ ልከን እኛ ቀበሌውን መያዝ እንችላለን፡፡
የትልቅነት መድረኩ የእኛ ቀበሌ ብቻ አይደለም፤ ዓለም የትልቅነት መድረክ ነው፡፡ ስለዚህ ትልቅ ለመሆን የምንገለው፣ የምናዋርደው፣ ወደኋላ የምናስቀረው ነገር የለም፡፡ አክራሪ ብሄርተኝነት ማለት ለእኔ ብሄርተኝነት ያለ ኢትዮጵያዊነት ዋና ያለ ውሃ ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ስሜት የሌለበት ብሄርተኝነት ውሃ በሌለበት ገንዳ መዋኘት ነው፡፡
አገሬን ሳስባት እንደ አረገዘች ሴት ነች ። ያረገዘች ሴት፣ እግሯ ያብጣል፣ ፊቷ ያብጣል፣ ወደላይ ወደላይ ይላታል፣ ትናንት የወደደችው ዛሬ ያስጠላታል፡፡ ይሄ ተፈርቶ ግን ጽንስ ይቋረጥ አይባልም፡፡
አገሬ አንድ ነገር ጸንሳለች፤ እሱም ለውጥ ነው፡፡ የለውጥ አስደናቂው ነገር እንቅስቃሴ ሳይኖር ለውጥ አለመኖሩ ነው፡፡ እንቅስቃሴ ካለ ደግሞ ሰበቃ (ፍሪክሽን) አለ፡፡ ይሄ እንቅስቃሴ ወደአልሆነ አቅጣጫ እንዳይሄድ ግን መሪ ያስፈልገዋል፡፡ ዓለም በለውጥ ሂደት ላይ ስለሆነች ኢትዮጵያ የማትለወጥበት ምንም ምክንያት የለም ። ኢትዮጵያ የተወጋችው ማደንዘዣ ብሄርተኝነት ነው፡፡
ሰርጀሪ የተወጋ ሰው ማደንዘዣውንሲያነሱለት ይነቃል፤ አሁንም ልክ እንደዚያ ነቅተናል፡፡ ድሮም ነበርን፤ ወደፊትም እንቀጥላለን፡፡ አሁን ከተወጋንበት ማደንዘዣ ነቅተናል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን ሳስብ ሁለት ነገር ወደውስጤ ይመላለሳል፡፡ ብዙ ጊዜ ሰው ቦንቦሊኖ ብትሰጡት ስለቀዳዳው ማውራት ደስ ይለዋል፡፡ አሁን የመጣውን ለውጥ ከመጠቀም ይልቅ ስላለበት እንከን ማውራት ተገቢ ነው ብየ አላምንም፡፡ አሁን ያለውን ለውጥ ሳስበው የአዋሽና የዓባይ ጉዳይ ይመጣብኛል ። ኢትዮጵያውያን የበላነው ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ ብርቱካን የሚመጣው ከአዋሽ ነው፤ የምንዘፍን ግን ለዓባይ ነው፡፡ አንድ ቀን ለአዋሽ ዘፍነን አናውቅም ። ዘንድሮ የሚያለቅሱ ሰዎች አፈር ለወሰደባቸው የሚዘፍኑ ብርቱን ላበላቸው ግን የሚያለቅሱ አይነት ናቸው፡፡
በማተለቅ መተለቅ ነው ኢትዮጵያዊነት፡፡ እኛ ላለንበት ቤተ እምነት ብቻ ሳይሆን ለዓለም ትልቅ አስተዋጽዖ ያበረከተችው የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ነች፡፡ ተወርቶ የማያልቅ ብዙ ጥበብ እና እውቀት አላት፡፡ ያንን እያደነቅን የምንተልቅ ህዝቦች ነን፡፡ እዚህ ጋ የዶሮ እርባታ ሲከፈት እዚያ ጋ የሸለመጥማጥ እርባታ መክፈት ኢትዮጵያዊነት አይደለም፡፡
ኢትዮጵያዊነት የዋህነት ነው፡፡ የዋህነት ማለት ባር ባር ማለት፣ ሞኝነት፣ አላዋቂነት ማለት አይደለም፡፡ የዋህነት በባህር ዳርቻ እንደተተከለ አለት ነው፡፡ በባህር ዳርቻ ያለ አለት ከባህሩ የመጣ አለት ሲመታው የመታውን ማዕበል እያፈራረሰ፣ እየናደ ይመልሰዋል፡፡ በዘመናት መካከል ኢትዮጵያዊነት ማለት እንዲህ ነው፡፡ በየዘመኑ የመጣውን፣ ክፋት፣ ጥላቻ እና አመጽ እያፈረሰች ያየች አገር ናት ኢትዮጵያ፡፡
የሚያስፈልገን አንድ ነገር ነው፤ ያም ትዕግስት ነው፡፡ ትዕግስት ማለት በሚለዋወጥ ሁኔታ ውስጥ የማይለዋወጥ ነገር መያዝ ነው፡፡ አሁን አንበሳ ነው ያልነውን በኋላ ሬሳ ነው አለማለት፤ አሁን ወርቅ ነው ያልነውን በኋላ ጨርቅ ነው አለማለት ነው፡፡
እኛ አገር ያሉ አክቲቪስቶችን እኔ አክቲቪስት ናቸው አልላቸውም፡፡ ‹‹ማይክሮ ዌቭ›› አክቲቪስቶች ናቸው፡፡ ማይክሮ ዌቭ ማለት የቀዘቀዘን ነገር አሙቆ የሚያቀርብ ነው፡፡ ያረጀ ታሪክ አሙቀው የሚያቀርቡ ናቸው፡፡ በድሮ ለቅሶ አዲስ ድንኳን ተክለው የሚያስለቅሱ ናቸው፡፡
አንድ ወቅት ላይ የፋርስ መንግስት ርሃብ ገጠመውና ብዙ ችግር ተፈጠረ፡፡ እናም እንዲህ ሆነ፡፡ አንድ ሰው ንጉሡ ግብር እንዲተውለት ማመልከቻ ሊያስጽፍ ማመልከቻ ጸሐፊ ጋ ይሄዳል ። ማመልከቻ ጸሐፊው ጠየቀ፤ ‹‹ስንት ልጅ አለህ›› ስድስት፣ ‹‹ስንት አረጋዊ ትረዳለህ›› ሁለት፣… እያለ መለሰ፡፡ ማመልከቻ ጸሐፊው አሳምሮ ጻፈው፡፡ ላንብብልህ አለና ለሰውየው አነበበለት፡ ፡
‹‹ክቡርነትዎ ሆይ፡ እኔ የእርስዎ ታማኝ ባሪያ፤ ዘመኔን ሁሉ በታማኝነት ስሰራ የቆየሁ ነኝ፡፡ ሆኖም ግን በገጠመን ርሃብ ምክንያት የዘር እህል ሁሉ በልቼ ለከፋ ውርደት ተዳርጊያለሁ፤ አንገቴን ደፍቻለሁ፡፡ ህጻናት ልጆቼ ባዶ እጄን ስገባ ያለቅሳሉ…›› እያለ ሲያነብለት ሰውየው (አስጻፊው ማለት ነው) ለቅሶውን አቀለጠው፡፡ ፡ ጸሐፊው ‹‹ምነው ምን ሆነህ ነው›› ብሎ ሲጠይቀው ‹‹እንዲህ ቸግሮኝ ነበር እንዴ ለካ!›› አለ፡፡
ሰውየው የሌለውን ችግር ሁሉ ጽፎ ነው ያስለቀሰው፡፡ የዘንድሮ ጸሐፊዎች እንደዚህ ነው እየጻፉልን ያሉት፡፡ እዚህና እዚያ ጥግ ሆነው በነጻ ዋይ ፋይ የሚጽፉልን ሰዎች የማናውቀውን ችግር እየጻፉ ነው የሚያስለቅሱን፡፡ አናውቅም እንዴ? እኛ አልኖርንም እንዴ? አማራ ከኦሮሞ፣ ሲዳማ ከወላይታ ትግራይ ከደቡብ ወይም ከጋምቤላ ጋር፤ አልተጋባንም? አብረን አልኖርንም? ወይስ ይህንን አያውቁትም ነው? የግል ጉዳይን የአገር ጉዳይ እያደረጉ ነው ያስቸገሩን!
Filed in: Amharic