>
5:13 pm - Thursday April 18, 4222

የፍትሕ መጽሔት ባልደረቦች የተቀነባበረ ወንጀል ተፈጸመባቸው!!! (የፍትሕ መጽሔት ዋና አዘጋጅ ዳዊት ታደሰ)

የፍትሕ መጽሔት ባልደረቦች የተቀነባበረ ወንጀል ተፈጸመባቸው!!!
የፍትሕ መጽሔት ዋና አዘጋጅ ዳዊት ታደሰ
– “ወንጀለኞቹ ገጀራ ይዘው አድፍጠው ነበር”
– “ላፕቶፕ እና ስልክ ነጥቀዋል”
– ጋዜጠኞቹ ለደህንነታቸው ፖሊስን ጥበቃ ጠይቀዋል
በ‹‹ልህቀት የኅትመት፣ ብሮድካስት እና ኮምዩኒኬሽን ሥራዎች ድርጅት›› ስር የሚታተመው ‹‹ፍትሕ›› ሳምንታዊ ፖለቲካዊ መጽሔት ዋና አዘጋጅ ዳዊት ታደሰ እና የመጽሔቱ አርት ዳይሬክተር እና ግራፊክስ ባለሟል ጋዜጠኛ ነብዩ መስፍን ምሽት ላይ ከቢሮ ሲወጡ አካላዊ ጥቃትና ወንጀል እንደተፈጸመባቸው አሳወቁ፡፡
ልህቀት ኮምኒኬሽን፣ በቀን ሰኔ 11 ቀን 2011 ዓ.ም በደብዳቤ ቁጥር ል/ኮ 02/0081/11 እና ል/ኮ/02/0082/11 ለየካ ክፍለ ከተማ የአድዋ ድልድይ እና አካባቢ የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ባስገባው ሁለት ደብዳቤዎች ላይ የታቀደ ወንጀል እንደተፈጸመባቸው አሳውቀዋል፡፡
ረቡዕ ሰኔ 5 ቀን 2011 ዓ.ም ከምሽቱ 5፡30 ሰዓት አካባቢ ከተቋሙ ዋና መሥሪያ ቤት በር ላይ በተደራጁ ሰዎች የተጠና ወንጀል በባልደረቦቻችን ላይ ተሰንዝሮ አካላዊ ጉዳት እና የንብረት ዘረፋ ተፈጽሟል፡፡
‹‹ይሁንና የተፈጸመብን ወንጀል ‹ተራ የሌብነት ድርጊት ነው› ብለን ለማመን ተቸግረናል፤ እንዲሁም በቀጣይ ሥራችንን በተረጋጋ ሁኔታ እንድንሰራ ፖሊስ ጣቢያው በጉዳዩ ላይ የደረሰበትን ማስረጃ እንዲያሳውቀን እና በሳምንት ለሁለት ቀናት ረቡዕ እና ሃሙስ በሥራ ምክንያት ስለምናመሽ ፖሊስ ጥበቃ እንዲመድብልን ስንል በትህትና እንጠይቃለን፤›› ብለዋል፡፡
በየካ ክፍለ ከተማ የአድዋ ድልድይ እና አካባቢ የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ መርማሪ የሆኑት ኢንስፔክተር ዘሪሁን ተፈራ በጣቢያው ለተገኘው ዘጋቢያችን ‹‹እኛ ፖሊሳዊ ሥራችንን በአግባቡ እየሰራን ነው፤ ወንጀለኞች አቅደው ተዘጋጅተው ወንጀል እንደሚፈጽሙት ሁሉ፤ እኛም አቅደንና ተዘጋጅተን ነው የምንይዛቸው›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከተጠቂዎች የሚመጣው ሪፖርት ሁሉ ለሥራችን ይረዳናል ያሉት ኢንስፒክተሩ፣ አሁን ወንጀል ሰሪዎቹ ይዘውት የተንቀሳቀሱትን መኪናን አውቀናል፤ በማን ባለቤትነት እንደተመዘገበም ለይተናል፤ ይህንንም ለየአካባቢው ፖሊስና ትራፊክ ፖሊስ አባላት ልከናል፤ በቅርቡም በቁጥጥር ሥር ይውላል፤ በወንጀሉ ተሳታፊ የነበሩ ሰዎችን ሁሉ እንይዛቸዋለን›› ብለዋል፡፡
  ‹‹በእለቱ ወደ ማተሚያ ቤት የምንገባበት ቀን ስለሆነ እኔ እና የመጽሔቱ አርት ዳይሬክተር እና ግራፊክስ ባለሟል ነብዩ ሥራ ስለሚበዛብን ከምሽቱ 5፡30 ሰዓት አካባቢ ከቢሮ መብራት አጥፍተን ወጣን፡፡
ከፎቅ ወርደን ወደ መኪና ገብተን ሞተር እያሞቅን ሳለን፣ በኔ በኩል (ጋቢና) በሩን አልዘጋሁትም ነበርና አንድ ልጅ መጥቶ አናገረኝ፤ ምንድን ነው የምትፈልገው እያልኩ እያወራሁ ሳለሁ በነብዩ በኩል ሦስት ልጆች መጡና በሩን ከፍተው ትልቅ ገጀራ፣ የቢራ ጠርሙስ፣ ድንጋይ አውጥተው አሳዩንና እኔን አወረዱኝ፤ ኪሴን ፈተሹና፣ ስልካችንን ወሰዱ፤ አንደኛው ልጅ የመኪናውን ሞተር አጠፍቶ ቁልፉን በእጁ ያዘ፤ ሌላኛው ልጅ የመኪናችንን የኋላ የእቃ ማስቀመጫ ኮፈን ከፈተ፡፡
የመጽሔቱ ዲዛይንና ሌይ አውት የተሰራበትን ላፕ ቶፕ ወሰዱ፤ ከዛም እኔን በገጀራው በጠፍጣፋው በኩል ወገቤን መቱኝ፤ እንዳትንቀሳቀሱ፣ እንዳትወጡ ብለው ወደ ኋላ መሮጥ ጀመሩ፤ የአስፋልቱን አካፋይ ብረት ዘለው ወደ ምትጠብቃቸው ‹ቪትዝ› መኪና ገቡና አመለጡ፡፡ ብሏል፡፡
የመጽሔቱ አርት ዳይሬክተር እና ግራፊክስ ባለሟል ጋዜጠኛ ነብዩ መስፍን ስለ ወንጀሉ አፈፃጸም ሲያስረዳ፣ የእለቱ ሥራችንን አጠናቀን ከቢሮ ወርደን ወደ መኪና ስንገባ፣ በእለቱ አራት ሰዓት ላይ በፈረቃው መሠረት መምጣት የሚገባው መብራት ባለመምጣቱ፣ ሥፍራው ጨለማ ነበርና አድፍጠው ሲጠብቁን የነበሩት ወንጀለኞች በቀላሉ ወደ መኪናችን መጥተው አንደኛው ትልቅ ስለታም ገጀራ፣ ሌላው ሁለት ጠርሙስ ይዞ፣ አንደኛው ደግሞ ረጅም ዱላ ይዘው በተቀናጀ መንገድ አዋከቡን፡፡
አንዱ ዓይኔ ላይ ሚጥሚጣ ዱቄት በተነብኝ፤ ሌላኛው የመኪናውን ሞተር አጠፋ፤ ሌላው የመኪናውን ኮፈን ከፈተ፣ የተቀሩት እኛን እየፈተሹ ከኪሳችን ብርና ስልክ ወሰዱ፤ መጽሔቱ እየተሰራበት ያለውን ላፕቶፕ ኮምፒውተር ወሰዱና በቪትዝ መኪና አመለጡ፡፡ በጣም የተደራጁና የተዋቀሩ ነበር የሚመስሉት፤ በቀላሉ አመለጡ፡፡ በቅርብ ርቀት ፖሊስ ጣቢያ ስላለ፣ ሄደን አመለከትን ሲል ለዘጋቢያችን አስረድቷል፡፡ #Ethio-Online
በመጨረሻም:- ፍትሕ መጽሔት ላይ አፈና ለማድረግ የተሄደበት እሳፋሪ አካሄድና የተጓዙበት ርቀት ለትዝብት ዳረጋቸው እንጂ መጽሄቷን በነገው እለት ገበያ ላይ ከመዋል ሳያግዳት ቀርቷል።
Filed in: Amharic