>
4:25 pm - Thursday May 19, 2022

ነፃ አውጪው ማነው? (ዘመድኩን በቀለ)

ነፃ አውጪው ማነው?  
       ዘመድኩን በቀለ
“ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም ” አይደል የሚባለው? መቸም ይሄ ጆሮአችን የማይሰማው ነገር የለው ይኸው ዛሬ ደግሞ ሌላ ጉዳኛ ሰው ጉድ የሆነ ኦዱ ለቅቆብን ሊያዘፍነን ነው። ማነህ ጎዶኛዬ ያዝ እንግዲህ!  ንሳ ተቀበልልኝማ አንተው።
•••
” በቄሮ ትግል #ፌስታሉን ይዞ ከእስር ወጥቶ ሲያበቃ ዛሬ “ ባለአደራ መንግሥት” ብሎ ራሱን መሾም አልያም “ ባላተራ መንግሥት” ብሎ ለውጡን ማጣጣል በምንም ስሌት ተቀባይነት የለውም። መንግሥታችንን ለመፈታተን ባለተራ ባለአደራ እያለ የምያላዝነውን ወደ ትክክለኛ መስመር ለመመለስ እንሠራለን። “
• ይሄን ያለው የቀድሞው ኦህዴድ የአሁኑ የኦዴፓ ጸሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ Addisu Arega Kitessa የኦሮሞ ወጣቶች ናቸው በተባለ ኮንፈረንስ ለይ ያስተላለፈው መልዕክት ነው። ይሄ የአቶ አዲሱ ንግግር ነው እንግዲህ ዛሬ በዕለተ ሰንበት ብዙ ብዙ የሚያናግረኝ።
•••
ቀድሞውኑ ሲጀመር ፦
•••
ሲጀመር በዚህ ዘመን በቄሮ ትግል ብቻ ነፃ የወጣች ኢትዮጵያ የለችም። እንደኔ እምነት ኢትዮጵያ በራሷ ልጆች ቅኝ ግዛት ስር የወደቀች ሀገር ናት። ኢትዮጵያ የቀጥተኛውና በዓይን በሚታየው የነጮቹ ቅኝ ግዛት ሥር ባትወድቅም በተዘዋዋሪ መንገድ ግን በውክልና በራሷ ልጆች በኩል ቅኝ የምትገዛ ሀገር ከሆነች ሰንብታለች። እናም ኢትዮጵያ ነፃ ወጥታለች ማለት ቀልድ ነው። ትናንትም ዛሬም ኢትዮጵያችን በገዳይዋ በኢህአዴግ እጅ ናት። ምንም የተለወጠ ነገር የለም። ትናንትም ዛሬም ኢህአዴግ ነው ጠፍጥፎ እየገዛን ያለው። ዋሸሁ እንዴ?
•••
እናም ከዚህ ተነስተን ስንመለከት ለውጥ እየተባለ ስለሚደሰኮርልን ነገር ብዙ ባናሽቃብጥ መልካም ነው የምለውም ለዚህ ነው። የሚገርመው ደግሞ አንደኛው አሽቃባጭ ራሴው መሆኔ እኮ ነው። የእስረኛ መፈታት ግድ ነበር። Hr126 ጉረሮ ማነቋ ህወሓትን ወደ ጓዳ እንድትደበቅ ማድረጉም ትክክል ነበር። አሮጌውን ኢህአዴግ ሸሽጎ አዲስ ፊት ኢህአዴግ ከፊት ለፊት ማምጣቱም አማራጭ የሌለው አማራጭ ነበር። ይሄም ለውጥ ከተባለ ለዚህ ለውጥ መምጣት ባለቤት አለው። በግል ብዙዎች ሞተዋል፣ ታስረዋል፣ ተሰደዋል።
•••
እኔ በበኩሌ አሁን በቄሮ ትግል ነፃ ወጣች የምትባለዋን ኢትዮጵያን አላውቃትም። ቄሮ የሚባለው መንፈስ የሆነ ቡድን ግን መኖሩን አውቃለሁ። አይጨበጥ፣ አይዳሰስ እንጂ ሲዘፈንለትና ሲሞት ሲሰደድም አውቀዋለሁ። ለማስተር ፕላንም ቢሆን ሲታገል እንደነበርም አስታውሳለሁ። ለኢትዮጵያ ነፃነትና አንድነት ብሎ ሲታገልግ ድምጹንም ሲያሰማ ግን አላውቀውም። ኦሮሞ ፈርስት።
•••
የቄሮ ትግል ለለውጡ ደጋፊ ሆኖ የሚጠቀስ እንጂ ለውጡን ያመጣ ዋነኛው ሞተር ነው ብሎ መጥቀስ አይቻልም። እንደዚያ ማለት አግባም አይደለም። እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ለውጡ ለውጥ ነው ከተባለም የዚህ ለውጥ ተብዬውን ያመጣው ያለምንም ጥርጥርና ግርግር የጎንደሩ አብዮት፣ የዐማራው ነፍጥ የፋኖም ፍልሚያ ነው። እሱ ነው ለውጥ ተብየውን ከብርሃን ፍጥነት በቀደመ መልኩ በኢትዮጵያ ምድር እንዲገለጥ ያደረገው። አሁንም የዐማራው መደራጀት ኢትዮጵያን ይለውጣታል ባይ ነኝ። በጸሎትም በነፍጥም ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ የሚያደርጋት ይኸው ነው። ለደፋሮች የኃይል ሚዛን የግድ ነው።
•••
ወያኔ የወደቀችው በቄሮ ትግል አይደለም። እሷ የቄሮን ልብ አሳምራ ታውቀዋለች። አንድ ጥይት ተኩሳ 50 ሺ ቄሮ ናይሮቢ ድረስ ስታስሮጥ የከረመች፣ የጭስ ጥይት ተኩሳ 4 ሚልየን ኦሮሞ በደብረ ዘይት ሆራ ማተራመሷን በዚህም ተረጋግጠው በመቶዎች የሚቆጠሩ መሞታቸውን ሁሉም ያውቃል። ፋኖም፣ ዘርማም፣ ኢጄቶም ይሄንን ያውቃሉ። ቄሮ ማለት እጁን አጣምሮ ቆሞ በአግአዚ ስናይፐር አናት አናቱን ሲቀነደብና ሲረፈረፍ የከረመ እነ ጃዋር መሀመድ በሞቱና በሬሳው ቢዝነስ ሠርተው የከበሩበት የዋህ ቡድን መሆኑም ይታወቃል።
•••
እነ በቀለ ገርባ፣ እነ ዶር መራራ ጉዲና፣ እነ አህመዲን ጀበል በካቴና ታስርው ፍዳቸውን ሲበሉ እነሱን መንዳት የለመደችዋ ህወሓት አፋኝ ጀሌ ቡድኗን ከመቐለ ጎንደር ድረስ ልካ ስታበቃ “ ከሕግ አግባብ ውጪማ አልያዝም” ብሎ ደጃፉ ድረስ ከሕግ አግባብ ውጪ በሌሊት ሊይዙት የመጡትን ቅጥረኞች በእጅ ሽጉጥ ብቻ የረፈረፈው ነፍጠኛው ፋኖ የፋኖም አለቃ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ መስሎኝ። እናም መጣ ለሚባለው ለውጥ የለውጡም ዋነኛ ባለቤት መሆንና መጠቀስም የነበረበት ፋኖ እንጂ ቄሮ አልነበረም። የሆነው ግን የተገላቢጦሽ ነው።
•••
ያኔ ታዲያ አዲሱ አረጋ የት ነበር ብለን ስንጠይቅ አዲሱ የህወሓት አሽከር ሆኖ የአቦይ ስብሃትን ካልሲ ሲያጥብ፣ ለዓባይ ፀሐዬ ስኳር መቃሚያ ከወንጂ ሸዋ፣ ከመተሃራ ማንኪያና ጭልፋ ሲያቀብል፣ ለእቁባቶቻቸውም ከአዶላ ወርቅ፣ ከጅማ ቡና ሲጭን የነበረ የህወሓት አሽከር ነበር። አዲሱ አረጋ በህወሓት ቤት ሳለ ቄሮ የተባለን ኦሮሞ የኦሮሞንም ወጣት ሱሪውን ዝቅ አድርጎ በሳማ ሲገርፍ፣ ዘቅዝቆ በርበሬ ሲያጥን፣ በኦነግ ስም፣ በአሸባሪ ስም የኦሮሞን ወጣት በየእስርቤቱ እንደከብት ሲያጉር፣ እግሩን ሲቆርጥ፣ በየትምህርት ቤቱ የኦሮሞ ተማሪዎችን በኦሮሞነታቸው ብቻ ኦነግ የሚል የዶቦ ስም በማውጣት ሲገድል፣ ሲያስገድል፣ ሲያሰድድ፣ ሲያፈናቅል፣ እነ ዳንኤል ብርሃነንና ፍፁም ብርሃነን የነፃነት አርማዎች የዲሞክራሲ ተምሳሌቶች እያለ ሲያወድስ የነበረ የጎባጣ አሽከር ነበር።
•••
የምንሳሳተው እስክንድር ነጋን ከእንደዚህ አይነት ሆድ አደር ጋር ማወዳደር ስንጀምር ነው።  አስክንድር ነጋ ግን አዲሱ አረጋ የሚፈራቸውን ስማቸው ሲጠራ ሱሪውን የሚያረጥቡትን እነ መለስ ዜናዊን፣ እነ አባይ ፀሐዬን፣ እነ ጌታቸው አሰፋን እንቅልፍ ይነሳቸው ነበር። ያውም እሱ በብዕሩ እነሱ በታንክ። እስክንድር የኦሮሞ ህዝብ ነፃነት እንዲያገኝ ሲል በአዲሱ አረጋ ሥርዓት የመከራ እንጀራ እየበላ የቄሮን በደል ተሸክሞ በወኅኒ ቤት ተቆልፎበት ሲማቅቅ የነበረ ጀግና ነው።
•••
አዎ አዲሱ አረጋ በንፁሐን ኦሮሞዎች ደም ሲሰባ፣ ሲወፍር፣ ሲቅለጠለጥ እስክንድር ነጋ ግን በአዲሱ አረጋ ሥርዓት በወኅኒ ቤት ታስሮ ከስቷል፣ ጠቁሯል። አዲሱ አረጋ ከንፁሐን ጉሮሮ በተዘረፈ የኢትዮጵያ ገንዘብ ባለ ቤት፣ ባለ ሥልጣን፣ ባለ ሀብት ሲሆን እስክንድር ነጋ የራሱን ሀብት፣ የራሱን ንብረት፣ የራሱን ቤት የአባት የእናቱን ውርስ የአዲሱ ጌታ አጅሬ ህወሓት በአሸባሪነት ፈርጃው በግፍ በፍትሕ ስም በፍርድቤት ተወርሶ ባዶ እጁን ቀርቶ ነበር። ለዚህ ነው አዲሱ አረጋ እስክንድር ከወኅኒ ሲወጣ በእጁ ይዞ በነበረው ፌስታል ሲያላግጥ የተመለከትነው።
•••
አዲሱ አረጋ ጊዜ የሰጠው ድንጋይ ሰባሪ ቅል ነው። በትምህርት ዝግጅትም፣ በእውቀትም፣ በዲሲፕሊንም ሆነ በማንኛውም ጉዳይ አዲሱ የእስክንድር የእግሩ እጣቢ እንኳ አይደርስም። እስክንድር እንደ አዲሱ ያለ ህሊናውን በአደባባይ ቀርጥፎ የሚበላ አንድ 10 አዲሱን የሚመስል ሆዳም ካድሬ ጠፍጥፎ በማፍረስ እንደገና እንደ አዲስ ህሊና ያለው ሰው፣ ለመርህ የሚኖር ሰው አድርጎ መሥራት የሚችል ዕውቀት ያለው ሰው ነው።
•••
አስክንድር ህሊና ያለውና ሰው የሚባለውን የሰውነት መለኪያ መሥፈርት የሚያሟላ ፍጥረት ነው። ዘመን አይቀያይረውም። ህሊናውንም አይሸጥም። ቁስ አይለውጠውም። በቃ ጥንቅቅ ያለ የመርህ ሰው ነው። ፍርሃትን አያውቀውም። ጀብደኛ ሳይሆን ከልቡ ጀግና ነው። የህዝብ ድምጽ ነው። ፍርፋሪ ለቃቃሚ አይደለም። ለሆዱ ሳይሆን ለህሊናው የሚኖር ሰው ነው። አይከረባበትም። አይገለባበጥም። የተገለጠ እውነት ያለው ሰው ነው። ለምን እንደሚኖር፣ ለማን እንደሚኖር ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው ነው። ለሀገር የሚከፈለውን ሁሉ ለመክፈል ቅሽሽ የማይለው ሰውም ነው። የድሆች ድምጽ ነው። እንደነ ጋሽ ደበበ እሸቱ ዘመን መጣልኝ። ቀንም ወጣልኝ ምኒሊክ ቤተ መንግሥት ገባሁ ዐቢይን ጨበጥኩ ብሎ ህዝብን የሚከዳ ይሁዳም አይደለም።
•••
አዲሱ አረጋ ትናንት የህወሓት ካድሬ ሆኖ የኦሮሞን ህዝብ ሲያስፈጅ፣ ሲያሰድድ፣ ሲያሳስር፣ ሲያስገድል የነበረ ህሊና ቢስ ሰው ነው። በኦሮሚያ ከአንድ ቤት ሁለት ሦስት ሰው በአግአዚ ጥይት እየተለቀመ የረገፈው በእነ አዲሱ አረጋ፣ ለማ መገርሳ፣ ዐቢይ አህመድ የጋራ ፓርቲ በኦህዴድ አጋፋሪነት ነው። ከጊንጪ የሞቱት ወንድምና እህት የአንድ ቤተሰብ አባላት የአቶ አዲሱ አረጋ የጥይት ውጤትና የኢህአዴግ ፓርቲ የግፍ ሰለባ ውጤቶች ናቸው። ዛሬ የለውጡ ዋና አጋፋሪ ነን የሚሉት አቶ ገዱ፣ ዶር ዐቢይ፣ ኦቦ ለማ፣ አቶ ደመቀ በሙሉ የትናንት ገዳይ አስገዳዮች የነበሩ ኢህአዴጎች ነበሩ። ዛሬም ኢህአዴግ ናቸው። ትናንት እስክንድርን ያሰሩ፣ ኦሮሞንም ዐማራንም፣ ሲዳማ ጋንቤላውንም ኢትዮጵያንም በጅምላ የፈጁ፣ ያስፈጁ ግለሰቦች ናቸው። እናም አሁን ኢህአዴግ ሆኖ እስክንድርን ለመተቸት አንዳቸውም ሞራል የላቸውም።
•••
አቶ አዲሱ አረጋ ቀላማጅ ነው። እወደድ ባይ ጥገኛም ሰው ነው። ከኦህዴድ ውጪ፣ ከካድሬነት ውጪ እንጀራ ቆርሶ መብላት እንደማይችል የሚያውቅም ሰው ነው። እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አፉን ከፍቶ፣ ፊቱን ጸፍቶ በአምቦው ስብሰባ ወቅት የአኖሌ ሃውልት የወያኔና የኤርትራዊው የተስፋዬ ገብረአብ የፈጠራ ውጤት ነው ብሎ በመመስከሩ ምክንያት እነ ጃዋር እንደ ዶር ፀጋዬ ስሜ ቀርጥፈው ሊበሉት ሲሉ ከጥርሳቸው ንክሻ ለማምለጥና ለመዳን ሲል በግልጽ ማሩኝ ብሎ በአደባባይ ሲቀባጥር ያየነው ሰፊ ሆድና ጠባብ ጭንቅላት የታደለ፣ የተሸከመ፣ እንደ እስስት በየዘመናቱ የሚለዋወጥ ህሊናውን ሽጦ ቅርጥፍ አድርጎ የበላ ወገበ ነጭ ወፍራም ካድሬ ነው። ትናንት የህወሓት፣ ዛሬ ደግሞ የኦዴፓ፣ ነገም ዕድሜ ከሰጠው የኦነግ ካድሬ ሆኖ እስኪሞት ራሱን እንደማያ እየቀያየረ የሚኖር ምስኪን ግለሰብም ነው። እናም ይሄን እወደድ ባይ አቋመ ቢስ ካድሬ መርሳቱ ነው የሚሻለው።
•••
ጃንሜዳ ሆዱ ካድሬው አዲሱ አረጋ ከካድሬነት ሳይላቀቅ በኦሮሚያ ገጠር እየዞረ ከምስኪኑ የኦሮሞ ገበሬ በሽልማት መልክ ብልኮና ቅቤ ሲሰበስብ እስክንድር ነጋ ግን የመናገር ነፃነት ዓለምአቀፍ ሽልማቶችን፣ ዕውቅናና ክብርን በህወሓት ኦፒዲኦ ኢህአዴግ መንግሥት 18 ዓመት ተፈርዶበት በታሠረበት ወኅኒ ቤት ሆኖ ይሸለም ነበር።
1. 2004ዓ.ም (2012) PEN/Barbara Goldsmith Freedom to Write Award
2. 2006ዓ.ም (2014 ) World Association of Newspapers’ Golden Pen of Freedom Award
3. 2009ዓ.ም (2017) International Press Institute World Press Freedom Hero
4. 2010 (2018) Oxfam Novib/PEN Award እስክንድርን ከሸለሙ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች መካከል ዋነኞቹ ናቸው።
•••
ነገሬን ለመቋጨት ያህል ለውጡ በፋኖ ነፍጥ እንጂ በቄሮ ነውጥ የመጣ አይደለም። እደግመዋለሁ ለውጡ በፋኖ ነፍጥ የመጣ ነው። አዳሜ ጫጫጫ ልትል ትችላለህ ። እኔ ታዲያ ምንተዳዬ ምንስ አገባኝ ጫ ጓም በል እኔ ምን አገባኝ። ቄሮ ሁለተኛ ደረጃ ነው የሚይዘው። አዎ መንገድ ዘግቷል። ፋብሪካ አቃጥሏል። ሆቴል አውድሟል። በሺህ የሚቆጠር ወጣትም ባዶ እጁን አጣምሮ ሰልፍ በመውጣት በአግአዚ እጅ ታርዷል። ፋኖ ባይነሳ ኖሮ ግን እስከአሁን ድረስ እርዱም፣ እስሩም፣ ግድያውም ቀጣይ፣ ወያኔም እንዲሁ ቀጣይ ነበረች። እውነቱ ይሄው ነው።
•••
እናም እኔ እስከሚገባኝ ድረስ እስክንድር ነጋ በእነ አዲሱ አረጋ ታስሮ ሲሰቃይ ከቆየ በኋላ ራሱ እስክንድር እንደ ሻማ ቀልጦ ለእነ አዲሱ አረጋና ለኢህአዴጎቹ ሁሉ ጭምር ያበራና ነፃ ያወጣቸው ጀግና ኢትዮጵያዊ የነፃነት ታጋይ ነው። በበዕሩ ጫፍ ብቻ አምባገነኖችን የሚያንቀጠቅጥ ጀግና። አከተመ።
••• እደግመዋለሁ ፦ 

• እስክንድር ነጋ ማለት የዘመኑ ቁጥር ፩ ነፃ አውጪ ጀግና አርበኛ ማለት ነው።

• ኮተት ካድሬ አዲሱ አረጋንም፣ 
• ራሱ ጠሚዶኮ ዐቢይ አህመድንም፣ 
• ሱሳችን ለማ መገርሳንም፣ 
• ሁሌ ምክትል ነሽ ደመቀ መኮንንም፣
• እንዳሉሽ ገዱ አንዳርጋቸውንም፣ 
• አይጨበጤው ዶር ብርሃኑ ነጋንም፣
• ፀረ ዐማራው አንዳርጋቸው ጽጌንና 
• እንደልቡ ጀዋር መሀመድን ከእኔ በቀር ሁሉንም ነፃ ያወጣ ወንድ እናቱ የወለደችው ጀግና ኢትዮጵያዊ ነው።
• አዳሜ ስትፈልግ “ ቋቀምበጭጧ” ብለህ ፈንዳት እንጂ እውነቱ ይሄው ነው። 
ሻሎም !  ሰላም ! 
ሰኔ 15/2011 ዓም
ከራየን ወንዝ ዳር።
Filed in: Amharic