>
5:13 pm - Sunday April 18, 3999

የአማራ መሰረት ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፡  ሁሉ፣ቆም ብለን ማሰብና መራመድ ይገባል!!! (ነአምን ዘለቀ)

የአማራ መሰረት ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፡  ሁሉ፣ቆም ብለን ማሰብና መራመድ ይገባል!!!
ነአምን ዘለቀ
ኢትዮጵያ ሀገራችንን ከጥፋትና ከእልቂት ለማዳን ቆም ብለን በሰከነ ሁኔታ ማሰብና መራመድ የሚያስፈልግበት እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ ጊዜ ላይ እንገኛለን።
ዛሬ ከፊታችን ያፈጠጠው መሰረታዊ ጥያቄ፣ አብይ አህመድን እንደግፍ ወይንም አንደግፍ የሚለው አይደለም። የዛሬው ማእከላዊ ጥያቄ ፣ የዛሬው ዋና ጥያቄ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ትቀጥል ወይንስ አትቀጥል የሚለው ነው። አብይ መጣ ፣ ከበደ፣ ዋቅጅራ፣ ወይንም ግደይ ፣ ይህቺ ታሪካዊት ሀገር፣ ይህቺ መከረኛ ሀገር፣ እትብታችን የተቀበረባት፣ የምንወዳት፣ ሌት ተቀን የምንጨነቅላት ኢትዮጵያ ሀገራችን ፣ በተማሩ ልጆቹ በተደጋጋሚ የተከዳና የተበደለ ፣ በድህነትና በችጋር የሚማቅቀው ፣ ነገር ግን ጨዋና ኩሩ የሆነው እብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ አብሮነት እንዴት ይቀጥል ነው ዋናው፣ መሰረታዊው፣ ማእከላዊው ጥያቄ፣ የዛሬው ጥያቄ ፣ የአሁን ሰአት ዋነኛ ጥያቄ ይሄው ነው።
ሰሞኑን “ኣማራው ተጠቃ፣ ተበደለ፡ ተገፋ” በሚል ሽፋን ፣ በአብይ አህመድ “የኦሮሞ/የኦዴፓን የበላይነት” ለመጫን እየሰራ የሚገኝ የትሮጃን ፈረስ ተደርጎ በስፊው የሚነዛው ጥላቻ፣ የሚረጨው ሰፊ መርዝና ቅስቀሳ ሰፊው የአማራን ህዝብ ጥቅም (፣ በአማራው ክልል ብቻ ሳይሆን በኦጋዴን፣ በሀረር፣ በባሌ፣ በአርሲ፣ በኢሉባቡር፣ በወለጋ፣ ወዘተ፣ በሌሎች አካባቢዎች የሚገኘውን ከ 10 ሚሊዮን በላይ አማርኛ ተናጋሪ ማህበረሰብ ) የአማራውን ህዝብ ደህንነትና ዋስትና ለማረጋገጥ ምን ያህል እንደሚጠቅም፡ ህልውናውንም እንደምን አርጎ ለማረጋገጥ እንደሚያገለግል ቆም ብሎ የታሰበበት አለመሆኑ ግልጽ ነው።
በትናንሽና በፍጹም የማይናበቡ ፣ የጋራ ራእይ፣ የጋራ ስትራቴጂ በሌላቸው በየጎጡ የተደራጁና አማራን እንወክላለን በሚሉ እንደ አሸን የፈሉ ቡድኖች የሚደረገው ይሄው በጣም የከረረ ጥላቻ፣ ማለቂያ የሌላቸው ብዙ ብዙ የውሽት ትርክቶች ሰፊውን የአማራ ህዝብ ጥቅምም ሆነ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ለማስቀጠል ፈጽሞ የማይበጅ፣ እንዲያውም በአማራው ክልልም ሆነ በበርካታ አካባቢዎች በጎጥና በአካባቢም ጭምር ወርዶ የእርስ በእርስ ግጭቶች ሊወልድ የሚችል አደጋ ያዘለ ሁኔታ እያደገ መሆኑን የሰሞኑ ክስተት ያመላክታል። ይህ ደግሞ የሶማሊያ፣ የሊቢያ፣ የሶሪያን እልቂትና መበታተን የሚደግም፡ ከዚያም የባሰ የምድር ሲኦል እንደሚፈጥር በተረጋጋ አዕምሮ ልብ ያለው ሁሉ ልብ ሊለው ይገባል።
ይልቅስ በዴሞክራሲያዊት ኢትዮጱያ የአማራው ዘላቂ ጥቅም የሚጠበቅበት፣ የሁሉም ህዝቦች አብሮነት የሚረጋገጥበት፣ የኢትዮጵያን እንድነት የምናስቀጥልበትን ሁኔታዎችና መንገዶችን ፣ ሰከን ብሎ ማሰብ፣ በስሜት ሳይሆን በስትሪቴጂያዊ አስተሳሰብ፣ በጥበብና በስልት ፣ በጋራ ፣ ሰጥቶ በመቀበል እንጂ ፣ ሰሞኑን በሶሻል ሚዲያ እንደሚራገበው አማራውን እንወክላለን የሚሉ በልዩ ልዩ ቡድኖች የተደራጁም ያልተደራጁም አክራሪ ብሄርተኞች እጅግ በሚያጦዙት መንገድ ፈጽሞ ሊሆን እንደማይችል የሮኬት ሳይንስ አውቀት መሆን የማያስፈልገው ሃቅ ይመስለኛል።
ሰደድ እሳቱ ሲጀመር እያንዳንዱ ቤት አንደሚያንኳኳ ቆም ብሎ ማሰብ፣ ከሌሎች ሀገሮች ውድመት፣ ውድቀትና፣ ምስቅልቅልነት  መማር -ሰአቱ ከመድረሱ በፊት ቆም በሎ ማሰብ ብልህነት፣ ማስተዋልም ነው። ስለዚህ፣ ለሰላም ፣ ለመረጋጋት፣ ማእከላዊ መንግስት የተከፈተውን ምህዳር ተጠቅሞ በሰላማዊ ፣ ህጋዊ፣ ስልታዊና ስትራቴጅካዊ አካሄድ በመከተል በሰላማዊና በተደራጀ መልክ የአማራውን ህዝብ ጥቅም፣ ደህንነት ለማሰጠበቅ መንቀሳቀስ እንጂ የሰፈር የጦር አበጋዞች/ Warlords  (በሶማሊያና በሊቢያ እንዳየነው)  ፣ ከህግና ከስርዓት ውጭ የራሳቸውን ፍላጎት በጉልበት ለመጫን የሚፈልጉ አፈንጋጮችን (በሶሪያ እንደተከሰተው Rogue military commanders) በማጀገን የአማራውን ህዝብ ተገፍቻለሁ፣ ተጠቅቻለሁ ብሎ እንዲነሳሳ ሰፊ ቅስቀሳ ማድረግ ታሪክ ይቅር የማይለው ፣ የአማራውን ህዝብንም ሆነ፣ የአማራው ማህበረሰቦች በደም ፣ በህይወቱ፣ በላቡ ገብሮ ፣ ለግንባታዋ ብዙ ለተዋደቀላት lታላቋና lታሪካዊቷ ኢትዮጵያ  የማይበጅ፣ ወደ ጥፋት፣ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት፣ አልፎም ወደ ውድመትና ወደ መበታተን ሊያደርሰን የሚችል ሂደት እየተመለከትን ነው።
በዚህ ሁሉ ትርምስ ደግሞ ዛሬ የሚፈነጥዘው፣ ይህን ሰፊ ትርምስ ለራሱ በሚገባ እየተጠቀመ የሚገኘው፣ እንደ አንድ ሰው የቆመው፣ እስከ አፍንጫው የታጠቀውም ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ሕወሃት) ብቻ ነው። ሌላው ተከፋፍሎአል፣ በአብይ አህመድ ላይ በሚወርደው የጥላቻ ውርጅብኝም ሀገሪቷን እንደ ሙጫ አጣብቆ ደካማ ቢሆንም የያዘውን ስርአተ መንግስት(state)፣ ማጭከላዊ መንግስቱንም ለማዳከም ብዙ የድንጋይ ናዳ አየወረደ ነው። በየእለቱ በተደራጀም በአልተደራጀም መልኩ እየተደረገ የሚገኘው ይሄው ነው።
ሕዝብን እርስ በእርስ ሊያባላ፡ ሊያጫርስ የሚችል፣ ምንም አማራጭ ሃሳብ፣ ራእይና ፣ ድርጅትም ሆነ ስትራቴጂ ለማቅረብ የማይችሉ፣ ነገር ግን አማራውን እንወክላለን የሚሉ፣ እንዲሁም በአብይ አህመድ ላይ የግል ጥላቻና ጥርጣሬ ያላቸው በርካታ ግለሰቦችና ቡድኖች ጭምር ተሳታፊ የሆኑበትን  ሁኔታ  በከፍተኛ ስሜት በማጦዝ፣ የተገፊነትን ስሜት በመቀስቀስ ላይ የተመሰረተ ሰፊ ዘመቻ ያነጣጠረውና እየተጓዘ ያለው በዚሁ ግብ ላይ በመመርኮዝ ነው። የእነዚህ ቡድኖች ምንም መናበብም ሆነ ፣ የጋራ አማራጭ፣ እንዲሁም ለሀገራችንና ለህዝባችን አሻግሮ የሚያይ ራእይ የሌላቸው መሆንና ፣ እርስ በእርሳቸው በዓላማና በሃሳብ መናበብ  ቀርቶ በአንድ ላይ  እንኳን ተቀምጠው በአግባቡ በምክኒያታዊነት መነጋገር፣ መደማመጥና መሰማማት  የማይችሉ፣ ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ሃይሎች የሚገፋውና የሚረጨው መርዝ ሁሉንም (እነሱንም ጨምሮ) ወደ ፍጹማዊ ኪሳራ ፣ የዜሮ ድምር ፓለቲካ (zero-sum game) የሚወስድ፣ ማንም ምንም ወደማያተርፍበት የሲኦል መንገድ አገራችንንና ህዝባችንን እየገፋ መሆኑን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዛሬ ላይ በሚገባ መገንዘብ አስፈላጊ የሆነበት ወቅት ላይ የደረሰን ይመስለኛል። ነገ በጣም ይዘገያል (Too little too late)።
ክዚህ አሳፋሪና ለሀገራችን ህልውና ብሎም ለኢትዮጵያ 105 ሚሊዮን ህዝብ አብሮነት፣ ለኢትዮጵያ አንድነት ቀጣይነት እጅግ አስጊ ሁኔታ በተፈጠረበት በአሁኑ ወቅት አሸናፊ የሚሆነው ማነው? ሁሉንስ ድልና ወርቅ አፋሽ የሚሆነው ማነው? ብቸኛ ተጠቃሚስ ይኖራል ወይ? በሰላም ደሴት በደስታና በፍስሃ ሊኖር የሚችለውስ ማነው? ስለእውነት፡ ስለሃቅ ለመናገር ማንም አሸናፊ እንደማይሆን፣ ማንም እንደማያተርፍ በእርግጠኝነት መተንበይ ይቻላል ። ሁላችንም ተያይዘን ወደ እልቂት ፣ ወደ ሁለንተናዊ ውድቀት፣ ወደ ሲኦል እያዘገምን ይመስለኛል።
ስለዚህ ወግኖቼ ቆም ብለን ማሰብ ብልህነት ነው፣፡  ነገን ማሰብ፣ በተረጋጋና በምክንያታዊነት ዛሬን በትግስትና በስልት መራመድ አስፈላጊና ወሳኝም ናቸው። የአማራውንም ደህንነት፣ የሌላውን ኢትዮጵያዊ ማህበረሰቦች/ብሄሮች፣ አብሮነት፣ እንዲሁም  የሌላውን እኩልነት፣ መብት፣ ደህንነት፣ ለማምጣት በጥንቃቄ፣ በህግ አግባብ፣ በሰላማዊ መንገድ፣ አስቦ ፣ በአስተውሎ መራመድ የነገን ውድመት፣ የሀገር መበታተን፣ የህዝብንም እልቂት የሚከላከል ሁሉም ህዝቦች በጋራ በሰላም፡ በዴሞክራሲ ፣ በህግ የበላይነት፡ በእኩልነት የሚኖሩባት ኢትዮጵያን የሚያረጋግጥልን ብቸኛ መንገድ መሆኑን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ፣ ሁሉም የአማራ መሰረት ያለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ በውጭም በሀገር ውስጥም ሊያጤነው የሚገባ ይመስለኛል። የመጨረሻው ደወል እያቃጨለ መሆኑ እየተሰማኝ ነው። ኢትዮጵያ እንደ ሀገር፣ ሁሉም ሕዝቦች፣ ማህበረሰቦች፣ በእኩልነት፣ በፍትህ፣ በሕግ የበላይነት የሚኖሩባት ኢትዮጵያን ሁሉም ኢትዮጵያዊ፣ የአማራ መሰረት ያለን  ኢትዮጵያውያን ሁሉ በጥሞና አስበን፣ አስተውለን፣ አቅደን መንቀሳቀስና ሀገራችንን ከጥፋት የማዳኛው ወቅት አሁን ነው፣ ዛሬ ነው።
እግዚአብሔር ሀገራችንና ሕዝባችንን ይጠብቅልን፣ ስላሙን ያውርድልን
Filed in: Amharic