>
5:13 pm - Saturday April 20, 9912

በሰማነው ልክ እንጠይቃለን ....!  (መስከረም አበራ)

በሰማነው ልክ እንጠይቃለን ….! 
መስከረም አበራ
ከሰሞኑ በሃገራችን የተከሰተውን የባለስልጣናት መገዳደል ተከትሎ ልቡ ያላዘነ አይኖርም፡፡ማንም ሆነ ማን በጥይት መሞት የለበትም፣ነፍስን መውሰድ የሚችል እርሱ ያበጃት ባለቤቷ ፈጣሪ ብቻ ነው፡፡ሆኖም የሆነው ሌላ ነው-መሆን ያልነበረበት እጅግ አሳዛኝ ነገር፡፡ ምን ማድረግ ይቻላል? ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ እጅግ የተደባለቀው የፖለቲካችን ጎራ ደግሞ የተፈጠውን ነገር እንዴትነት ለመመርመር የሚያስቸግር አድርጎታል፡፡ ይህ ድብልቅልቅ አስተውሏችንን ነጥቆ በመደናገር የሚሞላ ነገር አለው፤እንደቤተሰብ ሆኖ ላሰበው ደግሞ የሃዘኑ ምሬት “ምን አመጣብን?” የሚያሰኝ ነው፡፡
የኢህአዴግን  ፖለቲካ የተጣባው ድብቅነት፣በችግር ላይ መተኛት፣በሆድ እየተቋሰሉ በካሜራ ፊት እጅ ለእጅ ተያይዞ መታየት፣ማስመሰል ችግርን ሳይጎረምስ መፍታት አላስችል ብሎ ለዚህ እንዳበቃ ግልፅ ነው፡፡አሁን ድርጊቱ ከተከሰተ ወዲህ እንኳን ልብ ብሎ ለታዘበ እነዚህን  የኢህአዴግ የቤታቤት ችግሮችን ያስተውላል፡፡ አንደኛው የኢህአዴግ ፓርቲ ባህል የደደረ ችግር ህዝብን በአንድ ወገን ፕሮፖጋንዳ ማደንቆር ነው፡፡”ኢንተርኔት የዘጋነው ሃገር እንዳትፈርስ ነው” ብለው ሁሉን ነገር ከጠረሙ በኋላ አማራጭ ለሌለው ህዝብ የሚግቱት እነሱ እንዲሰማ የሚፈልጉትን፣ሊደብቁ የፈለጉትን የሚያድበሰብሰውን፣የጠሉትን ጭራቅ የወደዱትን መልዓክ አድርጎ የሚያቀርበውን ራስ አዟሪ ፕሮፖጋንዳ ነው፡፡
ራሳቸው በሚከፍቱ በሚዘጉት ሚዲያ የሚቀርበው መረጃው ፣ምስክርነቱ ፣አድናቆቱ ሁሉ ይህንኑ የሚያጠናክር ሰሚን “የት ልድረስ!” የሚያስብል ተመሳሳይ ነገር ነው፡፡ በዚህ ላይ በየደቂቃው የሚቀያየር መረጃም ያለበት ነገር ይቀርባል፤በዚህ ሁኔታም መንግስትን እንድናምንም ይጠበቃል፡፡ ኢንተርኔት መለቀቁ ችግር ይፈጥራል ከተባለ በተቻለ መጠን ሚዛናዊ ነገር ማቅረብ ያባት ነው፡፡ እንኳን ሚዛናዊ ነገር ሊቀርብ ቀርቶ የሞቱትን ሰዎች የቀብር ስነስርዓት እንኳን እኩል መዘገብ አልተቻለም፡፡ ጀነራል አሳምነው ከሟቾች ወገን ናቸው፤መሞታቸው ከተነገረ በኋላ አስከሬናቸው የት እንደገባ፣ቀብራቸው የት እንደሚፈፀም ካለመነገሩ የተነሳ አልሞቱም የሚባል ወሬ ሁሉ ተጀምሮ ነበር፡፡ስለተቀሩት ሟቾች ቀኑንም ማታውንም ሲዘገብ ለአንዱ ሟች ሶስት ደቂቃ ወስዶ እንዴት እንደሞተ፣የት እንደሚቀበር ለመንገር የተቸገረው መንግስት የሚዘውረው ሚዲያ ብቻ ሳይሆን “ገለልተኛ እና ነፃ ነኝ” የሚለው ሚዲያ ሁሉ መሆኑ የፖለቲካችንን ክፉኛ መወላከፍ ያስረዳል፡፡
 ይህ የፕሮፖንዳቸው መንፈስ ራሱ ግድያው ከመከሰቱ በፊት መንግስት ለማን ምን አይነት ስሜት እንደነበረው የሚጠቁም እንደሆነ እንኳን አይረዱም! ስለሞተ ሰው ቀብር ለመናገር እስከ መቸገር የደረሰ መንግስት ለህዝብ  ስለይቅርታ እና ፍቅር ሊሰብክ ሲሞክረው የኖረ መሆኑ አጃኢብ ነው!የጀነራል አሳምነውን ቀብር ስነስርዓት ለመዘገብ ያልፈለገው ኢቲቪ  የሎሬት ፀጋየን ሞት ካልተናገረው ኢቲቪ የሚለየው ከስክሪኑ ስር 57 ቁጥርን መፃፉ ብቻ ነው፡፡የአማራ መገናኛ ብዙሃን እና የአዴፓ ባለስልጣናት እየተፈራረቁ ያወረዱብን የፕሮፖጋንዳ ዶፍ እነሱ ፈለጉትን ያህል ወደ እነሱ እውነት ጎራ ሊነዳ ፋትሯል፡፡የአዴፓ ካድሬዎች ነገረ ስራ በአዴፓ የሎሌነት ልማድ መቀየር ላይ ተደርጎ የነበረውን  ጭላንጭል ተስፋ ማመናመኑም አይቀርም፡፡በበኩሌ አዴፓ እና አገልጋይነት ይነጣጠላሉ ብየ አስቤም ስለማላውቅ የአዴፓ ባለስልጣናት ሰሞኑን በክልሉ የተከሰተውን ሁኔታ አስመልክቶ የቀላመዱት አስገማች ነገር ብዙም አልደነቀኝም!
የአዴፓ፣ኦዴፓ እና የፌደራል መንግስት ባለስልጣናት(የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩን ጨምሮ፣ጠቅላይ ሚኒስትሩም ጭምር) በአማራ ክልል መፈንቅለመንግስት ተደረገ ብለው አፋቸውን ሞልተው መናገራቸው ሳያንስ መፈንቅለ መንግስቱን ያደረገው ጀነራል አሳምነው ፅጌ እንደሆነ ደንቀፍ ሳያደርጋቸው እርግጠኛ ሆነው ይናገራሉ፡፡በተለይ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ “ባገኘነው መረጃ መሰረት መፈንቅለ-መንግስት መካሄዱ እርግጥ ነው አንድ ብላችሁ አንዳትጠራጠሩ፣ወደፊት እያጣራን የምናሳውቀው ነገር ቢኖርም ነገሩን ያቀነባበረው ግን ጀነራል አሳምነው መሆኑ በምንም የማይቀየር ሃቅ ነው” ብለው ደምድመው ያረፉት ነገሩ ከተከናወነ ሃያ አራት ሰዓት እንኳን ሳይሞላው ነው፡፡
ከዛ በኋላ ንጉሱ ጥላሁን የተባሉ ሰው እየተመላለሱ፣የአዴፓ ባለስልጣናት እየተፈራረቁ ሶስት ዳኛ ብዙ ምስክር ሰምቶ፣ሰነድ አገላብጦ ያረጋገጠውን ሃቅ እንደሚያወሩ እርግጠኛ ሆነው በፍፁም ምቾት ጀነራል አሳምነውን ሲረግሙ ሰነበቱ፡፡ይህ ነገር መለስ ዜናዊ በፓርላማ ተቀምጦ ፍርድ ቤት በያዘው የነእስክንድር ነጋን አሸባሪነት ላይ በከፍተኛ እርግጠኝነት ኮራ ብሎ ሲያወራ ከነበረው ልዩነቱ ምን እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም፡፡
በሰላም እና ፍቅር ሰባኪነታቸው የምናውቃቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ትናንት የሃዘን መግለጫ ብለው በፃፉት ፅሁፍ ያወረዱት ለስድብ የሚዋሰን ውርጅብኝ ኢንተርኔት እስከመዝጋት አደረሰን ለሚሉት የሃገር ማረጋጋቱ ነገር የሚበጅ አይመስለኝም፡፡እንደሚያስቡ እንድናስብ ፈልገው የሚነግሩን መረጃም እነሱ እንደሚያስቡት ፍፁም፣ጥያቄ የማይነሳበት ነገር አይደለም፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ህይወታቸው ባለፈበት ቅፅበት የፌደራል ፖሊስ እና መከላከያ ሰራዊት እንደ ንፋስ ሽው ብሎ ከአዲስ አበባ ባህርዳር የተገኘው በማን ጋባዥነት እንደሆነ የነገረን የለም፡፡ዶ/ር አብይ ከቀናት በፊት በደሴ ከተማ ተገኝተው እናንተ ውስጥም በጀቱን ሁሉ ለልዩ ሃይል ስልጠና የሚጨርስ ጌታቸው አሰፋ አለ ያሉት ነገር የተፈጠረው ነገር ለመፈጠሩ ምክንያቱ ጀነራል አሳምነው ብቻ ናቸው ወይ የሚለውን ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡ የአዲስ አበባው የጀነራል ሰዓረ ግድያ ከአማራ ክልል መፈንቅለ መንግስት ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከነገሩን ከቀናት በኋላ ዛሬ ማታ የሰላም እና ደህንነት ግብረሃይ በሚባል የድንገቴ ግብረሃይል ባወጣው መግለጫ ደግሞ የባህርዳሩ እና የአዲስ አበባው ግድያ መያያዝ አለመያያዙን ቀስ ብለን አጣርተን አናሳውቃለን ብለዋል፡፡
ጀነራል ሰዓረን የገደላቸው ሰውየ ደግሞ አንዴ ቆስሎ ተያዘ ፣ከዛ ሞተ፣በመጨረሻ ደግሞ ቆስሎ ወደ ህክምና ሄደ ተብሏል፡፡የጀነራል ሰዓረን ሞት በተመለከተ የሚሰጠው እጅግ የተሳከረ ነገር የሚያጠያይቀው ነገር ብዙ ነው፡፡በነገሩን ልክ፣ካወሩት ተነስተን ይህን ጠየቅን እንጅ ከሚነግሩን ወጣ ብለን፣ልቦናችንን ተከትለን እንጠይቅ ከተባለ ጥያቄያችን ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የኢህአዴግ ካድሬዎች እነሱ ለህወሃት ሲያደገድጉ እምቢ ማለትን ያሳያቸውን ጀነራል አሳምነውን እነሱ ታግለው ያስፈቱት መሆናቸውን ደጋግመው የሚያወሩት ነገር፣ጀነራሉ አደረገ የሚሉትን ነገር ሁሉ ያደረገው የአማራ ህዝብ በሰላም ውሎ እንዳያድር አስቦ ፣ስልጣን ፈልጎ ነው የሚሉት ነገር  በተለይ ሳይወዱ ሳቅ የሚያመጣ ነገር ነው፡፡
Filed in: Amharic