>

በአብን አባላት እና ደጋፊዎች ላይ የተጀመረው የጅምላ እስር ባፋጣኝ ሊቆም ይገባል!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

በአብን አባላት እና ደጋፊዎች ላይ የተጀመረው የጅምላ እስር ባፋጣኝ ሊቆም ይገባል!!!
ያሬድ ሀይለማርያም
የሰሞኑን ግርግር ተከትሎ ቁጥራቸው ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ የአብን አባላት ታስረው አንዳንዶቹ በቤተሰብ እንኳን እንዳይጠየቁ የተደረገ መሆኑን የድርጅቱ አመራሮች በመግለጽ ላይ ናቸው። ይህ አይነቱ የጅምላ እርምጃ ለከፍተኛ የመብት ጥሰት እና ግርግሩን ለድብቅ የፖለቲካ አላማ ለመጠቀም ለሚፈልጉ የመንግስት አካላት በር ይከፍታል። በባህርዳር እና በአዲስ አበባ ያሉ የድርጅቱ አባላት ሰሞኑን በክልሉ ውስጥ ከተፈጠረው ግጭት እና ትርምስ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ተጠርጥረው ሊሆን ይችላ፤ ጉዳዩ ተጣርቶም ነጻ ይወጣሉ ብሎ ለማሰብ ይቻል ይሆናል።
ይሁንና በበርካታ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ውስጥ የአማራ ተወላጅ በሆኑ ባለሃብቶች፣ የድርጅቱ ደጋፊዎች እና አባላት ላይ የተጀመረው የጅምላ እስር ግን ከሰሞኑ የመፈንቅለ ትርምስ ይልቅ ተያያዥነት ያለው የሚመስለው በቅርቡ አቶ አዲሱ አረጋ በክልላችን የእኛን የፖለቲካ አቋም የሚጋፋ ወይም የሚጻረር አቋም ያለው የፖለቲካ ድርጅት እንዲንቀሳቀስ አንፈቅድም ከሚለው ጋር የተያያዘ ይመስላል።
የፌደራል መንግስት ይህ ጉዳይ በአንክሮት ተከታትሎ እንዲህ ያሉ የጅምላ እስሮችን ባፋጣኝ ማስቆም ይኖርበታል። አብን እንደ ድርጅት ሊጠየቅበት የሚገባም ነገር ካለ መንግስት ድርጅቱን በአገሪቷ ሕግ መሰረት ሊጠይቀው ይገባል። በሕግ ፈቃድ አግኝቶ የሚንቀሳቀስ ድርጅት አባላትን በዚህ መልኩ ማዋከብ፣ ማሰር እና በእስር ላይም ያሉትን በቤተሰብ እንዳይጎበኙ እና የሕግ አማካሪም እንዳያገኙ ማድረግ ግን ሕገ መንግስቱን እና አገሪቱ የፈረመቻቸውን አለም አቀፍ ድንጋጌዎች የሚጥስ ተግባር ነው።
አንደኛውን ብሔረተኛ እያጠበደሉ ሌላኛውን ብሔረተኛ ማሳደድ አገሪቱ የተጋፈጠችውን ችግር ያገዝፈው ይሆናል እንጂ ወደ መፍትሔም አይወስድም።
እየተስተዋለ ቢሆን መልካም ነው።
Filed in: Amharic