>

ነጠብጣቹን ስናገጣጥም  ነገርየው እንዲህ ሆኖ እናገኘዋለን፤ (ዘመድኩን በቀለ)

ነጠብጣቹን ስናገጣጥም ነገርየው እንዲህ ሆኖ እናገኘዋለን፤
ዘመድኩን በቀለ
★★★ ጸሐፊው የትግራይ ሰው ነው።  
 
★ እነ ዶር አምባቸውና ጀነራል አሳምነው ጽጌ ለምን እንደተገደሉ ይናገራል። በማን እንደተገደሉ ፍንጭ ይሰጣል።
 
★ እነ ጀነራል ሰዓረና ጀነራል ገዛኢ ለምን እንደተገደሉና በማን እንደተገደሉም ፍንጭ ይሰጣል። ማረጋገጫም አለኝ ይላል። 
 
★ ስለ ትግራይና ዐማራ የጦርነት ፕሮጀክትም ፍንጭ ይሰጣል።
 
★ እርግጠኛ ሆኖም በቅርብ ቀን “ ኢትዮጵያ ፍርክስክሷ” የሚወጣበትን ምክንያትም ይናገራል። 
 
★ ጦማሩ እንደ እንደ ገንፎ የሚዋጥ ነው ብዬ አልመክርም። ባይሆን እንደ ዓሣ በብልሃት ብሉት ብዬ እመክራለሁ። መልካም ንባብ። 
 ጸሓፊው ትግራዋይ ነው። ዘጸአት ሴቭ አድና በሚል የብዕር ስም ለህወሓት ጥብቅና ይዞ በመሟገት ይታወቃል። በሙያው ዶክተር እንደሆነም የሚያውቁት ይናገራሉ። ህወሓት ለምን ትተችብኛለህ በማለት ይህ ሰው ስሜን ጠቅሶ ሁለት ሦስት ጊዜ እንደጦመረብኝ እንዳጥረገረገኝም አስታውሳለሁ። እናም ዛሬ ደግሞ ከዚያ መንደር ያሉ ወገኖች ስለ “ መፈንቅለ መንግሥቱ ” ምን እንደሚያስቡና በጉዳዩ ዙሪያ የሰጡትን አስተያየት ይዤላችሁ ቀርቤያለሁ።
•••
መፈንቅለ መንግሥት ተብዬውን ጉዳይ በተመለከተ የእነ ጃዋር መሃመድን ምልከታ የሰማን ሰዎች አሁን ደግሞ ከዚያኛው ሰፈር የህወሓት ሰዎች በጉዳዩ ዙሪያ ደግሞም ለጉዳዩ እጅግ በጣም ቅርብ ናቸውና እስቲ የሚሉትን እንስማቸው በጥሞናም አድምጧቸው።
..በማስተዋል እንዲነበብ ይሁን፤ ብሎ ነው ጸሐፊው ጦማሩን የሚጀምረው።
•••
እነ አቶ አሳምነው ፅጌ በስቃይ ከተሞላ የእስር ህይወት እንደተፈቱ እንደ እርሳቸው ያሉ በትግራይ ህዝብ ላይ ከፍ ያለ የጥላቻ ስሜት፣ የበቀል፣ የደም-መላሽነት ስሜት ላይ የነበሩ ሰዎችን በማሰባሰብ የአማራ ክልል የፀጥታው ዘርፍ እንዲቆጣጠሩ የተደረገው የሰዎቹን እምቅ የበቀል ስሜት እንደ መሳርያ በመጠቀም በትግራይና በአማራ መካከል የማያባራ መዳማትና ማቋሰል እንዲኖር፣ በውጤቱም ሁለቱን ክልሎች በማይነሱበት ደረጃ እንዲዳከሙ ከመፈለግ ነው የሚሉ ሰፊ መላምቶች አሉ፡፡
•••
ለዚህም ይሆናል አቶ ገዱ በአማራ ክልል የፕሬዚዳንት ቦታ ተቀምጠውም እያለ እርሳቸው በማያውቁትና ከእርሳቸው ቁጥጥር ውጪ በሆነ ሁኔታ በርካታ ገንዘብና የመሳርያ ዓይነት ወደ ክልሉ እየፈሰሰ ነበር። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም በተለይም በጎንደርና በጎጃም የተኩስ ስልጠና እየወሰዱ፣ እየታጠቁ ነበር። ለዚህ ሁሉ ስልጠናና መሳርያ ግዢ የሚሆን በቢልዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ከዐረብ ሐገሮች ነበር የሚፈሰው፡፡ ይህንን ሁሉ የሚያስፈፅመው የክልሉ የሰላምና የደህንነት ቢሮ፣ የፀጥታ መዋቅሩ ነበር፤ በሌላ በኩል በቀጥታ አቶ አሳምነው ፅጌ ነበሩ የሚቆጣጠሩት፡፡
•••
አቶ ገዱ “ይኽ ነገር እንዴት ነው? ወዴት ወዴት እየሄድን ነው?” ብለው መጠየቅ ሲጀምሩ፤ “ከትግራይ ጋር መቋሰል ለማን ጥቅም ተብሎ?” የሚል ጥያቄ ማንሳት ሲጀምሩ “ዳተኛ” ተብለው ተገመገሙ። በመጨረሻም ለሳምንታት ያህል በምስጢር ከተንሳፈፉ በኋላ በይፋ ስልጣን እንዲለቁ ሆነ፡፡  ዶ/ር አምባቸው ወደ ስልጣን ሲመጡ የዚህን አማራን በመቶ ሺህ የማስታጠቅና ከትግራይ ጋር የመዳማት ዕቅድ ደጋፊ ነበሩ፡፡ ሆኖም ክልሉ ማስተዳደር ሲጀምሩ፤ በክልሉ ያለውን ሁኔታም በጥልቀት እየተገነዘቡ ሄዱ። መቶ ሺዎችን ማስታጠቅና ትግራይን ለመጨፈጨፍ መሞከር ሄዶ ሄዶ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል እየገባቸው ሄደ። ከኋላ ሆኖ ቢልዮኖችን እያፈሰሰ “ግፋ!” እያለ ያለው አካል ዓላማው በውል እየተረዱ መጡ፡፡ በመሆኑም ነገሮችን ሰከን ባለ አእምሮ ማየት፣ ማስተዋል ጀመሩ። ከጀርባ ምን እየተደገሰ እንዳለ በመረዳትም ይህን ወደ ሴራ ወደ ማክሸፍ መሄድ ጀመሩ፡፡
•••
ጀነራል አሳምነውም ጽጌም እንዲሁ ከባለፉ ጥቂት ሳምንታት ጀምረው ከኋላ ሆኖ ቢልዮኖችን እያፈሰሰ “ግፋ!” የሚላቸውን ኃይል እኩይ ዓላማውን በውል እየተረዱ የመጡ ይመስላል(በእርግጥ ስለዚሁ ሴራ ቀደም ብለው የተረዱትና ለታከቲክ ብለው እንደማያውቁ ሆነው አምቀው የያዙትም ሊሆን ይችላል)፡፡ ለዚሁ ማሳያም ከሦስት ሳምንታት በፊት በአንድ መድረክ ‘የግራኝ መሐመድ የወረራ ታሪክ’፣ ‘ውጤቱ የተከተለው የኦሮሞ መስፋፋት’ን በተመለከተ ተናገሩ፤ “አሁንም ተመሳሳይ ፍላጎት ያለ ስለመሆኑ” ገለፁ፡፡ በመቀጠልም በሌላ መድረክ “ያለ የክልሉ የሰላምና የደህንነት ቢሮ እውቅና ውጪ የፌደራል መንግሥት ማንም የአማራ ተወላጅ የሆነን የክልላችን ነዋሪ እንዲያስር አንፈቅድለትም” አሉ።
★ እነዚህ ንግግሮቻቸው የአሳምነው ፅጌ አፈሙዝ ወደ ትግራይ ብቻ ሳይሆን ወደ አዲስ አበባም ወደ ኦሮሚያም እንደሆነ ለወዳጅም ለጠላትም ግልፅ ሆነ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትሩና በመላው የኦሮሞ ልሂቃን ዘንድ አቶ አሳምነውን እንደ ትልቅ የስልጣናቸው፣ የዕቅዳቸው አደጋ አድርጎ መመልከት እያደገ መጣ፡፡
•••
ጀነራል ሰዐረ መኮንን የተገደሉት ዶ/ር አምባቸው በተገደሉ በደቂቃዎች ውስጥ ነው። ጀነራሉ በተገደሉበት ሰዓት በቤታቸው ግቢ ውስጥ ባለው ሳር ላይ ወንበር ስበው ከሜ/ጀ ገዛኢ ጋር እየተጨዋወቱ ነበር። ቤተሰብ ደግሞ ከቤት ውስጥ ነበር፡፡ የግል ጠባቂያቸው በግቢው ውስጥ ነበር። የቤቱ ጠባቂ የሪፓብሊከን ጋርድ አባላትም በቤቱ በአራቱም መዐዝናት ነበሩ፡፡
•••
ድንገት ተከታታይ ተኩስ ተሰማና ከቤት ውስጥ የነበሩ የጀነራሉ ቤተሰቦች ከቤት ወጥተው፤ ከቤቱ አጥር ውጪ የነበሩ የጀነራሉ ሾፌርና ሌሎች ሰዎች ወደ ግቢ ገብተው እነ ጀነራል ወዳሉበት ሲያማትሩ ሦስቱ ሰዎች(ጀ/ል ሰዐረ፣ ሜ/ጀ ገዛኢና የጀነራል ሰዐረ ጠባቂ) በደም ተጨማልቀው ወድቀው ነበር፡፡ የጀነራሉ ጠባቂ ከአንገቱ ስር ነበር የተመታው፡፡ ጠባቂው ቆስሎ እያጣጣረ እያለ ነው የቤቱ የጥበቃ አባላት ደጋግመው የመቱት፡፡ ይህንን ከጀነራሉ የቤተሰብ አባላትና ከጀነራሉ ሾፌር አረጋግጫለሁ። “ጥበቃው በእጁ ሽጉጥ ይዞ ነበር” በሚል መነሻ ነው እንግዲህ “በግል ጥበቃቸው ተገደሉ” እየተባለ እዚህም እዚያም እንደ ገደል ማሚቶ እየተስተጋባ ያለው፡፡
•••
የጀነራሉ ጠባቂ ሁለቱን ጀነራሎች ገድሎ እራሱን አጠፋ ነው እየተባለ ያለው፡፡ ሁሉም ነገር በግል ጠባቂው ላይ ተለጠፈና በዚሁ ተድበስብሶ እንዲቀር እየተሞከረ ያለው፡፡  እራስን እስከ ማጥፋት የሚደርስ ጥቃት(የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት) ለመፈፀም የሚያበቃ፣ የሚገፋፋ ምን ታላቅ ምክንያት ቢኖር ነው? ሆኖም በጊዜው ከጠባቂው በተጨማሪ ቤቱን የሚጠብቁ አራት የሪፓብሊካን ጋርድ አባላት ነበሩ፤ ሦስቱ ሰዎች በእነዚሁ የሪፓብሊካን ጋርድ አባላት ወይም ከውጪ/ከሩቅ በአልሞ-መቺ (ስናይፐር) ተገድለው ሊሆን የሚችልበት ሰፊ ዕድልም አለ። ጠባቂው ሽጉጥ የመዘዘውም ተኩሱና ግድያው እንደተጀመረ ሊሆን ይችላል፡፡
•••
ሌላው የግድያው አጠራጣሪነት ይበልጥ የሚያጎላው ጉዳይ “ጀነራል ሰዐረ በአማራ ክልል ላይ የተነሳው የመፈንቅ-መንግሥት ሙከራ ለማክሸፍ አመራር ሲሰጡ ነበር፤ በዚሁ መሐል ነው ጥቃቱ የደረሰባቸው” ነው የተባለው፡፡ ሆኖም ይህ ሐሰት ነው፡፡ በሁለቱ ግድያዎች መካከል የደቂቃዎች ልዩነት ነው የነበረው። ጀነራሉ ሲገደሉ በቤታቸው ከረዥም ጊዜ በኋላ በአካል ካገኟቸው ከድሮ ጓደኛቸው ከሜ/ጀ ገዛኢ ጋር እየተጨዋወቱ ነበር። በባህርዳር እየሆነ ስለነበረው ነገርም መረጃ አልነበራቸውም፡፡ “ጀነራል ሰዓረ የባህርዳሩን መፈንቅለ-መንግስት ለማክሸፍ አመራር ሲሰጡ ነበር” ማለት “ገዳዮቹ ጀነራሉን የገደሉት ቀደም ብለው አስበውበትና ተዘጋጅተውበት ሳይሆን በጀነራሉ ሥራ ስለተበሳጩ ነው እርምጃ የወሰዱት” እንደማለት ነው፡፡ ይህ የግጭት አቅጣጫውን(axis of confrontation) ወደ ጀ/ል ሰዓረ-አሳምነው ለመውሰድ የሚደረግ ከንቱ ጥረት ነው፡፡
★ እውነቱ- ዶ/ር አምባቸውም ጀነራል ሰዓረም በተመሳሳይ ሰዓት፣ እጅግ በተጠና ሁኔታ ነው የተገደሉት፡፡
•••
ዶ/ር አምባቸው በአዴፓና በህ.ወ.ሐ.ት መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት ለማጥበብ፣ የህዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለመመለስ መንቀሳቀስም ጀምረው ነበር፡፡ በዚሁ ፍላጎት መሰረትም ዶ/ር አምባቸው ወደ ህ.ወ.ሐ.ት ሰዎች ዘንድ ተደጋጋሚ የስልክ ግንኙነት ለማድረግ ሞክረዋል። አንድ ሁለት ተወካይ በመላክም ግንኙነቱ ለማሻሻል እየተንቀሳቀሱ ነበር፡፡
በዚሁ ሁሉ መሐል ነው እንግዲህ ጀነራል ሰዓረ፣ ዶ/ር አምባቸው፣ ብ/ጀ/ል አሳምነው፣ ወ.ዘ.ተ የተገደሉት፡፡
•••
ብ/ጀ/ል አሳምነው ፅጌን በእጅ መያዝ ይቻል ነበር፡፡ “አትግደሉኝ፣ የምናገረው ብዙ ሚስጢር አለኝ” እያሉ እንደተገደሉ ነው እየሰማን ያለነው፡፡ የሆነ እንዲደበቅ የተፈለገ ምጥጢር አለ ማለት ነው፡፡ የጀነራል ሰዓረ ገዳይም የተባለው ሰውም ያው እራሱን አጠፋ ተብሏል(ቆይቶም ‘እራሱን አቆሰለ’)፡፡
•••
እነ ዶ/ር አምባቸውን የገደለው ብ/ጀ/ል አሳምነው ፅጌ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል። እርግጠኛ ሆኖ ማውራት የሚቻለው ግን የሐሳቡ ባለቤት ጀ/ል አሳምነው አይደሉም። እርሳቸው ገድለው ቢሆን እንኳ የሌላ ወገን ፈረስ በመሆን ብቻ ነው፡፡ ስለአንድ ነገር እርግጠኛ መሆን እንችላለን፤ ጀነራል አሳምነው ያለ የፌደራል መንግስቱ ቁንጮ ባለስልጣናት ሙሉ እውቅናና ድጋፍ መለመላቸው በሚባሉ 190 ሰዎች ብቻ የክልል ፕሬዚዳንትና ሌሎች ባለስልጣናትን በመግደል መፈንቅለ-ክልላዊ-መንግሥት ለመፈፀም፣ አዲስ ክልላዊ መንግሥት በማቋቋም የክልል ጠቅላይ ለመሆን ሊነሳና እንዲህ ያለ የዕብደት ሥራ ሊፈፅም ፈፅሞ  አይችልም። ይህ ፈፅሞ ሊታሰብ የማይችል፣ ይህ ከዕቃ-ዕቃ ዓይነት ጨዋታ ተለይቶ የማይታይ ከንቱ ጨዋታ ነው፡፡
•••
ይህ ምን ማለት ነው- ወይ አንተ ባህርዳር ላይ ይህንን አድርግ፤ እኔ ደግሞ የአዲስ አበባውን ሥራ እሠራለሁ ብሎ የገፋፋቸው ትልቅ የፌደራል መንግሥት ሰው አለ ወይ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት (ለምሳሌ ከሓላፊነትህ ሊያወርዱህ እያሴሩብህ ነው) ብሎ በማታለል እነ አምባቸውን ለማሰር እንዲንቀሳቀስ በማግባባት ኋላ አሳምነው እነሱን ለማሰር ሲንቀሳቀስ የራሱ ሰዎች በማዝለቅ ግድያ የፈፀመ አካል አለ። ያበለዚያ አቶ አሳምነው ከምኑም የለበትም። ገዳዮቹም ከአዲስ አበባ የተላኩ ናቸው፤ የሰሞኑ በአሳምነውና በአምባቸው መካከል አለመስማማት አለ የሚል ወሬን ነው የተጠቀሙበት፡፡
•••
በዚህም አለ በዚያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሦስት ምቾት የሚነሷቸው፣ ‘የመንገዴ-እሾሆች’ የሚሏቸው ሰዎች በደቂቃዎች ልዩነት ተወግደውላቸዋል – ሁለት ፅንፈኛ የአማራ ብሄርተኞች(ዶ/ር አምባቸውና ጀነራል አሳምነው)፤ እንዲሁም በወታደሩ ዘንድ ከፍተኛ ተሰሚነት የነበራቸውና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለደቂቃ እንኳ ከዕይታቸው ዞር እንዲሉ የማይፈልጓቸው ታላቁ፣ ጀግናው የመከላከያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ሰዓረ መኮንን፡፡ ከዚያ በላይ ደግሞ የአማራ ክልል ሰላም እንዲናጋ፣ ቅቡልነት ያለው መንግስት እንዳይኖር ፣ አዴፓም እንዲፈረካከስ ማድረግ ላይ ትልቅ ስኬት አስመዝግቧል፡፡ ከዚህ በኋላ አማራ ክልልን አዲስ አበባ ሆኖ በሪሞት ኮንትሮለር የሚዘውራት ሁለተኛይቱ የሱማሌ ክልል ትሆናለች የሚል ምኞትም ሰንቆ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ ይህ ደግሞ ትግራይን ውረሩ ብሎ እስከ ማስወረርና ሁለቱን ክልሎች በማጫረስ ልዕልናውን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ የጥርጊያ መንገዱ እንደተከፈተለት ይሰማው ጀምሯል፡፡
•••
ከዚህ በኃላ የጠቅላዩ የ”ንግስና” ወይም የ’ቦካሳ’ነት ጉዞ ወይ አልጋ በአልጋ ይሆናል ወይም ኢትዮጵያ በቅርብ ቀናት ፍርክስክሷ ይወጣል፤ ነገሮች ከዚህ ቀደም በነበራቸው ፍጥነት አይቀጥሉም ፤ ይህንን እርግጠኛ ሁኜ ልንገራችሁ፡፡ በማለት ዶክተር ጦማሩን ይቋጫል።
•••
ሻሎም !   ሰላም !  
ሰኔ 23/2011 ዓም
ከራየን ወንዝ ዳር።
Filed in: Amharic