>
4:46 am - Friday July 1, 2022

መፈንቅለ መንግስት ወይስ መንግስታዊ ወንጀል??? (ያሬድ ጥበቡ)

መፈንቅለ መንግስት ወይስ መንግስታዊ ወንጀል???
ያሬድ ጥበቡ
ሌሊት በሰመመን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የዶክተር አምባቸው ቀብር ላይ የተናገሩት በተደጋጋሚ በእዝነ ህሊናዬ እያቃጨለ አላስተኛህ አለኝ። እናም ተነስቼ በጋላክሲ 8+ ስልኬ ይህን መተየብ ጀመርኩ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ቅዳሜ እለት ለሥራ ወደ ዲሲ ከመነሳታቸው በፊት ከአዴፓ መሪዎች ጋር ከመገደላቸው ከሰአታት በፊት ምን ተነጋግረው እሁድ ጠዋት ዲሲ ሲደርሱ አስደንጋጩ ዜና እንዴት እንደደረሳቸው አውስተዋል። በራሳቸው ቀጥተኛ አነጋገር፣ “ዛሬ ያጣናቸው ወንድሞቻችን ጓዶቻችንን ወደውጪ ከመውጣቴ ከሰአታት በፊት ፣ ከሦስቱም ጋር በተከታታይ ስለመጪው ሥራዎቻችን ፣ እኔ በሄድኩበት ጉዞ ልሠራቸው ስለሚገቡ ጉዳዮች ምክረሃሳቦቻችንን በስልክ ተወያይተን ነበር ። ሰው ባሰበው አይውልምና ያልተጠበቀው ሆነ” ይሉናል። ከተያያዘው የቪዲዮ ፋይል ከ1:14 እስከ1:47 ደቂቃ ያለውን የ33 ሴኮንዶች መልእክት ማድመጥ ይችላሉ።
እንደሚታወቀው ወደ ዋሽንግተን ዲሲ የሚበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ 500 ከአዲስ አበባ የሚነሳው ከሌሊቱ 5:00 (አምስት) ሰአት ላይ ነው። ስለሆነም፣ የባህርዳሩ የምሽቱ 11:00 ሰአት ስብሰባ በተጀመረበትም ሆነ፣ በዚያው ሰአት አካባቢ በክልሉ መሪዎች ላይ ግድያዎች በተፈፀሙበት ሰአት፣ በተጨማሪም ከምሽቱ ሶስት ሰአት  ላይ ጄኔራል ሰዓረ ላይ ግድያ በተፈፀመበት ወቅት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ደመቀ መኮንን አዲስአበባ ውስጥ ነበሩ ማለት  ነው።
እስካሁን መንግስታዊ ሃይሎች የሰጡንን መረጃዎች ታሳቢ ብናደርግ ከምሽቱ 11 ሰአት ላይ የባህርዳሩ ግድያዎች፣ ከምሽቱ ሶስት ሰአት ላይ የጄኔራል ሰዓረ ግድያ ተካሂዷል። ሁለቱም ግድያዎች በተካሄዱባቸው ሰአታት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አንድም ቤታቸው፣ አለያም ቢሯቸው፣ አለበለዚያም አዲስአበባ ቦሌ አየር ማረፊያ ቪአይፒ ላውንጅ ውስጥ ነበሩ ።
በተጓዳኝ ፌዴራል መንግስቱ ስለ ባህርዳሩ ግድያዎች መቼ አወቀ ብለን ስንጠይቅ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮሙኒኬሽን ሃላፊ ለአቶ ንጉሱ ጥላሁን ከ11:20 ጀምሮ ስልኮች ተደውለውላቸው እንደነበር እናውቃለን። ታዲያ አቶ ንጉሱ ለዓለሙ መፈንቅለመንግስት ብለው ያወጁትን አጣዳፊና አሳዛኝ ዜና ከመናገራቸው በፊት፣ ከማንም በላይ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑትን አቶ ደመቀ መኮንንን ደውለው ያነጋግሯቸዋል ብለን እናስባለን። አቶ ንጉሱም ብቻ ሳይሆኑ ከተኩሱ የተረፉት የአዴፓ አመራሮች ሁሉ መጀመሪያ የሚደውሉት ወደ ፓርቲያቸው ሊቀመንበር ወደምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ይሆናል ብለን ማሰብ ትክክል ነው ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም ቢሆኑ የባህርዳሩን ግድያ እንደሰሙ ከማንም በፊት መናገርና መወያየት ያለባቸው የአዴፓ ሊቀመንበር ከሆኑት ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትራቸው ከአቶ ደመቀ ጋር ነው።  ታዲያ አቶ ደመቀ በግድያዎቹ ወቅት አዲስአበባ ከነበሩ ለምን ሳይሰሙ ቀሩ? እንዴት ወይ ከምንሊክ ቤተመንግስት ወይም ከባርዳር ከተኩስ ካመለጡና ከግድያ ከተረፉ፣ ወይም ፖሊስ ኮሚሽን ውስጥ  “ታግተን ተይዘን ነበር” ካሉ የክልሉ የፀጥታ ሹማምንት አንዳቸው (የክልሉ የኮሙኒኬሽን ሃላፊ እንደነገረን ከታገቱት የፀጥታ ሹማምንት አንዱ የሆኑትን የፖሊስ ኮሚሽነር አበረ አዳሙን ስልካቸው ላይ ደውሎ በ11 ሰአት ላይ እንዳናገራቸው መረጃ ስለሰጠን፣ ታጋቾቹ ስልካቸው አልተወረሰም ነበርና) የገጠማቸውን የፀጥታ ችግር ለማሳወቅ በቅድሚያ ከሚደውሉላቸው ሰዎች መሃል የአዴፓ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ደመቀ መኮንን እንደሚሆኑ ፈፅሞ የማያጠራጥር ነው ። ታዲያ ይህ ሁሉ አፈሰማይ ዜናውን ሊያደርሳቸው እየቻለ አቶ ደመቀ እንዴት የግድያዎቹን አሰቃቂ ዜናዎች ሳይሰሙ ከሌሊቱ በ5 ሰአት በሚበረው የኢትዮጵየ አየር መንገድ በረራ 500 ሃገር ለቀው ሊሄዱ ቻሉ? እንዴት?
ለምን አሳዛኙን ዜና አውሮፕላናቸው መሬቱን እስኪለቅ እንዳይሰሙ ተደረገ? በጣም የማይገባ ጉዳይ ነው። የማይገባም ብቻ ሳይሆን፣ መፈንቅለ መንግስት ተብዬው ቧልት በቀሽም ብእር የተፃፈ ቀሽም ድራማ እንደሆነ፣ ቀሽም ድራማም ብቻ ሳይሆን ሥልጣንን በተገቢው ጊዜ መጠቀም ያለመቻልና፣ ከእጅና ቁጥጥር ያመለጠ ሲመስል ደግሞ በፍፁም ጭካኔ የመጠቀም ጉድለትን የሚያሳይ እንዳይሆን እፈራለሁ።
እንዴት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶክተር አቢይ አህመድ ለምክትላቸው ደውለው “ደሜ ፣ መፈንቅለ መንግስት እየተካሄደብን ስለሆነ የዛሬ ሌሊቱን የዲሲ በረራህን ሰርዝና ወደቢሮዬ ባፋጣኝ ና” ሳይሏቸው ቀሩ?
እንዴት አቶ ንጉሱ “የፓርቲያችን የአዴፓና የክልላችን አመራሮች ተገድለዋል የሚል ዜና ደርሶኛልና፣ የፓርቲው ሊቀመንበር እንደመሆንህ መጠን የዲሲ መንገድህን ተውና፣ ና ተያይዘን ወደ ባህርዳር እንሂድ” ሳይሏቸው ቀሩ?
እንዴት፣ ታገቱ ከተባሉትና ስልካቸውን ካልተነጠቁት የክልሉ የፀጥታና ደህንነት ባለሥልጣናት አንዳቸው እንኳ ለአዴፓ ሊቀመንበርና የሃገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ለአቶ ደመቀ መኮንን ስልክ ደውለው ሳያሳውቋቸው ቀሩ?
እንዴት የብሄራዊ ፀጥታው ሃላፊ የነበሩት የወንዛቸው የወሎ ሰውና የፓርቲያቸው የአዴፓ አባል የሆኑት ሌተና ጄኔራል አደም “ደሜ እረ ጉድ ፈልቷል፣ የፓርቲያችን መሪዎች ተገደሉ የሚል መረጃ አሁን ደረሰኝ፣ አንድ ነገር እናድርግ” ሳይሏቸው እንዴት ቀሩ? እንዴት? እንዴት? እንዴት?
የናንተን አላውቅም፣ በእኔ በኩል ግን ከመፈንቅለ መንግስት ይልቅ የአማራ ክልል የሚሊተሪ አቅሙ እየበረታ ነው ብለው ያሳደሩትን ስጋት ለመቆጣጠር በመንግስት ሃይሎች የተፈፀመ ወንጀል ነው የሚል ድምዳሜ ላይ እየደረስኩ ነው።
ከላይ ያነሳሁት የአቶ ደመቀ ሁኔታ፣ የጄኔራል አሳምነው በተመሳሳይ ሰአት የተለያየ ቦታ መገኘት፣ የጄኔራል አሳምነው ድምፅ ነው የተባለው ፋይል ለ8ቀናት ከህዝብ ጆሮ መጋረዱ ወይም ያልነበረ መሆኑ፣ ጄኔራል  ሰዓረ ከመገደላቸው በፊት መፈንቅለ መንግስቱን ለማክሸፍ እየተጉ እያስተባበሩ ነበር ተብሎ ከተነገረን በኋላ እግር በእግር ከወዳጃቸውና በጡረታ ከተገለሉት ምናልባትም ከወያኔ ጋር ቅርበት አላቸው ተብለው ከሚጠረጠሩት  ከጄኔራል ገዛኢ ጋር እየተጫወቱ ነበር የሚል የተምታታ መረጃ መቅረብ፣ የነጄኔራል ሰዓረ ገዳይ ነው የተባለው አስር አለቃ መሳፍንት መኮንን መጀመሪያ ተይዟል፣ ከዚይ ራሱን አጥፍቷል፣ ከዚያ ቆስሎ በእስር ላይ ይገኛል የሚሉ እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ መረጃዎች ላይ አሁን ሌሊት በእንቅልፍ ሰመመን አቶ ደመቀ በዶክተር አምባቸው ቀብር ላይ የተናገሩት በህሊናዬ ያቃጨለብኝ ሃቅ፣ በተጨማሪም ታግተው ነበሩ የተባሉት የፀጥታና ደህንነት ባለሥልጣናት መታሰር፣ በሰላማዊ ትግል የሚያምኑ ጋዜጠኞችና የአዲስአበባ ባለአደራ ምክርቤት አባላት በሰአታት ውስጥ መታፈስ በሙሉ የሚጠቁሙት አስቀድሞ በታሰበ ሆኖም በተዝረከረከ መንገድ በታቀደ ሁኔታ የሚካሄድ የመንግስታዊ ሃይሎች ወንጀል ነው።
ከመንግስታዊ ሃይሎች ውስጥ ማን ተጠያቂ ነው የአማራ ክልል፣ የትግራይ ክልል፣ ወይስ በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ የሚመራው የፌዴራል መንግስቱ ወይም ሁሉም በየደረጃው የተሳተፉበት ወንጀል ይሆን የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ግን ከአስር ሺህ ማይልስ እርቀት መናገር ስለማንችል በአስቸኳይ እንዲቋቋም የጠየቅነው ነፃና ገለልተኛ የአጣሪ ኮሚሽን ሲቋቋም ውሎ አድሮ የምናውቀው ይሆናል። እስከዚያው ቸር ይግጠመን።
Filed in: Amharic