>
5:13 pm - Sunday April 19, 6082

እምዬ ኢትዮጵያን እንታደግ! (ዶ/ር ዘላለም እሸቴ)


እምዬ ኢትዮጵያን እንታደግ!

ዶ/ር ዘላለም እሸቴ

 

በአስተዳደግ ኢትዮጵያዊነትን ኖረን፥ ከኢትዮጵያዊነት ውጭ ስብእና ሳይኖረን ቆይተን፥ በዘመናችን በኢትዮጵያ ምድር ኢትዮጵያዊም ሆነ አማራ መሆን ያልቻልን ሕዝብ ሆነናል። አቶ ጀዋር መሀመድ “ብሔርተኝነት ኒኩሌር ነውና አያያዙን ካላወቃችሁበት አደጋ አለባችሁ” እያለ እንዴት ብሔርተኛ መሆን እንደምንችል ሊያስተምረን ባለ ጊዜ ሆነ። ትላንት ኢትዮጵያ ትበታተን ሲለን የሞገትነው ወንድማችን፥ ዛሬ የብሔርተኝነት አሰልጣኛችን ሊሆንልን ፈልጎ ዝምታውን በዚህ ንግግር ሰበረ።

መላው ምንድነው? ነፃ አውጭ ነኝ ብሎ ጫካ የገባ “የብሔር ፖለቲከኛ” ሁሉ አዲስ አበባ ገብቶ ሳለ፥ ዛሬ ደግሞ እኛ በተራችን ጫካ እንግባና ራሳችንን ነፃ እናውጣ? ደግሞስ ለዘመናት ለኢትዮጵያ ዘብ ቆመን፥ ዛሬ የኢትዮጵያን ግባተ መሬት እንጀምርና ሴራው ግቡን ይምታ?

ለ 27 ዓመታት ሳንደራጅ መከራ አየን ተብሎ፥ ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅን መሪ ሲመጣ ይህንን አመራር የተቀበልነው በሁለትዮሽ ስትራቴጂ ነው። በአንደኛ ደረጃ ራሳችንን እንደ “ብሔር” ለማዳን መንቀሳቀስ፤ በሁለተኛ ደረጃ ኢትዮጵያዊነት እውነት ሲሆን ያኔ በትይዩ ለኢትዮጵያዊነት ዘብ መቆም።

ችግሩ ኢትዮጵያዊነትን ለማለምለም፥ ማንም ራሱን በሃላፊነት ባላቀረበበትና፥ ሁሉም በየጎሣው ጎራ በተሸሸገበት ሁኔታ፥ ኢትዮጵያዊነት እንዴት ከቃላት ባለፈ እንደሚገለጥ አይገባኝም። እስራኤል የዮርዳኖስን ባህር ከመሻገር በፊት መሪዎች እግራቸውን በሚፈሰው ባህር ውስጥ ማጥለቅ ነበረባቸው። ታዲያ ለኢትዮጵያ መሻገር ማን ይቅደም?

መፍትሄው በአዲስ መልክ የሁለትዮሽ ስትራቴጂ መተለም ነው። በአንደኛ ደረጃ ታይቶ በማይታወቅ ጥብቅ የዓላማ አንድነትና ፅናት መደራጀት ነው። ይህ ሲደረግ በሕወሓት ጥብቆ ውስጥ ተገብቶ ሳይሆን፥ በኢትዮጵያዊነት ስብዕና ላይ ተመስርቶና፥ ሌላውን ኢትዮጵያዊ ወገን፥ ቤተኝነት ተስምቶት እንዲቀላቀል በሩን ክፍት በማድረግ ነው። ኢትዮጵያዊነት የጠማው ምድረ ኢትዮጵያ ሕዝብ ሰብሳቢ እየጠበቀ ነው። በሰብዓዊ ማንነቱ የሚኮራውን ሁሉ፥ ጎሣን ሳይለይ፥ ሁሉን በቅንጅት አቅፎ የሚይዝ ድርጅት ሊሆን ይገባል።

ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ሸብቦ ከያዘው ከሸር ፖለቲካ ጥፋት የሚዳነው፤ ሕዝብ በምርጫ እንዲያሸንፍ ዕድል ሲፈጠርለት ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢትዮጵያዊነትን አይመርጥም ብለን የምናምን ከሆነ አንድ ነገር ነው። ሕዝብ መድረክ ቢያገኝ አብሮነትን ይመርጣል የምንል ከሆነ ግን፥ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን ዕድል በዲሞክራሲ የሚመርጥበት አድማስ ይፈጠርለት። በፊታችን ያለው ምርጫ መንግስትን ለመምረጥ ብቻ ተደርጎ አይታሰብ። በፊታችን ያለው ምርጫ ዓላማ፥ ህዝብ ኢትዮጵያዊነትን እንዲመርጥና በሕወሃት ተሰርቆ የተቀበረው ሀገር፥ በትንሳዔ ወደ ሕዝብ እንዲመለስ በዋነኛነት ታሳቢ ይሁን።

በአሜሪካ አገር ጥቁር መሆን ከእኛ የሚጠይቀው አንድ ነገር አለ። ያም ከነጩ ዕጥፍ ሰርተን ከነጭ እኩል መሆን መቻል ነው። በኢትዮጵያ ምድር ደግሞ ከሁሉም እጥፍ ሸክም ተሸክመን፥ ኢትዮጵያዊነትን የምናሻግር እኛ እንሁን። እስከ መቼ? ቢባል የታሪክ አጋጣሚ ስለሆነ ነው። አባቶቻችን አብሮነትን አስቀድመው፥ ከኢትዮጵያዊነት ጋር ፍቅር አስይዘው አለፉ። ታዲያ በነጋዴ ፖለቲካ ሴራ “ኢትዮጵያዊነት ባዕድ” ሆኖ ተገኘ። ቢቸግርና የመኖር ሕልውና ጥያቄ ውስጥ ሲገባ፥ ጎሠኝነት ውስጥ በመሸሸግ ራስን ለማዳን ቢታሰብ ምን ይገርማል?

እስቲ ራሳችንን እንፈትሽ። ሕወሃት ኢትዮጵያን በዘጠኝ ጎሣዎች አዋቅሮ ሲያበቃ፥ ከሰባ በላይ የሆኑ ጎሣዎች ምንም ቦታ ሳይሰጣቸው አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው፥ በሀገራቸው እንደ ባይተዋር ተቆጥረው የሚኖሩ ናቸው። ሌሎቹም በሕይወታቸው ዘመን ኢትዮጵያዊነትን ተላብሰው የኖሩ ሆነው ሳሉ፥ በጎሠኝነት ተዋቅረው፥ ወንድሞቻቸውን እንደ ባላንጣ እንዲቆጥሩና እንዲጋጩ ምክንያት ሆኗል። ሕዝብና ኢትዮጵያዊነትን እያወከ የማይገረሰስ እንቅፋት የሆነው ሕገ መንግስቱ ነው። ሕገ መንግስቱ ብዙ ጥሩ ነገር ይዞ፥ በውስጡ ግን አብሮነትን የሚበትን አጀንዳ አዝሎ ግራ የሚያጋባ ነው። ይህን በታኝ አጀንዳ ነቅሶ ለማውጣት ከተፈለገ፥ መንገዱ በዲሞክራሲ የምርጫ መሳሪያ መጠቀም ነው። ኢትዮጵያ የምታሸንፍበት ምርጫ እንዲሆንላት ከተፈለገ ደግሞ፥ አሁን ባለው የምርጫ አካሄድ ዝም ብሎ በጭፍን መንጎድ ሳይሆን፥ ነቅተን በአዲስ ሀገር አድን አካሄድ ስንሄድ ብቻ ነው።

ሕወሓት በስትራቴጂ ያስቀመጠችው ሕገመንግስት እንዳይነካ፥ ጥግ ይዛ ዋ! እያለች ታስፈራራለች። ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅነውና የምንወደው ጠ/ሚ ፓርቲ ሳይቀር፥ በዚህ ጉዳይ አንደራደርም ብሎ ኢዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ለማድረግ ችላለች። ይህ ዘረኝነት በታኝ አጀንዳ፥ ቀስ በቀስ ሁሉም ራሱን ለማዳን እንዲሮጥና፥ አንዱ በሌላው ላይ ጠላት እንዲሆን ተደርጎ የተቀመመ መርዝ ነው። ለዚህ መርዝ ማርከሻ መድሓኒቱ አንድና አንድ ብቻ ነው። ያም የሕዝብን የኢትዮጵያዊነት ስነልቦና አውቆና አምኖ፥ ራስን መስዋዕት አድርጎ፥ ራስንም ኢትዮጵያንም በአብሮነት ማዳን ነው። አለበለዚያ ለየራስ በነፍስ ወከፍ እየሮጥን፤ ሁላችንም ተያይዘን ገደል መግባት ይሆናል።

እስከ መቼ እንገፋለን ብለን በንዴት ታሪክ የጣለብንን አጋጣሚ ባንጠቀም፥ ብዙ ኪሎ ሜትር ወደ ታች ቆፍረን ወርቁ ጋ ልንደርስ አንድ ሴንቲ ሜትር ሲቀረን ቁፋሮውን እንዳቆምን ይቆጠራል። ከዶ/ር አብይ መንግስት አንድ ነገር ብቻ እንጠይቅ። ያም በዲሞክራሲ እውነተኛ ምርጫ ይሆን ዘንድ ነው። ሌላው በሕዝብ እጅ ነው። ታዲያ እንደተለመደው በሸር ፖለቲካ እየተከፋፈልን ወደ ምርጫ ሄደን፥ በግርግር ኢትዮጵያን የበለጠ ቅርቃር ውስጥ ከተን፥ ኢትዮጵያ ከምትበተን፤ እኛ አስቀድመን ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ከተቀበረችበት ነፍስ እንድትዘራ እንንቃላት። እስካሁን በኢትዮጵያዊነት ላይ ከሌሎች ወገኖች ጎን ሆነን፥ በህብረት ያበረከትነው አስተዋፅዎ ዋጋ የሚኖረው፤ ዛሬ ለትላልቅ ጎሳዎች ብቻ ሳይሆን ለአናሳ ጎሳዎችም ጠበቃ ቆመን አብረናቸው ሆነን በመያያዝ መቀናጀት ስንችል ብቻ ነው። ወደ 80 የሚሆኑ ብሔረሰቦች ጋር መቀናጀት ትተን፥ ራሳችንን ለመታደግ ስንሮጥ፥ ሁላችንም እንዳንበላላ፥ የሁሉም ሰብሳቢ እንሁን።

ለነገ ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁለት አማራጭ እንዲኖረው ዕድል እንስጠው። በአንድ በኩል ዘረኝነትን የሚያነግሱ ፖለቲከኞችና አክትቪስቶች ድርጅቶቻቸውን ይዘው በየጎሳዎቻቸው ዙሪያ ለምርጫ ሊቀርቡ እየተጣደፉ ነው። ሌላ አማራጭ ለመስጠት፥ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሁሉ አቅፈንና ይዘን፥ እንደ አንድ ተደራጅተን ኢትዮጵያዊነትን እንዲመርጥ በር እንክፈትለት። ጥቂት ልሂቃን ኢትዮጵያን እንደፈለጉ የሚዘውሩበትን አቅም ለመስበርና፤ እውነተኛ የሕዝብ ልባዊ ምርጫ እንዲሆን፥ ለሕዝብ አቅም የሚሰጠው የምንደራጅበት አውድ ነው። እንደለመድነው በተቀደደው ቦይ እየነጎድን፥ ተከፋፍለን ወደ ምርጫ የምንሄድ ከሆነ፥ አንድም ምርጫው ጋ ሳንደርስ እንዳንቀር፥ ወይም ከምርጫው ማግስት እንዳንነካከስና እንዳንጠፋፋ እፈራለሁ።

ኢትዮጵያዊነት ማለት ሁሉም በእኩልነት ተከብሮና ተወድሶ፥ በአንድነት በፍታዊ ተጠቃሚነት የሚኖርበት፥ በሰውነቱ ብቻ የሚኮራበት፥ ባህሉንና እሴቱን የሚያንፀባርቅበት፥ ራሱን በራሱ እያስተዳደረ በመደመር የሚገለጥበት እንጂ ጎጠኞች የሚያጥላሉትና የሚያወናብዱት፥ ኢትዮጵያዊነት ላይ ጥላሸት እየቀቡ ራሳቸው የፈበረኩት ትርክት አይደለም። ስለዚህ ከሌላው ጋር ተቀናጅቶና ተያይዞ፥ ለኢትዮጵያዊነት መፈታት “ኢትዮጵያዊነትን” እንደ አንድ አማራጭ ለምርጫ ይዞ ይቅረብ።

የተለመደውን የፖለቲካ አካሄድ በአፍጢሙ ደፍተው፤ በሰው ስብዕና እርስ በርስ እንደ ወንድማማች በመያያዝ ታሪክ የሚሰሩ ተዐምረኛ የኢትዮጵያ የጭንቅ ጊዜ ልጆች ይገለጡ! ያኔ ኢትዮጵያ በአግላይ ጥቂት ጎሣ አጥር ሌላውን ጨፍልቃ የምትከልል፥ አፈናቃይ ጎሣዊ ፌድራሊዝምን የምታቀነቅን ብኩን ሳትሆን፤ በመልከአምድር የተከለለችና፥ 80 ብሔረሰብን በእኩልነት የሚስተናገድበትና ራስን የሚያስተዳድርበት፥ ደግሞም የመደመር ፍልስፍናን በፌድራሊዝም ውቅር ውስጥ ያካተተችና፥ ለእንቆቅልሿ መላ ያገኘች ድንቅ የፍቅር ሀገር ትሁን።

አልረሳሁትም። በሁለተኛ ደረጃ የሚባል አማራጭ ነገር የለም። ኢትዮጵያ ትወለድ ዘንድ እሙን ነውና።

ፈጣሪ ይርዳን!

ኢሜል፡ Z@myEthiopia.com

Filed in: Amharic