>

ሕወሓት በመግለጫው የመከላከያ ሰራዊት ሐገርን ከመፍረስ እንዲያድን ጥሪ አቀረበ!!! (ወዲ ሻምበል)


ሕወሓት በመግለጫው የመከላከያ ሰራዊት ሐገርን ከመፍረስ እንዲያድን ጥሪ አቀረበ!!!
ወዲ ሻምበል
ህወሓት ስብሰባውን ሲያጠናቅቅ የፌደራል መንግስትን በብዙ ጉዳዮች በማስፈራራት ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል ሙሉውን ቃል በቃል ለመተርጎም ረጅምና አሰልቺ  ስለሆነ ካነበብኩት አንዳንዶቹን አንኳር ሐሳቦች  ለመጥቀስ “በከፍተኛ የጦር መኮንኖችና በብአዴን ባለስልጣናት ላይ የተደረገው ግድያ መንግሥት በገለልተኞች እንዲያጣራና ለኢትዮጵያ ህዝብ ያሳውቅ። እንዲሁም በስመ ለውጥ ትምክህተኞች አሃዳዊ ስርዓት ለመመለስ እየሞከሩ ስለሆነ ይህንን የሚቃወሙ ህዝቦች እንደ ትናንትና አብረን እንታገላቸው።
ብአዴን የገዛ ችግሩ ወደሌላ ከማስተላለፍ በአስቸኳይ የኢትዮጵያ ህዝብን ይቅርታ ካልጠየቀ ህወሓት ከእንደዚህ አይነት ድርጅት ጋር አብሮ ለመስራት አይገደድም።
ኢህአዴግ ትላንት ወደነበረው ትክክለኛ መስመር ተመልሶ አገርን ከትምክህተኞች ማዳን አለበት። እንደዚሁም የደቡብ ህዝብ ጥያቄ በህገመንግስቱ መሰረት መፈታት አለበት የኃይል እርምጃ የሚወሰድ ከሆነ አደገኛ ሁኔታ ሊፈጠር ስለሚችል ይህንንም እንቃወማለን።ህወሓት ከመነሻው ጀምሮ ህዝብን ትምክህተኛ ብሎ አያውቅም ትምክህተኞች ግን የአማራ ህዝብን ትምክህተኛ ተብለሀል እያሉ ህዝብን ያነሳሳሉ።
ህወሀት ኢህአዴግንም እየፈራረሰ ነው ይላል:-
ለሐገሬ የመፍትሔ አቅጣጫ አስቀምጫለሁ ያለው ኢሕአዴግ የአቅጣጫው ቀለም ሳይደርቅ ወደ መፈረካከስ እያመራ መሆኑን ገልጿል።
ሕወሓት በመግለጫው ብአዴን / አዴፓ ይቅርታ ካልጠየቀ ከፓርቲው ጋ መስራት እንደማይችልም ገለጿል ።
ኦሕዴድ ኦዴፓ ኢሕአዴግን አንድ ለማድረግ ያቀደው ሐሳብ በመኮላሸቱ እና አብዛኛው መዋቅሩ በኦነግ በመጠለፉ አጣብቂኝ ውስጥ ነው ።አዴፓም የውስጥ አደገኛ ሽኩቻው ከሕዝብ ጥላቻና ከሰሞኑ ሴራ ጋር ተደማምሮበት በፓለቲካ ስካር እየተሰቃየ ነው።
ሌላኛው የደቡቡ ፓርቲ የኢሕአዴግ አጋር በደቡብብ ክልል በተነሱ የክልል እንሁን ጥያቄዎች ለመበታተን ተቃርቧል። በተቀመጠው ስብሰባ ላይ ከባድ ልዩነት እየጦዘ ስለሆነ ኦዴፓ እጁን አስገብቶ የደቡብን ፖለቲካ እያማሰለው ፓርቲውን በጣር እያስቃሰተው ነው።
ሕወሓት የመከላከያ ሰራዊት ሐገርን ከመፍረስ እንዲያድን ጥሪ ሲያቀርብ ኢሕአዴግ ኮማ ውስጥ እንደሆነ በመግለጫው መስክሯል ። የሀገራችን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ቀውስ የኢሕአዴግን እድሜ እንደሚያሳጥረው ከወዲሁ በፈጣሪው ሕወሓት መግለጫ ውስጥ አንብበናል።
ድምፅ ወያነ
ከህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ!!!
 
የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ሀምሌ 2፣ 2011 ዓ/ም ባካሄደው የአንድ ቀን አስቸኳይ ስብሰባ በቅርቡ ባጋጠመው የከፍተኛ ወተሃደራዊ መሪዎችና የአማራ ክልል አመራሮች ላይ የጋጠመው ግድያ መነሻ በማድረግ በአገሪቱ እየተባባሱ በመጡት ሁለንተናዊ ችግሮች ይህንን ተክተለው ወደፊት ሊኖር ከሚችለው አጠቃላይ ሁኔታ ለሃገራችንም ሆነ ለክልላችን ከሚኖራው ትርጉም አንፃር በመገምገም በአስቸካይ ሊፈፀሙ የሚገባቸዉ ወሳኝ አቅጣጫዋችና ውሳኔዎች አስቋምጧል፡፡
በዚህ ወቅት የሃገራችን ህልውና ከከፋ ወደ ባሰ ደረጃ ሊወሰድ የሚችል በመጠኑና ስፋቱ እጅግ አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡ በየግዜው እየተከማቸ የመጣው በተለይም ካለፈው አመት ጀምሮ የአገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ ሁኔታ እየተበራከተ የአደጋው ፍጥነት በየቀኑ እየጨመረ በመሄድ በቅርቡ በከፍተኛ የአገሪትዋ ወታደራዊና የክልል አመራሮች ላይ ያጋጠመው በግፍ የመግደል ደረጃ ደርሰዋል፡፡
ትላንት የአገሪቱ ህልውና ክብር አሳልፎዉ የሰጡና ኢትዮጽያን ለመበታተን ሌት ተቀን የማይተኙ ሃይሎች በስመ ለውጥ ግንባር በመፍጠር አሰላለፍ ባልለየ መልኩ ተደብላልቆ አንድ ላይ እንዲሆኑ በመደረጉ በጥፋት ላይ ጥፋት እየተደራረበ አሁን ላለንበት ደረጃ ላይ በቅተናል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ለዚች ሃገር ክብርና ህልውና ሲሉ እድሚያቸዉ ልክ የታገሉትን የሚታደኑበት፣ የሚታሰርበት እና ጥላሸት የሚቀቡበት ሁኔታ ተፈጥራዋል፡፡
ህዝቦች በሰላም እጦት ሳብያ እንዲሰቃዮ፣ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ህይወትና ንብረታቸው የሚያጡበት፣ እንዲሸማቀቁ፣ መጠለያ አጥተው ብርድና ፀሃይ እየተፈራረቃቸው እንዲጣሉ፣ በሃገሪቱ ታይቶ በማይተወቅ ደረጃ የግጭትና በሚልኖች የሚቆጠሩ ዜጎች የመፈናቀል አደጋ የተበራከተበት፣ ከምንም ግዜ በላይ ህግና ስርዓት ማክበር ያልተቻለበት፤ ሃገር ጠባቂ አጥታ ፅንፈኛ ሃይሎች የሚፈጥዙባት እየሆነች ፀረ ህገ መንግስትና ፌደራላዊ ስርዓት የሆኑ ፅንፈኛ የትምክህት ሃይሎች እንዳሻቸው የሚሆኑበት ሁኔታ ተፈጥርዋል፡፡
ህወሓት የትምክህት ሃይሎች ሲል፣ የህዝብ መብትና ጥቅም ረግጠው የግል ፍላጎታቸውና ያሻቸውን ለመፈፀም የሚጋጉትን ጥቂት ሃይሎች እንጂ ህዝብን ፈረጅ አያውቅም አይችልምም፡፡
በማንኛውም መመዘኛ ትምክህተኛ ተብሎ የሚጠራ ህዝብ የለም:: የሁሉም ህዝቦች ፍላጎት እና መሻት አንድና ተመሳሳይ ነው፡፡ ሰለሆነ ወዳጅም ጠላትም ማወቅ ያለበት ህወሓት ትላንት፣ ዛሬም ሆነ ነገ ለህዝብ የላቀ ክብር የሚሰጥና ህዝባዊ እምነትም አንግቦ የሚታገል ድርጅት መሆኑ ነው፡፡ ባለፉት ግዚያት ከአማራ ህዝብ ጎን በመሰለፍ ፀረ ትምክህተኛና ገዢ መደቦች የታገለና የላቀ መስዋእትነት የከፈለ ድርጅት ነው፡፡
ስለ ሆነም የአማራ ህዝብ ትምክህተኛ ብሎ ሊጠራ አይችልም:: ሆኖም እነዚህ ፀረ ህዝብ የትምክህት ሃይሎች የቆየውን ሃላቀር ህልማቸው ለማስፈፀም እንደ ህዝብ ትምክህተኛ ተብለሃል በማለት ህዝበን እያደናገሩ ይገኛል፡፡በአማራ ህዝብ ስም እየነገዱ በአሉባልታ ወሬ ህዝቡ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀዉ ደሙን ለመምጠጥ አኮብኩቦው እየጠበቁ ይገኛሉ፡፡ ቢሆንም ግን እንደ ማነኛውም የኢትዮጽያ ህዝብ የአማራ ህዝብም ለሰላም፣ ለልማትና ዴማክራሲ ሲል መስዋእት በመክፈል አዲስትዋን ኢትዮጽያ በመፍጠር የራሱ ሚና የነበረውና ያለው ህዝብ ነው፡፡
ተጀምሮ የነበረዉ ተስፋ ሰጪ ልማትና እድገት ብአሁኑ ወቅት መሪ አልባ ሁኖ ቅልቁለት መውረድ የጀመረበት ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ የፀጥታና የድህንነት ተቋማት ከምንም ግዜ በላይ የአገሩቱን ሰላምና ድህንነት መጠበቅ አልቻሉም፡፡ የጀግኖቹ የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራሮች ግድያ የሚያረጋግጠው እውነትም መንግስት የህዝቡን ሰላምና ድህንነት ማክበር ተስኖት በግፍና ጭካኔ የስልጣን ፍላጎታቸውን ማርካት የሚፈልጉ የትምክህት ሃይሎት እንዳሻቸዉ የሚፈነጩበት፣ በመንግስት መዋቅር ውስጥ መሽገዉ የህዝቦች አለኝታ የሆነዉን ህገ-መንግስትና የፌደራል ስርዓት ለማፍረስ በግላጭ የሚቀሳቀስበት ሆኔታ ተፈጥረዋል፡፡
በእንደዚህ አይነት ሁኔታም በየቀኑ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ለመገመት አዳጋች የሆነበት ደረጃ ላይም ተደርሷል፡፡ የአገሪቱ ሁኔታ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ እየታወቀም ከፍተኛ ባለስልጣናትን በማስወገድ በቀላሉ ስርአት የማፍረስ ተግባር በይፋ የሚያወግዝና የጠራ አቋም በመያዝ የሚደረግ ትግል አልታየም፡፡ በተቃራኒው ሁሉንም የለውጥ መሪዎች ነበሩ በማለት ይህንን እኩይ ተግባር ቀጣይነት እንዲኖረውና በዚህ ተግባር ላይ እጅ የነበራቸው አካላት ከተጠያቂነት እንዲያመልጡ ሆን ተብሎ ያለ ሃፍረት ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ሌላው ቀርቶ የሃገሪቱ ሰላምና ደህንነት እንዲጠበቅ ሓላፊነት የተሸከሙ የፀጥታና የደህንነት አካላት በተፈፀመው ጥፋት ላይ ተጠያቂነትን በሚያረጋግጥ መንገድ እየተሰራበት አይደለም፡፡
በመሆኑም የሃገሪቱን ህልውና የከፋ አደጋ ላይ መሆኑን በመገንዘብ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ቀደም ብሎ ያስቀመጣቸውን የትግል አቅጣጫዎች በማጠናከር በቅርቡ ከተፈጠረው ሁኔታ በመነሳት የሚከተሉትን አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች አስተላልፏል፡፡
1. በጀግኖች የመከላክያ ሰራዊት አመራሮች ላይ የተፈፀመው የግድያ ወንጀል ከሃሳብ ጀምሮ እስከ ተግባር በቀጥታና በተዘዋዋሪ ተሳትፎ የነበራቸው የውስጥና የውጭ ሃይሎች በገለልተኛ አገራዊ ወገን በፍጥነት እንዲጣራ፣ የፀጥታና ደህንነት አመራሮች በዚህ ሴራ ላይ የነበራቸውን ሚና ይሁን ግዴታዊ ሃላፊነታቸው ባለ መወጣታቸው ለተፈፀመው ጥፋት ተጠያቂ እንዲሆኑና የማጣራት ሂደቱና ውጤቱ በየግዜው ለኢትዮጵያ ህዝብ ግልፅ እንዲደረግ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
2. በዚህ ወቅት ሃገርን እየበታተነ ያለው ከዚህም ከዚያም የተሰበሰበው የትምክህት ሃይል ነው፡፡ ይህ ሃይል ዕድል አግኝቶ እንደፈለገው እንዲሆን እያደረገ ያለው ደግሞ አዴፓ ነው፡፡ በመሆኑም አዴፓ ባጠቃላይ በተፈፀመው ጥፋት፣ በተለይም ደግሞ በድርጅቱ አመራሮች ላይ ባጋጠመ ግድያ ላይ በጥልቀት በመገምገም ተጠያቂነት እንዲኖር በማድረግና ግልፅ አቋም በመውሰድ ለኢትዮጵያ ህዝቦች ይቅርታ መጠየቅ አለበት::
ከዚህ ዉጭ የውስጥ ችግሮችን ለመሸፈን ጥፋቱን በሶስተኛ ወገን አለበት በማለት ማሳበብ እና ሌሎች ረጃጅም እጆች አለበት ወዘተ በማለት ህዝቡን ማወናበድ መቆም አለበት፡፡ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ መኖር እንደማይቻል ህዝቡም ተገንዝቧል፡፡ ስለዚህ አዴፓ በሁሉም ጉዳዮች ላይ የውስጥ ችግሮችን በዝርዝር በመገምገም ግልፅ አቋሙን እንዲያሳዉቅ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ጥሪዉን ያቀርባል፡፡ ይህ ሊሆን ካልቻለ ግን ህወሓት ከእንዲዘህ አይነት ሀይል ጋር አብሮ ለመስራትና ለመታገል እንደሚቸገር መታወቅ አለበት፡፡
3. እስከ አሁን የጋጠመው መሰረታዊ ችግር በኢህአዴግ ውስጥ በተፈጠረው የጐራ መደበላለቅና በግልፅ ወገንተኝነት ላይ በተመሰረተ ትግል እየታገዘ ሁሉንም ጥገኛና ደባል አስተሳሰቦች ተሸክሞ የሚኖር ድርጅት እየሆነ በመምጣቱ ነው፡፡ በመሆኑም የሃገራችንን ህልውናና ደህንነት ዋስትና እንዲኖረው ኢህአዴግ ወደ ነባሩና የሚታወቅበት መለያዉ የሆነ ባህሪና እምነት ተመልሶ ከጐራ መደበላለቕ በጠራና ግልፅ ወገንተኝነት የተመሰረት ትግል እንዲካሄድና በቀጣዩ አመት በህገ‐መንግስቱ መሰረተ መካሄድ ያለበትን ሃገራዊ ምርጫ እንደ ግንባርና መንግስት አቋሙን ለኢትዮጵያ ህዝቦች ግልፅ እንዲያደርግ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ያሳስባል፡፡
4. የአገር መከላከያ ሀይል ህገ‐መንግስታዊ ስርዓቱንና የአገሪቱን ሉአላዊነት ከማንኛውም አደጋ ለመከላከልና ለመጠበቅ የተሰጣችሁን ህገ-መንግስታዊ ሀላፊነት ከምንም ግዜ በላይ ውስጣዊ አንድነታችሁን በማጠናከር የአገራችሁን ሰላምና ደህንነት በመጠበቅ ረገድ ሃላፊነታችሁና ግዴታችሁን እንድትፈፅመ ጥሪ በማቅረብ ይህን ለመፈፀም በምታደርጉት ትግል ላይ ህወሓትና የትግራይ ህዝብ ዛሬም እንደ ትላንቱ ከጐናችሁ በመሆን በፅናት እንደሚታገል ያረጋግጥላቹሃል፡፡
5. ህወሓት ህገ-መንግስታዊና ፌደራላዊ ሃይል እንደ መሆኑ መጠን ህዝብና ሃገር ካለዉና ለወደፊትም ከተጋረጠባቸዉ አደጋ ለማዳን ተመሳሳይ ዓላማ ካላቸው ህገ-መንግስታዊና ፌደራላዊ ሃይሎች ጋር ሰፊ መድረክ በመፍጠር ለመታገልና ባስቸኳይ ወደ ተግባር እንዲሸጋገር የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ወስኗል፡፡
6. በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል እየተነሱ ያሉትን ክልል የመሆን ጥያቄዎች ህገ-መንግስታዊ በሆነ መንገድ ሊፈቱ ይገባል፡፡ ከዚህ ውጭ የህዝብን ጥያቄ በሃይል ወይም በሌላ መንገድ ለመፍታት የሚደረግ ጥረት ፍፁም ተቀባይነት የለውም፡፡
7. የፌደራል መንግስት በዚህ ሃገር ዉስጥ አስተማማኝ ሰላም እንዲያረጋግጥ፣ ህግና የህግ የበላይነት እንዲያከብር፣ የዜጐች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሊያረጋግጥና ህገ-መንግስትና ህገ-መንግስታዊ ስርዓትን ሳይሸራረፍ እንዲተገብር የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ በድጋሚ ያሳስባል፡፡
የተከበርክ የትግራይ ህዝብ
በመስመርህና ድርጅችህ ዙርያ ተሰልፈህ በየግዜው ላጋጠመህ ቁጥር ስፍር የሌለው ሴራና ተግዳሮት በመበጣጠስ ወደፊት እየተራመድክ ትገኛለህ፡፡በፅናትህ፣ ትእግስትህና ብልህነትህ አማካኝነት ከያዝከው መንገድ ዝንፍ ሳትል በአላማህና መስመርህ ፀንተህ እየታገልክ ትገኛለህ:: ተስፋ እንድትቆርጥ፣ እንድትመበረከክና አንገትህ እንድትደፋ በማሰብ ኮትኩተህ እና አንፀህ ያሳደግካቸውን ምርጥ ታጋዮችህ እንድታጣ አድርገዋል፡፡ ቢሆንም ግን መስዋእት ላንተ አዲስ አይደለም፡፡ምርጥ ታጋይ ልጆችህን ከፍለህ ለዚህ በቅተሃልና:: አሁንም ቢሆን ያጋጠመህን ችግር አልፈህ ለበለጠ ትግል እና ለማይቀር ድል ተዘጋጅ፡፡ እውነተኛና ፍትሃዊ ትግል እስከካሄድክ ድረስ በአላማ ላይ የተመሰረተ ፅኑ አንድነትህን እስካረጋገጥክ መጪዉ ግዜህ በአንፀባራቂ ድል የታጀበ ነው፡፡ በመሆኑም አንድነትህ አጠናክረህ ከመስመርህና ከድርጅትህ ጐን ተስለፍ፡፡በየግዜው የሚፈጠሩትን ሁኔታዎች በንቃትና በትዕግስት ተከታተል፡፡
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች
ትላንት በድህነትና ኃላቀርነት ተቆራኝተን እንድንኖር ፈርዶብን የነበረውንና በህዝቦች መስዋእትነት ያስወገድነውን የትምክህት ሃይልና በሱ የሚመራዉ አሃዳዊ ስርዓት ዳግም አፈሩን አራግፎ በመነሳት በህዝብ ልጆች መስዋእትነት የተፃፈ የህዝቦች ቃልኪዳን የሆነውን ህገ-መንግስትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማፍረስ በውስጥና በውጭ ሃይሉን አጠናክሮ ላይና ታች እያለ ይገኛል፡፡ ስለዚህም ሰላማችንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓታችንን በመጠበቅ በዋነኝነትም ደግሞ የሃገራችንን ህልውና በማረጋገጥ ረገድ በጋራ እንድንታገል የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ክብርና ሞገስ ለጀግኖች ሰማእታት
የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ማእከላይ ኮሚቴ
ሀምሌ 03/2011 ዓ/ም
መቐለ
Filed in: Amharic