>
7:41 am - Wednesday December 7, 2022

አንዳርጋቸው በአትላንታ፣ ስድስት ጥያቄወች (መስፍን አረጋ) 

አንዳርጋቸው በአትላንታ፣ ስድስት ጥያቄወች

መስፍን አረጋ 

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በፀረወያኔ ትግል ያንበሳውን ሚና የተጫወተ የጦቢያ አንበሳ በመሆኑ ዘላለማዊ ክብር ይገባዋል፣ ይኖረዋልም፡፡ ይህ ማለት ግን አንዳርጋቸው ያጠፋ ሲመስለን አጥፍተሃል፣ የተሳሳተ ሲመስለን ተሳስተሃል ልንለው፣ ግራ ሲያጋባን ደግሞ ማብራሪያ ልንጠይቀው አንችልም ማለት አይደለም፡፡ ይህ አጭር ጽሑፍ የተጻፈው በዚህ መንፈስ ነው፡፡

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የኢዜማ (የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትሕ ፓርቲ) የትውውቅና ሕዝባዊ ውይይት ፕሮግራም (አትላንታ፣ ጆርጅያ) ላይ ባደረገው ንግግር የሚከተሉትን ሁለት ዐብይት ነጥቦች ነጥቧል፡፡

• ኢዜማ አደባባይ ወጥቶ ስላልጮኸ ዝም ብሎ የሚቀመጥ እንዳይመስላችሁ፡፡ የጦቢያን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት ይረዳል ብየ ያሰብኩትን በታኅሳስ ወር መጀመርያ ያዘጋጀሁትን ባለ 21 ገጽ ሰነድ ላርበኞች-ግንቦት ሰባት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴና ለሁሉም ያገሪቷ መሪወች አቅርቤያለሁ፡፡

• የዐብይ አሕመድ መንግሥት የራሱ ፍኖትካርታ (roadmap) ስላልነበረው ወደ ተግባር የገባው እኛ (አርበኞች-ግንቦት ሰባት) የሰጠነውን ፍኖትካርታ በመከተል ነው፡፡ በዚህ ፍኖትካርታ ላይ በሰፊው እንዳብራራነው የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ የዲሞክራሲ ጥያቄ ሳይሆን የጦቢያ ህልውና ጥያቄ ነው (ዲሞክራሲ የሚኖረው አገር ስትኖር ነውና)፡፡ የጦቢያ ህልውና ደግሞ ጥያቄ ውስጥ የገባው ክልሎች በቋንቋ/በዘር መሥፈርቶች በመከለላቸው እንዲሁም በዘር የተደራጁ ፓርቲወች በመፈጠራቸው ነው፡፡ በበለጠ ደረጃ የጦቢያን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ያስገባው ግን፣ እነዚህ በዘር የተደራጁት ክልሎችና ፓርቲወች መሣርያ የታጠቁበት ሁኔታ መፈጠሩ ነው፡፡ ስለዚህም የጦቢያን ሕልውና ለማረጋገጥ የሚፈልግ መንግሥት የመጀመርያ ሥራው መሆን ያለበት ማዕከላዊ መንግሥትን ለመገዳደር (challenge) ማለትም ለመፈታተን የሚያስችል ጉልበት ያለው አንድም ክልል እንዳይኖር ማድረግ ነው፡፡ የፌደራል መንግሥት በማናቸውም ክልል ውስጥ የፈለገውን መፈጸም የማይችልበት ፊደራላዊ አደረጃጀት ለጦቢያ ስለማይሠራ፣ የፌደራል መንግሥቱ ጉልበት በክልሎቸ ኪሣራ መጠናከር አለበት፡፡

አነዚህን ሁለት ነጥቦች መሠረት አድርጌ አቶ አንዳርጋቸውን (በስብሰባው ውስጥ ብገኝና እድሉ ቢሰጠኝ ኖሮ የምጠይቀውን) የሚከተሉትን ስድስት ጥያቄወች በጽሑፍ ልጠይቀው እወዳለሁ፣ ካክብሮት ጋር፡፡

• አንደኛውን ነጥብ በሚመለከት፡፡ ማናቸውም የፖለቲካ ፓርቲ ፖለቲካዊ አጀንዳውን በቅድሚያ ለሕዝብ ይፋ በማድረግ በዚህ አጀንዳው መሠረት ሕዝብ እንዲመርጠው ይጣጣራል እንጅ፣ አጀንዳውን ለፖለቲካ ተፎካካሪው በሕቡዕ አያቀርብም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰነድ ላንድ ፓርቲ የሚያቀርብ ቡድን ፓርቲውን የሚደግፍና በፓርቲው የሚደገፍ ፖሊሲ አፍላቂ (think tank) እንጅ ፓርቲውን የሚፎካከር ተፎካካሪ ፓርቲ አይደለም፣ ሊሆንም አይችልም፡፡ ስለዚህም ኢዜማ አፍቃሪ ኢህአዴግ (ይልቁንም ደግሞ አፍቃሪ ዐብይ) የሆነ የፖሊሲ አፍላቂ እንጅ ኢህአዴግን የሚፎካከር አማራጭ ፓርቲ አይደለም ማለት ነው፡፡ በተግባር አማራጭ ፓርቲ ሳይኮን በስም ብቻ ዜግነትን የማራምድ አማራጭ ፓርቲ ነኝ በማለት ሕዝብን ማደናገር ፖለቲካዊ ሸፍጥ አይደለምን?

• ሁለተኛውን ነጥብ በሚመለከት፡፡ ይህ ነጥብ በመርሕ ደረጃ የሚደገፍ ነጥብ ነው፡፡ የሚደግፉት ደግሞ ከጎጠኞቹ ወያኔወችና ኦነጋውያን በስተቀር ሁሉም ጦቢያውያን መሆናቸው አያጠያይቅም፡፡ ነገር ግን ሰይጣኑ እትንትኑ ነው (the devil is in the details)፡፡ የፌደራል መንግሥትን የሚገዳደሩ ክልላዊ ልዩ ኃይሎችን ማፈራረስ አለብህ ባላችሁት መሠረት፣ ዐብይ አህመድ ያማራን ክልል ልዩ ኃይል አፈራርሷል፡፡ ካማራ ክልል ልዩ ኃይል እጅግ የበለጡት የኦሮምያና የትግራይ ክልሎች ልዩ ኃይሎች እያሉለት፣ ያማራን ክልል ልዩ ኃይል ዐብይ አህመድ አስቀድሞ ያፈራረሰው አስቀድመህ ማፈራረስ ያለብህ እሱን ነው ስላላችሁት ነው ወይስ ከፍኖትካርታው ውጭ በራሱ ተነሳሽነት ነው? ካላችሁትስ ለምን? ምክኒያታችሁ ምንድን ነው? ብላችሁት ከሆነ ደግሞ (ምክኒያታችሁ ምንም ይሁን ምን) የዐብይ አህመድ ኦነጋዊ ጦር የክልሉን ልዩ ኃይል በማፍረስ ሰበብ ባማራ ሕዝብ ላይ እየፈጸመ ላለው ከፍተኛ ወንጀል ቀጥተኛ ተጠያቂ መሆናችሁን ታምኑበታላችሁ?
• በዘር የተደራጁ ፓርቲወችን ማጥፋት አለብህ ባላችሁት መሠረት፣ ዐብይ አህመድ አብንን ለማጥፋት ተነሳስቷል (ከተሳካለት)፡፡ ግማሽ ምዕተ ዓመት ያስቆጠሩት ኦነግና ወያኔ እያሉለት፣ ሁለት ዓመት እንኳን ያልሞላውን አብንን ለማጥፋት ዐብይ አህመድ የተነሳሳው አስቀድመህ ማጥፋት ያለብህ እሱን ነው ስላላችሁት ነው ወይስ ከፍኖትካርታው ውጭ በራሱ ተነሳሽነት ነው? ካላችሁትስ ለምን? ምክኒያታችሁ ምንድን ነው? ለጦቢያ አንድነት እጅግ አደገኛ የሆኑት ወኔና ኦነግ ቅንጣት ሳያሳስቡት፣ ያማራ ብሔርተኝነት እጅግ ያሰጋኛል ያለውስ ያሰጋሃል ስላላችሁት ነው ወይስ ከሰነዱ ውጭ በራሱ አስተሳሰብ? ካላችሁትስ ለምን? ምክኒያታችሁ ምንድን ነው?

የዚህን ጥያቄ መልስ ካቶ አንዳርጋቸው እስከምሰማ ድረስ የኔን ግምት ልናገር፡፡ የዜግነት ፖለቲካ አራምዳለሁ የሚለው የዲባቶ (doctor) ብርሃኑ ኢዜማ፣ ከኦሮሞወችና ከትግሬወች ሊያገኝ የሚችለው ድጋፍ ከሞላ ጎደል ኢምንት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ኢምንት የሆነበት ምክኒያት ደግሞ ኦነግና ወያኔ ላያሌ ዓመታት በትግሬወችና በኦሮሞወች ላይ የረጩት እኩይ የዘረኝነት መርዝ ነው፡፡ ኢዜማ ከፍተኛ ድጋፍ ሊያገኝ የሚችለው ጦቢያዊነቱን ከሚያስቀድመው ካማራ ሕዝብ ነው፡፡ ያማራ ሕዝብ ደግሞ በመላው ጦቢያ ላይ የተሠራጨ የኦሮሞን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የኦሮሞንና የትግራይን ሕዝብ ድምር የሚበልጥ ሰፊ ሕዝብ ነው፡፡ ስለዚህም ኢዜማ ባብዛኛው ያማራ ሕዝብ ከተደገፈ፣ በምርጫ እንደሚያሸንፍ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ኢዜማ ባብዛኛው ያማራ ሕዝብ እንዳይደገፍ የሚያደርገው እንቅፋት ደግሞ አብን ነው፡፡ ስለዚህም አቶ አንዳርጋቸው ለዐብይ በሰጡት ሰነድ ላይ አብንን እንዲያጠፋ ባጽንኦት ቢያሳስቡት አይገርም ማለት ነው፡፡ አቶ አንዳርጋቸው በርግጥም ይህን ማሳሰቢያ ለዐብይ አህመድ ሰጥተው ከሆነ ደግሞ፣ ከሰኔ 15 ክስተት በኋላ በአብን ላይ እየተፈጸመ ባለው ወንጀል ላይ የሳቸውና የዲባቶ ብርሃኑ እጅ አለበት ማለት ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ኢዜማ ተፎካካሪወቹን ለማሸነፍ ያቀደው በሐሳብ ብልጫ በምርጫ ሳይሆን፣ በኃይል ብልጫ በርግጫ ነው ማለት ነው፡፡ ኦነጋውያንስ በኦሮሞ ብልጫ በሜንጫ ቢሉ ምን ይፈረድባቸዋል?

• የኢዜማ መሪ ዲባቶ ብርሃኑ ነጋ ‹‹ዐብይ አህመድ ከኔ በላይ ጦቢያዊ ነው›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ዐብይ አህመድ ኦፒዲኦ ነው፡፡ ኦፒዲኦ ደግሞ (የኦፒዲኦ ፈጣሪ መለሰ ዜናዊ በትክክል እንደተናገረው) ፋቅ ቢያደርጉት ኦነግ ነው፡፡ ስለዚህም ዐብይ አህመድ የኦፒዲኦን ጭምብል (mask) ያጠለቀ ኦነግ ነው፡፡ ኦነጋዊ ደግሞ መቸም ቢሆን ለጦቢያና ለጦቢያዊነት አስቦ የሚያውቀው? ገና በልጅነቱ ወያኔ ጉያ ገብቶ ፀረጦቢያ መርዝ እየተጋተ አድጎ በወያኔ ቁንጮ ድርጅት ውስጥ ከፍተኛ ሹም ለመሆን የበቃ ኦነጋዊ ግለሰብ ድንገት ተነስቶ በጦቢያዊነት ሲምልና ሲገዘት፣ ከመጠራጠር ይልቅ ከማናችንም በላይ ጦቢያዊ ነው ማለት እብድነት አይሆንም? ዐብይ አህመድን በሙሉ ልባችሁ ልታምኑት እንዴት ቻላችሁ? እንቁላሎቻችሁን ሁሉ ባንድ ቅርጫት ውስጥ የከተታችሁት፣ ዐብይ አህመድ ምን ዐይነት ቃል ቢገባላችሁ ነው? ቃሉን ቢያጥፍስ?

• ጦቢያ የመሪ መካን የሆነች ይመስል ዐብይ አህመድን አማራጭ የለውም ማለት፣ የልብ ልብ ተሰምቶት አምባገነን እንዲሆን መገፋፋት አይሆንም ወይ? ዐብይ አህመድ ከቀርብ ጊዜ ወዲህ እያሳየ ያለው ፉከራ፣ ዛቻ፣ ንቅትና፣ ትዕቢት ያምባገነንነት ዳር ዳር አይደለም ወይ? ጃዋርና መሰሎቹ የበለጠና የበለጠ አክራሪ እየሆኑ የመጡት አማራጭ የለውም የተባለለትን ዐብይን በርግጥም አማራጭ እንደሌለው በማሳየት ኦነጋዊ ዓላማቸውን ለማሳካት እንደሆነ መገመት አይቻልም ወይ?
• ዐብይ አህመድን በግልጽ ደግፎ የማያውቀው ወያኔ ከሰኔ 15 ወዲህ ቀንደኛ ያብይ አህመድ ይፋዊ ደጋፊ ሁኗል፡፡ ይህ ድጋፉ ደግሞ ዐብይ አህመድ ኦነጋዊ ሥራውን የሚሠራው ከወያኔ (በተለይም ደግሞ ከደብረጽዮን) ጋር እየተናበበ በመቀናጀት እንደሆነ በግልጽ ያሳያል፡፡ ይህ መናበብና መቀናጀት ግንቦት ሰባት ለዐብይ አህመድ በሰጠው ሰነድ ውስጥ የተካተተ ነበርን? ከተካተተስ ለምን? ኦነግና ወያኔ ባማራ ላይ ተመሳጥረው እንዲተባበሩ የተፈለገበት ምክኒያት ምንድን ነው?
• የሚከተሉት ደግሞ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲመልሳቸው ሳይሆን እንዲያስብባቸው ብቻ የተወረወሩ ጥያቄወች ናቸው፡፡

• ከጥቂት ወራት በፊት አንተው ራስህ (አንዳርጋቸው ጽጌ) ለዋልታ ቴሌቪዥን (ስሜነህ ባይፈርስ) በሰጠኸው ቃለ መጠየቅ ላይ ኢሳትን የመሠረተው ግንቦት ሰባት እንደሆነ በግልጽ ጠቁመኻል፡፡ ስለዚህም ስለ ኢሳት ምንነትና ማንነት በደንብ ታውቃለህ ማለት ነው፡፡ በአትላንታው የኢዜማ ስብሰባ ላይ የተገኘው ደግሞ ኢሳት ብቻ ነው፡፡ እንደማናቸውም ሚዲያ የኢሳት ጋዜጠኞች የሚያንጸባርቁት የቀጣሪያቸውን አመለካከት ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ እነዚህ የኢሳት ጋዜጠኞች (በተለይም ደግሞ ሲሳይ አጌና) በዐብይ አህመድ የመጣ ባይናችን መጣ ብለዋል፡፡ ስለዚህም የኢሳትና የዐብይ አህመድ ግንኙነት እስከምን ድረስ ነው? የሕዝብ ዓይና ጆሮ የነበረው ኢሳት የዐብይ አንደበትና አይምሮ የሆነው ለምንድን ነው?

• የኢሳት የቦርድ አባል ነዓምን ዘለቀ፣ ኤርምያስ ለገሰን እነቅፋለሁ ብሎ አንተን ሲዘልፍ ምን አልከው? ወያኔን ለመጣል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገው ማን ነው? የወያኔን ጉድ በበሳል ትንተና የሚያጋልጠው ኤርምያስ ለገሰ ነው ወይስ ማንም በማያነብለት በእንግሊዘኛ እየሞነጫጨረ ጊዜውን በከንቱ የሚያጠፋውና ያለ ምንም ፋይዳ አስመራ እየተመላለሰ የመዋጮ ገንዘብ በከንቱ የሚያባክነው ነዓምን ዘለቀ? ነዓምንም አንድም ቀን ተችተው የማያውቁት ወያኔና ኦነግ ኤርምያስን ነክሰው የያዙት ለምን ይመስልሃል?

• የጠላትን ውስጠ ሚስጠር የሚያወቅ ሰው ወደ ወገኑ ተመልሶ ትግሉን ሲቀላቀል እሰየው ይባላል እንጅ እንዴት ይወገዛል? ወያኔ ደርግን ያሸነፈው በደርግ ውስጥ በሰገሰጋቸው የውስጥ አርበኞቹ አልነበረም ወይ? ዐብይ አህመድና ለማ መገርሳ ደግሞ ኦነግን ከድል አፋፍ ያደረሱት የጦቢያዊነት ካባ ለብሰው በሀገር ወዳድ ጦቢያውያን መካከል ሠርገው በመግባት አይደለም ወይ?

• ኦነጋውያን የተነሱት ጦቢያን ለመግደል ስለሆነ፣ አገር ወዳድ ጦቢያውያን ጦቢያን ለመታደግ ከኦነጋውያን ጋር የሚያደርጉት ትግል የሞት ሽረት ትግል ነው፡፡ ይህን የሞት ሽረት ትግል ባሸናፊነት ለማጠናቀቅ የሚቻለው ደግሞ በሀገር ወዳድ ጦቢያውያን መኻል የተሰገሰጉት ዐብይ አስተኔ ኦነጋውያን በግልጽ ተለይተው በወረንጦ ሲነቀሉ ነው፡፡ አለበለዚያ ትርፉ እንደ ሸንበቆ ወጥቶ ወጥቶ እንደ ሙቀጫ በመንከባለል ታጥቦ ጭቃ መሆን ነው፡፡

• ዐብይ አህመድ የኅሊና እስረኞችን የፈታው፣ የኅሊና እስርን ስለሚቃውም ነው ወይስ ሀገር ወዳድ ጦቢያውያንን በማታለል ትንሽ ሰጥቶ ብዙ ለመውሰድ ነው? በመቃወም ቢሆን ኖሮ በአብን እና በባላደራ ላይ የሚፈጸመውን ያሁኑን አፈሳ ምን አመጣው?

• ዐብይ አህመድ ሚዲያን ነጻ ያደረገው በሚዲያ ነጻነት ስለሚያምን ነው ወይስ ኦነጋዊ ሚዲያወች (OMN, OBN, LTV ወዘተ.) እስከሚጠናከሩ ዓይን ውስጥ ላለመግባት ነው፡፡ በሚዲያ ነጻነት የሚያምን ቢሆን ኖሮ አስራት ሚዲያን የሚያፍነው፣ ሰናይ ሚዲያ እንዳይቋቋም የሚያሰናክለው ለምንድን ነው?
• ዐብይ አህመድ ተቃዋሚወችን ወደ ሀገር ግቡ ያለው በሰላማዊ ትግል ስለሚያምን ነው ወይስ ኦነጋውያንን አሰባስቦ ለማጠናከር ነው? በሰላማዊ ትግል የሚያምን ቢሆን ኖሮ፣ ጃዋርንና ዳውድን እየተንከባከበ አብንንና ባላደራን የሚያዋክበው ለምንድን ነው?

• ዐብይ አህመድ በመጀመርያወቹ ጥቂት ወራቶች ያደረገው ወያኔ እስከሚደላደል ድረስ በመጀመርያወቹ ዓመታት ካደረገው በምን ይለያል? መንግስቱ ኃይለማርያምና መለስ ዜናዊ ገድለው ለቅሶ ይደርሳሉ፣ ባህል ነው፡፡ ዐብይ አህመድ ደግሞ ገድሎ ችግኝ ይተክላል፣ ለውጥ ነው፡፡ የባህል ለውጥ፡፡

በዋርካ ያሾፈ እንዳብይ ማን አለ
አውኳል በማለት ኦዳ እየከለለ፣
ከንቀቱ ብዛት ኮርቶ እየሸለለ
ምሣር እንኳን ሳይል በሜንጫ እንደጣለ፣
መታሰቢያ ብሎ ባሕርዛፍ ተከለ፡፡

መስፍን አረጋ EMAIL mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic