>
5:13 pm - Thursday April 19, 1962

ጀኔራል ተፈራ ማሞ እና ኮሎኔል አለበል አማረ የርሀብ አድማ ላይ ናቸው!!! (ሀይለእየሱስ አዳሙ)

ጀኔራል ተፈራ ማሞ እና ኮሎኔል አለበል አማረ የርሀብ አድማ ላይ ናቸው!!!
ሀይለእየሱስ አዳሙ
 
እነ ጀኔራል ተፈራ ማሞ፣ ኮሎኔል አለበል አማረ፣ ኮሎኔል ባምላኩ እና ሌሎች አብረዋቸው በባህር ዳር 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ የታሰሩ የአማራ የጸጥታ ዘርፍና  ልዩ ፖሊስ አመራሮች የምግብና መጠጥ ማቆም አድማ መጀመራቸውን ዛሬ ማምሻውን ባነጋገርኳቸው ግዜ ነግረውኛል። በነገራችን ላይ ምንም አይነት የጤና መጓደል የሌለበት ሙሉ ጤነኛ ሰው ያለምግብና ውሃ መቆየት የሚችለው ቢበዛ ለሶስት ቀናት ነው። ጀኔራል ተፈራ እድሜው የገፋ እና ለ9 አመታት በትህነግ እስርቤትና በማእከላዊ ከፍተኛ ሰቆቃ የተፈጸመበት ሰው ነው። የምግብና የመጠጥ ማቆም አድማው ህይወቱን ለሞትና ለከፋ ጉዳት የሚያደርስ ነው። አዴፓ ባስቸኳይ ስብሰባ በፖለቲካ ውሳኔ መፍታት አለበት። አዲስ የተመረጠው የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ተመስገን ጥሩነህ ይህንን ጉዳይ ዋናው አጀንዳው አድርጎ አፋጣኝ ውሳኔ ማሳለፍ አለበት። ጄኔራል ተፈራን ጨምሮ አብረውት በታሰሩት የጸጥታና ልዩ ፖሊስ አመራሮች ላይ ክልሉ በሚያስተዳድረው እስርቤት ውስጥ አንዳች ነገር ከተፈጠረ ክልሉ ወደለየለት ትርምስና ብጥብጥ ውስጥ እንደሚገባ መገመት አያዳግትም።
 በቪዲዮው ላይ በሰማያዊ ቲሸርት የሚታየው  ጀኔራል ተፈራ ሲሆን ከጎኑ ያለው ኮሎኔል አለበል ነው። ከጀርባቸው በሽርጥ የሚታየው ኮሎኔል ባምላኩ ነው። ምግብ እና መጠጥ ካቆሙ 24 ሰአት ስለሞላቸው ድምጻቸው በጣም ዝቅተኛ ነው። በሁሉም ፊት ላይ የመዛል እና የመዳከም ምልክት አስተውያለሁ። ቪዲዮው በርቀት በሞባይል የቀረጽኩት ስለሆነ ለጥራቱ ማነስ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ሰላምታ ካቀረብኩላቸው በሁዋላ “ሀይለየሱስ” ብሎ ሲጠራኝ የምትሰሙት ኮሎኔል አለበል ሲሆን የምግብ ማቆም ማድረጋችሁን ሰማሁ ስላቸው ከፊት ሁኖ “ምን እናድርግ መብታችንን አፈኑት” ሲል የምትሰሙት ጀኔራል ተፈራ ነው። የፌዴራል ፖሊሶችና ሲቪል የለበሱ ደህንነቶች ዙሪያዬን ስለከበቡኝ ሙሉውን መቅረጽ አልቻልኩም።
 ከጥያቂያቸው መካከል፦
 1. ያለ አግባብ ታስረናል።  ከ9አመት የጨለማ እስር ቤት ሰቆቃና የስደት ኑሮ በሁዋላ የአማራን ህዝብ ለማገልገል ሀላፊነት ብንቀበልም በማናውቀው ጉዳይ በፌዴራል መንግስት ክስ ታስረን ዛሬም በእስር በመማቀቅ ላይ እንገኛለን።
 2. በርቀት እጅ ከማውለብለብ ውጭ ከቤተሰብና ጠበቃ ጋር መገናኘት አልቻልንም።
 3. ፍትህ ተጎድሎብናል
 4. በቀጠሮ በመጉላላት በእስር እየተንገላታን ነው
 5. የዋስትና መብታችን አልተከበረም
 6. አዴፓና የክልሉ መንግስት ይህንን በፌዴራል በሀሰት የተቀነባበረ የበቀል ክስ ውድቅ አድርጎ ባስቸኳይ ይፍታን
 6. የአማራ ህዝብን ለማገልገል ነው የመጣነው። በፊትም ህዝቡ ታግሎ ነው ያስፈታን አሁንም ህዝቡ ድምጽ ይሁነን
Filed in: Amharic