>

ጥቁር አንበሶችና የኦነግ ጅብ (መስፍን አረጋ)

ጥቁር አንበሶችና የኦነግ ጅብ

መስፍን አረጋ

በእኔ ነግስ እኔ ነግስ ውጊያ በመቀስቀስ
አንበሳና አንበሳ ተፋልመው እርስ በርስ
አንደኛው ድል ሆኖ የሞት ጽዋ ሲቀምስ
ሌላኛው ሲያጣጥር ግቢ ነፍስ ውጭ ነፍስ፣
የሞተን ተራምዶ የቆሰለን ገድሎ ጅቦ ሆነ ንጉስ፡፡

ያገርህ፣ የምነትህ፣ ያንተነትህ ዳራ
ባንድኛችሁ እንኳ እንዲኖር ሲጠራ
ሳትፋለም በፊት ከወንድምህ ጋራ
የጋራ ጠላትህ መሞቱን አጣራ፡፡

ጅብ ከሚበላህ በልተኸው ተቀደስ፡፡ የኦነግ (የኦሮሞ አላልኩም) ስግብግብ ጅብ ያማራና የትግሬ (የወያኔ አላልኩም) ጥቁር አንበሶችን ለመብላት አሰፍስፏል፡፡ ሊበላቸው ያሰፈሰፈው ግን አንበሶቹን ፊት ለፊት በመግጠም አይደለም፣ ሐሐምንነቱንና ማንነቱን በደንብ ያውቃልና፡፡ የጅቡ ምኞት የሸንዙን (Sun Tzu) መስዋእትነት የማይጠይቅ የሁለት ነብሮች ስልት በሁለቱ ጥቁር አንበሶች ላይ መጠቀም ነው፡፡ ሁለቱ አንበሶች ተፋልመው አንዱ ሙቶ ሌላኛው ቆስሎ ሲያጣጥር፣ የቆሰለውን በመግደል ያንበሶቹን ግዛት መጠቅለል፡፡

በሁለት አንበሶች ትግል፣ አንዱ ሙቶ ሌላው ሲቆስል
የቆሰለውን በመግደል፣ ግዛታቸውን መጠቅለል፡፡

የኦነግ ጅብ በሕይወት ዘመኑ አንድም ጊዜ አደን ወጥቶ የማያውቅ፣ በየቆሻሻ መጣያው እየተልከሰከሰ ቁሪሳ የሚለቃቅም ሙትቻ የመንደር ጅብ ስለሆነ፣ የመስፋፋት ምኞቱ ሙሉ በሙሉ የተንጠለጠለው ሚናው ኢምንት በሆነበት በሁለት ነብሮች ስልት ላይ ነው፡፡ በመሆኑም የመስፋፋት ምኞቱ ይሳካ ዘንድ ወንድማማቾቹ የአማራና የትግሬ ጥቁር አንበሶች የግድ መፋለም አለባቸው፡፡ ስለዚህም አማራና ትግሬን የሚያፋጅ እሳት ካለ እሳቱን ማራገብ፣ ከሌለ ደግሞ እሳቱ መለኮስ የግድ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ደግሞ ኦነግ እድለኛ ነው፣ ደደቢት ላይ በይፋ የተለኮሰ እምብዛም አራግቡኝ የማይል እጅግ አደገኛ እሳት አለለትና፡፡ ይህ እሳት ደግሞ የወያኔ ባላባቶች ላማራ ሕዝብ ያላቸው (ምክኒያቱ በውል የማይታወቅ) እጅግ የመረረ ጥላቻ ነው፡፡

የወያኔ ባላባቶች ማለት ወያኔ የሚባለውን ጎጠኛ ድርጅት እንዳሻቸው ወዳሻቸው የሚዘውሩትን ጉምቱ ሰወች፣ እንደዚሁም የነዚህን ሰወች ዘመድ አዝማዶችና የጥቅም ተባባሪወች የሚያካትት፣ በደምና በጥቅም የተሳሰረ ማፍያተኔ (ማፍያአስተኔ፣ mafia-esque) ቡድን ማለት ነው፡፡ ይህ ማፍያተኔ ቡድን ራሱን በራሱ የትግራይ ሕዝብ እንደራሴ ቢያደርግም፣ ሰፊውን የትግራይ ሕዝብ ቀርቶ በዚህ ቡድን እንደ በግ የሚነዳውን ተራውን የወያኔ ተጋዳላይ አይወክልም፡፡

በወያኔ ባላባቶች ድውይ እሳቤ መሠረት፣ ያማራና የትግራይ ሕዝቦች መስተጋብር ወይም ጨዋታ የግዱን መሆን ያለበት ዜሮ ድምር ጨዋታ (zero sum game) ነው፡፡ ይህን ድውይ እሳቤያቸውን ደግሞ በሃያ ሰባቱ የፍዳ ዘመን በደንብ በመተግበር በግልጽ አሳይተውታል፡፡ ትግሬ በማንነቱ የሚኮራው አማራ በማንነቱ ከተሸማቀቀ፣ ትግሬ በኢኮኖሚ፣ በባህል፣ በጤናና በሌሎች ረገዶች የሚበለጽገው አማራ በነዚሁ ረገዶች ከቆረቆዘ፣ የትግሬ ሕዝብ የሚጨምረው ያማራ ሕዝብ ከቀነሰ፣ ትግሬ ናጽነት የሚኖረው አማራ ቅኝ ከተገዛ፣ ባጠቃላይ ደግሞ ትግሬ የሚድነው አማራ ከሞተ ብቻ ነው፡፡ የዚህ ዜሮ ድምር ጨዋታ የመጨረሻ ጦስ (effect) ደግሞ አማራንና ትግሬን ዜሮ (ሬሳ) አድርጎ የኦነግ ጅብ ቁሪሳ ማድረግ ነው፡፡

የኦነጉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ አህመድ፣ የሱና የጃዋር ልዩ አማካሪወች የሆኑትን ሕዝቅኤል ጋቢሳንና ሌንጮ ለታን በቅርቡ ወደ መቀሌ የላካቸው፣ አማራንና ትግሬን እንዲያፋጅ በተለኮሰው ወያኔያዊ እሳት ላይ ቢንዚን ለመጨመር እንደነበር አያጠያይቅም፡፡ ወያኔና አዴፓ በቅርቡ ያወጧቸው መግለጫወች ደግሞ ያማራንና የትግሬን ሕዝብ ዘላቂ ጥቅሞች ታሳቢ ያደረጉ ልፈፋወች ሳይሆኑ፣ እሳቱን ይበልጥ በማቀጣጠል የሁለቱንም ሕዝቦች ውድቀት ያፋጥናሉ ተብለው የታመነባቸው ተራ ዘለፋወች ናቸው፡፡ ስለዚህም ወያኔ መግለጫውን እንዲጽፍ የገፋፋው፣ የአዴፓን መግለጫ ደግሞ ያረቀቀው ራሱ ዐብይ አህመድ ባይሆን እንጅ ቢሆን አያስገርምም፡፡

የማልጠራጠራቸው ሰወች በማልጠራጠርባቸው መቸቶች ላይ ሆን ብለው ሳይሆን እንደዘበት ሲናገሩ እንደሰማሁት፣

• የወያኔ ባላባቶች ራስ የሆነው አቦይ ስብሐት ‹‹ያማራ ለማኙ እንኳን ከትግሬ አይለምንም›› ሲል የተደመጠ፣ ባማራ ጥላቻ ደቁኖ የቀሰሰ አዛውንት ነው፡፡
• የወያኔ ጠቅሊሞ (generalisimo) መለስ ዜናዊ፣ ታላቁ ቀያኔ (poet) ከበደ ሚካኤል በጻፉት ‹‹ተረትና ምሳሌ›› ላይ ያነበበውን ‹‹የሮማውያን አንገት አንድ ቢሆንልኝማ!›› (would that the Roman people had but one neck) የሚለውን የካሊጎላን (ceasar caligula) ጥቅስ በመቀየር ‹‹ያማራን አንገት አንድ አድርገው ቢሰጡኝ፣ አንዴ ቆርጨው እገላገል ነበር›› እስከማለት የደረሰ ባማራ ጥላቻ የሰየጠነ ሰይጣን ነው፡፡
• ሰየ አበርሓ፣ ሳሞራ ዩኑስ፣ ዐባይ ፀሐይና የመሳሰሉት ወየንቲወች ደግሞ አማራን እንደ ሲጋራ ረግጠን ጥለነዋል፣ ያማራንና የኦርቶዶክስን አከርካሪ ሰብረነዋል ወዘተ. እያሉ የሚበሻቀጡ፣ አማራን በመዘለፍ ጀግንነት የሚሰማቸው ጋጠወጦች ናቸው፡፡

ስለዚህም የወያኔ ባላባቶች አማራ ለሚባለው ሕዝብና አማራነት ለሚወክላቸው ጽንሳቦች (concept) በተለይም ደግሞ ለጦቢያዊነት ያላቸው ጥላቻ እስከ ግብዓተ መሬት የማይለቅ ሥር የሰደደ ጥላቻ መሆኑ አያስገርምም ማለት ነው፡፡ አማራን አዋረድን ብለው በእስረኛ አፍ ላይ በመጸዳዳት ራሳቸውን እንዲያዋርዱ የገፋፋቸው፣ አማራን ለማርከስ ሲሉ ብቻ ራሳቸውን ሶዶማዊ ለማድረግ ያነሳሳቸው ይኼው (ምክኒያቱ በውል የማይታወቅ) ሥር የሰደደ ጥላቻቸው ነው፡፡

የወያኔ ባላባቶች ትግራዋይነታቸውን የሚገልጹት ባማራ ጥላቻቸው ስለሆነ፣ ማናቸውም ድርጊት አማራ የሚሉትን ሕዝብ ኢምንት የሚጎዳ እስከሆነ ድረስ እነሱን ጃምንት ቢጎዳም ከበሮ ያነሱለታል፡፡ ማናቸውም እሳት አማራን በወላፈኑ የሚገርፍ እስከሆነ ድረስ እነሱን ቢያንጨረጭርም እሳቱን ለመለኮስ አያንገራግሩም፡፡ ያማራ ደሳሳ ጎጆ እስከፈረሰ ድረስ የነሱ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ ቢደረመስ፣ ያማራ ሐብት እስከተዘገነ ድረስ የነሱ ሐብት ቢታፈስ፣ ያማራ ስም እስከጠለሸ ድረስ የነሱ ሐበሻዊ ስም ቢጠቀርሽ፣ የ 50% አማራ ሐይማኖት እስከጠፋ ድረስ የ 96% ትግሬ ሐይማኖት ቢጠፋ፣ ባጠቃላይ ደግሞ ያማራ አንድ ዓይን እስከጠፋ ድረስ የነሱ ሁለቱም ቢደረገም ዴንታ የላቸውም፡፡

የኦነጋውያን እሳት ፀረሐበሻ እሳት ስለሆነ፣ አማራን ቢበላ ቀጥሎ የሚበላው ትግሬን እንደሆነ የወያኔ ባላባቶች በርግጠኝነት ያውቃሉ፡፡ ይሄን እያወቁ ግን እሳቱን ለማንቀልቀል ይንቀለቀላሉ፡፡ ጃዋር ሙሐመድና በቀለ ገርባ በመድረክ፣ በዐብይ አህመድ የሚመራው ኦዴፓ/ኦነግ ደግሞ በመግለጫ፣ አዲሳባ የኦሮሞና የኦሮሞ ብቻ ናት ሲሉ፣ የወያኔ ባላባቶች ምንትሳቸው ቄጠማ ይቆርጣል፡፡

የወያኔ ባላባቶች አስራ ሰባት ዓመት በሌት ጅብነት፣ ሃያ ሰባት ዓመት ደግሞ በዝብ ቀትርነት የትየለሌ ሐብት ዘረፉ፡፡ ከዚህ የትየለሌ ሐብት ጥቂቱን በመቆንጠር ባንድ ቀን ባጸደቁት አፓርታዊዳዊ የሊዝ አዋጅ አማካኝነት ካማራና ከጉራጌ በነጠቋቸው መሬቶች ላይ አብዛኞቹን ያዲሳባ ሕንፃወች አነጹ፡፡ ስለዚህም የኦነጋውያን ያዲሳባ እቅድ ቢሳካ ከማንምና ከምንም በላይ የሚጎዱት ራሳቸው የወያኔ ባላባቶች መሆናቸውን ነጋሪ አያስፈልጋቸውም፡፡ እንዲህም ሆኖ የወያኔ ባላባቶች ላማራ ካላቸው ጥላቻ የተነሳ የኦነግን እኩይ እቅድ ለማሳካት ከራሱ ከኦነግ በባሰ ቁርጠኝነት ተነሳስተዋል፡፡ የታከለ ኡማ ዓላማ ያማራንና የጉራጌን ቆሎ ይዞ ወደ ትግሬ አሻሮ መጠጋት እንደሆነ ይበልጥና ይበልጥ ግልጽ እየሆነላቸው፣ በኦቦ ታከለ የመጣ ባይናችን መጣ ይላሉ፡፡

ኦነጋውያን በማያሻማ ቋንቋ እንደገለጹት፣ መሠረታዊ ዓላማቸው የኦሮሞ የበላይነትን በድፍን ጦቢያ ላይ በማስፈን ሐበሻ የሚሉትን ትግሬወችን የሚያካትት ሰፊ ሕዝብ በገዛ አገሩ በጦቢያ ላይ የበይ ተመልካች ማድረግ ነው፡፡ በሌላ አባባል የኦነግ ዓላማ ጦቢያዊነትን ገድሎ በኦሮሙማ መተካት ነው፡፡ በኦሮሙማ ዳፋ ጦቢያዊነትን የደፋው ደግሞ ሌላ ማንም ሳይሆን ወያኔ ነው፡፡ አለያማ አንድም ቀን ሁነኛ ውጊያ አድርጎ የማያውቀው፣ እድሜ ልኩን የሻቢያ መንገድ ጠራጊ የነበረው አነግ፣ ጦቢያዊነትን ሊደፋው ቀርቶ ጫፉን አይነካውም ነበር፡፡ ስለዚህም የኦነጋውያንን እኩይ እቅድ ከስኬት አፋፍ ያደረሰው ወያኔ እንጅ ቱሪናፋው ኦነግ አይደለም ማለት ነው፡፡ ዐብይ አህመድና ግብራበሮቹ የሚሯሯጡት የቀረችውን ትንሽ መንገድ በመሄድ ከግባቸው ለመድረስ ነው፡፡ ነገር ግን ይህችንም ትንሽ መንገድ ራሳቸውን ችለው መሄድ የማይችሉ ሙትቻወች ስለሆኑ፣ አሁንም የወያኔ ድጋፍ የግድ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በተለይም ደግሞ ወያኔ ያማራን ሕዝብ ትኩረት ሙሉ በሙሉ እንዲስብላቸው ይፈልጋሉ፡፡

ጦቢያዊነት ያለ አማራ፣ አማራ ያለ ጦቢያዊነት አይታሰብም፡፡ ጠንካራ ጦቢያዊነት በጠንካራ አማራ፣ ጠንካራ አማራ በጠንካራ ጦቢያዊነት ነው፡፡ የኦነጋውያን ኦሮሙማ ደግሞ ጠንካራ ጦቢያዊነትን ሊያሸንፍ ቀርቶ ሊገዳደረው አይችልም፡፡ ስለዚህም ዐብይ አህመድ ያማራ ብሔርተኛነት መጠናከር ያሰጋኝል ሲል፣ ለማለት የፈለገው ጠንካራ ጦቢያዊነት የኦሮሙማ ሕልሜን ቅዠት ያደርግብኛል ነው፡፡ ጠንካራ ጦቢያዊነት የሚበጀው ደግሞ ላማራ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም አገር ወዳድ ጦቢያውያን ነው፡፡ ስለዚህም የወያኔ ባላባቶች ባማራ ጥላቻ ባይታወሩ ኖሮ፣ ካማራ ጋር ተባብረው የጦቢያዊነት ፀር የሆነውን ኦነግን በተፋለሙት ነበር፡፡ በእውነትም ለትግራይ ሕዝብ የቆሙ የትግራይ ሕዝብ እንደራሴወች ቢሆኑ ኖሮ፣ ፣ የትግራይ ሕዝብ መድህን የሆነውን ጦቢያዊነት በማዳከም በኦሮሙማ እንዲጠቃ ባላደረጉት ነበር፡፡

እንኳን ሰውና ሰው ዲንጋና ዲንጋ ይጋጫል፡፡ የዘመድ ጥል ደግሞ የሥጋ ትል ነው፡፡ እንደ ማናቸውም ወንድማማች ሕዝቦች፣ የአማራና የትግሬ ሕዝቦች ቅራኔወች ሊኖራቸው ይቻላል፡፡ እነዚህ ቅራኔወች ግን በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉ ተራ ቅራኔወች እንጅ መሠረታዊ ቅራኔወች ሊሆኑ አይችሉም፡፡ የጦቢያውያን መሠረታዊ ቅራኔ ከኦነጋውያን ጋር ነው፣ ጦቢያዊነትና ኦሮሙማ መቸም የማይታረቁ ተጠፋፊ ጽንሳቦች (concept) ናቸውና፡፡ ስለዚህም ይህ የጦቢያዊነትና የኦሮሙማ መሠረታዊ ቅራኔ ባንድ ወይም በሌላ መንገድ እስከሚፈታ ድረስ፣ ጦቢያውያን ሙሉ ትኩረታቸውን ማድረግ ያለባቸው በኦነጋውያን ላይ ብቻ ነው፡፡

እባብ ባለበት ጉንዳን አይፈራም፡፡ አብናቶቻችን (our forebears) በጣልያን ላይ፣ ቻይኖችም በጃፓኖች ላይ ያደረጉት ይህንኑ ነው፡፡ ጦቢያውያን አንድ ከሆኑ ደግሞ ፀረጦቢያውያን አንድ ቀን አያድሩም፡፡ ታከለ ኡማ ያማራንና ቆሎ ዘግኘ ወደ ትግሬ አሻሮ እጠጋለሁ ሲል፣ አንድ ጥሬ ሳያነሳ እጁን ይሰበስብ፣ ካልሰበሰበም ይቆረጥ ነበር፡፡ ጊዜው ትግሬና አማራ የሚናቆሩበት ሳይሆን ለህልውናቸው ሲሉ የግዳቸውን የሚተባበሩበት ነው፡፡

ያማራ ሕዝብ ግን (ወንድሙ የትግሬ ሕዝብ ተባበረውም አልተባበረውም) ለህልውናው ሲል ኦነግን መተናነቅ ግዱ ነው፡፡ በዚህ ትንቅንቅ ላይ ደግሞ አዴፓ የሚባለው ድርጅት አወንታዊ ወይም አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል፡፡ ይህን ጉደኛ ድርጅት በተመለከተ ደግሞ፣ ድኅረ ሰኔ 15 አያሌ ጉዶችን አሳይቶናል፡፡ ከነዚህ ጉዶች አንዱ (ዐብይ አህመድ በምትሓቱ ያደነዘዘው የጃዋር ዋና ተመሳጣሪ) ንግሱ ጥላሁን ወደ ግንባር መጥቶ፣ (የሰኔ 15 ጭፍጨፋ መጠናቀቁን ካረጋገጠ በኋላ ወደ አሜሪቃ ካቀናው) ከደመቀ መኮንን ጎን መቀመጡ ነው፡፡

ጋኖቹ አልቀው ምንቸቶቹ ጋን የሆኑበት የድኅረ ሰኔ 15 አዴፓ ላማራ ጥቅም ይቆማል ብሎ መጠበቅ፣ ከእባብ እንቁላል እርግብ መጠበቅ ነው፡፡ በራስ የመተማመን ጉድለት ክፉኛ በተጠናወተው፣ ዐብይ አህመድን ቀና ብሎ ማየት በማይችለው በደመቀ መኮንን የሚመራ ማናቸውም ቡድን ሆነ ድርጀት ለአማራ መርገምት እንጅ በረከት ሊሆን አይችልም፡፡ ደመቀ መኮንን ላማራ ሕዝብ መዋል የሚችልው ውለታ አንድና አንድ ብቻ ሲሆን፣ እሱም ሲያስፈልግ ነፍጠት በማለት ዐብይ አህመድን ልክ ልኩን መናገር ለሚችል ቆፍጣና አማራ ስልጣኑን መልቀቅ ነው፡፡ ለሜንጨኛ መድሐኒቱ ነፍጠኛ ነው፡፡
ጨዋነትና ትህትና የሚባሉት ያማራ ሕዝብ መለያ የሆኑት ግሩም እሴቶች በኦነግ መዝገበ ቃላት ውስጥ የሉም፡፡ በዚህ ረገድ ደግሞ ወያኔወች እንደ ኦነጎች ናቸው፡፡ ባጠቃላይ አነጋገር ደግሞ ሁሉም ጎጠኞች ለጨዋነትና ለትህትና ባዕዶች ናቸው፣ ጨዋነትና ትህትና ከጎጠኝነት ጋር አብረው አይሄዱምና፡፡ ስለዚህም ኦነጋውያን ጨዋነትን የሚያኩሉት (equate) ከፈሪነት፣ ትህትናን የሚያኩሉት ደግሞ ከበታችነት ነው፡፡ እነ ጃዋርን \የሚገባቸው\ አህያ የበቅሎ አባት በሚባልበት በካህንኛ (politically correct) ዘይቤ ሲነግሯቸው ሳይሆን፣ አህያ አህያ በሚባልበት በመዕምንኛ (politically incorrect) ዘይቤ ሲነግሯቸው ብቻ ነው፡፡ በዚህ ምክኒያት ነው ዐብይ አህመድን ጨምሮ ሁሉም ኦነጎች ለሚያዋርዷቸው ወያኔወች እየተሸቆጠቆጡ፣ በሚያከብሯቸው ብአዴኖች ላይ የሚበሻቀጡት፡፡

ሳያስፈቅድ ወደ መቀሌ ዝር የማይለው ዐብይ አህመድ ሳይፈቀድለት ወደ ባሕርዳር ሂዶ አምባቸውን የገደለው በራሱ ባምባቸው ጥፋት ነው፡፡ እነ አምባቸው ይሉኝታ ሳያጠቃቸው ዐብይ አህመድ እየዛተባቸው እንደሆነ ለሕዝባቸው በግልጽ ቢያሳውቁ ኖሮ፣ ራሳቸውን አድነው ያማራን ሕዝብ አሁን ከገባበት መቀመቅ ውስጥ ባላስገቡት ነበር፡፡ ጠያራም (airplane) ሆነ ሹርከኒፍ (helicopter) የክልሉን ፀጥታ መምሪያ ሳያሳውቅ ወደ ክልሉ የሚገባ ማናቸውም አየርኪናግ (aircraft) ቢያንስ ቢያንስ እንዲታገት ጥብቅ መመሪያ ሰጥተው ቢሆን ኖሮ፣ የኦነጉ መሪ ዐብይ አህመድ የኢንተራሃምዌው መሪ የሃብያሪማና (Juvenal Habyarimana) እጣ እንዳይደርሰው በመፍራት ከእኩይ ድርጊቱ በተቆጠበ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ በሮማዊው ቧልተኛ (satirist) ዴሲመስ ዩቬናሊስ (Decimus Juvenalis, 60 AD) ስም የተሰየመው ሃብያሪማና እና ዐብይ አህመድ በብዙ ረገዶች ይመሳሰላሉ፡፡ ዐብይ አህመድ እኔን ትነኩና መቶ ሺወች ባንድ ጀንበር ይታረዳሉ ማለቱ ደግሞ ምስስሉን ይበልጥ ያጠነክረዋል፡፡

ለማንኛውም የሆነው ስለሆነ፣ የሚሆነውም ስለሚሆን ጊዜው ሲደርስ ሒሳቡ ይወራረዳል፡፡ ላማራ ሕዝብ አሁን የሚያስፈልገው የዐብይ አህመድን የሚለማመጥ ደመቀ መኮንን ወይም የደመቀ መኮንን ዓይነት ውሽልሽል ሳይሆን፣ የዐብይን መቶ ሺወች ይታረዳሉ ዛቻ ቅንጣት የማይፈራ አማራዊ ጳውሎስ ካጋሜ (Paul Kagame) ነው፡፡ ደመቀ መኮንን ቦታውን ላብይ አህመድ የለቀቀው ዐብይ አህመድ ለጦቢያ ይበጃል ብሎ በማሰብ ከሆነ፣ የማይበጅ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ ለሚበጀው ላማራዊ ጳውሎስ ካጋሜ ሊለቅ ይገባል፡፡

የደመቀ መኮንን አዴፓ ባማራዊ ጳውሎስ ካጋሜ የሚመራ አማራዊ ድርጅት ቢሆን ኖሮ፣ ባሁኑ ጊዜ ሙሉ ትኩረቱን ማድረግ የነበረበት ያማራን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ባስገባው ኦዴፓ/ኦነግ ላይ እንጅ ወያኔ ላይ አልነበረም፡፡ የአዴፓ ውሻ የጮኸው የወያኔ ጅብ በሰሜን አቅጣጫ ከሄደ በኋላ ነው፡፡ የጮኸው ደግሞ ያማራ ጥቁር አንበሳ ፊቱን ወደ ሰሜን እንዲያዞር ነው፡፡ ያማራ ጥቁር አንበሳ ፊቱን ወደሰሜን እንዲያዞር የተፈለገበት ምክኒያት ደግሞ በሰሜን አቅጣጫ በወጣው በወያኔ ጅብ ምትክ በደቡብ አቅጣጫ እየገባ ያለውን በልቶ የማይጠግበውን ስግብግብ የኦነግ ጅብ እንዳያይና አባሮ እንዳይመልሰው ነው፡፡ ይህን ዓይነት ማዘናጊያ ደግሞ ዐብይ አህመድና ለማ መገርሳ የተካኑበት፣ ያማራ ሕዝብ የነቃበት የተበላ ቁብ ነው፡፡

ባሁኑ ጊዜ አማራን እያሸማቀቀ፣ እያፈናቀለ፣ እየገደለ፣ እያሰረና እያሰቃየ ያለው የኮልታፋው ዐብይ አህመድ ኦነግ እንጅ የዱዳው ደብረጽዮን ወያኔ አይደለም፡፡ የደብረጽዮን ሚና ከእገዛ ያለፈ አይደለም፡፡ በለማ መገርሳ እየተመራ በብርሃኑ ጁላ የሚታዘዘው የዐብይ አህመድ ኦነጋዊ ሠራዊት ካማራ ሕዝብ ጋር የሚያደርገውን ጦርነት በድል ያላጠናቀቀ ቢሆንም፣ አዴፓ ውስጥ በሰገሰጋቸው የውስጥ አርበኞቹ ከፍተኛ ድጋፍ በባህር ዳር ውጊያ ከፍተኛ ድል ተጎናጽፏል፡፡ በዚህ አካሄዱ ከቀጠለ ደግሞ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ጦርነቱን በስኬት ይደመድማል፡፡ በዚህ አካሄዱ በመቀጠል አለመቀጠሉ ላይ ወሳኝ ሚና የሚጫወተው ደግሞ መጭው ያማራ ክልል ፊምበር (president) ማለትም ፕሬዚዳንት ነው፡፡

ዐብይ አህመድ ባማራ ሕዝብ ላይ የጫነው የደህንነት አማካሪው ተመስገን ጡሩነህ ላማራ ሕዝብ ቦሪስ የልትሲን (Boris Yeltsin) እንጅ ቭላድሚር ፑቲን (Vladmir Putin) እንደማይሆን አስቀድሞ ለማወቅ ነበይ መሆን አያስፈልግም፡፡ የሚጠራጠር ደግሞ የዐብይ አህመድን ቆሪጥ እዩ ጩፋን አንድ ሺ ብር ከፍሎ መጠየቅ ይችላል፡፡ አሜሪቃውያን ራሳቸው በቀሰቀሱት ሁከት አሳበው ሎሌያቸውን ቦሪስ የልትሲንን መሠረታዊ ጠላታችን በሚሉት በሩሲያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ እንዳስቀመጡት፣ ዐብይ አህመድም በተመሳሳይ ዘዴ ሎሌውን ተመስገን ጡሩነህን መሠረታዊ ጠላቴ በሚለው ባማራ ሕዝብ አናት ላይ ወዘፈው፡፡ ዐብይ አህመድ ለተመስገን ጡሩነህ የሚሰጠው ልዩ ተልዕኮ ደግሞ በሲዳማ ዘይቤ ያማራን ክልል ቆራርጦ ለኦነግ ጅብ ቅርጫ ማቅረብ እንደሆነ ከወዲሁ መገመት ይቻላል፡፡

ጦቢያ እደዊሃ ሃበ አግዚአብሔር፡፡ ካያሌ እሳቶች ያወጣት የማይሰለቻት የጦቢያ አምላክ፣ አሁንም ከኦነግ እሳት ያወጣት ይሆናል፣ ይህ እሳት ከእስካሁኖቹ እሳቶች እጅግ የከፋ የሰደድ እሳት ነውና፡፡ ምናልባትም ደግሞ ያማራው ቦሪስ የልትሲን (ተመስገን ጡሩነህ) በጊዜ ሂደት የኦነግ ሎሌነቱ ያንገፈግፈውና ስልጣኑን በፈቃዱ ለቆ አማራዊ ቭላድሚር ፑቲን ይሾምልን ይሆናል፡፡ ይህ ግን የኛ ሳይሆን የጦቢያ አምላክ ሚና ነው፡፡ የኛ ሚና ከዐብይ አህመድ ፀረጦቢያ የሜዳና የሚዲያ ሠራዊት ጋር በሁሉም ረገዶች ጉሮሮ ለጎሮሮ ተናንቀን እየጣልን መውደቅ ነው፡፡ ይህን ሚናችንን እንድንወጣ ድፍረቱን፣ ኃይሉንና ብርታቱን እንዲሰጠን ደግሞ ለጦቢያ አምላክ ዘወትር መጸለይ ነው፡፡ ኦነግ የጦቢያን ሞት በከፍተኛ ፍጥነት እያፋጠነው ስለሆነ የበለጠ መፍጠን አለብን፡፡ ጊዜ የለንም፡፡ የሞት ሽረት ትግላችን ከኦነግ ጋር ብቻ ሳይሆን ከጊዜም ጋር ነው፡፡

ስለዚህም ሰፊው ያማራ ሕዝብ ሆይ፣ ያሁኑ የሞት ሽረት ትግልህ በማንነትና በምንትህ ላይ ከመጣብህ ከኦዴፓ/ኦነግ ጋር እንጅ ከትግራይ ሕዝብ ጋር እንዳልሆነ ልታውቅ ይገባሃል፡፡ ስለዚህም ባማራ ጥላቻ በታወሩት (የትግራይን ሕዝብ በማይወክሉት) በወያኔ ባላባቶች ትንኮሳ ተተንኩሰህ ከወንድምህ ከትግራይ ሕዝብ ጋር መፋለም ቀርቶ መጣላት የለብህም፡፡ አለያ ራስህንም ወንድምህንም በኦነግ ጅብ ታስበላለህ፡፡

የትግራይ ሕዝብ ደግሞ ወንድምህ ያማራ ሕዝብ ከኦነግ ጋር የሚታገለው ላንተም ለራስ ጭምር መሆኑን መዘንጋት የለብህም፡፡ ስለዚህም የወንድምህን ትግል መደገፍህ ቢቀር ማደናቀፍ የለብህም፡፡ በተለይም ደግሞ የማይወክሉህን የወያኔ ባላባቶች ተከትለህ፣ ኦነግን ደግፈህ ወንድምህን አማራን አዳክማለሁ ብትል የምትቆፍረው የወንድምህን ብቻ ሳይሆን ያንተኑ የራስህን መቃብር እንደሆነ ማወቅ አለብህ፡፡ በልቶ የማይጠግበው ስግብግቡ የኦነግ ጅብ ያሰፈሰፈው ማንነትህን፣ ባህልህን፣ ሐይማኖትህን፣ ፊደልህን፣ ሁለመናህን ቆረጣጥሞ ለመሰልቀጥ ስለሆነ፣ ሳይቀድምህ ቅደመው፡፡ ጅቡ ሳይበላህ በልተኸው ተቀደስ፡፡

ያገርህ፣ የምነትህ፣ ያንተነትህ ዳራ
ባንድኛችሁ እንኳ እንዲኖር ሲጠራ
ሳትፋለም በፊት ከወንድምህ ጋራ
የጋራ ጠላትህ መሞቱን አጣራ፡፡

በመጨረሻም ስለ ኦነግና ሻቢያ ጥቂት ልበል፡፡ የኦሮሙማ ሰደድ እሳት ባስቸኳይ ካልጠፋ አማራንና ትግራይን ብቻ ሳይሆን ባሕርጌንም (ኤርትራንም) የሚያሰጋ የሰደድ እሳት ነው፡፡ ስለዚህም ባሕርጋውያን (ኤርትራውያን) ለራሳቸው ሲሉ እሳቱን ማራገብ የለባቸውም፡፡ መሠሪወቹ የወያኔ ባላባቶች በሻቢያ ጫንቃ ስልጣን ይዘው ሲደላደሉ፣ ሻቢያን በጀርባው ወጉት፡፡ በወያኔ ባላባቶች ጉያ ሥር ያደገው መሠሪው ዐብይ አህመድ ደግሞ በሻቢያ እገዛ አማራና ትግሬን በልቶ ጡንቻውን ካፈረጠመ፣ እንዳይቀናቀነው በመፍራት ሻቢያን በማጅራቱ ያርደዋል፡፡ ጮሌው ዐብይ አህመድ ኢሳያስ አፈወርቂን ለሀገር መሪ በማይመጥን አጠራር፣ ኢሱ፣ ኢሱ እያለ የሚያቆለማምጠው ሊጠቀምበት ስለፈለገ ብቻ ነው፡፡ ጠቀሜታውን ሲጨርስ ደግሞ እንደ አሮጌ ቁና ወርውሮ ይጥለዋል፡፡ ስለዚህም ኢሳያስ አፈወርቂ በዐብይ አህመድ እንዳይጣል ከፈለገ ላማራና ለትግራይ ሕዝብ ብሎ ሳይሆን ለራሱ ሲል ይጣፍጥ፡፡ በተረፈ ግን የጦቢያ መኖርና አለመኖር የሚወሰነው በኦነግ፣ በወያኔ ወይም በሻቢያ ሳይሆን ባማራና በትግራይ ሕዝበ መተባበርና አለመተባበር ብቻና ብቻ ነው፣ ሁለቱ ከተባበሩ ምንም ኀይል አይሰባብራቸውምና፡፡

መስፍን አረጋ
Email: mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic