>
5:13 pm - Tuesday April 19, 2833

ዐብይ አህመድ በመስፍን እይታ (መስፍን አረጋ)

ዐብይ አህመድ በመስፍን እይታ

 

መስፍን አረጋ

 

ባንደበቱ አክብረን ብናወጣው ላይጌ
በምግባሩ ዘቅጦ ወረደ እግርጌ
ተነስ አይባልም ክብረቢስ ባለጌ፡፡
ዐብይ አህመድ፣ ዐብይ አህመድ
ያህያ ሥጋ ባልጋ ሲሉት ባመድ፡፡

የቅጥፈት ሊቅ

ዐብይ አህመድን በኔ እይታ ለመግለጽ የተነሳሳሁት ስለ ሰው ልቦና ያጠናሁ ልቦናሲነኛ (የስነ ልቡና ተመራማሪ፣ psychologist) ሁኘ አይደለም፣ የዐብይን ምንነት በጥቅሉ ለመረዳት ልቦናሲነኛ መሆን አያስፈልግምና፡፡ የዐብይ አህመድ አካሄድ ግልጽ ስለሆነ፣ ምንነቱን ለመረዳት ወል ስሜት (common sense) ወይም ሕገ ልቦና ብቻ በቂ ነው፡፡ የዐብይ አህመድን ተዛማጅ ድርጊቶች በመስመር በማገናኘት መስመሩን አርዝሞ የወደፊት ድርጊቱን አስቀድሞ መገመት የማይችል ሰው ሕጻን ወይም ሕጹጽ ብቻ ነው፡፡

ቡድሃፈናኞች (buddhists) እንደሚሉት ኋችማ (past) አችማን (present)፣ አችማ ፊችማን (future) ይገልጻል (If you want to know your present look at your past. If you want to know your future look at your present)፡፡ ነብዩ ኤርምያስ (17፡9-10) የሰውን ልብ ማን ይውቀዋል በማለቱ የተሳሳተ ይመስለኛል፣ የሰው ልብ በድርጊቱ ይታወቃልና፡፡ ያለፈው ድርጊት ያሁኑን፣ ያሁኑ ድርጊት የወደፊቱን ይጠቁማል፡፡ የማንነት ሚዛን ደም፣ የምንነት ሚዛን ድርጊት ነው፡፡ የሰውን ምንነት የሚወስነው የመጨረሻው ዳኛ አንደበቱ ሳይሆን ድርጊቱ ነው፡፡

የኦነጉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ባንደበቱ ጦቢያዊ ቢሆንም በድርጊቱ ግን ኦነጋዊ እንደሆነ ያደረጋቸውና የሚያደርጋቸው ድርጊቶች በግልጽ ይመሰክራሉ፡፡ ዐብይ አህመድ ኦነጋዊ ነው ማለት ደግሞ ፀራማራ (ስለሆነም ፀረጦቢያ) ነው ማለት ነው፣ የኦነግ አሌፍና ፓሌፍ (alpha and omega) ፀራማራነት ነውና፡፡ የዐብይ አህመድ ፀራማራነት ቁልጭ ብሎ የወጣው ደግሞ በሰኔ 15ቱ የባሕር ዳር ጭፍጨፋና ይህን ጭፍጨፋ ተከትሎ በሚፈጽማቸው እኩይ ድርጊቶቹ ነው፡፡

ስለዚህም ዐብይ አህመድ አንደበቱና ድርጊቱ አለመጣጣም ብቻ ሳይሆን ፍጹም የሚቃረኑ (ለቋንቋየ ይቅርታ ይደረግልኝና) ሞላጫ ወይም ቀጣፊ ነው፡፡ እንዳብዛኞቹ ቀጣፊወች ግን አይደለም፡፡ ዐብይ አህመድ ቅጥፈቱን ሚሊዮኖችን ለማሳመን ልዩ ችሎታ ያለው የቅጥፈት ሊቅ (master liar) ወይም ምርጥ ቀጣፊ ነው፡፡

ዐብይ አህመድ አሊ የኦነጉ ኦቦ
ሲዋሽ የማያፍር ዓይኑን በጨው አጥቦ፡፡
አጼ ምኒሊክን በክብር እያነሳ
በቁማችን ሸጠን ሎቦ ዳውድ ኢብሳ፡፡
አንዴ ቢሸውደን የሱ ነው እፍረቱ
ሁለቴ ቢደግም የኛ ነው ጥፋቱ፡፡

በዐብይ አህመድ ደረጃ የቅጥፈት ሊቅ ለመሆን ከልዩ ተሰጥኦ በተጨማሪ ልዩ ችሎታ ይጠይቃል፡፡ በተለይም ደግሞ ስለሚቀጥፉት ጉዳይ ማራኪ ትርክቶችንና ጥቅሶችን ማወቅን፣ ስለሚቀጠፈው ሕዝብ ምንነትና ማንነት ደግሞ በጥልቅ መረዳትን ይጠይቃል፡፡ በተጨማሪ ደግሞ አንደበተ ርቱዕ መሆን የግድ ያስፈልጋል፡፡ ኤዶልፍ ሂትለር (Adolf Hitler) እንዳለው ዓለም የሚገዛው በተጻፈው ሳይሆን በተሰበከው ነው (men are won less by the written than by the spoken)፡፡

የቅጥፈት ሊቅ ለመሆን ሲባል የተቀጣፊውን ሕዝብ ምንነትና ማንነት በጥልቀ ለመረዳት፣ አንደበታዊ ተሰጥዖን ለማዳበርና፣ አሳማኝ ትርክቶችን ለመፍጠር የሚደረግ ያላሰለሰ ጥረት ስነቅጥፈት ወይም ቅጥፈትሲን ሊባል ይችላል፡፡ ኤዶልፍ ሂትለር (Adolf Hitler)፣ ቤኒቶ ሙሶሊኒ (Benito Mussolini)፣ ዊንስተን ቸርችል (Winston Churchill)፣ ሮናልድ ሬገን (Ronald Reagan) ካለማችን እውቅ የቅጥፈት ሊቆች ውስጥ ጥቂቶቹ ነበሩ፡፡ ዐብይ አህመድ ደግሞ በጦቢያ ታሪክ ወደር የሌለው ዘረኛ የቅጥፈት ሊቅ (ቅጥፈትሲነኛ) ነው፡፡

• ዐብይ አህመድ የኅሊና እስረኞችን የፈታው፣ የኅሊና እስርን ስለሚቃውም ነው ወይስ ሀገር ወዳድ ጦቢያውያንን በማታለል ትንሽ ሰጥቶ ብዙ ለመውሰድ? በመቃወም ቢሆን ኖሮ በአብን እና በባላደራ ላይ የሚፈጸመውን አፈሳ ምን አመጣው?
• ዐብይ አህመድ ሚዲያን ነጻ ያደረገው በሚዲያ ነጻነት ስለሚያምን ነው ወይስ ኦነጋዊ ሚዲያወች (OMN, OBN, LTV ወዘተ.) እስከሚጠናከሩ ድረስ ዓይን ውስጥ ላለመግባት? በሚዲያ ነጻነት የሚያምን ቢሆን ኖሮ አስራት ሚዲያን የሚያፍነው፣ ሰናይ ሚዲያ እንዳይቋቋም የሚያሰናክለው ለምንድን ነው?
• ዐብይ አህመድ ተቃዋሚወችን ወደ ሀገር ግቡ ያለው በሰላማዊ ትግል ስለሚያምን ነው ወይስ ኦነጋውያንን አሰባስቦ ለማጠናከር? በሰላማዊ ትግል የሚያምን ቢሆን ኖሮ፣ ጃዋርን እያቀማጠለ እስክንድርን የሚያጎሳቁለው፣ ኦነግን እያጠናከረ አብንን የሚያዳክመው ለምንድን ነው?
• ዐብይ አህመድ በመጀመርያወቹ ጥቂት ወራቶች ያደረገው ወያኔ እስከሚደላደል ድረስ በመጀመርያወቹ ጥቂት ዓመታት ካደረገው በምን ይለያል? መንግስቱ ኃይለማርያምና መለስ ዜናዊ ገድለው ለቅሶ ይደርሳሉ፣ ባህል ነው፡፡ ዐብይ አህመድ ደግሞ ገድሎ ችግኝ ይተክላል፣ ለውጥ ነው፡፡ የባህል ለውጥ፡፡

በዋርካ ያሾፈ እንዳብይ ማን አለ?
አውኳል በማለት ኦዳ እየከለለ
ከንቀቱ ብዛት ኮርቶ እየሸለለ
ምሣር እንኳን ሳይል በሜንጫ እንደጣለ፣
መታሰቢያ ብሎ ባሕርዛፍ ተከለ፡፡

 

ዶክተር፣ ጠቅላይ ሚኒስትር?

በኔ አመለካከት ዐብይ አህመድ ዲባቶ (doctor) ወይም የጦቢያ ጠቅላይ ሚኒስቴር (ጠሚር) መባል የለበትም፡፡ ዲባቶ (ዲ/ቶ) ሊባል የማይችልበት ምክኒያት፣ የወያኔን ተቃዋሚወች 24/7 ሲሰልልና ሲያሰልል የኖረ ግለሰብ ከገንዘብ መንገድ ውጭ በሌላ መንገድ ዲባቶ መሆን ስለማይችል ነው፡፡ በዚህ ረገድ ደግሞ እነ ወርቅነህ ገበየሁን የመሳሰሉት አብዛኞቹ ዶክተር ተብየ የወያኔ ሹማምንቶች የዐብይ አህመድ ቢጤዌች ናቸው፡፡ የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው ለዲባቶነት አይሠራም፡፡ ዋናው ቁምነገር ግን ዲባቶ መሆን አለመሆን ሳይሆን ተግባር ነው፣ ትምህርት የግብ ማሳለጫ እንጅ በራሱ ግብ አይደለም፡፡ ባቋራጭ በተገኘ ጉላፕ (degree) መኮፈስ ደግሞ ግብዝነት ነው፡፡

ዐብይ አህመድ በጦቢያ ሕዝብ ቢመረጥ ኖሮ፣ የኔ ምርጫ ባይሆንም የሰፊውን ሕዝብ ድምጽ በማክበር ብቻ ጠሚር ማለት ግዴታየ ይሆን ነበር፡፡ ዐብይን የመረጠው ኢህአዴግ የሚባለው ወያኔና ሎሌወቹ የተሰባሰቡበት ድርጅት ነው፡፡ ወያኔን ለማስወገድ ደግሞ እልፍ አእላፍ ጦቢያውያን (በተለይም ደግሞ አማሮች) ተሰውተዋል፡፡ ስለዚህም ዐብይን ጠሚር ማለት፣ ወያኔን ሲፋለሙ በወደቁ ጀግኖች መሳለቅ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ግለሰብ መባል ያለበት (እንደሚመስለኝም እሱም ራሱ የሚመርጠው) ኦቦ እንጅ ጠሚር አይደለም፡፡ ጠሚር መባል ካለበት ደግሞ የኦነግ ጠሚር እንጅ የጦቢያ ጠሚር አይደለም፡፡ ጦቢያዊውን እስክንድር ነጋን ያለ ጥፋቱ እያጎሳቆለ፣ አሜሪቃዊውን አሸባሪ ጃዋር ሙሐመድን የሚያቀማጥል የዐብይ አህመድ አስተዳደር ኦነጋዊ እንጅ ጦቢያዊ ሊሆን አይችልም፡፡

ጉዱ የሚያስገድደው ጉደኛ?

አብዛኛውን ጊዜ እንድ ግለሰብ አንድን ነገር ከመጠን በላይ የሚያወግዘው ያንን ነገር ለማድረግ ወይም ለመሆን ስለሚፈለግ ወይም ደግሞ ያንን ነገር ማድረጉን ወይም መሆኑን ለመደበቅ ስለሚጣጣር ነው፡፡ ስለ ሰላምና ስለ ፍቅር አውርቶ የማይታክተው ዐብይ አህመድ፣ የሰላምና የፍቅር ቀንደኛ ጠላት ስለሆነ ይሆናል፡፡ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ መግደል መሸነፍ ነው የሚለው ዐብይ አህመድ፣ ማሸነፍ መግደል ነው በሚል መርሕ የሚመራ ደም ጠማሽ ስለሆነ ይሆናል፡፡ አባቱን ስማችውን ሳይጠቅስ እናቱን አለመጥን የሚያሞግሰው ዐብይ አህመድ በናቱ ምንነት አለመጥን ስለሚያፍር ይሆናል፡፡ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የብቸነት ኑሮ ትገፋ የነበረቸውን እማወራ (single mother) ሚስቱን አለመጠን የሚክባት ደግሞ በጓዳ የሚያዋርዳት የቤት ቀጋ የውጭ አልጋ ስለሆነ ይሆናል፡፡

በልጅነቱ ጫካ ገብቶ እድሜ ልኩን ወያኔን በታማኝ ሎሌነት ያገለገለው አብይ አህመድ የደበቀው ነውር ወይም ጉድ ሊኖረው ይችላል፣ አለው ተብሎም ይጠረጠራል፡፡ አንዳንዶቹ የዐብይ ድርጊቶችና ሹሞች ደግሞ ይህን ጥርጣሬ የሚያጠናክሩ ናቸው፡፡ ጥርጣሬው እውነት ከሆነ ደግሞ፣ ነውሩን ወይም ጉዱን የሚያውቁና መረጃ ያላቸው ሰወች በመረጃቸው እያስፈራሩት (black mail) አድርግ ያሉትን ሁሉ እንዲያደርግ ሊያስገድዱት ይችላሉ፡፡ ዐብይ አህመድ ጃዋርን አለቅጥ የሚፈራው፣ ለማ መገርሳን ደግሞ ‹‹የቀድሞ የግልጽ ያሁን የስውር አለቃየ›› እያለ አለቅጥ የሚሽቆጠቆጥለት ወዶ ሳይሆን ተገዶ ሊሆን ይችላል፡፡ ጃዋር ሙሐመድ ያገኘውን ክፍተት የሚበረግድ ወንበዴ ሲሆን፣ ለማ መገርሳ ደግሞ ባገኘው ቀዳዳ የሚገባ ሸለመጥማጥ ነው፡፡

አስተሳሰበ ድውይ

ስልጣን መያዝ ከባድ ቢሆንም፣ በያዙት ስልጣን መቆየት ግን የበለጠ ከባድ ነው፡፡ እርካብና መንበር የተሰኘው መጽሐፉ በግልጽ እንደሚያሳየው፣ የዐብይ አህመድ ሂወት ሙሉ በሙሉ የሚሽከረከረው የስልጣን አራራውን በማርካት ዙርያ ነው፡፡ ስልጣን ለማግኘት የማያደርገው የለም፡፡ በስልጣን እርካብ ላይ እንዴት እንደሚወጣጣ በደንብ እንደሚያውቅ በተግባር አሳይቷል፡፡ የበለጠ ከባድ ስለሆነው የስልጣን እድሜን ስለማራዘም ግን ፍንጭ እንኳን ያለው አይመስልም፡፡

ለዐብይ አህመድ ስልጣን ይጠቅም የነበረው በነቂስ የደገፈውን አማራን ይበልጥ አጠናክሮ፣ ግማሽ አማራ በመሆኑ በማንነቱ የሚጠራጠረውን ኦሮሞን እንዲቆጣጠርለት ማድረግ ነበር፡፡ በተቃራኒው ግን ላይጠራጠሩት የማይችሉትን ኦሮሞወች እንዳይጠራጠሩት በማሰብ አማራን ጨፍጭፎ ባማራ በመተፋት ከሁለት ያጣ ጎመን ሆነ፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ በኦሮሞወች ዘንድ ሙሉ ተቀባይነት ያለውን መሠሪ ግለሰብ (ለማ መገርሳን) ከቁልፍ ቦታ ላይ አስቀመጠ፡፡ ይህ ሁሉ የሚያመላክተው፣ የዐብይ አህመድ ቀሪ የስልጣን ዘመን በወራት እንጅ ባመታት የሚገለጽ አለመሆኑን ነው፡፡

ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆነው በውስጥም በውጭም የሚኖረው ጦቢያዊ ሊያመልከው እየዳዳው እንደ መሲህ ወይም ሙሴ ሲመለከተው፣ ይህን እልፍ አእላፍ ሕዝብ ባንድነት እየመራ የጎጠኝነትን ወንዝ አሻግሮ ወደ ቃልኪዳን ምድር በማስገባት ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ መጎናጸፍ ሲችል፣ ጥቂት የኦሮሞ ጽንፈኞችን ለማስደሰት ሲል ብቻ ራሱን በራሱ አዋረደ፡፡ ደረቱን ለጥይት ሊሰጥለት ዝግጁ የነበረው ሰፊ ሕዝብ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ድምጹን ላይሰጠው ወሰነ፡፡ በመልዐክ እንዳልተመሰለ፣ የሰይጣን ተምሳሌት ሆነ፡፡ በውሸት ትርክት ሳይሆን በእውነተኛ ታሪክ ተክኖ ቢሆን ኖሮ ለዚህ ሁሉ ቅሌት ባልተዳረገ ነበር፡፡
• ሙሉው ከክፍሎቹ ድምር ይበልጣል (the whole is greater than the sum of its parts)፡፡ ትንሽን ከማተለቅ ትልቅን በዚያው መጠን ማተለቅ ይቀላል፡፡ አንድ ሺ ብርን ሁለት ሺ ከማድረግ፣ አንድ ሚሊዮንን ሁለት ሚሊዮን ማድረግ ያነሰ ጥረት ይጠይቃል፡፡ የመቶ ክሮች ጥንካሬ ያንድን ክር ጥንካሬ ከመቶ ጊዜ በላይ ይበልጣል፡፡ ጎጠኞች የማይገነዘቡት ይህንን መሠረታዊ ሐቅ ነው፡፡

ጎጠኛ ማይም ነው ደንቆሮ የማያቅ
ከክፍሎቹ ድምር ሙሉው እንደሚልቅ፡፡
አንድ ክር ብቻውን አንድ ዐይጥ ካነሳ
መቶ ክር ቢሾረብ ያነሳል አንበሳ፡፡

• አጼ ቴድሮስ የተነሱት ያጎቴ የራስ ኃይሉ ግዛት (ቋራ) ይገባኛል ብለው እንጅ ጦቢያን አንድ ለማድረግ አስበው አይመስለኝም፡፡ የእቴጌ ምንትዋብን የጦር መሪ የደጃች ወንድይራድን ታላቅ ሠራዊት በታናሽ ጦር ድል ሲነሱት ግን የቋራ ብቻ ሳይሆን የድፍን ጦቢያ በር ወለል ብሎ ተከፈተላቸው፡፡ ያጼ ቴድሮስ ታላቅነት ደግሞ በሩ ወለል ብሎ መከፈቱን መገንዘባቸውና እድሉን መጠቀማቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ የታላላቅ ሰወች ልዩ ጠባይ ነው፡፡ አጼ ቴድሮስ ለትልቅ ሥራ የታጩ ታላቅ ሰው ባይሆኑ ኖሮ፣ ደጃች ወንድይራድን ድል ካደረጉ በኋላ በቋራ ዙርያ ያሉትን ሰፋፊ ግዛቶች ወደ ቋራ በማጠቃለል በቋረኞች እየተሞገሱና እየተወደሱ በመንደላቀቅ እድሜ ልካቸውን ይገዙ ነበር፡፡ እሳቸው ግን ለትልቅ ተልዕኮ የተመረጡ ትልቅ ሰው መሆናቸውን ስለሚያቁና በጽኑ ስለሚያምኑበት፣ በትንሿ ቋራ ተወሰነው ከሚንደላቀቁ በትልቋ ጦቢያ መማቀቅን መረጡ፡፡ ባጸደ ሥጋ ተጎሳቁለው፣ ባጸደ ነፍስ ተቀማጠሉ፡፡

• ናፖሊዮን ቦናፓርት ግብጽ ላይ በፈጸመው ወታደራዊ ጀብዱ በመላ ፈረንሳውያን የሚወደድ ጀግና ቢሆንም፣ ኮርሲካን ለመገንጠል የተነሳ ኮርሲካዊ ጎጠኛ ነበር፡፡ የፈረንሳይ አብዮት ያስከተለው ትርምስ ግን የኮርሲካን ብቻ ሳይሆን የመላዋን ፈረንሳይን ዕጣ የሚወስንበትን እድል ሰጠው፡፡ ታላቁ ናፖሊዮንም እድሉን በመጠቀም ጎጠኛነቱን እርግፍ አድርጎ ትቶ ፈረንሳይን ትልቅ በማድረግ ኮርሲካንም ትልቅ ለማድረግ ተነሳሳ፡፡ የኮርሲካ ብቻ ሳይሆን የመላ ፈረንሳይ ብሎም የዓለማችን ድንቅ ሰው ሆነ፡፡

• የኦዴፓ መሥራች መለሰ ዜናዊ በትክክል እንዳስቀመጠው ኦፒዲኦ ሲፉቁት ኦነግ ነው፡፡ የኦነግ አላማ ደግሞ በጦቢያ ፍርስራሽ ላይ የኦሮሚያን አጼጌ (empire) መገንባት ነው፡፡ እስካለፈው ዓመት ድረስ የሻቢያ መንገድ ጠራጊ የነበረው ‹‹ውጫዊው›› ኦነግ ደግሞ ጦቢያን አፍርሶ የኦሮሚያን አጼጌ \ሊመሠርት\ ቀርቶ አንድ መንደር እንኳን ሊቆጣጠር የማይችል ሙትቻ መሆኑ ግልጽ ነበር፡፡ ስለዚህም ‹‹ቲም ለማ›› የሚሰኘው ‹‹ውስጣዊ ኦነግ›› (በተለይም ደግሞ ለማ መገርሳና ዐብይ አህመድ) አዲስ እቅድ አወጣ፡፡ ይህም ዘዴ ጦቢያውያንን ሊሰሙት የሚቋምጡትን ትርክት እየተረከቱ በማታለል ገደል ጥሎ ያለ ምንም መስዋእትነት (በኦነግ በኩል ማለቴ ነው) የኦሮሚያን አጼጌ መመሥረት ነው፡፡ ይህ አዲስ እቅድ ደግሞ በሚያስደንቅ ፍጥነት ተሳክቶላቸው የኦሮሚያን ብቻ ሳይሆን የመላዋን ጦቢያን ዕጣ መወሰን የሚችልበትን አጋጣሚ ላብይ አህመድ ፈጠረለት፡፡ አብይ አህመድ ግን ለትልቅ ሥራ የተፈጠረ ትልቅ ሰው ስላልሆነ፣ ጎጠኝነቱን ሙጥኝ ብሎ ኦሮሙማ ላይ ሲርመጠመጥ አጋጣሚው አመለጠው፡፡ አገር ወዳድ ጦቢያውያንም አታለይነቱን ነቁበትና መቸም ላይመልሱ ፊታቸውን አዞሩበት፡፡ ጦቢያውያንን በሙሉ ከፍ ማድረግ ሲችል፣ አልሮሞወችን (non-oromos) ጥየ ኦሮሞወችን ብቻ ከፍ አደርጋለሁ በማለት ዜሮ ድምር ጨዋታ (zero sum game) ለመጫወት ሲፈልግ የጨዋታ ሜዳው ተቆፋፈረበት፡፡ የአልኦሮሞወችን ብቻ ሳይሆን የኦሮሞወችንም መቃብር የሚቆፍር ይዞ ሟች ሆነ፡፡

 

ዐብይና አዴፓ

ዐብይ አህመድ አንደ ዳግማዊ ቴድሮስና ቀዳማዊ ናፖሊዮን ትልቁ ስዕል የማይታየው አስተሳሰበ ድውይ ከመሆኑ በተጨማሪ ያመኑትን በደንደስ የሚጥል እኩይ ፈረስ መሆኑን በብአዴን (አዴፓ) ላይ የፈጸመው እኩይ ድርጊት በግልጽ ይመሰክራል፡፡ ጃዋር ሙሐመድና ተከታዮቹ እንደሚቦፍፉት ወያኔን በመሻር አብይ አህመድን ለመሾም ያንበሳውን ሚና የተጫወተው ቄሮ የሚባለው ባስለቃሽ ጢስ በርግጎ ገደል የሚገባው የውርጋጦች መንጋ አይደለም፡፡ ቄሮ ግርግር የሚፈጥር ግብታዊ መንጋ እንጅ ለውጥ የሚያመጣ ስርዓታዊ ድርጅት አይደለም፣ ሊሆንም አይችልም፡፡ በተማሪወች ግርግር ንጉሱ ሲወርዱ በቦታቸው የተተካው የራሳቸው ወታደር (ደርግ) እንደነበር ሁሉ፣ የቄሮ ግርግር ቢቀጥል ኖሮ የመጨረሻ ውጤቱ በሳሞራ ዩኑስ የሚመራ አምባገነን መንግስት ነበር፡፡ የጌታቸው አሰፋ እቅድም ይሄው ነበር፣ ገዱ አንዳርጋቸው አከሸፈበት እንጅ፡፡ በነገራቸን ላይ የኦሮሞ ወጣቶች እንዳይታሰሩ ያማራው ፕሬዚደንት ገዱ አንዳርጋቸው ከጌታቸው አሰፋ ጋር ሲተናነቅ፣ የኦሮሚያ ፕሬዚደንት ለማ መገርሳ ግን እንደ ባይተዋር ይመለከት ነበር፡፡ በቁርጥ ቀን ለኦሮሞ የቆመው ብአዴን አንጅ ኦፒዲኦ አልነበረም፡፡

ዐብይ አህመድን ለስልጣን ያበቃው ባገር ወዳድ ጦቢያውያን መራራ ትግል ጦቢያ ጦቢያ መሽተት የጀመረው ብአዴን (አዴፓ) ነው፡፡ ከስልጣን የሚያወርደውም (ለማ መገርሳ ካልቀደመው በስተቀር) ለጦቢያዊነት ሽንጡን ገትሮ የሚከራከር (ስለሆነም ከአብን ጋር የሚተባበር) አብናዊ አዴፓ ነው፡፡ ራሱ ዐብይ አህመድ ያማራ ብሔርተኝነት ያሰጋኛል ያለውም ይህን ሐቅ ስለተረዳ ነው፡፡ በአዴፓ ውስጥ በሰገሰጋቸው ሎሌወቹ አማካኝነት አብናዊ አዴፓወችን እያገሸሸ የግንቦት ሰባት ርዝራዥ የሆኑትን ኦነጋዊ አዴፓወችን (ተመስገን ጡሩነህ፣ ንጉሱ ጥላሁን፣ አበረ አዳሙ ወዘተ.) ወደ ግንባር የሚያመጣው ደግሞ ይህን ስጋቱን ለመቅረፍ ነው፡፡

ዐብይ አህመድ ባኳኋኑም በምግባሩም የሚመሳሰለው ከኢንተራሃምዌው መሪ ከሃብያሪማና (Juvenal Habyarimana) ጋር ነው፡፡ እኔን ትነኩና መቶ ሺወች ባንድ ጀንበር ይታረዳሉ ማለቱ ደግሞ ምስስሉን ይበልጥ ያጠነክረዋል፡፡ ላማራ ሕዝብ አሁን የሚያስፈልገው የዐብይን መቶ ሺወች ይታረዳሉ ዛቻ ቅንጣት የማይፈራ አማራዊ ጳውሎስ ካጋሜ (Paul Kagame) ነው፡፡ ደመቀ መኮንን ቦታውን ላብይ አህመድ የለቀቀው ዐብይ አህመድ ለጦቢያ ይበጃል ብሎ በማሰብ ከሆነ፣ የማይበጅ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ ለሚበጀው ላማራዊ ጳውሎስ ካጋሜ ሊለቅ ይገባል፡፡

ኦነጋዊ ግማሽ አማሮች

አብዛኞቻችን አገር ወዳድ ጦቢያውያን በኢተስፋ ላይ በመተሰፍ (hope against hope) የዐብይ እናት አልኦሮሞ (non-oromo) መሆን የዐብይን የኦሮሞ ጎጠኝነት ስሜት ያለዝበዋል የሚል እምነት ነበረን፡፡ ታሪክ የሚመሰክረው ግን የዚህን ተቃራኒ ነው፡፡ በብሔር አባልነት የሚጠረጠሩ ግለሰቦች በብሔርተኝነት ከተለከፉ የብሔሩ አባል መሆናቸውን ለማስመስከር ሲሉ ብቻ የማያደርጉት የለም፡፡ ሂትለር ይሁዳወችን ያለ ርኅራኄ የጨፈጨፈበት አንዱ ምክኒያት የይሁዳ ደም አለበት የሚባለውን ጭምጭምታ ለማስተባበል ነበር፡፡ ጌታቸው አሰፋን ጌታቸው አሰፋ ያደረገው ያባቱ አማራነት ነው፡፡ ዐብይ አህመድ ደግሞ ግማሽ ካማራ ከመሆኑ በተጨማሪ ካማራ ጋር የተጋባ በመሆኑ፣ ፀራማራ ልሁን ካለ ፀራማራነቱ ከጌታቸው አሰፋ ቢብስ እንጅ አያንስም፡፡

ዐብይ አህመድ፣ ፀጋየ አራርሳና የመሳሰሉት ግማሽ አማራ የኦሮሞ ጎጠኞች በኦሮሞነታቸው ስለሚጠረጠሩ፣ ባይነ ቁራኛ እንደሚጠበቁና እያንዳንዷ ድርጊታቸው በጢኖፓይፋ (microscope) እንደምትመረመር አሳምረው ያውቃሉ፡፡ ትንሽ ቢሳሳቱ ግዙፍ ውለታቸው መና ቀርቶ ከሃዲወች እንደሚባሉ ነጋሪ አያስፈልጋቸውም፡፡ እስከጣፈጡ ድረስ ተላምጠው የሚተፉ አገዳወች እንደሆኑ በደንብ ያውቃሉ፡፡ ስለዚህም እነዚህ ግማሽ ኦሮሞወች ለኦሮሞ ጥቅም ሽንጣቸውን ገትረው የቆሙ መሆናቸው ጥርጣሬ ውስጥ እንዳይገባ ሲሉ ብቻ ከኦሮሞወች የጸነፉ ጽንፈኞች መሆን አለባቸው፡፡ ከለማበት የተጋባት፡፡

ዐብይ አህመድ ለኦነግ ዓላማ መሳካት ሲል ማናቸውንም ጭራቃዊ ድርጊት ለማድረግ ቅንጣት እንደማያቅማማ በባሕርዳር ድርጊቱ በግልጽ ቢያሳይም፣ ግማሽ ኦሮሞ በመሆኑ ብቻ ኦነጋውያን መቸም ቢሆን በሙሉ ልብ አያምኑትም፡፡ ስለዚህም ኦነጋውያን ትናንት ከሚያምኑት የበለጠ ዛሬ እንዲያምኑት ከፈለገ ትናንት ካደረገው የከፋ ዛሬ ማድረግ አለበት፡፡ ስለዚህም አገር ወዳድ ጦቢያውያንን (በተለይም ደግሞ አማሮችን) በተመለከተ የበለጠ እና የበለጠ ጭራቅ እየሆነ ይሄዳል፡፡ ባጭሩ ለመናገር ዐብይ አህመድ በማንነቱ ምክኒያት እኩይ አዟሪት (vicious circle) ውስጥ የገባ የኦነግ አውሬ ነው፡፡ ካዟሪቱ ነጻ የሚያወጣው ሞቱ ብቻ ነው፡፡ ሌሎቹ ግማሽ ኦሮሞ ኦነጋውያንም እንዲሁ፡፡

ሌላ ምሳሌ ለመስጠት ያህል የቡርቃ ዝምታን ምንነት በትክክል የተረዳውን ወያኔን ለረዥም ጊዜ ያገለገለውን አዲሱ አረጋን እንውሰድ፡፡ የቡርቃ ዝምታ ማለት አማራንና ኦሮሞን እሳትና ጭድ በማድረግ የከፋፍለህ ግዛው ዘመኑን ለማራዘም ወያኔ የቀመመው የውሸት ትርክት ማለት ነው፡፡ የትርክቱ ውሸትነት በኦፒዲኦ አባል በግልጽ ተነገረ ማለት ደግሞ የኦነግ የውሸት ትርክት የማዕዘን ዲንጋይ የሆነው አኖሌ ፈረሰ ማለት ነው፡፡ አኖሌ ፈረሰ ማለት ደግሞ የኦነግ ትርክት ሙሉ በሙሉ ተንኮታኮተ ማለት ነው፡፡ የኦነግ የውሸት ትርክት ተንኮታኮተ ማለት ደግሞ የኦነጋውያን እንጀራ ተዘጋ ማለት ነው፡፡

እንጅራቸው /ሊዘጋ/ በመሆኑ ክፉኛ የተደናገጡት ኦነጋውያን አዲሱ አረጋን ከፉኛ በማስደንገጥ ተንበርክኮ ይቅርታ እንዲጠይቅ አስገደዱት፡፡ ይቅርታ መጠየቁ ስላላረካቸው ደግሞ በማንነቱ ላይ መጡበት፡፡ አዲሱ አረጋ ደግሞ በማንነቱ ሊጠረጠር እንደማይገባ ለማሳየት ሲል ብቻ የጽንፈኞች ጽንፈኛ ለመምሰል ሞከረ፡፡ ስለዚህም አዲሱ አረጋ ሐቁን ባወጣ የተቀጣ፣ መናገር ያልፈለገውን እንዲናገር የተገደደ፣ ሊታዘንለት እንጅ ሊታዘንበት የማይገባ የኦነግ እስረኛ ነው፡፡ ከኦነግ እስር ተፈትቶ ቀን ሲወጣለት፣ የኦሮሞ ጽንፈኞችን ለማስደሰት ሲል ብቻ የበለጠ ጽንፈኛ በመምሰል ካንገት በላይ የዘለፈውን እስክንድርን ከልቡ ያወድሰዋል፡፡ የዚያ ሰው ይበለን፡፡

 

መስፍን አረጋ
mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic