>
5:18 pm - Sunday June 15, 0859

የአንዳርጋቸው ጽጌ ነገር. . . (አቻምየለህ ታምሩ)

የአንዳርጋቸው ጽጌ ነገር. . .
አቻምየለህ ታምሩ
አንዳርጋቸው ጽጌ በትናንትናው እለት ከአባይ ሜዲያ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ነው ያለውን «የዘር ፖለቲካ» ሲያወግዝ ሰምተነዋል። ይገርማ! ነገሩ ጅብ በማያውቁት አገር ሄዶ ቆርበት አንጥፉልኝ ይላል አይነት ሆነብኝ። የኢትዮጵያን ፖለቲካ የዘር ፖለቲካ በማድረግ ከበከሉት ተውሳኮችና ጸረ አማራ ፖለቲካን በሁለት እግሩ እንዲቆም ካደረጉት የ ያ ትውልድ አባላት  መካከል  በግንባር ቀደምትነት ከሚሰለፉት ሰዎች መካከል አንዳርጋቸው ጽጌ አንዱ ነው። አንዳርጋቸው ጽጌ በ1970 ዓ.ም. ከማንም በፊት የፋኖ ትግል የጀመረው አማራን የማጥፋት አላማ የያዘ «የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ንቅሳቄ» የሚባል ሕወሓት የመሰረተለትን ድርጅት በመምራት ነበር።
ወረድ ብዬ ብዙ ሰው የማያውቀውን የአንዳርጋቸው ጽጌን ጸረ አማራነትና በ1970 ሕወሓት ስለመሰረተለት የኢሕዴንና የብአዴን እናት ድርጅት ታሪክና  አንዳርጋቸው ጽጌ ሌላውን ዘረኛ ብሎ  ጣቱን ወደሌላ  ሊያስጠቁም የሚያስችል  የኋላ ታሪክና ዛሬም ላይ ቢሆን የሞራል ልዕልና  እንደሌለው የሚያስረግጡ እውነታዎችን ማቅረብ እሻለሁ።
አንዳርጋቸው ገና በጧቱ የኢሕአፓ ፋኖ ሆኖ በወያኔ ተማርኮ ወደ ሕወሓት እንደገባ ወያኔዎች ያቋቋሙለትን ጸረ አማራ ድርጅት ይመራ ነበር። በሌላ አነጋገር ወያኔ ኦሕዴድን፣ ብአዴንን፣ ደሕዴንን፣ ወዘተ ሳይመሰርት ለመሰሪ አላማው ድርጅት ያቋቋመው ለአንዳርጋቸው ጽጌ ነበር። አንዳርጋቸው ጽጌ ከአንድ አመት ተኩል በላይ ወያኔ ባስቀረጸለት ማሕተምና በሰጠው ቢሮ እየኖረ አድዋ ውስጥ ከአንድ አመት ተኩል በላይ የመራው ወያኔ ያቋቋመለት ድርጅት «የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ንቅሳቄ» ይባል ነበር።
ይህ በአንዳርጋቸው ጽጌ ይመራ የነበረው የሕወሓት ድርጅት የሕወሓትን ጸረ አማራ የፖለቲካ ፕሮግራም ቃል በቃል ፕሮግራሙ በማድረግ የተመሰረተ ሲሆን ወያኔ ይህን ድርጅት አቋቁሞ አንዳርጋቸውን መሪ ያደረገው ለመሀል አገሩ ትግል በመሳሪያነት ሊጠቀምበት ነበር። አንዳርጋቸው ጽጌ በኢሳት ሎንዶን ስቱዲዮ ከወንድማገኝ ጋሹ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ የትግሬዎችን ደግነት ሲያወራ ትግራይ ከወያኔ ጋር ሲታገል «ተቅማጥ ታምሜ በነበረበት ወቅት መጸዳዳች አልችል ብዬ በሰገራየ ላይ ስወድቅ አንድ የትግራይ ልጅ ሰገራየን ጠረገልኝ» ሲል ያወሳው ታሪክ ሕወሓት ያቋቋመለትን የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ንቅሳቄ ሲመራ በነበረበት ሰዓት ያጋጠመውን ነበር። ሰገራየን ጠረገልኝ ያለው ወጣትም ሕወሓት የመደበልትን ሰላይ ነበር።
አንዳርጋቸው ጽጌ ድርጅቱን አንድ አመት ተኩል ከመራ በኋላ ወደ ሱዳን ሄዶ ሳይመለስ በመቅረቱ አንድ አመት ያህል ከጠበቁት በኋላ ሌላ ሰዎችን አሰባስበው አንዳርጋቸው ይመራው የነበረውን «የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ንቅሳቄ» እንዲረከቡ አደረጉ። ይህ የሆነው በ1973 ዓ.ም. ነው። በዚህ መሰረት በ1973 ዓ.ም. አንዳርጋቸው ጽጌ ይመራው የነበረውን «የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ንቅሳቄ» በድርጅቱ ስም ላይ የአንድ ቃል ለውጥ በማድረግ ማለትም «አብዮታዊ» የምትለዋን ቃል «ዲሞክራሲያዊ» በሚል ቀይረው «የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ [ኢሕዴን] ወይንም የዛሬውን ብአዴን በነ በረከት ሰምዖን ፊት አውራሪነት እንደገና እንዲቋቋምና የአንዳርጋቸው ጽጌው «የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ንቅሳቄ» የተፈጠረለትን አላማ ይዞ የወያኔን ጸረ አማራ ፕሮግራም ወደ ተግባር እንዲያወርድ ተደረገ።
ይህ ከሆነ ከአስር አመታት በኋላ አንዳርጋቸው ጽጌ በ1983 ዓ.ም. ወያኔ አዲስ አበባ ሲገባ ከሚኖርበት ሎንዶን ተነስቶ ወደ አዲስ አበባ በማቅናት ኢሕዴንን የተቀላቀለው እንደ አዲስ ድርጅት ሳይሆን ከጅምሩ ሲመራውና ወደ ነበረውና ጥሎት ወደሄደው እናት ድርጅቱ ተመልሶ እንዲገባ ግብዣ ቀርቦለት ነው። አንዳርጋቸው ጽጌ ብአዴን ውስጥ የገባው በዘር ፖለቲካ ስለሚያምን ነው።  ምንም  እንኳ ቁም ነገር  ባይሆንም  አንዳርጋቸው ጽጌ የአማራ ድርጅት ውስጥ የገባው ግን  እህቱ እንደነገረችን ዘሩ አማራ ሳይሆን ነው። የአንዳርጋቸው ጽጌ እህት ወ/ሮ ብዙአየሁ ፅጌ ከሶስት ዓመት በፊት «ለውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ»  በሚፍ በጻፉት ማስታወሻ  ስነ አንዳርጋቸው የሚከተለውን ጽፈው ነበር፤ «አንዳርጋቸው የቤተሰባችን የመጀመረያ ወንድ ልጅ ስለነበረ ብርቅዬ መሆን  የጀመረው የካቲት 1 ቀን 1947 ዓ.ም አዲስ አበባ በሚገኘው ቀዳማዊ  ኃይለ ስላሴ ሆስፒታል ከእናታችን ከወ/ሮ አልታዬ ተሰማ  ሮቢ እና ከአባታችን ከአቶ ፅጌ  ሀብተማርያም ጨሜሳ ከተወለደ ቀን ጀምሮ ነው።»  ይህ የእህቱ ምስክርነት ነው። እንደሚታወቀው  ባገራችን ዘረኞች መስፈር ዘር  የሚቆጠረው ባባት ነው። በዚህ መስፈር ነው እንግዲህ  አባዱላ ገመዳ እናቱ አማራ ሆና የኦሮሞ ድርጅት መሪ የሆነው ዘሩን ባባቱ ቆጥሮ ነው።
እንግዲህ! አንዳርጋቸው ጽጌ ዛሬ ላይ ራሱን ከደሙ ነጻ አድርጎ በሁለት እግሩ ያቆመውን በዘር ላይ ተመሰረተ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የመተቸት የሞራል ልዕልና የለውም። ከአማራ አንጻር መቆም የዘር ፖለቲካ አራማጅ አያደርግም፤ ሰዎች ሲያደርጉት ሐጢያት፤ እሱ ሲያደርገው ግን ጽድቅ ካልተባለ በስተቀር የዘር ፖለቲካን የሚተቸው አንዳርጋቸው ጽጌ ራሱ ያኔ ፋኖ በነበረበት ወቅት ብቻ ሳይሆን ዛሬ ላይም ጭምር ከጸረ አማራ አስተሳሰብ ያልተላቀቀ የዘር ፖለቲካ አራማጅ ነው። ይህን በማስረጃ ማቅረብ እችላለሁ።
አንዳርጋቸው ጽጌ በ1970 ዓ.ም. ሕወሓት ያቋቋመለትን «የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ንቅሳቄ» ሲመራ ይመራበት የነበረው የፖለቲካ ፕሮግራም የምናውቀው ጸረ አማራው የሕወሓት ፕሮግራም ነበር። አንዳርጋቸው ይህንን ሕወሓት ያቋቋመለትን ጸረ አማራ ድርጅት ተለይቶ ለአመታት ሎንዶን ቢቆይም ፋኖ የሆነበት ጸረ አማራ አመለካከቱ ግን አልለቀቀውም ነበር። ወያኔም ጥሪ ያደረገለት የቆየውን ጸረ አማራ አመለካከቱን ስለሚያውቅና ወደ አቋቋሙለት ጸረ አማራ ድርጅት መመለስ እንደሚችል ማረጋገጫ ስለሰጣቸው ነበር። በዚህም መሰረት በ1983 ዓ.ም. ወደ እናት ድርጅቱ የቀድሞው «የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ንቅሳቄ»፤ የኋላው «የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ» እና የአሁኑ ብአዴን ከተመለሰ በኋላ በፋኖነት የታገሉለትን ጸረ አማራ አጀንዳ በመንግሥትነት ከተሰየሙ በኋላ ለማስፈጸም በድርጅቱ ፕሮግራም ጸረ አማራ አቋማቸውን በማስፈርና ይህንንም በማርቀቁ ረገድ በቀዳሚዎቹ የወያኔ ሎሌዎች መካከል አንዱ አንዳርጋቸው ጽጌ ነበር። በዚህ የድርጅቱ ፕሮግራም መግቢያ ላይ እንደሰፈረው ወያኔ «የአማራ ክልል» በሚል ከፈጠረው ክልል ውጭ የሚኖሩ አማሮችን «በአማራ ብሔር ስም የሚነግዱ ነፍጠኛ» ፣ «ትምክህተኞች» እና «ሌሎችን ብሔር፣ ብሔረሰቦች ጨቋኞች» ሲል ይገልጻቸዋል፤ የነ አንዳርጋቸው ጽጌ ድርጅትም እነሱንም እንደማይወክል ይነግረናል።
ባለፉት ሀያ ሰባት የመከራ አመታት በሐረር፣ በኢሉ አባቦራ፣ በመተከል፣ በጅማ፣ በአርሲ፣ በወለጋ፣ በጉራ ፈርዳ፣ወዘተ. . . ይኖሩ የነበሩ አማሮች ቤታቸው እየተቃጠለ፣ ንብረታቸው እየተወረሰ፣ ያለፍርድ እየተገደሉ፣ እጃቸው እየተቆረጠና ቤት ተዘግቶባቸው እየተቃጠሉ እንዲፈናቀሉ ሲደረጉ በአማራ ስም የተቋቋመው ብአዴን ዝም ብሎ ያየውና ሽርጣም እያሉ ይሰድቧችኋል እያለ ሲያስጨፈጨፍና ዝም ብሎ ሲያይ የኖረው እነ አንዳርጋቸው ጽጌ በጻፉት ፕሮግራም እየተመራ ነበር።
የአንዳርጋቸው ጽጌ ጸረ አማራነት በዚህ አያበቃል። ግንቦት ሰባትን ከመሰረተ በኋላም ድርጅቱ በልሳኑ ቁጥር 25 ጥቅምት 27 2001 ዓ.ም. በርዕሰ አንቀጹ የወጣውን ጸረ አማራ አቋም መውሰድ እንችላለን። በዚህ ርዕሰ አንቀጽ ለዘመናት ግንቦት ሰባት ኢትዮጵያን ሲገዛ የኖረው የአማራው ኤሊት ያለውን ካሁን በኋላ ሥልጣኑን ለኦሮሞውና ለደቡቡ ማስረከብ እንዳለበት፤ ድርጁቱም ለዚህ እንደሚታገል ያትታል።ይህን ጸረ አማራና ጸረ ዴሞክራሲ የሆነ የግንቦት ሰባት ርዕሰ አንቀጽ የጻፉት አንዳርጋቸው ጽጌና ሌላ ለጊዜው ስሙጥ መጥቀስ የማልፈግለው ሰው እንደሆነ ባደረግሁት ማጣራት ለማረጋገጥ ችያለሁ። በሌላ አነጋገር የአንዳርጋቸው ጽጌ ግንቦት ሰባት የሚታገለው አማራን ከፖለቲካ ስልጣን ለማግለል ነው ማለት ነው። ሕወሓትም ሆነ የቀድሞው የአንዳርጋቸው ጽጌ ድርጅት «የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ንቅሳቄ» ያደረጉት ይህንን ነበር። አንድ እሳቤ ከአማራ አንጻር ሲሆን ዘረኛነት አይሆንም ካልተባለ በስተቀር ከዚህ በላይ ዘረኛነት ምን ኖሮ ነው አንዳርጋቸው ጽጌ ዛሬ ላይ ሌሎችን በዘረኛነት የሚከሰው?
ምን ይኼ ብቻ! አንዳርጋቸው ጽጌ ከእስር እንደተፈታ በኢሳት ሎንዶን ስቱዲዮ ቀርቦ በሰጠው ቃለ ምልልስ «የሸዋ መንግሥት» ሲል የጠራውን የኢትዮጵያ መንግሥት የአማራ መንግሥት አድርጎ በማቅረብ ወያኔዎች በትግሬነት ተደራጀተው ከመሰረቱት የሕወሓት አገዛዝ ጋር አንድ አይነት አድርጎ በማቅረብ የመንግሥትነት ተራው ለሁሉም እንዲደርሰው ሲል እየተናገረ ነበር። አንዳርጋቸው ጽጌ ከወያኔ በፊት የነበሩትን የኢትዮጵያ መንግሥታት የአማራ መንግሥታት አድርጎ ያቀረባቸው ካሁን በኋላ የሚደረገው ለውጥ ከአማራ አንጻር መሆን እንዳለበት ሲነግረን ነው። በርግጥ ይህ እሳቤ የአንዳርጋቸው ጽጌ እሳቤ ብቻ ሳይሆን የ ያ ትውልድ በሙሉ የግራ ፖለቲካ ትርክት ነው።
ባጭሩ የአማራ ልጆች በአማራነት የተደራጁት አንዳርጋቸው ጽጌና የትውድል አጋሮቹ ባደረጉት ጸረ አማራ የዘረኛነት ትግልና በወለዱት ፖለቲካ የዘር ማጥፋት ሰለባ የሆነውን አማራን ለመከላከል እንጂ እንደነሱ የዘረኛነት ትግል ለማድረግ አይደለም። ስለዚህ አንዳርጋቸው ጽጌ የአማራን ልጆች በአማራነት መደራጀትና መታገል በዘረኛነት ፈርጆ ማውገዙን ማቆም አለበት። ሕሊና ካለው ወደ ውስጥ በመመልከት ከፍ ሲል የዘረዘርሁትንና ያጎነጠውን ጸረ አማራ አቋሙን አስተካክሎ የአማራን ሕዝብ ይቅርታ መጠየቅ አለበት። የእሱ እሳቤ ሰለባ የሆንነውን እኛን ግፉዓንን በዘረኛነት መክሰሱ ነውረኛነት ብቻ ነው።
ከታች የታተመው[ያሰመርሁበት] ሕወሓት የመሰረተለት  «የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ንቅሳቄ» የሚባለው የአንዳርጋቸው ጽጌ ድርጅት ታሪክ  circumstantial evidence ነው። የታተመው ማስረጃ ገብሩ አስራት ከጻፈው «ሉዓላዊነትና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ» መጽሐፍ የተገኘ  ነው።
Filed in: Amharic