>

ውሻ በአጥንት ይጣላል በጅብ ይተባበራል' - እንዳልል - ውሾቹ እንጂ ጅቡ የለም! (ታዬ ቦጋለ አረጋ)

ውሻ በአጥንት ይጣላል በጅብ ይተባበራል’ – እንዳልል – ውሾቹ እንጂ ጅቡ የለም!
ታዬ ቦጋለ አረጋ
መቀሌ መሻጊዎቹ ዘንድ ምሽግ አጠናካሪዎቹ ለምን ጎራ ጎራ ይላሉ?! ከመጋረጃው በስተጀርባ ያለው ምስጢር
 
በርግጥ ማይም ነኝ። በቀለም ብዙም ባልዘልቅም – ከተማሩ ማይማን ላቅ ያለ ኢትዮጵያዊ መቆርቆር  እንዳለኝ ግን ይሰማኛል። 
*
ወደ ጉዳዬ ልግባ፦ ወያኔዎች አርቲስት ኤቢሳ አዱኛን ከነህይወቱ ከመኪና ኋላ አስረው ጎትተውታል። ነቀምት እናት ልጇ አስከሬን ላይ ተቀምጣለች። የጀግኖቹ ምድር አምቦ ለሩብ ክፍለዘመን በልጆቿ ደም ታጥባለች። ኢሬቻ በእቅድ ወገን በአስለቃሽ ጪስ ገደል ገብቶ እንዲሞት ሆኗል። እስር ቤቶች በኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ተሞልተው ነበር። ጨለንቆ ሞያሌ ሻኪሶ ሻሸመኔ ለቀምት… ዜጎች በአግአዚ ስናይፐር ተመትተው ወድቀዋል። በየእስር ቤቱ የደረሰው ሰቆቃ ይህንን ያህላል – ያንን ይመስላል ብሎ ለመግለፅ እጅግ አዳጋች ነው። እውነተኞቹ የኦነግ ታጋዮች “የሳራ በረሀ ምስጢር” የሚል ዶኩመንተሪ የተሠራባቸው በወያኔ ዋጋ ከፈሉ። ህዝቡ እንደ ህዝብ ጠባብ ተባለ። ኦዴፓ – ‘ብትፋቅ ኦነግ ነህ’ የሚል ቅጥያ ተሰጠው። በዚያ ቀውጢ ወቅት ከትግሉ ጎን የቆሙ ሌሎች – ገዳዮቻችን ደግሞ ሌሎች ነበሩ።
*
ይህ ዘመነ ፅልመት ተገፈፈ ብለን አፍታም ሳንቆይ – እርቅ ሳይመሰረት – ደማችን ሳይደርቅ – ኦነግ በአቦይ ስብሓት ነጋ እጅ ተጋብዞ – የጥፋት ቃልኪዳን ተቀብሎ – ለውጡ በጀመረው መልካም ግንኙነታችን ላይ – የጥላቻ ውሀ ቸለሰበት።
*
የሚገርመው ዛሬም መቀሌ በሯን ለጥላቻ አበጋዞች በርግዳ – ታሪክን ማዋረድና ሳትጨርሰው ደደቢት ተራራ ስር አርግዛው የተቀመጠቺውን የሀገር ማፈራረስ ተልዕኮ – እንደ ዳማ ጠጠር በምትገፋቸው – ተሰሪ “ምሁራን” እያስኬደቺው ነው።
‘ዝለሉ’ ስትላቸው – ‘እስከየት?’ የሚሉት ኢወገኖችና አለቆቻቸው – ወደፊት  አጥፊና ጠፊ መሆናቸውን ጠንቅቀው ይተዋወቃሉ። ያጋጠማቸው ፀረ-ኢትዮጵያ ትብብር ነው።
“ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም” እስከ ማለት የዘለቀ ምሁራዊ ድንቁርና!?!
 
 ሲጀመር ጥያቄው በራሱ ለአቅመ ውይይት ባልበቃም ነበር!
ለነገሩ እንሟገት ከተባለ ኢትዮጵያዊ ማንነት የሌላቸው ሚጢጢ ስብዕናዎችና ሌላ ዜግነት የያዙ ግለሰቦች – ‘ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም’ ቢሉ ሊገርመን አይገባም።
*
ሲቀጥል፦ በአገርአቀፍ ፈተና፣ በዓለማቀፍ ፓስፖርት፣ በመታወቂያችን የሚገለፀው ማንነታችንና ከነፍስና ከስጋችን ጋር የተሳሰረው እኛነታችን ኢትዮጵያዊነት ነው።
*
ሲሠልስ፦ ተራ አጀንዳ በሰጡን ቁጥር አንረበሽ። የኢትዮጵያዊ አለመሆን ወይም የኢትዮጵያዊ ማንነት አለመኖር ማረጋገጫ ቡራኬ መቀበያ – ሮጦ መወተፊያ፣ መወሸቂያና ማረጋገጫ መቀሌ መሆኗ ገርሞኛል።
“ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም” ሲባል ማጨብጨብ – በርግጥ መንበጫበጭ ነው። በጭበጭ! በጭበጭ! ጨብጨብ!
*
ሲጠቃለል እኔ ኢትዮጵያዊ ማንነት አለኝ። ቆይ ቆይ ረጋ ሰከን ደርበብ ወገኖቼ – ኢትዮጵያዊ ማንነት የሌላቸውና ጭር ሲል ከየተደበቁበት አገር ጉረኖ የወጡ – ትንንሽ ስብዕናዎች የሌላቸውን የለንም ቢሉ ምን ይገርማል?!
እኔና እናንተ ኢትዮጵያዊ ማንነት አለን። የሌላቸው የላቸውምና ‘ኑ ሀገር እንሥራ!’
*
የበታችነት ስሜት ስቃይ – በቀላሉ ማይድን በሽታ
ምዕራባውያን ዐረቦችና ዶላሮች ፈትተው ለቀቁብን!
ማንነት፦ ሰውነት ኢትዮጵያዊነት ዜግነት – ከእንግሊዝኛው አታሳክሩት። ዋናው የቃላት ስንጠቃው ሳይሆን -ሀሳቡ የተነሳበት አውድ –  ከበስተጀርባው ያለው ኢትዮጵያዊነትን የማዳከም የማክሰም የማደብዘዝ አጀንዳ ነው።
እናንተ ትደበዝዛላችሁ ትዋረዳላችሁ ታንሳላችሁ!
ኢትዮጵያችን ግን በመቶ ሚሊየን ልጆቿ ትደምቃለች።
* መነሻቸው ምንድነው?! የሚለው ላይ ዐይኔን ሳልጨፍን ገለፅሁ። 
*
ቢያድለን ኖሮ – ሀገርን በማደርጀት ሂደት የምሁራን ሚና በሚል ርዕስ ስለምወዳት ፍቅር መፃፍ መሻቴ ነበር። በጥባጭ ሳለ ማን ጥሩ ይጠጣል?! ሆነና ከፍተው አከፉን።
*
ያየኋችሁ የጌዴኦ ተፈናቃይ ወገኖቼ ወደ ቀደመ ቀያችሁ መመለሳችሁን ሰምቼ ደስ ቢለኝም፤ አሁንም ሽፍታው አላሳርፍ እንዳላችሁ መገንዘብ ችያለሁ። በስልጢና በጉራጌነታችሁ ከሲዳማ የተፈናቀላችሁ ወገኖቼ በቅርቡ መጥቼ ዐያችኋለሁ።
ህልም አለኝ “I have a dream” – አንድ ቀን ከጎጥ የበረት አስተሳሰብ ወጥተን፤ ከተራ ብሽሽቅና ፉክክር ተላቅቀን – ለተራበው 10ሚሊየን ወገናችን፣ ባህር አቋርጦ ሲሄድ ለሚያልቀው ተስፈኛ ወጣት፤ ጎዳና ጠርዝ ላይ በብርድ ለሚቆራመዱ 100ሺህዎች ቤተሰቦች፣ በዛሬ 6,000 ዓመት ማረሻ ስለሚያርሰው ወገን፤ በወጣትነታቸው በሴተኛ አዳሪነት ህይወታቸውን ስለሚገፉ ልጆቻችንና እህቶቻችን፤ በቤት ኪራይ እጦት ስለሚንገላታው ወገን፤ የኑሮ ውድነት ስላጎበጠው ህዝብ፤ ስለ ሠላሳ ሚሊየን የአእምሮ ህመምተኛ – (27 ዓመት በዐይኑ ያየውን ግፍ ረስቶ፤ ከእስር ሲፈቱት – ምኒልክ አስሮ የፈታው ከሚመስለው… ወያኔ ገርፋው ምኒልክ ላይ ቂም ስለሚይዝ…)
በአጠቃላይ እኔም ከአተካሮ አእምሮዬ ፀድቶ … እምዬ ኢትዮጵያ ገነት ስለምትሆንበት ሁኔታ የሚመክሩ ምሁራን ወደፊት እንደሚመጡ ተስፋ አለኝ። “I have a dream” -ልጆቻችን የፍቅር ሐውልት ሠርተው – ሥሩ ቁጭ ብለው ማኪያቶ እየጠጡ – ምጣኔ ሀብት፣ ባህል፣ ፖለቲካ፣ ሰውነት የሚያክሙበት >  የእድገት ሆስፒታል ገንብተው።
ፈጣሪዬ ሆይ አርጅቼም ቢሆን – ያን ዕለት ሳታሳይ አትውሰደኝ።
ሰይፍ የሚያነሱ በሰይፍ ይወድቃሉ። ደም የሚያፈስሱ ደማቸው ይፈስሳል። ብንሞትም አሟሟታችን እንደእነርሱ የውሻ ሳይሆን – እንደ አርበኞች በክብር (በፍቅር አርበኝነት) ነው።
እመኑኝ ይህቺን ሀገር ለማዳን የኢትዮጵያ አምላክ አያንቀላፋም።
Filed in: Amharic