>

ፊት-ለፊት ልንጋፈጠው የሚገባ የተረኝነት ስሜት!!! (ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ)

ፊት-ለፊት ልንጋፈጠው የሚገባ የተረኝነት ስሜት!!!

ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ

የተረኝነት ስሜት በሰዎች ሕይወት ውስጥ የሚንጸባረቅ፤ ተፈጥሯዊ ስሜት ነው። ይህ የተረኝነት ስሜት፤ እንደ ተጠቃሚው እና እንደ ሁኔታው፤ በጎም፤ አደገኛም ጎን አለው። በብዙ ነገሮች፤ ተራ ጠብቀን የምናደርጋቸው ነገሮች፤ ጥሩ ሥነስርዓት ያስይዙናል። በአስተዳደርም ጉዳይ፤ ወጣቱ ትውልድ፤ ተራውን ተከትሎ የአባቶቹን ሥራ ተርክቦ፤ ሥራቸውን ያሻሽላል ተብሎ ይጠበቃል። የተረኝነት ስሜት ለሃገር እድገት በጎ የሚሆነው፤ ሁሉም፤ በአንድነት የተረኝነት ስሜት ሲሰማው እንጂ፤ የተወሰኑ ሰዎች ብቻ “ተረኛ ነኝ” ስለዚህ እኔ ብቻ የፈለግኩትን የማድረግ መብት አለኝ ሲሉ፤ ሥራቸው አግላይ እና አድሎአዊ ሲሆን አይደለም። ባለፉት በርካታ ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ በብዙ የህብረተሰባችን ክፍል በተፈጠረ “የተረኝነት ስሜት” አግላይ እና አድሏዊ የሆኑ በርካታ የግፍ ሥራዎች ተሰርተዋል። ከትላንትና የተረኝነት ስሜት ሳንላቀቅ፤ ዛሬም ሌሎች “ተረኝነት” ተሰምቷቸው፤ “ጊዜው የእኔ ነው፤ እኔ ከአንተ በላይ ነኝ” ሲሉ በንግግራቸው ብቻ ሳይሆን፤ በሥራቸውም ይታያል። በተለይ በሃገራችን ገኖ የሚታየው የተረኝነት ስሜት “የእኔ ወገን የሆነ ባለሥልጣን ነው፤ ስለዚህ እኔም የተለየ ሥልጣን አለኝ” ወይም ከባለሥልጣን ጋር ግንኙነት አለኝ ከሚል ስሜት ይመነጫል። ሰዎች እንዲህ ዓይነት የተረኝነት ስሜት የሚሰማቸው፤ መንግሥት፤ ወይም ገዢ ፓርቲ ስለሚያበረታታቸው ብቻ ሳይሆን፤ ብዙውን ጊዜ፤ በራሳቸው የግል ፍላጎት እና ስግብግብነት ነው። በእርግጥ መንግሥት እና የመንግስት ባለሥልጣናት፤ በሚሰሩት እና በሚናገሩት ነገር “የተወሰነውን የኅብረተሰብ ክፍል” የተረኝነት ስሜት ካንፀባረቁ፤ ተረኛ ነን ለሚሉ ጽንፈኛ ሃይሎች ያልተጠበቀ አደገኛ ጉልበት ይሰጣሉ።

እንዲህ ዓይነት አደገኛ የተረኝነትን ስሜት እንዳያንሰራራ፤ መንግስት እና ባለሥልጣናት፤ ለሚናገሩትም ነገር ይሁን ለሚሰሩት ስራ፤ ጥንቃቄ መውሰድ አለባቸው፤ ይህ ብቻ ሳይሆን፤ በተረኝነት ስሜት፤ ለሚሰራ አድሎዋዊም ሆነ አግላይ ድርጊቶች፤ ድርጊቱን በሚፈፀም ግለሰብም ይሁን ቡድን ላይ የሚያስቀጣ ሕግ ሊኖር ይገባል። ከዚህ በተጨማሪ፤፤ መንግሥት ዜጎችን በማስተማር እና፤ በተረኝነት ስሜት ሕግ ሲጥሱ፤ እርምጃ በመውሰድ፤ ዜጎችን ሊያስተምር እና አቅጣጫ ሊያሲዝ ይገባል። ይህ የተረኝነት ስሜት፤ ለኢትዮጵያ ብቻ የተለየ አይደለም። ቢያንስ ላለፉት 10 ዓመታት በአሜሪካን ሃገር ሳይቀር፤ ያይነው ስሜት ነው።

የተረኝነት ስሜት፤ ሰዎች በማወቅም፤ ባለማወቅም፤ የግል ጥቅማቸውን ለማሳካት የሚጠቀሙበት እኩይ ዘዴ በመሆኑ፤ መንግስት፤ ገዥው ፓርቲ፤ እና ተቋማት፤ ደጋፊዎቻቸውን በመምከር እና በማስተማር መሪ ሚና መጫወት ቢኖርባቸውም፤ እያንዳንዱ ዜጋም፤ ይህን የተረኝነት ስሜት፤ በሚችለው መንገድ ማስተማር እና በጽናትም መጋፈጥ ይኖርበታል። እንደ አውሮፓ አቆጣጠር፤ በ1996 ዓ.ም. ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ስመለስ፤ በበርካታ ሰዎች ላይ የናጠጠ የተረኝነት ስሜት አይቻለሁ። ወቅቱ በሕወሃት የሚመራው ኢሕአዲግ ሥልጣን ከጨበጠ አምስት አመትን ያስቆጠረበት ከመሆኑም በላይ፤ ከሻዕቢያ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ይሰራበት የነበር ወቅት ስለነበር፤ ብዙው “የትግርኛ ተናጋሪው ኅብረተሰብ”፤“የተረኝነት” ስሜቱ ብዙዎችን እንዳሳዘነ አስተውያለሁ። በወቅቱም ከአንድ ዘመዴ ጋር በነበረኝ ውይይት ባለጠበኩት ሁኔታ “አሁን እኮ ጊዜው የትግሬ ነው” ሲል ውስጤን የተሰማኝ ስሜት የሚሰቀጥጥ ነበር። ዘመዴንም ሁለተኛ እንዲህ ዓይነት ነገር እንዳያስብ እና፤ በእንዲህ ዓይነት ስሜት እንዳይነዳ መከርኩት፤ “መንግሥት ይመጣል፤ መንግሥት ይሄዳል፤ ነገ ከዚሁ ሕዝብ ጋር ነው መልስህ የምትኖረው”፤ በሚልም ገሰጽኩት፤ እግዚአብሔር ይስጠው፤ ተግሳፄን ተቀብሎ፤ ሌሎችንም ይመክር ነበር። ይህን ያነሳሁት፤ አንዳንድ ሰው ካለማወቅ እና በግብዝነት፤ ወይም ወደ ነፈሰበት በሚነፍስ ስሜት፤ በተረኝነት ስሜት ሃገርን እና ሕዝብን የሚጎዳ ሥራ ሊሰራ እንደሚችል ለመጠቆም እና፤ ሁላችንም ሰዎችን የመምከር ሃላፊነት አለብን ለማለት ነው። ሰዎች በተረኝነት ስሜት፤ ጉዳት የሚያደርስ ነገር ሲሰሩ ዝም ካልናቸው፤ ጉልበት እየጨመሩ ይሄዳሉ፤ የሚያደርሱት ጉዳትም እየጨመረ ይመጣና፤ በሃገር የሚያደርሱት ጉዳት የከፋ ይሆናል።

እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2008 ዓ.ም. ባራክ ኦባማ የአሜሪካንን ፕሬዝዳንትነት በምርጫ ሲያሸንፉ፤ ብዙ ጥቁር አሜሪካውያን የተረኝነት ስሜት ተሰምቷቸው ነበር። በወቅቱ እኖርበት በነበረው ሜምፈስ፤ ቴነሲ፤ ብዙዊች በከተማ የሚኖሩ ጥቁር አሜሪካኖች፤ ለነጮቹ፤ ጥሩ አመለካከት ስላልነበራቸው፤ ኦባማ ያሸነፉ ጊዜ፤ ነጮቹን ማጥቃት የሚችሉ መስሎ ታያቸው። ጥቁር አሜሪካውያን ወጣቶችም በብዛት ተሰባስበው እየጮኹ፤ “ኦባማ አሁን ልክ ያገባችኋል፤ 400 ዓመታት በባርነት የገዛችሁበት ጊዜ አከተመ፤ እናንተን ከሥራ አባሮ ለእኛ ሥራ ይሰጣል፤ ቤት ለእኛ ይሰጣል፤ ገንዘብ ለእኛ ብቻ ይሰጣል፤ ሥልጣን ለጥቁር ብቻ ይሰጣል፤ ወዘተ” እያሉ ከተማዋን አወኳት። ብዙዎቹ፤ ነጮች፤ ጥቁሮቹን፤ በትዝብት፤ በፍርሃት፤ እና በቁጭት ብቻ ነበር የሚያዩዋቸው። ምንም እንኳን በርካታ “የጥቁር አሜሪካውያን መብት ተሟጋቾች” ኦባማ ለጥቁር አሜሪካውያን ብቻ የተለየ ትኩረት እንዲያደርጉ ቢወተውቱም፤ ኦባማ “እኔ የጥቁር አሜሪካውያን ፕሬዝዳንት አይደለሁም፤ የሁሉም አሜሪካውያን ፕሬዝዳንት ነኝ” በማለት ሃላፊነታቸው ለሁሉም ዜጋ መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት ከበርካታ “አክራሪ የጥቁር መብት ተሟጋቾች” “እኛ አስመርጠንህ ከዳህን” በሚል በርካታ ትችትን አስተናግደዋል።

ዛሬ ደግሞ የተረኝነት ስሜቱ ወደ ጽንፈኛ ነጮች ዞሯል። በዘመነ ዶናልድ ትራምፕ፤ ጽንፈኛ ነጮች፤ አሜሪካን የነጮች ብቻ ሃገር መሆን አለበት በሚል ስሜት ተነሳስተው፤ ነጭ ያልሆነውን ሁሉ፤ አሜሪካንን ለቆ እንዲወጣ ድምፃቸውን እያሰሙ ነው። በርካታ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ የእነዚህ የጽንፈኛ ነጮች ቡድን እና አባላት እየተበራከተ፤ አንዳንዶች፤ በአይሁዶች፤ በጥቁሮች እና፤ ነጭ ባልሆኑ አሜሪካውያን ላይ የግድያ ሁሉ እርምጃ በመውሰድ ላይ ይገኛሉ። በየግሮሰሪው እና በአንዳንድ የገበያ ቦታዎች፤ የተረኝነት ስሜት የተሰማቸው ጽንፈኛ ነጮች፤ በተለይም የውጭ ዜጋ የሚመስላቸውን ሁሉ፤ ያለስጋት እና በድፍረት “ወደ ሃገርህ ሂድ” እንድሚሉ በበርካታ የማህበራዊ ሚድያዎች ለማየት ችለናል።

ይህ የተረኝነት ስሜት፤ በአሜሪካን ሃገር ታይቶ በማይታወቅ መልኩ፤ “የቀለም እና የዘር ልዩነትን” እያሰፋ እና ሃገሪቱን ወደ አላስፈላጊ ግጭት እና ሁከት እየከተታት ይገኛል። ትራምፕ ግን ደጋፊዎችቻቸው በዚህ የዘረኝነት መንገድ እንዲቀጥሉበት፤ የሚገፋፉ በመሆናቸው፤ አንዳንዶቹ የግል ሚሊሺያ በማቋቋም፤ የሜክሲኮ እና የአሜሪካንን አዋሳኝ ድንበሮች፤ በታጠቁ አባላቶቻቸው “እየጠበቁ” ይገኛሉ። አንዱ የሚሊሽያ አባል፤ በአሜሪካን የፌድራል ፖሊስ እስከታሰረበት ጊዜ ድረስም፤ እነዚህ የግል ሚሊሽያዎች፤ ድንበር ጥሰው የሚገቡ ስደተኞችን ማሰር ጀምረው ነበር። ትራምፕ፤ የሚያስተላልፉት መልዕክት፤ የጽንፈኛ ነጮችን፤ የተረኝነት ስሜት የሚያበረታታ በመሆኑ፤ ከምንጊዜውም በላይ፤ የአንዳንድ የአሜሪካን ነጮች የዘረኝነት ስሜት ፈጦ ወጥቷል። ይህም ለወደፊቷ አሜሪካ አደገኛ እንደሆነ በብዙ ባለሙያዎች ይነገራል።

በዛሬይቱ ኢትዮጵያም፤ የኦሮሞ የተረኝነት ስሜት ፈጦ እየወጣ እያየን ነው። በአንዳንድ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ኦሮሞዎች፤ ኦሮሞ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያንን፤ በተረኝነት ስሜት መግፋት እንደጀመሩ፤ ዜናዎች እየወጡ ነው። ይህ በአስቸኳይ ሊቀጭ ይገባዋል። እንዲህ ዓይነት እኩይ ድርጊት፤ የለውጡን ሂደት የሚያደናቅፍ ብቻ ሳይሆን፤ ጥላቻን የሚያከር፤ ቂም የሚፈጥር እና፤ በሰዎች ሕይወት እና በሃገርም ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል ነው። ምንም እንኳን ዶ/ር አብይ፤ የኦሮሞ ድርጅት መሪ ቢሆኑም፤ ጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው ለኦሮሞ ሕዝብ ብቻ እንዳልሆነ፤ በተደጋጋሚ አስረግጠው መናገር አለባቸው። በተለያየ የፌደራል መንግሥቱ የስራ እርከን ላይ ያሉ የሥራ ሃላፊዎችም በየመስርያ ቤታቸው ላሉ ሰራተኞች ማስተላልፍ ያለባቸው መልዕክት፤ ዛሬ ተራው የሁሉም ዜጋ መሆኑ እና፤ ማንም ከማንም የማያንስ መሆኑን ነው። በተረኝነት ስሜት በደል የሚደርስባቸው ሰራተኞች፤ በደላቸውን የሚያሳውቁበት አሰራርም ሊዘረጋ ይገባል። በእኔ እምነት፤ በሚኒስትር ደረጃ፤ በቀጥታ ከላይ ወደታች መተላለፍ ያለበት መልእክት፤ ምንም እንኳን ይህ መንግሥት “የሽግግር መንግሥት” ነው ብለን ብንቀበልም፤ መንግስትነቱ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆኑን እና፤ የዘር አድልዎ በምንም መልኩ ተቀባይነት እንደሌለው አስረግጦ የሚነግር መሆን አለበት። የዘር አድልዎ የሚፈጽሙት ላይም አስተማሪ እርምጃ ሊወሰድ ይገባዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕግ ማውጣት እና መቀጫውንም ከበድ ማድረግ ይኖርበታል። በተረኝነት ስሜት ተበድለው ከስራ ይሚባረሩ ወይም ሌላ ጉዳት የሚደርስባቸው፤ ካሳ የሚያገኙበት አሰራርም በሕግ ይደንገግ።

ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች፤ የሙያ እና የሲቪክ ማህበራት፤ ሕበረተሰቡን በማስተማር፤ የተረኝነት ስሜት በተጠናወታቸው ሃይሎች፤ እንዳይገፋ፤ መብቱን ማስጠበቅ የሚችልበትን መንገድ ይምከሩ፤ ከሕግ አስከባሪው፤ እንዲሁም ከሎሎች የመንግሥት አካላት ጋር በጣምራ በመስራት፤ የተረኝነትን ስሜት እና ድርጊት፤ በጽናት መጋፈጥ እና መታገል ይጠበቅባቸዋል። የዜና አውታሮችም በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፊ ዘገባ በማቅረብ፤ ባለሙያዎችን በመጋበዝ፤ እንዲሁም ስሞታ ሲሰሙ በተገቢ እና ሚዛናዊ በሆነ ሁኔታ በመመርመር፤ እኩይ ድርጊቶችን፤ አስተማሪ በሆነ መንገድ ለሕዝብ ማቅረብ ይኖርባቸዋል።ነፍሱን ይማረው እና ወዳጄ ዶ/ር አብይ ፎርድ “ዲሞክራሲ ለሕዝቡ ሥራ ነው” ይል ነበር። የዲሞክራሲ አንዱ ገጽታ፤ ዜጎች በደል ሲደርስባቸው፤ የሕግ ተቋማትን ተጠቅመው፤ መብታቸውን ማስከበር ነው። ይህ በኢትዮጵያችን ያልተለመደ በመሆኑ ነው ሁሉንም ነገር በነውጥ እና በሰላማዊ ሰልፍ “ለመለወጥ” የሚሞከረው። እንደ ዜጋ ለራሳችንም፤ ለሌችም መብት መከበር መጮኽ ብቻ ሳይሆን፤ ያሉትን ተቋማት በመጠቀም፤ የተቋማቱን ጥንካሬም መፈተሽ ይኖርብናል። እያንዳንዳችን “በያገባኛል” ስሜት ተነሳስተን፤ የዜግነት ግዴታችንን ካልተወጣን፤ መብታችንን በመጠየቅ ብቻ፤ ወደ የምንፈልጋት ፍትሃዊ እና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ልናመራ አንችልም። ሁሉንም ነገር ከመንግሥት የምንጠብቅ ከሆነ፤ መንግሥት እራሱ በሕግ እንዲገራ የማድረግ መብታችንን መጠቀም የማንችል ደካማ ዜጎች እንሆናለን። በሃገራችን ጉዳይ በመሳተፍ፤ በአቅማችን ማድረግ የምንችለውን ሁሉ ካላደረግን፤ መንግስትንም ሆነ ባለስልጣናቱን “ስድ” ከመሆን አናግዳቸውም። የነቃ፤ ለመብቱ የሚሟገት ዜጋ ሲኖር ነው፤ መንግሥትም ሆነ ባለሥልጣናት፤ ለሕግ ተገዢ፤ ሕዝብን የሚፈሩ ሹሞች ሊሆኑ የሚችሉት።

አሁን ባለንበት የፖለቲካ ሂደት፤ “የኦሮሞ መብት ተሟጋች ነን” የሚሉ ሃይሎች፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ሆነ፤ ሌሎች የመንግስት አካላትን፤ ለኦሮሞ ብቻ እንዲያደሉ፤ ከፍተኛ ውትወታ ያደርጋሉ። አሁን ላለው ለውጥም ዋጋ የከፈለው “ኦሮሞ ብቻ ነው” የሚል ብርዝ ትርከት በተለያዩ የዜና አውታሮች እና በማህበራዊ ሚድያም ማሰራጨታቸውን ይቀጥላሉ። ምንም እንኳን ይህን የተረኛነት ስሜት አደገኛነት በመሪነት ማስተማር ያለባቸው የመንግሥት አካላት ቢሆኑም፤ ሁላችንም ደግሞ የድርሻችንን መወጣት ይኖርብናል። ጊዜው “የኦሮሞ ነው” ለሚል ሰው፤ ጊዜው የኦሮሞ ብቻ እንዳልሆነ፤ በማያሻማ ሁኔታ መንገር፤ ማስተማር እና፤ በመጋፈጥም ይህንን እኩይ አስተሳስብ ልንዋጋ ይገባል። ይህን አዲስ ምዕራፍ ከተጠቅመንበት፤ ለሃገራችን ብዙ በጎ ነገሮችን የምንስራበት ወቅት ይሆናል። ጅምሩን ስኬታማ ልናደርገው የምንችለው እኛ ብቻ ነን። በትንሹም ሆነ በትልቁ፤ “ጊዜው የእኛ ነው” ብለው ሊያሸማቅቁን የሚሞክሩትን፤ አደብ ግዙ፤ ጊዜው የሁላችንም ነው ልንላቸው ይገባል። የሚቀጡበትም ሕግ እንዲወጣ ልንወተውት ይገባል። ይህን ጽንፈኛ አስተሳሰብ በጊዜ ካልቀጨነው፤ ሥር ሰዶ፤ የማንወጣው ችግር ውስጥ እንደሚከተን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፤ ምልክቱንም ከአሁኑ እያየነው ነው።

ቸሩ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ይባርክ

Filed in: Amharic