>

ለቅሶዬን አየሁት!!! (ያሬድ ጥበቡ)

ለቅሶዬን አየሁት!!!
ያሬድ ጥበቡ
ዛሬ በእስር እንዲማቅቁ የተደረጉት የአማራ ወጣቶች፣ የዛሬ ሶስት አመት “በጎዳና የሚፈሰው የኦሮሞ ደም የኔም ደም ነው!” ብለው በጎንደርና ባህርዳር አደባባዮች ከገዳዮች ጋር የተጋፈጡ ጀግኖች ናቸው!!!
አዎን እኔም እንደሌላው ለቅሶዬን አየሁት። በአደባባይ፣ በህዝብ ፊት ምን ይሆን ያስለቀሰኝ ብዬ አሰብኩ። ባላወቅኩት ምክንያት ተካ ቺስታ ታወሰኝ። ተካ የእኔና ዶክተር መረራ የኮሌጅ አመታት ክላስሜታችን ነበር።  በ1967 አም አጋማሽ ላይ መለስ ተክሌ ፣ ግደይ ገብረዋህድና ረዘነ ኪዳኔ ማዘጋጃ ቤት ውስጥ የፈነዳው ቦምብ ተላክኮባቸው በግፍ ሲገደሉ ተካ ተከፍቶ ነበር። ተካ ሃይፐታይትስ ታመመና ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሆስፒታል ተኛ። እየተመላለስን ስንጠይቀው “ጓዶች በረሃ ወርጄ ይህን ግፍ ሳልበቀል እዚህ አልጋ ላይ ልሞት እኮ ነው” እያለ ያስቀን ነበር። የተካ ቁጭት ግን የምር ነበር ። እንደተሻለው በረሃ ወርዶ ተሓህትን (TPLF) ተቀላቀለ። በ1969 ሚያዚያ ወር ህወሓት ያገተብንን የአውራጎዳና መኪና ለማስለቀቅ እኔ የነበርኩባት የኢህአፓ ጦር አንዲት ጋንታ ታዝዛ ወደ እንትጮ ተጓዝን ። መኪናዋን ለማስለቀቅ እንትጮ ከተማ በምትገኝ ሻይ ቤት ውስጥ በጉዳዩ ላይ ሊደራደሩ ከመጡት የተሓህት መሪዎች ከአባይ ፀሀዬና ከመለስ ዜናዊ ጋ ተገናኘን። እኔ በወቅቱ ተራ ተዋጊ ብሆንም በኛ ወገን ከሚደራደሩት ከዶክተር ጌራና የአየርወለድ ባልደረባ ከነበረው ኮማንደራችን ከህብስቱ ጋር እንድሄድ ተደርጌ ነበር። አባይን ሳገኘው ስለተካ ቺስታ ጠየቅኩት። ሴሮ የሚባል ቦታ ላይ በውጊያ ላይ መሰዋቱን ነገረኝ፣ አላለቀስኩም ሆኖም አዘንኩ። በዚያ ዘመን ለታጋይ አይለቀስም፣ ጠብመንጃውን ይዘው ይታገሉለታል እንጂ። የተለየ ዘመን ነበር። ተካ የመጨረሻ እንቅልፍ ያንቀላፋባትን የሴሮ ቀበሌ ሄጄ ጎበኘኋት።
ቅዳሜ ላይ ሴንትፖል ሚነሶታ ላይ በተደረገ የመፅሀፌ ምረቃ ላይ ያለቀስኩት ለኤዲተሬ ለበሪሁን አዳነ ቢሆንም፣ ይህን ሁሉ አበሳና መከራም አሳልፈንም ዛሬም ሰላማዊ ዜጎች በጨካኝ የመንግስት ተዋናዮች ከመታሰርም አልፎ የፀሀይ ብርሃን የሚከለከሉበት ጭለማ ላይ መድረሳችን አሳዝኖኝ ነው። ለቅሶዬ ለኢትዮጵያ ነው። ለቅሶዬ በማንነቱ ብቻ የመንግስታዊ ሃይሎች የጥቃት ኢላማ ለተደረገው የአማራ ወጣትና ህዝብ ነው።
እነዚህን መስመሮች ስተይብ በቅድም አያቴ በወይዘሮ እህተ ቀበሌ፣ በደራ፣ ሰዎች በማንነታቸው የተነሳ በኦዴፓና ኦነግ ካድሬዎች እየተሰቃዩ ነው።  ይህ መቆም አለበት። ይህ በአስቸኳይ መቆም አለበት። አለበለዚያ ከ43 ዓመታት በፊት ተካ ቺስታ በረሀ እንደወረደው፣ ምሬታቸውን ለማስታገስ ፣ ከውርደት ሞትን የሚመርጡ ወጣቶች ከየዩኒቨርሲቲው፣ ከየጫትቤቱ፣ ከየትምህርትቤቱ ወደበረሀ ይወርዳሉ።
ይህን ማስቆም ግን ይቻላል። የታሰሩትን መፍታት። ዜጋን በማንነቱ አለማጥቃት። ኢትዮጵያዊውን በአማራነቱ የግፍ ሰለባ አለማድረግ።  ይህ መፍትሄ በጠቅላይ ሚኒስትሩና በገዢው ፓርቲ ኦዴፓ እጅ ያለ ቢሆንም፣ የአዴፓ መሪዎችም ለመፍትሄው አስተዋፅኦ ማድረግ ይችላሉ። እንደቀደመ ታሪካቸው የሌሎች መጋዦ ባለመሆን እንወክለዋለን ከሚሉት ህዝብ ጎን የመቆም ክህሎትም ግዴታም አለባቸው። “የለውጡ አመራር” የሚባለው መሪር ቀልድ መሆኑን አስታውቀው፣ የማንነት ጥቃቱ ካልቆመ፣ እዚህ ቧልት ውስጥ እንደማይሳተፉ አቢይን ቁርጥ ቀን መስጠት ይችላሉ። አዴፓ የአቢይ ተላላኪ እንዳይሆን፣ የህዝባቸውን ቁመና ወክለው ሳያቀረቅሩ መቆም ይችላሉ።
ከአዴፓም በላይ፣ የአማራ ህዝብ “በልጆቼ፣ ወንድሞቼ፣ ማንነቴ ላይ የተቃጣው የኦዴፓ መንግስታዊ ጥቃት አሁኑኑ ይቁም!” ብሎ በሰላማዊ መንገድ በየአደባባዩ ሊተም ይገባል። አማራውም ብቻ ሳይሆን፣ የማንነት ጥቃትን የሚቃወሙ ሁሉ፣ ከኦዴፓ ውጪ ያሉ የኦሮሞ ምሁራንና ኤሊቶች፣ እንደ ዶክተር መረራና አቶ በቀለ ገርባ ያሉ የፖለቲካ መሪዎች፣ እንደነ ዶክተር ዲማ ኖጎ ያሉ ጨዋ ሽማግሌዎች፣ አቢይ በማድረግ ላይ ያሉት ማተራመስ ውሎ አድሮ አብሮነትን የሚጎዳ መሆኑን ተረድተው “በስማችን እንዲህ አይነት ግፍ አይፈፀምም” ብለው “NOT IN OUR NAMES!” የሚል ዘመቻ ማስተባበር አለባቸው።
ዛሬ በእስር እንዲማቅቁ የተደረጉት የአማራ ወጣቶች፣ የዛሬ ሶስት አመት “በጎዳና የሚፈሰው የኦሮሞ ደም የኔም ደም ነው!” ብለው በጎንደርና ባህርዳር አደባባዮች ከገዳዮች ጋር የተጋፈጡ ጀግኖች ናቸው። የባህርዳሩን አሳዛኝ ክስተት እንደ ጭምብል ተጠቅሞ ከሚያካሂደው የማንነት ጥቃት አቢይ መቆጠብ አለበት። ያሰራቸውን መፍታትም ይኖርበታል። ለመሆኑ በኦሮሚያ የተረፈ የሃገር ሽማግሌ አለ? ካላችሁ ድምፃችሁን ማሰሚያው ወቅት አሁን ነው። አቢያችሁን ምከሩ!
Filed in: Amharic