>

ጋዜጠኛ በሪሁን አዳነ ሹመት እንጂ እስር አይገባውም!!! (ያሬድ ጥበቡ)

ጋዜጠኛ በሪሁን አዳነ ሹመት እንጂ እስር አይገባውም!!!
ያሬድ ጥበቡ
በሪሁን የመፅሃፌ አርታኢ ወይም ኤዲተርና ከማስተየብ እስከ ማረም፣ እስከ ማሳተምና ማከፋፈል አእምሮውን ፣ ጊዜውንና ጉልበቱን የሰጠኝ ወጣት ምሁር ነው። ከበሪሁን ጋር አንተዋወቅም ነበር። ከሶስት አመታት በፊት ለፋሲካ ድሮ በላከልኝ ስጦታው ነው የተዋወቅነው። ስጦታውም፣ ከየቦታው አሰባስቦ በአንድ ላይ ያስጠረዘው የመፅሃፌ ስብስብ ነበር ።
  ባለፈው ዓመት በነሃሴና መስከረም ወራት አዲስ አበባ ባደረግሁት ቆይታ ወቅት ከበሪሁን ጋር ብዙ ጊዜያት ለማሳለፍ እድል አግኝቻለሁ። በሪሁን የአማራ ብሄርተኛ ምሁር ነበር። ዝም ብሎ በስሜት ሳይሆን በጥልቅ  ምርምር ላይ ተመሥርቶ የደረሰበት አስተሳሰብ ነው።
   የብሄረሰቦች ፌዴራሊዝምን ከልቡ የሚያምን ሰው ነበር። አቋሙንም ሲከራከር ከበለፀጉት የአውሮፓ ሃገሮችም ጋር እያወዳደረ ጭምር፣ የብሪታንያንና በውስጧ ያቀፈቻቸውን የስኮቲሽ፣ ኢንግሊሽና አይሪሽ ብሄረሰቦች ህብረት ጭምር እያነሳ፣ አንድ የብሪታኒያ ዜጋ የወጣለት የአይሪሽ ብሄርተኛ ጭምር መሆን ይችላል ፣ ሁለቱ አይጋጩም የሚል ክርክር የሚያነሳና፣ በተመሳሳይ መንገድም አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ኦሮሞነቱን ፣ አማራነቱን የሚወድና የሚያከብር ቢሆን የሚቻል ብቻ ሳይሆን የሚመረጥም ነው የሚል ወጣት ምሁር ነበር እኔ የማውቀው በሪሁን ።
ለምን መፅሃፌን ለማሳተም ያን ያህል እንደደከመ ስጠይቀውም “ጋሽ ያሬድ የተራዘመ ሰላማዊ ህዝባዊ እምቢተኝነትን ለአስርተ አመታት የተከራከርክ፣ የፃፍክ፣ ያስተማርክ በመሆኑ፣ ሥራህን ስለወደድኩት ነው፣ ፅሁፎችህ ተበትነው እንዳይቀሩ ነው ያሰባሰባኳቸው” ብሎ ነው የመለሰልኝ።
ከ15 ቀናት በፊት ለሁለት ሳምንታት አዲስ አበባ በቆየሁባቸው ቀናት ከበሪሁን ጋር አልተገናኘንም፣ በስልክ እንኳ አላወራንም ። ለሚያውቁት ወዳጆቹ “በሪሁንን ማግኘት አልቻልኩም ስላቸው፣ በአስራት ሚዲያ ሥራ መጠመዱን” እንደሚገምቱ ነገሩኝ።
   በሪሁን የማንዴላና የማርቲን ሉተር ኪንግን አስተምህሮዎች ከፖለቲካ ሳይንስ እውቀቱ ጋር አዳበሎ፣ በኢትዮጵያ ያልተሞከረው የተራዘመ የህዝባዊ ሰላማዊ እምቢተኝነት ትግል ውጤት የሚያመጣና፣ ህዝቡንም የሚያጎለብት empowering መሆኑን የሚያውቅ ወጣት ምሁር ነው ።
  በሪሁን አዳነን በግድያና አመፃዊ የመንግስት ግልበጣ መክሰስ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ነው።
 በሪሁን ከአማራ ብሄርተኝነቱ ውጪ ምንም አይገኝበትም። የአማራ ብሄርተኛ መሆን ደግም ፈፅሞ ወንጀል አይደለም። የእነሌንጮን ምክር የሚያዳምጥ ጠቅላይ ሚኒስትር በምን  መለኪያ ነው የአማራ ምሁራንን በወንጀል ሊጠይቅ የሚችለው?
  የአቢይ አስተዳደር በሰላማዊ የአማራ ምሁራንና ባለሃብቶች፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ባለአደራ ምክርቤት አባላትና ደጋፊዎች ላይ የጀመረው የጅምላ አፈሳ አሁን ከማየታችን በፊት፣ ቅዳሜ ምሽት “የመንግስታዊ ግልበጣ” ክስ ሲጀምር፣ ተቀናቃኝ ነው ብሎ ያመነውን የአማራ ብሄርተኝነት ለመጨፍለቅ የተፈጠረ ጭምብል እንደነበር ግምቱ የነበረን ቢሆንም፣ ለሃገር መረጋጋት ስንል ዝምታን መርጠን ነበር ።
ሆኖም የዝምታችን ውጤት ፍፁም ሰላማዊ የሆኑ የበሪሁንን ዓይነት ለሃገር ሊተርፉ የሚችሉ ወጣት ምሁራንን ጭዳ የሚያደርግ ከሆነ፣ ምሬታችንን ይጨምረዋል ። ስለ በሪሁን ሰላም ወዳድነትና ህገመንግስቱን አክባሪነት በፍትህ አደባባይ ቆሜ ልመሰክርለት ፈቃደኛ ነኝ። በሪሁንና እሱን መሰል በግፍ የታሰሩ የአማራ ምሁራን፣ ባለሃብቶች፣ የጦር መኮንኖች፣ ወዘተ በአፋጣኝ ፍትህ ሊያገኙና ሊፈቱ ይገባቸዋል።
Filed in: Amharic