>
11:49 pm - Wednesday November 30, 2022

"መደመር" እና  የምርኮው ፖለቲካ!!! (ጌታቸው ሺፈራው) 

“መደመር” እና  የምርኮው ፖለቲካ!!!
(ጌታቸው ሺፈራው) 
ባለፉት 27 አመታት ከአገዛዙ በተቃራኒ የቆሙ በርካታ የፖለቲካ ቡድኖች ነበሩ። በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጭም ያሉ/የነበሩ፣ በሰላማዊም ሆነ በትጥቅ ትግል የሚታገሉ ቡድኖች ከአገዛዙ ጋር የነበራቸው ልዩነት ሰፊ ነው። ይሁንና ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ከኦነግ ውጭ  ያሉት የፖለቲካ ቡድኖች ምንም አይነት ድርድር  ሳያደርጉ  “ተደምረናል” ብለዋል። ተደምረዋል ሲባል አንድ ከገዥዎቹ ጋር መሰረታዊ ልዩነት ያለው ቡድን  የሚያደርገውን ድርድር ሳያደርጉ ነው።
ድርድር በአንድ ወቅት የሚታየው ክስተት፣ መልካም ሁኔታ ላይ ብቻ የሚወሰን አይደለም። ቀጣይነቱም ላይ እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል። የዶክተር አብይ አህመድ መንግስት በውጭም በሀገር ውስጥም ለነበሩት ቡድኖች የሰጠው ተስፋና፣ “ተደምረናል” ያሉበት የመጀመርያው ነገር “ስለ አንድነት፣ ስለ ነፃነት” መሰል ነገሮች መስበክ ነው።  በተጨማሪም የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት መጀመራቸው የፖለቲካ ቡድኖቹ ያለ መሰረታዊ ድርድር “ተደምረናል” እንዲሉ ያደረጓቸው ምክንያቶች ናቸው።
 አብዛኞቹ የፖለቲካ ድርጅቶች በቀናነት የተመለከቱት የፖለቲካና የሕሊና እስረኞች መፈታት ጉዳይ በሕዝብ ትግል እና በእነ ዶክተር አብይ እንጅ ድርጅቶቹ ተደራድረው የተወሰነ ባለመሆኑ አሁንም ለሁሉም ተፈፃሚ አልሆነም። የፖለቲካ ድርጅቶች ለረዥም ጊዜ በመደራደሪያነት ያቀርቡት  የነበረው “ሁሉም የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ይፈቱ” የሚል ጥያቄ እውን አልሆነም። እነ ዶክተር አብይ እንፈታለን ሲሉ “ካላችሁ መልካም ነው” ብሎ ማጨብጨብን የመረጠው፣ ጠረጴዛ ላይ ቁጭ ብሎ መክሮ አስገዳጅነት ያላስቀመጠቅ የፖለቲካ ሀይል አሁንም “ለምን ሁሉም አይፈቱም?” የማለት የሞራል  የበላይነት አላገኘም። አሁንም እስረኞች እየማቀቁ ከገዥዎቹ ጋር እየተጨባበጠ ከመቀጠል ውጭ አማራጭ አልፈለገም።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሀይሎች ለድርድር ያቀርባቸው የነበሩት የተቋማትና ሌሎች መሰረታዊ ለውጦች ጠረጴዛ ላይ ተቀምጦ  ተደራድሮ እንዲወሰኑ፣ አስገዳጅነት፣ የጊዜ ገደብ እንዲኖራቸው አላደረገም። ከዚህ ይልቅ እነ ዶክተር አብይ በራሳቸው ተነሳሽነት  እናደርገዋለን ለሚሉት ከማጨብጨብና ከማጀብ ያለፈ መሰረታዊ ለውጥ እንዲመጣ ጉዳዮችን ቆጥሮ፣ አስገዳጅነት እና ቀነ ገደብ አስቀምጦ አልተደራደረም። ለተፈፃሚነታቸው አልጠየቀም።
በተለይ በትጥቅ ትግል የቆዩት አሉን የሚሏቸው ወታደሮች የወደፊት እጣ ምን መሆን እንዳለበት እንኳ በቅጡ ሳይነጋገሩ ወደ ሀገር ቤት መግባቱን ቅድሚያ ትኩረት ሰጥተውታል። ኦነግ ብቻ በጎን ድርድር እያደረገ ይገኛል።  ከጫካ ጀምሮ ትህነግ/ህወሓትን የሚያውቀው ኦነግ “ተደመር” ሲባል እነ ዶክተር አብይን ዘሎ  በማቀፍ ብቸ አልተመለሰም። ወይንም በዚህ ብቻ አልተወሰነም። ከዚህ ይልቅ ወታደሮቹ ወደፊት የሚኖራቸውን እጣና ሌሎችም ጉዳዮች ተደራድሯል።  በድርጅቱ ውስጥ ነበሩ የተባሉት ወታደሮች፣ አባላትን የወደፊት የኑሮ ሁኔታ ያገናዘበ ድርድር ማድረጉ እየተነገረ ነው። ይህ ከአንድ ከትጥቅ ትግል ወደ ሰላማዊ መንገድ የሚመጣ ድርጅት ከመንግስት ጋር ሊያደርገው የሚገባ ትንሹ የድርድር ጉዳይ ነው።
 አርበኞች ግንቦት 7 እና አዴኃንን ጨምሮ ሌሎች ቡድኖች ግን የወታደሮቻቸው ቀጣይ እጣ ምን መሆን እንዳለበት  እንኳ ከመንግስት ጋር ቁጭ ብለው አልተወያዩም።  ወታደሮቹ ቤታቸውን ጥለው ትግል ላይ የቆዩ ናቸው። አውሮፓና አሜሪካ የቆየ፣ ወይንም ኤርትራም የነበረና ኑሮው የማይናጋ፣ በፖለቲካ አመራርነት የሚቀጥል ሁሉ ወታደሩ ወደ ሀገር ቤት ገብቶ ጎዳና ላይ ይውደቅ፣ የቀን ስራም ይስራ ሳያስጨንቀው ከመንግስት ጋር መተቃቀፉን ቅድሚያ ሰጥቷል።
በቤተሰብ ደረጃ በተፈጠረ ግጭት ባልና ሚስት ሲጣሉ  እንኳ ከሁለቱ ባሻገር የሌላ ሰው ችግርም ይኖራል። ለአብነት ያህል በባል ወይንም በሚስት ቤተሰቦች ያልተገባ ባህሪ የሚፈርስ ቤት፣ የሚኳረፉ ጥንዶች ይኖራሉ። ባል ወይም ሚስት ከራሱ/ከራሷ ውጭ ባለ አካል ይዘውት የነበረው ባህሪ ቀይሬያለሁ፣ አሻሽያለሁ ስላሉ ብቻ ተመልሰው አይጋቡም። ለትዳር መፍረስ፣ ወይንም መኳረፍ ምክንያት የነበሩ የቤተሰብ አባላት ከዛ ክፉ ባህሪያቸው መላቀቅ፣ መማር፣ ወይንም ከባልና ሚስቱ መራቅ፣ በመሃል እንደማይገቡ እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል። ይህ በባህላዊ ድርድር ወይንም ሽምግልና የሚሆን ነው። ይህ ሲሆን ጉዳዩ በዝርዝር ቀርቦ ነው።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ የተበላሸው ትህነግ/ህወሓት በሚባል ቡድን ነው። ይህ ቡድን አሁንም ባህሪውን አልቀየረም። እነ አብይ ከትህነግ ጋር ነው የሚሰሩት። እነ ዶክተር አብይ ትህነግ እስካሁን ይከተለው ከነበረው የተለየ የሚመስልና ተስፋ ሰጭ አካሄድ ስለጀመሩ ብቻ ተስገብግቦ ከማቀፍ በፊት ትህነግ የሚባለው ክፉ ድርጅት ከዚህ ባህሪው መቆጠቡን እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል። በእርግጥ የፖለቲካ ድርጅቶቹ በጭብጨባ በተጠመዱነት ወቅት  ትህነግ እነ አብይ የጀመሩትን ለውጥ ለማደናቀፍ ሲጥር ታይቷል። ለእነ ዶክተር አብይም፣ ለተቃዋሚዎችም ሆነ  ለኢትዮጵያ ይጠቅም የነበረው ቀጣይ የፖለቲካ ግንኙነቶች በድርድር ቢወሰኑ ነበር። ዶክተር አብይ “ኑ ግቡ” ብሎ ያመጣው ድርጅት ተስፋው ዶክተር አብይ እንጅ ሕግ አልሆነም። እነ ዶክተር አብይ ቢሸነፉ ትህነግ/ህወሓት “ጨዋታ ፈረሰ” ለማለት የሚያመቸውን እድል አግኝቷል። ዛሬ ይቅርና በቀደመ ፖለቲካ የተኳረፉ፣ ይቀናቀኑ የነበሩ ቡድኖች ግለሰቦች ተማምለው፣ በሽማግሌ ተደራድረው ነው ቀጣይ እጣቸው ይወስኑ የነበረው።
የእነ ዶክተር አብይ አህመድ መደመር ያልተፃፈ ህግ ነው። አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት ተብሎ የተፃፈ ሕግና አፈፃፀም አልተቀመጠለትም። አስገዳጅነት የለውም።  የሚቀጥለውና የሚወሰነው እነ ዶክተር አብይ እስካሉ ድረስ ነው። ሁሉም ነገር በእነ ዶክተር አብይ ይሁንታ፣ በጫጫታ እና በፖለቲካ ድርጅቶች ስሜታዊ ግንኙነት የተመሰረተ ነው። ባለፈው የነበረውን አፈና ከማሰብ እንጅ ወደፊት በምን መልኩ እንቀጥል ተብሎ አልታሰበበትም።  ይህ ደግሞ በአንድ ክስተት የሚፈርስ፣ አስገዳጅነት የሌለው፣ ሀላፊነት የሌለበት አድርጎታል።
በኢህአዴግና ተቃዋሚዎች መካከል በተደረገ ትግል ሕይወት ጠፍቷል። አካል  ጎድሏል። ሀገር ተናግቷል። ይህ ሁሉ በተፈፀመበት ሀገር አንድ ተስፋ አለው የተባለ የገዥዎች መሪ በየመድረኩ በሚያደርገው ተስፋ ሰጭ ንግግር  እና ገዥዎቹ ራሳቸው ያበላሹትን አንዳንድ ነገር ከወትሮው የአፈና ፖለቲካ አንፃር ሲታይ የተሻለ በሚመስል ሁኔታ እያስተካከለ ነው ስለተባለ የፖለቲካ ድርጅቶች  ከገዥዎች ጋር ዘለው የተቃቀፉበት መንገድ  አስገራሚ ነው። በተለያየ ረድፍ ተሰልፎ የተገዳደለ ገዥና ተቃዋሚ ቀርቶ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች እርስ በእርስ የሚያደርጓቸው መስተጋብሮች እንኳ እንዲሁ በተስፋና እና  በእምነት የሚከወኑ አይደለም። ድርድር፣ ቀነ ገደብ፣ ቅድመ ሁኔታ፣ ተፈፃሚነት፣ አስገዳችነት ሊኖራቸው የግድ ነው።
 የ”መደመር” ፖለቲካው  በአንድ ሀገር ጉዳይ ጠርዝና ጠርዝ ይዘው ሲፋለሙ የነበሩ ድርጅቶች ሊያደርጉት ይገባ ከነበረው የተለየና ለቀጣይነቱም ዋስትና የሌለው ነው። ድግስ የሚጠራ ግለሰብ እንኳ ወደ ድግስ ቤት ከመሄዱ በፊት “ማን ተጠርቷል? ማንስ አልተጠራም?” ብሎ ይጠይቃል። የማይፈልገው ሰው ካለ፣ መጠራት የነበረበት ሰው ሳይጠራ ከቀረ ይጠይቃል እንጅ በጠሪው ይሁንታ ብቻ ዝም ብሎ አይሄድም። በዚህ ረገድ  የመደመር ፖለቲካ ብዙዎቹ “ማን አለ፣ ምን አለ” ሳይሉ  በጠሪው ቀናነት ብቻ ተስገብግበው  የታደሙበት እየሆነ ነው። ምንም ሳያቅማማ፣ ሳይጠይቅ ዘው ብሎ የገባ ተጋባዥ ደግሞ “ያዝ” ያሉትን ከመያዝ ውጭ የተጠራበትን በግልፅ ለመተቸት የሞራል ብቃት አያገኝም።
እነ አብይ አህመድ በየ መድረኩ የተናገሩት መልካም ቃል፣ እስረኞችን የማስፈታት ጅምር፣ የአንድነትና ለዜጎች ክብር የመስጠት ቃልን ገዥ አድርጎ “እደመራለሁ” ያለው የተቃዋሚ ኃይል ነገ  ጉዳዮችን ቆጥሮ “ይህ አልተገፀመም” ብሎ መጠየቅ አይችልም። አልተደራደረበትም። አስገዳጅነት፣ ቀነ ገደብ አላስቀመጠም።  በእነ አብይ ይሁንታ እንጅ ተደራድሮ ስላልመጣ ዘው ብሎ ወደ ድግስ ከገባ እንግዳ የተለየ መጠየቅ፣ ማማረጥ አይችልም።  ከአሁን ቀደም የነበሩት የገዥ አለቆች ክፉነትና የእነ ዶክተር አብይን ቀናኢነት እንጅ  የወደፊቱን፣ የለውጡን ቀጣይነት፣ የራሱን ሚናና ጥቅም አሰላስሎ አልገባም። ቀጣዩን ለውጥ መሪ ወይንም አሳላጭ ሳይሆን አጨብጫቢ ሆኖ ነው የተደመረው። ነገ ማጨብጨቡን ከመቀጠል ወይንም ከመተው ያለፈ ለራሱ የሚያስጨበጭብለትን ስራ ለመስራት ቅድመ ሁኔታም ይሁን ሞራል ይዞ አልመጣኝ።
የተቃዋሚ ሀይሉ “ተደምሬያለሁ” ሲል የሕግ ማዕቀፍ ይዞ ሳይሆን በእነ ዶክተር አብህ ቃልና ጅምር እንቅስቃሴዎች ተማርኮ፣ አጨብጭቦላቸው፣ ተቀብላቸው ነው። ይህ የተቃዋሚ ሀይል የሚመጣው በእነ ዶክተር አብይ አህመድ ተማርኮ እንጅ ለቀጣይ ለውጥ አስገዳጅ፣ ተፈፃሚ ነገሮችን አስቀምጦ አይደለም።  ምርኮኛ ደግሞ ማራኪው እንዳለው ከመቀጠል የተለየ ብዙ አማራጭ የለውም። ለማራኪው እየዘመረ፣ ካልዘመረም ዝምታን መርጦ ከማለፍ የተለ አማራጭ አያገኝም።
እነ ዶክተር አብይ  አህመድ ተቃዋሚው በአንድም ይሁን በሁለት እጁ የያዘውን አግድሞ ጥሎ እጁ እስኪላጥ እያጨበጨበ ወይንም አጋጩን ይዞ እንዲመለከታቸው አደረጉ እንጅ ውል አልገቡለትም።  የታጠቀውንም  ያልታጠቀውንም ያለ ውል ትጥቁን አስፈትተው ማርከውታል። ይህ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ይሆናል ተብሎ ያልታሰበና ትልቅም  ድል ነው። ለእነ አብይ! እነ ዶክተር አብይ ተቃዋሚውን ያለ ፊርማና ውል  ከኋላቸው ሲያግተለትሊ ይህን ተቃዋሚ የማይወደውንና የማይፈልገውን ትህነግንም ለጊዜው ዝም አሰኝተዋል።  ትህነግ በጦርና በሀይል ያልፈታውን እያፏጩ ሰተት ብሎ እንዲገባ ያደረጉ  የተዋጣላቸው አዳኞች መሆናቸውን አሳይተዋል። ይህ ተቃዋሚ ነገ በሁለት እጁ የያዘውን ጥሉ ከማጨብጨቡ፣ ያለ ውል እየተጎተተ ከመግባቱ በፊት ድርድር ማድረግ ነበረበት። ድርድር አንድ የፖለቲካ ድርጅት ከሌላ ጋር የሚሰራበት የመጀመርያው መሳርያ ነው።  ይህን መሳርያ ጥሎ የገባው የፖለቲካ ሀይል እንደ ቀላዋጭ የሰጡትን ከመቀበል  ውጭ ሌላ አማራጭ የለውም።
እነ ዶክተር አብይ በበኩላቸው የመደመርን ፖለቲካ ለፅድቅ የሰሩት ያህል እየተመረቁበት፣ ሲያሳንሱም እየተለመኑ ይቀጥላሉ። በይሁንታ! ይህም እነሱ የበላይነት እስካገኙ ድረስ የሚቀጥል በመሆኑ ተቃዋሚው   በእነ ዶክተር አብይ የሚያገኘው ጥቅም እነሱ እስካሉ ድረስ የሚቀጥል በመሆኑ ክፉ እንዳይነካቸው ለገዥዎቹ ለእነ ዶክተር አብይ  መልካም እድል እየተመኘ፣ ከዚህ ሲያልፍም “ክፉ አይንካችሁ” እያለ እየፀለየ በተመፅዋችነት የሚቀጥልበት ቅርቃር ውስጥ ገብቷል።
Filed in: Amharic