>

ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ጥቁሩ የነጭ ጌታ!! (አቻምየለህ ታምሩ)

ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ጥቁሩ የነጭ ጌታ!!
አቻምየለህ ታምሩ
የማንነት ቀውስ ዋግ እንደመታው አገዳ ያኮሰሳቸው የዘመናችን የጥላቻ ብሔርተኞች የበታችነት ስነልቦናቸው ታሪክ በማርከስና ጀግኖችን በመዝለፍ የሚሽርላቸው እየመሰላቸው በዘመናቸው በድቅድቅ የባርነት ጨለማ ውስጥ አሳራቸውን እያዩ፤ በላያቸው ላይ የተጫነውን አገዛዝ የጭቆና ቀንበር ለመስበር ብርቱ ጥረት ከማድረግ ይልቅ ያለዘመናቸው ወደኋላ ተጉዘው ስላልኖሩበት ዘመን ፖለቲካ የወለደውን የሀጢዓት ክስ እየነዙ ማላዘናቸውን የታዘበ፤ እነዚህ ሰዎች በዘመናቸው አይናቸው እያየ ከሚፈጸመው በደል ይልቅ ከ140 ዓመታት በፊት የሆነውና በስሚ ስሚ ተወላጋግዶ ጆሯቸው ደርሶ የሰሙትን ወሬ ሳያያዩ የሚያምኑ፤ የሚያዩትን ግን ማስተዋል ስለሌላቸው ማመን ተስኗቸው ያለዘመናቸው የሚኖሩ «የፖለቲካ ብፁዓን» ብሎ ቢጠራቸው የሚበዛባቸው አይሆንም።
የግራ ፖለቲካ የወለደው ያለፈ አርቲቡርቲ ተጭኗቸው ነገን ሳይሆን ዘወትር በትናንተና ለመኖር የሚያተጋቸው የተወናከረው ፖለቲካቸውና የተኮላሸው የዛሬ ተግባራቸው ትናንትና «ተበድለናል» ከሚሉት በላይ የዛሬውን ሞታቸውን እያቀላጠፈ መሆኑን ግን ገና የተገነዘቡት አይመስልም። እነዚህ የጥላቻ ብሄርተኞች፤ የነጻነትን ብርሃን ፤ የዘመናዊነትን ጎዳና፤ የአንድነትን መሠረት ከወረሪና ከተስፋፊ ቅኝ ገዢ አውሮፓውያን በብርቱ ታግለው የክብርን አክሊል፤ የኩራትን መንፈስ ያወረሱንን ደጋጎቹን አያቶቻችንንና ታላቁን መሪያቸውን ዳግማዊ ምኒልክን በማንጓጠጥ ስለደከሙ ዛሬ በአለም ላይ በስደት፤በርሃብና በውርደት እንድንታወቅ ባደረገን፤ ፋሽስት ጥሊያን ከፈጸመብን ጭካኔ በላይ ክፉ እያወረደብን ባለው አረመኔያዊ አገዛዝ ላይ የሚያሳርፉት አቅም በማጣታቸው ወያኔን «በጥልቅ ሊታደስ» እንጂ በጠንካራና በተባበረ ክንድ ሊወገድ የማይችል ሀይል አድርገው ቢመለከቱት የሚፈረድባቸው አያደርጋቸውም።
በዚህ የሰለጠነ ዘመን በተጫናቸው ባሪያ አሳዳሪ ፋሽስታዊ አገዛዝ ላይ ድል መቀዳጀት ያልቻሉ ደካማና ልፍስፍስ የጥላቻ ግብረሃይሎች ሁሉ ጀግኖች አያቶቻችንን ለመዝለፍ ሲንጠራሩ ይበልጥ እየተዋረዱ መሆናቸውን እንኳ አለመረዳታቸው የሚያስገርም ነው።
ያለፈውን ታሪክ ስኬት እንደመነሻ አድርጎ ከዚያ በላይ ለመስራት መነሳት የማይፈልግ ትውልድ ባለፈው ትውልድ ብቻ ሳይሆን በራሱ ትውልድ ታሪክም ሲያፍር የሚኖር ትውልድ ነው። የዳግማዊ ምኒልክ ጥላቻ ርዕዮታለማቸው የሆነ የእርስ በእርስ መተላለቅ ነጋሪት ጎሳሚዎችና የጥላቻ ዶክተሮች ፖለቲካ የሚፈጥረው ትውልድ ግን የሚያፍረው ባለፈው ትውልድና በራሱ ትውልድ ታሪክ ብቻ ሳይሆን የወደፊቱንም ትውልድ እጀ ሰባራ አድርጎ በታሪኩና በአገሩ ሲያፍር እንዲኖር የሚያደርግ ነው።
ተወደደም ተጠላም ዳግማዊ ምኒልክ ወደፊትም ለማግኘት የሚያዳግት፤ በታሪክም ያልታዩ የመላው ጥቁር አለም ክስተት ናቸው። በካድሬዎቹ «ታላቁ መሪ» እየተባለ የሚሞካሸው ጨካኙ አውሬ መለስ ዜናዊ በቢሊዮን ዶላር የውጭ ርዳታና ብድር እየጎረፈለት፤ ከሌላው አለም ሊያገኘው የሚችለውን «ስልጣኔ» ሁሉ እያገኘ ማድረግ ያልቻለውን ነገር አጤ ምኒልክ ግን በጠላት ተከበው፤ ከግራ ከቀኝ የሚመጣባቸውን ጠላት በትክሻ፣ ባህያና በበቅሎ የተያዘ በሶ፣ ቆሎና ጥሬ እየበሉ፤ በወጣ ገባውና አስቸጋሪው አገራችን እየተንገላቱ፤ተበታትኖ ይኖር የነበረውን ህዝብ ከነበረበት paradigm አውጥተው ወደ ሌላ paradigm በመክተት ለኑሮ አስፈላጊያቸው የሆነውን ነገር ሁሉ በሀገራቸው ውስጥ ሰርተውና አሰርተው ራሳቸውን ችለው በመኖር በሰላምና በአንድነት የቆመች ታላቅ አገር መመስረት ችለዋል።
ድሮ፤ ያኔ ድሮ፤ ይህ የታያቸው አለቃ ገበረሃና « ገብረሃና ሞቷል» ብለው ቤተ መንግስት ወሬ እንዲወራና ለተዝካራቸው ማውጫ የሚሆነ አጤ ምኒልክ ወደ ትውልድ መንደራቸው ናባጋ ጊዮርጊስ ጠገራ ብር እንዲልኩ ካስደረጉ በኋላ፤ ጠገራ ብራቸውን ጨርሰው ወደ ምኒልክ ቤተ መንግስት በመምጣት እጅ ነስተው ቆሙና «ምነው አለቃ ሞተሀል አልተባለም?» ብለው ዳግማዊ ምኒልክ ቢጠይቋቸው «ጃንሆይ በሞትሁበት ሰማይም ሆነ በኖርሁባት ምድር እንደምኒልክ የሚሆነኝ ሰው ባጣ ተመልሼ መጣሁ» ሲሉ መለሱላቸው አሉ።
ዳግማዊ ምኒልክም ስቀው «የአንተ መላ ወትሮስ መቼ ጠፋንና» ብለው መሽቶ ኖሮ ወደ ግብር ቤታቸው አመሩ።
አለቃም እዚያው ታድመው አመሹና አዝማዋን «ተቀበይ» በማለት የሚከተለውን ውስጠ ወይራ ሁለት ዘለላ ግጥም በማፍሰስ «ሞቷል» ካስባሉ በኋላ «ሄደው ባዩት» አለምም ሆነ ከዚያ በፊት ምድር ላይ እንደምኒልክ የሚሆናቸው ሰው እንዳጡ እንዲህ መሰከሩ…
ምንሊክ መጓዙን የምትጠይቁኝ፤
ፊትም አላለፈ ኋላም አይገኝ።
አለቃ እውነት አላቸው። ጥቁሩ ሰው ዳግማዊ ምኒልክ ነጭን ድል በመንሳት የነጭ ጌታ የሆኑ የምድሪቱ ብቸኛው ጥቁር ንጉስ ነገስት ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ ዳግማዊ ምኒልክ አሸንፈው ብቻ ሳይሆን ተሸንፈውም ማሸነፍ የሚችሉ ብልህ መሪ ነበሩ።
ይህ የአጼ ምኒልክ የአእምሮ የበላይነት ነው እንግዲህ የዝቅተኝነት ስሜትና ጥላቻ ቀስቅሶ ለኦነግና ለወያኔ ፖለቲካ የሆነው። አጼ ምኒልክ ማንንም ሳያስገድዱ በብልህነታቸውና በሩህሩህነታቸው ብቻ እምዬ ተብለዋል። የምኒልክን ሩህሩህነት ወዳጆቻቸው ብቻ ሳይሆኑ ተቃኞቻቸውና ጠላቶቻቸው ፈረንጆችም አይተውታል።
ተቀናቃኞቻቸው አጤ ቴዎድሮስ ሸዋን እንዲገዙ የሾሟቸው በዛብህ አባ ደክር፣ የወላይታው ገዢ ካዎ ጦናና የጎጃሙ ንጉስ ንጉስ ተክለ ኃይማኖት የምኒልክ ሩህሩህነት ደርሷቸዋል።
ይህ የዳግማዊ ምኒልክ የአእምሮ ሀይል የበላይነት የቀሰቀሰው የዝቅተኝነት ስሜትና ጥላቻ ስሜት የወለዳቸው ወያኔና ኦነግ ግን የኒህን ታላቅ ሰው አሻራ ሊያጠፉ ተነሱ። ታሪካቸው ይሰረዝ ዘንድም ብራና ፍቀው ቀለም በጥብጠው በጥላቻ ሞተር እየታገዙ ዘመቱባቸው።
የጥላቻ ሀውልት አቆሙባቸው፤ ስማቸው እንዳይነሳም የሚያስቀስፍ እግድ ጣሉ።
የአያቶቹን እውነት አላስቀብር ያለው ብላቴናው ቴዎድሮስ ካሳሁን ግን አስታዋሽ ነውና …ከኦነግ ‹‹ምኒልክ ሂትለር ነው›› እስከ ወያኔ ‹‹ምኒልክ ቅኝ ገዢ ነው›› ድረስ ለተጎሰሙ የጥላቻ ነጋሪቶች ዘመን በማይሽረው «የጥቁር ሰው»ዘፈኑ. . .
ኢትዮጵያ ሀገሬ የአፍሪካ መገኛ ናት፣
የነፃነት አርማ የሉአላዊነት፤
ያናብስቶች ምድር የአርበኞች ተራራ፣
በአለም አደባባይ ግርማሽ የተፈራ፤
የጥበብ ምልክት የፍቅር ማደሪያ፣
ኑሪ ለዘላለም ቅድስት ኢትዮጵያ፤
ዳግማይ ምኒልክ፣ ዳግማይ ምኒልክ፣
ምኒልክ፣ ምኒልክ፣ ዳግማይ ምኒልክ… ሲል በይፋ የዳግማዊ ምኒሊክን የሀገር ባለውለታነት ታሪክ ጠቅሶ ተከራከረ።
ቴዎድሮስ ካሳሁን ይህንን የዳግማዊ ምኒልክን ዘመን የማይሽረው ታሪክ በመመስከሩ ብዙ እንግልትና ስቃይ ደርሶበታል። በችሎታው ያገኝው ስፖንሰር ከቴዎድሮስ ካሳሁን ጋር እንዳይሰራ ተደርጓል፤ ካገር እንዳይወጣ ታግዶ የውጭ አገር ትርዒቶቹ ተሰርዘውበታል፤በአገር ውስጥም ሊያቀርባቸው ያዘጋጃቸው አገር አቀፍ ትዕይንቶቹ ፍቃድ ተነፍጓቸዋል።
ይህንን ሁሉ መስዕዋትነት የከፈለው እንደ ወያኔ ድሀ እየመተረ፣ እርጉዝ እየገደለ አገር ስለዘረፈ አይደለም። ቴዎድሮስ ካሳሁን ይህንን ሁሉ መስዕዋትነት የከፈለው የአያቶቹን እውነት አላስቀብር ብሎ የዳግማዊ ምኒሊክን የሀገር ባለውለታነት የሻረውን የወያኔንና የኦነግ የተባበረ ፕሮፓጋንዳ ብቻውን ደምንሶ ከመቶ ሀያ አመታት በፊት የሆነውን ያንን የመላው ጥቁር ህዝብ ታላቅ ገድል ዛሬ የሆነ ያህል እንዲሰማን የሚያደርግ መንፈስ የመጫን ኃይል ያለው ድንቅ የዘፈን ክሊፕ በታሪክ ምንጣፍ ላይ በመቅረጹ ነው።
ዳግማዊ አጤ ምኒልክን የሚያወግዙ የዘር ፖለቲከኞች ማገናዘብ የማይፈልጓቸው አስር ነጥቦች አሉ፤
አንድ፡-
ከመቶ በላይ የነበረውን የተበጣጠሰ ብሔረሰብ ቀድመው በዘመኑ ይሰራበት በነበረው በኃይልም ሆነ በዲፕሎማሲ ባንድ ጥላ ስር ባያሰባስቡት ኖሮ ቅኝ ገዥዎች እያናጠሉ ሁላችንንም ቅኝ ይገዙን እንደነበረ አለማሰብ፤
ሁለት፡-
በዋናነት በሸዋ አማሮች፣ በሸዋ ኦሮሞዎችና በሸዋ ጉራጌዎች የሚመራው ጦራቸው እንደ ነጭ ወራሪ በቀለም ልዩነት የዘር ግንብ የሚገነባ ሳይሆን ካስገበረው ህዝብ ጋር ተጋብቶ፣ ቋንቋውን ተላምዶ፣ሀገሩን ሀገሬ ብሎ ኗሪ መሆኑንና በዚህም የተነሳ ዛሬ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔረሰብ በነጮች ፊት ቀና ብሎ እንዲሄድ ማስቻሉን ለመረዳት አለመፈለግ፤
ሶስት፡-
ንጉስ ምኒልክ ያስገበሯቸው ግዛቶች እንደ ሀገር ህልውና ያልነበራቸው ስለነበሩ መልስው ወደግዛታቸው ጠቀልሏቸው እንጅ በቅኝ ግዛት ያዟቸው የሚባለው ትረካ እንደሆነና አንዳችም የቅኝ ግዛት ማሳያ በኢትዮጵያ ውስጥ አለመከሰቱን አለማገናዘብ፤
አራት፡-
የስኬት ጉዳይ እንጅ መስፋፋት የሁሉም ብሄሮች አጀንዳ እንደነበረ ለመረዳት አለመፈለግ፤
አምስት ፡-
በተለይ የኦሮሞ ምሁራን የኦሮሞን assimilation ታሪክ በደግ እያነሱ ምኒልክ ማንነታችንን ጨቁነዋል ሲሉ የሚያቀርቡት ግን double standard መሆኑን ለማጤን አለመቻል፤ የምኒልክ ወደ ደቡብ መዝመት ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያዊ የነበረው ኦሮሞ ከሰሜን ወደ ሰሜን በአገሩ ውስጥ ተስፋፍቶ የያዛቸውን አካባቢዎች የኦሮሞ ነባር ይዞታ አድርገው እንዳጸኑ አለመገንዘብ [ በነገራችን ላይ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ መወቀስ ካለባቸው ንጉሰ ነገስቱ የአያቶቻቸውን አገር መልሰው አንድ
ለማድረግ ሲዘምቱ ከዘመቻቸው ሁለትና ሶስት መቶ አመታት በፊት ኦሮሞ ተስፋፍቶ የያዛቸውን የሌላ ብሔረሰቦች አካባቢዎች የኦሮሞ ይዞታ አድርገው ማጽናታቸውና በሌሎች ላይ ኦሮሞ ገዢ አድርገው መሾማቸው ነው]
ስድስት፡-
የንጉስ ምኒልክ ዘመን የመገበርና የማስገበር እንጅ የሪፈረንደም ዘመን አለመሆኑን ከሰለጠኑት ከጀርመኑ ቢስማርክና ከጣልያኑ ጋሪባልዲ ታሪክ ለመማር አለመቻል፤
ሰባት ፡-
በነጮች የተገዙትን እነ ሶማሊያና ሩዋንዳን እያዩ ምኒልክ ከሚገዛን በነጭ በተገዛን ብሎ መመኘት፤
ስምንት፡-
በምኒልክ አስተዳደር ውስጥ የነበሩ የሌሎች ብሄረሰብ አባላትን ተሳትፎ በማሳነስ «የአገር ማቅናት» ዘመቻውና አስተዳደሩ የአንድ ብሄር ብቻ እንደነበረ ማስመሰል፤
ዘጠኝ፡-
የንጉስና የባላባት አስተዳደር [Empire State ] በሁሉም ብሔረሰቦች ዘንድ ይሰራበት የነበረ መሆኑ ተዘንግቶ ምኒልክ እንዳመጡት አድረጎ ማስቀመጥ፤ ለዚህ
ምሳሌ የሚሆን የከፋው ንጉስ ጋኪ ሸረቾ ከምንሊክ ጦር ጋር ለመዋጋት በተቃረቡበት ወቅት በወቅቱ ምስራቅ አፍሪካ ኡጋንዳ ተቀማጭነት የነበረው የእንግሊዝ ወታደሮች አዛዥ ለከፋው ንጉስ ድጋፍ ሊያደርጉላቸው ሲጠይቋቸው የሰጧቸው መልስ ነው።
ጋኪ ሸረቾ ለእንግሊዙ ወታደራዊ አዛዥ ሲመልሱ፤ እርዳታውን እንደማይፈልጉ በመግለጽ «እሱ ካሸነፈኝ ሀገሩን ጠቅልሎ ይገዛል፤ እኔ ካሸነፍኩት ደግሞ የሱን አገር እጠቀልላለሁ» ካሉ በኋላ «ይህ የርስ በርስ ውጊያ ነው፤ ባይሆን ከውጭ ከባህር ማዶ ለሚመጡት መዋጊያ ትረዳናለህ» በማለት የወቅቱን የምስራቅ አፍሪካ የእንግሊዝ ወታደራዊ አዛዥ መልሰውታል። የዛሬዎቹ የጥላቻ ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮች ግን በዚያ ዘመን ጋኪ ሻሪቾ የነበራቸውን አይነት ቅንነትና እውነት የላቸውም።
አስር፡-
ምኒልክ በአሁኑ ደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ያደረጉት የግዛት ማስመለስ ዘመቻ ከሰሜን ህዝቦች ጋር እንዳደረጉት ሁሉ ግዛት ከማስፋት ባለፈ ሌላ አላማ እንደሌለው እየታወቀ ጦርነቱ ዘር ለማጥፋት እንደተደረገ ማስመሰል።
ዘለዓለማዊ ክብር በብልህነታቸው ታይቶ ተሰምቶ የማይታወቅ ታሪክ ለጻፉት ዳግማዊ አጤ  ምኒልክ!
Filed in: Amharic