>
5:13 pm - Saturday April 19, 9203

"ንጹሃን ዜጎች በጸረ ሽብር ህጉ እንዲከሰሱ የተደረገው ዶ/ር አብይ ባስተላለፉት የቀጥታ ትዕዛዝ ነው!!!" (የሰብአዊ መብት ተሟጋችና ጋዜጠኛ እስክንድ ነጋ)

“ንጹሃን ዜጎች በጸረ ሽብር ህጉ እንዲከሰሱ የተደረገው ዶ/ር አብይ ባስተላለፉት የቀጥታ ትዕዛዝ ነው!!!”
የሰብአዊ መብት ተሟጋችና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ
 (ኢትዮ 360 – ነሐሴ 14/2011) :-ንጹሃን ዜጎች በጸረ ሽብር ህጉ እንዲከሰሱ የተደረገው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባስተላለፉት የቀጥታ ትዕዛዝ መሆኑን የሰብአዊ መብት ተሟጋችና ጋዜጠኛ እስክንድ ነጋ አስታወቀ።
 የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት ባልደራስ ሰብሳቢ አቶ እስክንድር ነጋ ከኢትዮ 360 ጋር በነበረው ቆይታ እንደገለጸው የጸረ ሽብር ህጉ ፍትሃዊነት ይጎለዋል በሚል ይስተካከላል ተብሎ ነበር።
 ነገር ግን ይሄን ህግ ይስተካከላል የተባለው ነገር ሳይስተካከል ስራ ላይ ለማዋል የጠቅላይ ሚኒስትሩን ይሁንታ ይጠይቃል።ለዚህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሙሉ ፈቃደኝነት ንጹሃን ዜጎች ወደ እስር ቤት እንዲጋዙ ፍቃዳቸውን ሰተዋል ይላል።
 ይህ የሚያሳየው ደግሞ በአሁን ሰአት ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ባለስልጣኖቻቸው ከህግ በላይ መሆናቸውን ነው።
 እነዚህ ያለምንም ጥፋታቸው፣ በፖለቲካ አቋማቸው ብቻ የህሊና እስረኞች እንዲሆኑ የተፈረደባቸውን ዜጎች ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ተገኝቶ ማነጋገሩን ይገልጻል የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አቶ እስክንድር ነጋ።
 አቶ እስክንድር እንደሚለው ከሆነ እስረኞቹን ባነጋገረበት ወቅት አንድ ነገርን መታዘብ ችሏል።- የእስረኞቹን የሞራል ጥንካሬና የአላማ ጽናት ብሎም እውነተኛነት።
 የህሊና እስረኞቹን የምርመራ ሒደት ምን እንደሚመስል መጠየቁን የሚገልጸው እስክንድር በህሊና እስረኞች ላይ ፍርድ ቤት ያቀረበው ክስና በምርመራ ወቅት የሚቀርቡ ጥያቄዎች ፍጹም የማይገናኙ መሆናቸውንም ይናገራል።
 የፍርድ ቤት ክሳቸው በአማራ ክልል ተፈጸመ በተባለው መፈንቅለ መንግስት እጃችሁ አለበት የሚል ሲሆን በምርመራ ወቅት ግን የሚነሳላቸው ጥያቄ ከግለሰቦች ጋር ያላቸውን ግንኙነትና ከእነዚህ ሰዎች ጋር ለምን ስራ ትሰራላችሁ የሚሉና ሌሎች ጉዳዮች መሆናቸውን ይገልጻል።
 ከዚህ ባለፈም ለህሊና እስረኞቹ ትልቅ ህመም የሆነው ከአንድ አመት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተገባው ቃል ከአንደበት ያልዘለለ የውሸት ትርክት መሆኑ ነው ይላል እስክንድር።
 ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን በሱዳን እስር ቤት የነበሩትን ወገኖች አስፈትተው መምጣታቸው ተሰምቷል፣ ይሄ ተግባር የሚያስመግናቸው ቢሆንም እሳቸው በሚመሩት ሃገር፣ በእሳቸው ፊርማ ንጹሃን ወደ እስር ቤት እየተጋዙ መሆኑ ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩን አካሄድ ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው ይላል።
 እስክንድር እንደሚለው ከሆነ በእስር ቤቱ ውስጥ በ2010 በአዲስ አበባ ከተነሳው ግርግር ጋር በተያያዘ እጃቸው አለበት በሚል የታሰሩ ወጣቶች እስካሁን ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ እስር ቤት ታጉረው እንደሚገኙና ለጥቂት ደቂቃ ቢሆን አናግሯቸዋል።
 እነዚህ ወጣቶች ወደ እስር ቤት ሲጋዙ በጸረ ሽብር ህጉ ተከሰው አይደለም።ስለዚህ ወንጀላቸው በግልጽ ተቀምጦ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ማድረግ ሲቻል ይሄ ግን ሳይሆን ቀርቷል።
የሆኑ አካላት ወንጀሉ ውስጥ አሉበት በሚል እንዲታሰሩ ተፈልጓል ለዚህ እስር ደግሞ የአዲስ አበባ ወጣቶች ተመርጠዋል ይላል የሰብአዊ መብት ተሟጋቹና ጋዜጠኛው እስክንድር ነጋ።
 ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሃገሪቱ ስር ነቀል ለውጥ መቷል ብለው በአደባባይ ሲናገሩ ተሰምቷል፣ አሁን በሃገሪቱ ያለው እውነታ ግን ከትላንቱ ምንም ያልተሻለና ጭራሽ በባሰ መልኩ ነገሮች እየተጠጋገኑ መቀጠላቸውን ይገልጻል።
 አሁን ላይ የኢትዮጵያ ጉዳይ ከድጡ ወደ ማጡ እየሄደ ነው የሚለው እስክንድር ለዚህ ማሳያ ደግሞ በእስር ቤት ያለምንም ሃጢያታቸው ከቀድሞ በባሰ መልኩ ግፍ እየተፈጸመባቸው ያሉት የህሊና እስረኞች ናቸው።
 በእስር ቤት ጉብኝቱ ለሁለተኛ ጊዜ የ28 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ የተሰጠባቸውን የጄኔራል አሳምነው ጽጌን ባለቤት እንዳገኘ የሚናገረው እስክንድር እኚህን ሴት ሃዘናቸውን ሳይጨርሱ ወንጀሉ ውስጥ ይኑሩበት አይኑሩበት ሳይጣራ ሚስት በመሆናቸው ብቻ ከቤተሰባቸው ነጥሎ በእስር ቤት ማጎር አግባብነት የሌለውና የፍትህ ስርአቱ እያከተመለት መምጣቱን ማሳያ ነው ይላል።
 እንደ ሃገር እየተደረገ ያለ እውነታ ቢኖር ሰላማዊ ትግል የሚያደርጉ ሰዎችን ማሳደድና ማሰር ነው።-የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት ባልደራስ ደግሞ የዲሞክራሲ ስርአቱ እስኪከበር ድረስ ትግሉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል አቶ እስክንድር ነጋ።
 ከዚህም ሌላ ይላል እስክንድር መጪው ምርጫ ተደረገም አልተደረገም የአዲስ አበባ ጉዳይ አልቋል።ነዋሪዋ የኢንጂነር ኩማን አስተዳደር በክብር መሸኘትና የኢሕአዴግ አገዛዝ አዲስ አበባ ላይ ሙሉ በሙሉ መሸነፉን መንገር ብቻ ነው የሚጠበቅበት።
 እዚህ ላይ ማጭበርበር እንፈጽማለን የሚል አካሄድ ካለ ግን ከአለም አቀፉ ማህበረሰብም ሆነ ከኢትዮጵያውያን የሚኖረው ምላሽ የከፋ ይሆናል ባይ ነው።
 የሌሎቹን የኢትዮጵያ አካባቢዎች ወቅታዊ ሁኔታ ካየን ግን ሃገሪቱ ገና ለምርጫ የተዘጋጀች ሃገር አለመሆኗን መረዳት ይቻላል ሲል እስክንድር ከኢትዮ 360 ጋር በነበረው ቆይታ ገልጿል።
 እስክንድር ሃሳቡን ሲያጠቃልልም ኢሕአዴግ በአዲስ አበባ ብቻ አይደለም በአጠቃላይ እንደ ሃገር መሸነፍ አለበት፣ይህንን ለማድረግ ደግሞ ብዙ ስራ ይጠይቃል ብሏል።
Filed in: Amharic