>
5:13 pm - Sunday April 20, 7113

ክቡርነትዎ የፀረ-ሽብር ህጉን ለአዲስ ዓመት በሚለኮሰው የዳመራ እሳት ውስጥ አቃጥሉ፤ እስረኞቹንም ፍቱልን!!! (ያሬድ ጥበቡ)

ክቡርነትዎ የፀረ-ሽብር ህጉን ለአዲስ ዓመት በሚለኮሰው የዳመራ እሳት ውስጥ አቃጥሉ፤ እስረኞቹንም ፍቱልን!!!
ሬድ ጥበቡ
“የማይሰበረው” ኤርምያስ አመልጋ ለመፅሀፉ ምረቃ በዛሬው ምሽት ከቂሊንጦ እስርቤት የላከው መልእክት የሚደመጥ ሆኖ ተሰምቶኛል። የግፍ ፅዋው ሞልቶ እየፈሰሰ ነው፣ እረ ተዉ እንደማመጥ፣ እንከባበር፣ እንተዛዘን!
ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ በህግ አምላክ! በፀረ ሽብር ህጉ ያሰርካቸውን ሁሉ ፍታና ሃገሩን ወደሰላምና ተስፋ መልሰው። የኢኮኖሚ ድቀቱና ሥራአጥነቱ እንዲሁም የኑሮ ውድነቱ በአዲስ አበቤዎች የምግብ እጥረት ገፅ ላይ ባልተለመደ መንገድ እየታየ ነው። ከቤተመንግስትህ ጀርባ ወዳሉ መንደሮች በእግርህ ወረድ ብትል እነዚህን የተራቡ ህፃናትና ወጣቶች ታያለህ። ወደቢሮህ ህንፃ  ዶክተር አርከበን ለመገናኘት ሰኔ ሶስት ቀን መጥቼ ስመለስ፣ ከቤተመንግስቱ ጀርባ በእግሬ ስሄድ ያየሁትን ረሃብ የምታውቀው አልመሰለኝም። ብታውቀውማ ኖሮ የኢኮኖሚ አማካሪህ ማድረግ የነበረብህን ኤርምያስ አመልጋን በግፍ አስረህ በዱሮውና ቋቅ ባለን የወያኔ እብሪት ለመቀጠል ባልዳዳህ ነበር። አሁንም ልቀቀውና ያማክርህ፣ በዙሪያህ የሰበሰብካቸው የምእራብ አማካሪ ወጣቶች ይዘውህ ገደል ከመግባታቸው በፊት ቆም ብለህ ለደቂቃ አስብ።
የቤተመንግስትህን አዲስ የሲሚንቶ አጥሮች ተደግፈው የሚያድሩት ረሃብተኞች፣ አይናቸው የተከፈተ ቀን ይዘምቱብሃል። ያኔ የለገጣፎም ሆነ የቡራዩ ቄሮዎች አያስጥሉህም። ወታደሮችህ አምፀው ግቢህ የገቡ ቀን ቡራዩና ለገጣፎ ክተት በማለት ላይ ነበሩ በማለትህ ነው ይህን ማለቴ። ለዚህም መፍትሄ ትፈልግለት ይሆናል። የቤተመንግስቱን ዙሪያ ነዋሪ ሁሉ በልማት ስም በማፈናቀል፣ ለ”ልማታዊ ከበርቴዎች” ወይም ለሸገር ወንዝ ልማት ፕሮዤ ብለህ ታፈናቅላቸው ይሆናል። ከዚህ የተሻለና ቀላል መፍትሄ ግን ልጠቁምህ።
እስራትና ብካይ ይብቃ በል። የፀረ ሽብር ህጉን በህዝብ አደባባይ ቅበረው። ሥራአጥነትና ድህነት እንዲወገድ የሃገሪቱን እምቅ አቅም ሁሉ ያካተተና ከዘረኝነት የፀዳ ብሄራዊ ወይም ሃገራዊ የምክክር ጉባኤ አዘጋጅ። በእስር ከሚገኙት መሃል ኤርምያስ አመልጋን፣ ዳንኤል ግዛውንና በረከት ስምኦንን የመሰሉ ባለሃሳቦች እንዲሳተፉበት ጋብዛቸው። ከዳያስፖራም በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩን እንዲሁ አሳትፍ። ይሄ ከትውልድ ትውልድ ሲንከባለል የመጣውን የወዳጅ/ጠላት እሳቤ እምቢ በል። በሃሳብ ብንለያይም፣ ሁላችንም ሃገራችንን ከመውደዳችን የተነሳ ተጨንቀን አምጠን የወለድነው መሆኑን ግን በማመን እንከባበር። ሃገሬውን በብሄረሰብ፣ በእድሜና በሃይማኖት ከፋፍለህ አትይ። ስለሥልጣንህ ለፍንካች ቅፅበትም አትጠበብ። ታሪክ ለመስራት ግን ትጋ። ወደመጀመሪያ ስድስት ወራት ሰብእናህ ተመለስ። ትልቁ ስስ ብልትህ (Achilles heel) አዲስ አበባ ስለሆነ፣ ተጨነቅበት። ባለፉት 45 ዓመታት ሃገሪቱ ስትታመስ የፅናት መልህቅ ሆኖ አንድነቷን ጠብቆ ያቆየው አዲስ አበባ ነው። የሠራን ነገር አትነካካ። ለኦሮሞ ብሄርተኞች አዲስ አበባ ዙሪያ ሌሎች አስር ከተሞችን ገንባላቸው። በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ከተሞች የግድ የአዲስ አበባ አካል መሆን የለባቸውም። የኦሮሞ ብሄርተኞችም የግድ የተሠራን ከተማ መውረስ የለባቸውም። አዲስ መስራት ይችላሉ። ወያኔ የገነባቸውን ህንፃዎችና ቪላዎች እያዩ ከመቋመጥ፣ እኛ የተሻለ መገንባት እንችላለን እንዲሉ አግባባቸው፣ መንገዱን አሳያቸው እንጂ፣ አዲስ አበባ ላይ አትደራደራቸው።
ከታከለ መምጣት ወዲህ አዲስን ኦሮሙማ ለማድረግ የተሰሩትን ነውሮች ሁሉ ሰው ሳይሰማ በጭለማ አስተካክላቸው። አየህ፣ ከተማን ብሄሮች አይገነቡም። ሰሞኑን በኦሳ ጉባኤ “የኦሮሞ ከተሞችን ኦሮሞ ስለማድረግ” ሲወራ ሰማሁ መሰለኝ። ከታላቁ የኦሮሞ ፍልሰት በፊት የኦሮሞ ህዝብ ከብት አርቢ ህብረተሰብ ስለነበር፣ ከተሞች አልነበሩትም። ዛሬ ኦሮሚያ በሚባለው ክልል ከተሞችን የቆረቆረው የኢትዮጵያ መንግስት ነው። በመጀመሪያ በቀላሉ ለመከላከል የሚያስችሉ ከፍታ ያላቸው ወታደራዊ ነቁጣዎች ነበሩ። ስለሆነም የመጀመሪያ ቆርቋሪያቸው ነፍጥ ያነገበ የኢትዮጵያ ወታደር ወይም ነፍጠኛ ነበር። ለአገልግሎቱ መንግስት ሊከፍለው ስለማይችል አካበቢው ላይ ባሉ አርሶአደሮች ላይ ቀላድ ተጥሎ እያስገበረ ይጠቀም ነበር። ታዲያ ይህ ግብረበል ጦር ምግብም፣ ልብስም፣ መጠጥም፣ ወሲብም ያስፈልገው ስለነበር በሰፈራው ዙሪያ ከየአቅጣጫው ያልፍልኛል ያለ አንጥረኛም፣ ግንበኛም፣ ነጋዴም፣ ኮማሪም፣ ሸማኔም ወደነዚህ ወታደራዊ ነቁጣዎች ተመሙና የኢትዮጵያ ህብረበሄራዊ ከተሞች ተፈጠሩ።
አሁን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገኙ የነዚህ ከተሞች ነዋሪዎች ዜጎችህ ቢሆኑም በሁለተኛ ደረጃ ዜግነት “ገበሮ” ሆነውልሃል። ባላነበውም እንደምሰማው የዚህ ግፍ ምንጩ የኦሮሚያ ክልል ህገመንግስት ነው አሉኝ። የዜጎችህን መብት ማስከበር ያንተ የጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሆኑ ሃላፊነት ሊሰማህ ይገባል። ሰው እንዴት በገዛ ሃገሩ ሁለተኛ ደረጃ ዜጋ ይደረጋል? እስቲ ሚስትና ልጆችህን አስባቸው! በነዚህ በኦሮሚያ ክልል ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን መብት በተመለከተ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ አፍ በፈቱበት ቋንቋ የመማር ወዘተ መብቶች እስኪ አስከብርላቸው። ብዙ ይጠበቅብሃል። እናቴ ከተናግሮ አናጋሪ ይጠብቅህ ትል ነበር ። ኤርምያስ አመልጋ ከቂሊንጦ በላከው የእስረኛ ደብዳቤ ሆዴን ባር ባር አሰኝቶ እኔንም ብዙ አናገረኝ።
ለባለሥልጣን ብዙ መናገር ግን ተገቢ ነው። ክቡር ጠቅላይ  ሚኒስትር፣ እባክዎን መጪውን አዲስ ዓመት ምክንያት አድርገው በፀረ ሽብር ህጉ የታሰሩትን ሁሉ፣ ከሰኔ 15 አሳዛኝ ክስተት ጋር በማነካካት የታሰሩትን የአስራት ሚዲያ ጋዜጠኞች፣ የባለአደራ ምክርቤት አባላት፣ የአማራ ክልል የደህንነት ባለሥልጣናት፣ የአብን ህጋዊ የፓርቲ አባላትና መሪዎችን ሁሉ ፍቱና፣ ፓርቲዎ ኦዲፒ በአዲስ አበባ ላይ የሚያደርገውን ትንኮሳና ማንአለብኝ መግለጫዎች አስቁመው፣ ለአዲስ ዓመት ዋዜማ በህዝብ አደባባይ በሚቀጣጠል የአዲስ ዓመት ዳመራ እሳት ውስጥ የፀረ ሽብር አዋጁን አቃጥሉና፣ ሃገርዎን ወደድህነትን መዋጋት ፊቷን እንድታዞርና ህዝቧም ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፎ እንዲቆም አመራርዎን ይስጡን። ፈጣሪ ቀናውን ያሳይዎ!!
Filed in: Amharic