>
8:54 am - Tuesday July 5, 2022

ጦማረ ኤርሚያስ - አልተሰበርኩም፣ አልሰበርም!!! (ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት)

ጦማረ ኤርሚያስ – አልተሰበርኩም፣ አልሰበርም!!!
ኤርሚያስ አመልጋ – (ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት)
በአንተነህ ይግዛው
.
አልሆነም!…
ይህቺን ምሽት ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ውስጥ እንጂ በመካከላችሁ እገኝ ዘንድ፣ ይህን መልዕክት በደብዳቤ አደርሳችሁ እንጂ በአንደበቴ አስደምጣችሁ ዘንድ አልሆነም!
ያም ሆኖ ግን… በዚህች ምሽት ከእናንተ ጋር በሰፊ አዳራሽ ውስጥ ለመታደምና የህይወት ታሪኬንና ስራዎቼን የሚዳስሰውን መጽሐፍ አብሪያችሁ በማስመረቅ ደስታዬን ለመጋራት ባለመታደሌ ቅር ቢለኝም፣ በዚህች ቅጽበት ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ቅጽር ግቢ ውስጥ በሚገኝ ጠባብ ክፍል ውስጥ ይህንን ደስታዬን የሚጋሩ የእስር ቤት ጓዶችን በዙሪያዬ ባለማጣቴ መጽናናቴ አልቀረም፡፡
ተስፋ አድርጌ ነበር… አመታትን የፈጀው ይህ መጽሐፍ በይፋ የሚመረቅባትን ይህቺን ልዩ ምሽት፣ በእስር ቤት ሳይሆን በመካከላችሁ ተገኝቼ በፍንደቃ እንደማሳልፋት ተስፋ አድርጌ ነበር፡፡
በአክሰስ ሪልስቴት ጉዳይ በማዕከላዊ እስር ቤት ለ128 ቀናት አስሮ ሲያሰቃየኝ ቆይቶ ድንገት እንዳሰረ ድንገት ፈትቶ የለቀቀኝ መንግስት፣ ብዙም ሳይቆይ ነበር ከኢምፔሪያል ሆቴል ሽያጭ ጋር በተያያዘ ባልሰራሁት ወንጀል እንደልማዱ ከስምንት ወራት በፊት መልሶ ያሰረኝ፡፡ ሊያስጠይቀኝ የሚችል ወንጀል እንዳልሰራሁ አውቅ ነበርና፣ ህግ እስከተከረበ ድረስ ነጻ እንደምወጣ እርግጠኛ ሆኜ ነበር ወደ ቂሊንጦ የገባሁት፡፡ የተፋጠነ ፍትህ አገኛለሁ ብዬ ተስፋ አድርጌ ነበር፡፡ ጉዳዩ ቢበዛ በ3 ወራት ጊዜ ውስጥ እልባት ያገኛል ብዬ ጠብቄ ነበር፡፡ የጠበቅኩት ግን አልሆነም፤ ከዛሬ ነገ ፍትህ አገኛለሁ በሚል ተስፋ ጊዜያትን ብገፋም፣ ይህ ነው የሚባል ፍትህ ሳላገኝ ይሄው በእስር እየማቀቅኩ 8 ወራትን አሳለፍኩ፡፡ እነሆ ዛሬም ታሪኬን የያዘው መጽሐፍ እኔ ባለታሪኩ በሌለሁበት እየተመረቀ ነው፡፡
መንግስት የዋስትና መብቴን ነፍጎ ወህኒ ከወረወረኝ በኋላ በቂሊንጦ ጠባብ ክፍል ውስጥ ባሳለፍኳቸው ስምንት ወራት ውስጥ ብዙ ነገሮች ተበላሽተዋል፡፡ አገርን ሊለውጡና ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጡ ከሚችሉት ጅምር ፕሮጀክቶቼ መካከል አብዛኞቹ፣ እስር ቤት በመግባቴ ሳቢያ ተሰናክለው ቀርተዋል፡፡ ከአፍሪካው ቁጥር አንድ የኢንቨስትመንት ባንክ ጋር አጋርነት በመፍጠር ላቋቁመው ያቀድኩት አዲስ የኢንቨስትመንት ባንክ ከንቱ ሆኖ ቀርቷል፡፡ ትልቅ ህልም ያነገበን ሰው ሰበብ ፈልጎ ማሰር የማይደክመው መንግስት፣ እኔን ብቻ ሳይሆን በመላው አለም በሊደርሺፕና ማኔጅመንት መስክ የካበተ ልምድ ካለው አንድ የውጭ ኩባንያ ጋር በመቀናጀት በመስኩ ደረጃውን የጠበቀ ስልጠና የሚሰጥና አገራዊ ፋይዳው የጎላ ኩባንያ ለማቋቋም የወጠንኩትን ትልቅ ህልም ጭምር ነው እስር ቤት ያጎረው፡፡
የአሊባባን ፕሮጀክት
ከፍተኛ ጥረት በማደረግ ከአለማቀፉ ኩባንያ አሊባባ ጋር በኢትዮጵያ ተግባራዊ ላደርገው ያቀድኩት ትልቅ ፕሮጀክትም ቢሆን፣ በመታሰሬ ሳቢያ የተወሰነ ቢጓተትም አበቃለት የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡ ኩባንያው አሁንም ድረስ እኔ ከእስር ተፈትቼ ፕሮጀክቱን በጋራ ተግባራዊ ማድረግ የምንችልበትን ቀን በትዕግስት እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡ በነገራችን ላይ የአሊባባን ፕሮጀክት ባሰብኩ ቁጥር ሁሌም ግርም የሚለኝ አንድ ነገር አለ፡፡
የአገሬ መንግስት አገርና ህዝብን የሚጎዳና ዋስትና የማያሰጥ ከፍተኛ ወንጀል ፈጽሟል፤ የዋስትና መብቱ ተከብሮለት ከእስር ቤት ቢወጣ ወንጀሉን ለመሸፋፈን ይሞክራል፤ ከህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ አገር ጥሎ ይጠፋል፤ ስለማላምነው ዋስትና አልሰጠውም ያለኝን እኔን… አለማቀፍ ዝናን ያተረፈው የባዕድ አገሩ ኩባንያ አሊባባ ግን፣ ለአገር ለወገን የሚጠቅም ፕሮጀክት አብሮኝ ሊተገብር የተነሳ፣ የምተማመንበትም የማምነውም ሰው ነውና ከእሱ ጋር ያለኝን አጋርነት አላፈርስም በሚል ጽኑ አቋም የምፈታበትን እለት በትዕግስት ለመጠባበቅ መፍቀዱን ሳስብ ሁሌም ግርም ይለኛል፡፡
የጀመርኳቸውን ሰፋፊ ፕሮጀክቶች ሜዳ ላይ በትኜ ቂሊንጦ እንድወርድ ቢወሰንብኝም፣ እኔ ግን እስር ቤት ሆኜም ስራ አልፈታሁም፡፡ በዚህች ምሽት በምትመርቁት መፅሐፍ ውስጥ እንደተጠቀሰው፣ መንግስት አካሌን እንጂ አእምሮዬን ማሰር የሚችልበት አቅሙም ችሎታውም የለውም፡፡ የእኔ ቢሮ ያለው አእምሮዬ ውስጥ ነው፡፡ እሱን ይዤ ነው ቂሊንጦ የወረድኩት፣ ቢሮዬን ይዤ ነው የታሰርኩት፡፡ በግንብ አጥርና በፍርግርግ ብረት ብታጠርም፣ ከቅዳሜና እሁድ በስተቀር ሳምንቱን ሙሉ ስራ ላይ ነኝ፡፡ አዳዲስ የቢዝነስና ኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ሃሳቦችን አፈልቃለሁ፡፡ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የተለያዩ ጽሁፎችን አዘጋጃለሁ፡፡ ከአዲስ አበባ ግርግር ወጣ ብዬ በእስር ባሳለፍኳቸው ያለፉት ስምንት ወራት ሁለት መጽሐፍትን ጽፌ ያጠናቀቅኩ ሲሆን፣ የሌሎች 3 መጽሃፍትን ንድፍ በማጠናቀቅ ከሰሞኑ ጽሁፍ ለመጀመር እየተዘጋጀሁ ነው፡፡
ፍርድ ቤት ይፈቅዳል ማረሚያ ቤቱ ይከለክላል
የምፈልገውን ያህል ባይሆንም አነብባለሁ፡፡ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ጋዜጦችና መጽሔቶች እንዲገቡልኝ ለፍርድ ቤት አቤቱታዬን አቅርቤ ነበር፡፡ ፍርድ ቤት ተገቢነት ያላቸው የህትመት ውጤቶች እንዲገቡልኝ ለማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር፡፡ ያም ሆኖ ግን ወዳጅ ዘመዶቼ በብዛት ከሚልኩልኝ በርካታ መጽሃፎች፣ መጽሔቶች፣ ጥናቶችና ሪፖርቶች መካከል የማረሚያ ቤት ፖሊሶችን ግምገማ አልፈው ከእጄ የሚደርሱት እጅግ እጅግ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በእስር ቤት ቆይታዬ ከፖሊስ ግምገማ አልፈው የገቡ ከ20 በላይ መጽሐፍትን አንብቢያለሁ፡፡ ሁሌም በየሳምንቱ የማይቀርብኝና ሳላቋርጥ የማነብበው ዘ ኢኮኖሚስት መጽሔት ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ግን ከታሰርኩበት ዕለት አንስቶ የአገር ውስጥ መጽሔቶችና ጋዜጦችን አንብቤ፣ ሬዲዮም ሰምቼ አላውቅም፡፡
16 እስረኞች በአንድ ክፍል…
በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ዞን 4 ውስጥ በሚገኘውና 80 ስኩየር ሜትር ያህል ስፋት ባለው ክፍል ውስጥ እኔን ጨምሮ 16 እስረኞች እንኖራለን – የኢንሳውን ቢኒያም ተወልደ፣ ከብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር በተያያዘ የታሰሩ 8 ሰዎች፣ ሰኔ 16 ቀን በመስቀል አደባባይ በተፈጸመው የቦንብ ፍንዳታ በቁጥጥር ስር የዋሉ 5 ሰዎች እንዲሁም በሞተር ብስክሌት ከተፈጸመ ወንጀል ጋር በተያያዘ የታሰሩ 2 ፖሊሶች፡፡
ማንበብ፣ መጻፍና ስፖርት መስራት በዕለት ከዕለት የእስር ቤት ህይወቴ ውስጥ የማይጓደሉ ሶስት ነገሮች ናቸው፡፡
የኔ ነገር… የረሳሁት አራተኛ ነገር አለ! – ካቦነት!
በዞን አራት ክፍል ውስጥ አብረውኝ የታሰሩትን 15 ሰዎች የመቆጣጠር ስልጣን የተሰጠኝ ከፍተኛ ባለስልጣን ሆኜ በካቦነት ተሹሜላችኋለሁ! ሹመት ያዳብር አትሉኝም!?…
መሳቅ ነው የሚሻለው… እየሳቁ የሚሆነውን ሁሉ መታዘብ ነው እንግዲህ…
እውነቱን ለመናገር ግን፣ በአንድ በማላውቀው ምክንያት እንደ አሮጌው ኢህአዴግ ሁሉ፣ አዲሱም ኢህአዴግ እኔን ማጥቃትና ስራዎቼን ማሰናከልን ተልዕኮው ያደረገ ይመስለኛል፡፡ ሲሆንብኝ የኖረውና እየሆነብኝ ያለው ነገር ሁሉ በግለሰብ ላይ ከሚፈጸም ግፍና በደል ባለፈ በአገሪቱ የፖለቲካና የህግ ስርዓት ላይ ጥቁር ጥላውን የሚያሳርፍ ኢፍትሃዊነት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ እርግጥ የሚደረገው ሁሉ የሚደረገው በእኔ ላይ ብቻ አለመሆኑን አውቃለሁ፡፡ አገራቸውን ሊጠቅሙና ተጨባጭ ለውጥ ሊፈጥሩ የሚችሉ ሌሎች ግለሰቦችም፣ የኢህአዴግ አባል ለመሆን ወይም ስርኣቱን ለመደገፍ ባለመፍቀዳቸው ብቻ እንደጠላት እየታዩ ሲበደሉና በፍትህ እጦት ሲንገላቱ ማየት የተለመደ ክስተት ሆኗል፡፡
መንግስት ላለፉት 20 አመታት ሰበብ እየፈለገ ያለአግባብ ሲፈጽምብኝ በቆየው መልከ ብዙ በደልና ጥቃት በቢዝነሴ፣ በመልካም ስምና ዝናዬ እንዲሁም በቤተሰቤ ላይ እጅግ ከፍተኛ ጥፋትና ኪሳራ አድርሶብኛል፡፡ ይህን ልክ የለሽ ጥፋትና ኪሳራ ራሱ መንግስትም ሆነ ማንም ሰው በምንም ሊያካክስልኝ አይችልም!
ደስ የሚለው ግን፣ በደል እየቆጠረ የማይቆዝም፣ ጥቃትን ፈርቶ የማይርድ ልብ መታደሌ ነው! በተመታ ቁጥር የሚጠነክር፣ በተገፋ ቁጥር የሚጸና፣ በታጠፈ ቁጥር የሚቀና፣ የማይበገር መንፈስ ነው የተሰጠኝ – የማይሰበር!
የማውቃችሁም የማላውቃችሁም በሙሉ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ!
ብታውቁኝም ባታውቁኝም፣ በችሎት አዳራሽ እየተገኛችሁ አጋርነታችሁን ስታሳዩኝ፣ በማህበራዊ ድረገጾች ስለእኔ ፍትህ ስትጮሁ፣ ስለእኔ በትጋት ስትጽፉና ስትዘግቡ፣ ቂሊንጦ ድረስ እየመጣችሁ ስትጎበኙኝ የከረማችሁ እንዲሁም በዚህች ምሽት መጽሐፌን ለማስመረቅ የተሰባሰባችሁ የማውቃችሁም የማላውቃችሁም በሙሉ… አንድ ነገር በእርግጠኝነት ልነግራችሁ እፈልጋለሁ – እስር ቤት ሆኖ ይህን ደብዳቤ እየጻፈላችሁ የሚገኘው የአሁኑ ኤርሚያስ፣ በደልና ጥቃት ቅስሙን ሰብሮት ተስፋ የቆረጠ ሳይሆን ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንካራ ልብ፣ ከምንጊዜውም የተሻለ ጽኑ መንፈስ የተላበሰ ኤርሚያስ ነው!
በግፍ ከተወረወረበት የቂሊንጦ ቅጽር ግቢ የበለጠ ጠንክሮ ለመውጣት የተዘጋጀ፣ ከምንጊዜውም በላይ ከፍ ብሎ፣ ከመቼውም በላቀ ተስሎ አዲስ ታሪክ ለመስራት የሚያኮበኩብ አዲስ ኤርሚያስ ነው ይህን ደብዳቤ ልኮ እንኳን ለዚህች ዕለት አደረሰን አደረሳችሁ የሚላችሁ!

አልተሰበርኩም፣ አልሰበርም!

ነሐሴ 15 ቀን 2011 ዓ.ም
ኤርሚያስ አመልጋ
(ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት)
Filed in: Amharic