>

ኢታርእየኒ ሙስናሃ ለኢትዮጵያ (የኢትዮጵያን ጥፋቷን አታሳየኝ) ከይኄይስ እውነቱ

ኢታርእየኒ ሙስናሃ ለኢትዮጵያ (የኢትዮጵያን ጥፋቷን አታሳየኝ)

ከይኄይስ እውነቱ

የዛሬውን አስደንጋጭ ርእስ የመረጥኩት ኢትዮጵያ አገራችን የምትገኝበት አስከፊ ሁናቴ ወይም ምድር ላይ የሚታየው ጽድቅ መራር ከመሆኑ የተነሳ ባለአእምሮ እንደሆነ ሰውና እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ከማሳሰብም አልፎ ሥጋቴ ጥግ ቢደርስብኝ እኔም በርእሰ መጻሕፍቱ እንደተመዘገቡ ደጋግ ሰዎች ጩኸቴን ለሕይወት ባለቤት ባደባባይ ለማሰማት ነው፡፡

ነገረ ኢትዮጵያን በውስጥ በአፍአ፣ በቀኝ በግራ፣ በፊት በኋላ እያገላበጥኹ አቅሜ በፈቀደው መጠን ስመረምረው ቀንድና ጭራ፣ መያዣ መጨበጫ የሌለው ውል አልባ ይሆንብኛል፡፡ ዕብደትና ድንቁርናው በእጅጉ ከመሰልጠኑ የተነሳ ከንቱዎች ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ለማጥፋት እየተጣደፉ ይገኛሉ፡፡ ለጥፋቱ የውጭም አይዟችሁ ባዮች አሏቸው፡፡ የሚናገር እንጂ የሚያዳምጥ የለም፡፡ የሚያዳምጥ የሚመስለውም ጭንቅላቱን በግልጽና በሥውር የሚነቀንቅ ነው፡፡

ነውሩ ሁሉ ምንቀረኝ እየተባለ ንቅስ ተደርጎ የተፈጸመበትና እየተፈጸመ ያለበት ዘመን ላይ እንገኛለን፡፡ ሥጋ የለበሱ አጋንንት ተፈትተው የተለቀቁባት አገር ሆናለች ኢትዮጵያችን፡፡ ዋና መገለጫውም ወያኔ ትግሬ፣ በኦነግ/ኦሕዴድ የሚመራው ‹አዲሱ ወያኔ› (Neo-Woyane)፣ በ‹ፖለቲካ ድርጅት› ሽፋን በጐሣ የተሰባሰቡትም ሆነ ከዛ ውጭ ተሰባስበናል የሚሉት ቊጥራቸው ከመቶው የዘለቀው የአዲሱ ወያኔ አጃቢዎች፣ ንስሓ ከገቡት ውጭ (የገቡ ካሉ) የኢትዮጵያን ፖለቲካ ምስቅልቅል ውስጥ የከተቱትና አሁንም ራሳቸውን ዋና ተዋናይ አድርገው ትውልዱን ግራ የሚያጋቡት ራሳቸውን የ‹ያ ትውልድ› ብለው የሚጠሩት አብዛኛው አባላት (በቅርቡ ከነዚህ መካከል አንዱ ከኢትዮጵያ ምድር ሰው ጠፍቶ ለጥፋቷ 24/7 ሲሠራ የነበረውን ‹ብዔልዜቡል› በረከትን አማክሩት ሲል ለአገዛዙ ‹ምክሩን ለግሷል›)፣ የዘረኝነት (መንደርተኝነት) ልክፍት፣ ቅጥ ያጣ የሥልጣንና የንዋይ ፍትወት፣ ኢትዮጵያን÷ መልካም ታሪኳንና እሤቶቿን ሁሉ አምርረው የሚጠሉ የትውልድ ጕድፎች፣ ከመጣው አገዛዝ ጋር ጭራቸውን እየቆሉ የሕዝብን ሰቆቃ የሚያራዝሙ፣ አንዳንዶችም ዐቢይን በማወደስ የተጠመዱ ‹ምሁራን›፣ በንቅዘትና በማን አለብኝነት ከባለጉት ተረኞች ጋር ተደምረው የሕዝቡን ሕይወት ሲዖል ያደረጉ ስግብግብ ነጋዴዎች፣የማሠማሪያውን መንጋ አጥፍተውና በትነው ተቅበዝባዥ ያደረጉ በመንፈሳዊ ድርቀትና ድቀት የተመቱ በሃይማኖት ሽፋን የሚንቀሳቀሱ ‹እረኞች›፣ የመንደር ወሮበሎችን የሚያበረታቱ የእንጨት ሽበት የወረራቸው ‹ሽማግሎች›፣ ወዘተ. የነውረኞቹ ስብስብ ውስጥ የሚጠቃለሉ ናቸው፡፡

ጉልበተኞቹ አገዛዞች መንግሥታዊ ሥልጣንን እና ኃይልን ሕግን ለማስከበር÷ፍትሕ ርትዕን ለማደላደል ሳይሆን፤ ሥርዓተ አልበኝነትን ለማንገሥ፣ ዜጎችን ለማፈናቀልና ለማጉላላት፣ የርስ በርስ ግጭት ለመለኰስ፣ አገራዊ አንድነትን ለማናጋት፣ ለዝርፊያና የግል ጥቅም ማደላደያ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ እንደ አሸን የፈሉትና አዲሱን ወያኔ በአጃቢነት የተቀላቀሉት (ተቃዋሚም÷ተፎካካሪም ያልሆኑት) የፖለቲካ ነጋዴዎችም የሥልጣን ፍርፋሪ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ የወያኔን ነቀርሳ ሰነድ አዝለው ስለምርጫ ያወራሉ፡፡ ተቀድዶ የታሪክ ቆሻሻ ቅርጫት ውስጥ ከመጣል በቀር ለመሻሻሉ ምንም ዓይነት ዕድል የሌለው የወያኔ/ኦነግ ሰነድ አይነካብንም የሚለው የባለጌዎቹ ቁንጮዎች ጩኸት አሁንም ቀጥሏል፡፡ ሰብእናቸው ከአውሬ የከፋው እነዚህ ጉዶች ሳይገባቸው ስለ ሕግ የሚያወሩት በጠራራ ፀሐይ የዜጎችን ሰብአዊ መብቶቸ እየጣሱ ነው፡፡ ዐቢይም ሆነ ‹ዘመዶቹ› ባደጉበትና በለመዱበት ብቻ ሳይሆን ክፋቱን አልቀውት በአሳፋሪ መንገድ ቀጥለዋል፡፡ የቀደመውም ሆነ የአዲሱ ወያኔ አገዛዞች ያመረቷቸው በዜጎች ደምና በአገር ሀብት ዝርፊያ እጃቸው የጨቀየ ወንጀለኞች እስከ ነውራቸው (ጥቂት የማይባሉትም በዐቢይ አገዛዝ ውስጥ ሥልጣን ተሰጥቷቸው) በዐደባባይ ይንጎማለላሉ፡፡ በታሪክ ደጋግሞ እንደታየው በዳዮችን የምትሾም የምትሸልም፤ የአገር ባለውለታዎችንና ተቆርቋሪዎችን የምትወነጅል የምታሳድድ አገር ሆና ቀጥላለች፡፡ ባጠቃላይ ማኅበረ ፖለቲካዊና አኮኖሚያዊ ቀውስና ድቀት ውስጥ እንገኛለን፡፡

እንኳን ለጅምላ ጥፋት እየተጋን፤ አንድ ሆነን÷ በመከባበር ተነጋግረን÷ተደማምጠን÷ ዜጎች ሁሉ በአገራቸው ጉዳይ ያገባቸዋል ብለን (ዕጣ ፈንታችን÷ዕድል ተርታችን ለአገዛዞችና በውሸት ተቃዋሚነት ስም ለሥልጣን በቋመጡ አጃቢዎቻቸው ሳንተው) ብሔራዊ የሽግግርና የምክክር ጉባኤ ጠርተን ብንመክርም እንኳ ከገባንበት ዐዘቅተ በቀላሉ የምንወጣው አይመስልም፡፡ አሁን በያዝነው መንገድ በቡድንም በተናጥልም አንድም አትራፊ አይኖርም፡፡ የዓለሙ ሁሉ መሳቂያና መሳለቂያ ከመሆን በቀር፡፡ ይህ ዓይነቱ እገሌ ከእገሌ ሳይባል ሁሉም ሙልጩን የሚቀርበት ውጤት የኢትዮጵያን ጠላቶች ካልሆነ በቀር ማንን ሊያረካ እንደሚችል አላውቅም፡፡ በአርዓያ ሥላሴ የተፈጠርን ሰው ነን ካልን እንደ ሰው እናስብ እንደ ሰው እንኑር!!! አለበለዚያ በኢትዮጵያ ምድር አገር እበትናለሁ እያለ ማንም ማንንም ሊያስፈራራ አይችልም፡፡ 80 መንደሮች በተናጥል አገር አይሆኑም፡፡ ወይ አብረን ተያይዘን እንለማለን ወይ አብረን ተያይዘን እንጠፋለን፡፡ ለጥፋት መካከለኛ መንገድ የለውም፡፡ አሁንም ሆነ ወደፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የትኛውም ክ/ሃገር ራሱን ችሎ መቆም አይችልም፡፡ በበጀት አንፃር እንኳን ብናየው ወያኔ በዘረጋው የውሸት ፌዴራላዊ መዋቅር እያንዳንዱ ክ/ሃገር የሚተዳደረው ከማዕከላዊ መንግሥት በሚደረግ የበጀት ድጎማ ሳይሆን የበጀት ምደባ ነው፡፡ ከ70 – እሰከ 90 በመቶ የሚሸፈን ወጭ ድጎማ ሊሆን አይችልም፡፡ ክፍላተ ሀገራቱ እንኳን ራሳቸውን የቻሉ አገሮች ሊሆኑ ቀርቶ የእውነተኛ ፌዴራላዊ ሥርዓት አባላት ለመሆን ብቃቱ የላቸውም፡፡ ለምን ራሳችንን እናታልላለን?

እስከ መቼ በአእምሮም በቁስም የለየልን መናጢዎች ሆነን እንቀጥላለን? እስከ መቼ ዋናና አንኳሩን ጉዳይ ትተን በመደበኛውም ሆነ በማኅበራዊው የብዙኃን መገናኛዎች በጭፍጫፊ ጉዳዮች ላይ መላ ኃይላችንን እናባክናለን? መቼ ይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ የሕዝብ ድምጽ የሚሰማው? መቼ ይሆን ሕዝብ ያልመረጣቸው/ያልወከላቸው ጮሌዎች አገር ማመሳቸውን የሚያቆሙት? መቼ ይሆን አገዛዞችን ሲያገለግሉ የኖሩትና እያገለገሉ ያሉት ደካማ ተቋማት የሕዝብን ፍላጎት የሚያስተናግዱት፣ ለእውነትና ለሕግ ተገዢ የሚሆኑት? መቼ ይሆን ተቋማዊ ገጽታ የተላበሰው ቡድናዊና አገራዊ ሸፍጥና ቅጥፈት የሚያበቃው? መቼ ይሆን ከመንደር ወጥተን በአገር፣ በክፍለ ዓለምና በዓለም ደረጃ የምናስበው? መቼ ይሆን ሌሎች አገሮች የደረሰቡት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ደረጃና ብልጽግና በቁጭት የሚያነሳሳን? መቼ ይሆን አገዛዞቻችን ከድንቁርና ወጥተው የአገርንና የሕዝብን ጥቅም የሚያስጠበቁት፣ ለሥልጣን ሲሉ የባዕዳንን እና ተቋሞቻቸውን አጀንዳ ከማስፈጸም የሚታቀቡት? ባለቤት አልባ አድርገውን ብሔራዊ ምሥጦሮቻችንን የሚያባክኑት? መቼ ይሆን ዜጎች ከመንጋነት ወጥተው እንደ ግለሰብ በራሳቸው ለራሳቸው ቆመው በሰውነት የሚያስቡት? ምርጫ ፍላጎታቸውን በነፃነት የሚወስኑት? ለምን ማንም እንደ ከብት በፈለገው መንገድ ያሠማራናል? መቼ ይሆን ‹ሰው› ሆነን የምናልፈው? እነዚህ ሁላችንን የሚመለከቱ ጥያቄዎቸ እንቀጥል ካልን ማብቂያ የላቸውም፡፡ ጊዜና ቦታ ስለሚገድበን ለጊዜው በዚሁ እናብቃ፡፡ ለጠቢብ አንዲት ቃል ትበቃዋለች ይላልና ታላቁ መጽሐፍ፡፡

በመግቢያዬ ላይ ያነሳሁት የአስተያየቴ ርእስን በጸሎት መልክ ለእግዚአብሔር አምላክ ያቀረቡት ‹‹ በሆድ ሳልሠራህ ዐውቄሃለሁ÷ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ÷ ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ፡፡›› የተባለለት ከዐበይት ነቢያት አንዱ የሆነው የነቢዩ ኤርምያስ ደቀመዛሙርት ኢትዮጵያውያኑ አቤሜሌክና ባሮክ ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ ነቢዩ ኤርምያስ በክፉዎች እጅ ተላልፎ ዐዘቅተ ኵስሕ (መፀዳጃ ቤት) በተጣለ ጊዜ ያወጣው ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ ነው፡፡ ሁለቱ የነቢዩ ኤርምያስ ደቀመዛሙርት መምህራቸው የፄዋዌን ነገር (እሥራኤላውያን በባቢሎን ተማርከው ለ70 ዘመናት በባዕድ ምድር በስደት እንደሚኖሩ÷ በባርነት እንደሚያዙና እንደሚገዙ) ሲናገር እየሰሙ የኢየሩሳሌምን ጥፋት አታሳየን እያሉ አጥብቀው ይጸልዩ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም የነዚህን ቅዱሳን ጸሎት ሰምቶ ለነቢዩ ኤርምያስ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ከመአቱ በልዩ ጥበብ ሠውሮአቸዋል፡፡ ነቢዩ ኤርምያስ ከገባበት ዐዘቅተ ኵስሕ ኢትዮጵያዊ አቤሜሌክ እንዳወጣው ዛሬ ኢትዮጵያ ከገባችበት ‹‹ዐዘቅተ ኵስሕ›› የሚያወጣት አቤሜሌክ ያላት አይመስልም፡፡ ሕዝብ ‹ባሕረ ኤርትራን› ያሻግሩናል፣ ወደ ‹ምድረ ከነዓን› ይመሩናል ብሎ ተስፋ የጣለባቸው ‹ሙሴዎች› እና ‹ጸያሕያነ ፍኖት› ሐሳውያን ሆነው መገኘታቸው ብቻ ሳይሆን ባደጉበት ቆሻሻ የፖለቲካ ባህል÷ በዘረኛና ደናቁርት የመንደራቸው ሰዎች ተጽእኖ ሥር ወድቀው የቁልቁለቱን መንገድ ከጀመሩት ውለው አድረዋል፡፡ ታዲያ ምን ይሻለናል?

ከእምነቱም ከበጎ ሥራውም አንዳች የሌለን የዚህ ዘመን ሰዎች ከኵተት እስከ ሽበት የክፋትንና የጥፋትን ጥግ ማየትና መስማት ዕጣ ፈንታችን ሆኖአል፡፡ ባይሆን ከዕብደቱና ድንቁርናው ተፋትተን ወደ ቀልባችን ከተመለስን፤ በእምነት ተቋማት አመራር ላይ ጥቂት መንፈሳውያን አባቶች ካገኘን፤ ለራሳቸውና ለሕዝብ የታመኑ÷ እውነትን ገንዘብ ያደረጉ ጥቂት ቅን መካርና ገሣጭ ሽማግሎችን ካገኘን፤ በጋራ ጥረታችንና ከልብ በሆነ ጸሎት ተደግፈን የጋራ ቤታችን ኢትዮጵያን ከሁሉም በላይ ከቅኝ አገዛዝ በነፃነት ያሸበረቀ መልካም ታሪኳን፣ ውብ ባህሏንና እሤቶቿን ይዘን፣ የገፀ ምድርና የከርሠ ምድር ሀብቶቿን በሥራ ላይ በማዋል፣ ለሁላችን የምትበቃና የምትመች አድርገን በሰላምና በእኩልነት ለመኖር ተስፋውና ዕድሉ አለ፡፡ ይሁን እንጂ በተለይ ላለፉት ሦስት ዐሥርታት ያየነው እና የምናየው ግን ከዚህ በተቃራኒው በመሆኑ በግሌ አምላኬን ኢታርእየኒ ሙስናሃ ለኢትዮጵያ (የኢትዮጵያን ጥፋቷን አታሳየኝ) እያልኩ ወላዲተ አምላክን እና ቅዱሳንን ጥግ አድርጌ እማፀነዋለሁ፡፡

አዎ! አምላከ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያን ትንሣኤ እንጂ ጥፋቷን አያሳየን፡፡

Filed in: Amharic