>

ብፁዓን አባቶች ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው ነው!! (ሀብታሙ አያሌው)

ብፁዓን አባቶች ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው ነው!!
ሀብታሙ አያሌው
የቋሚ ሲኖዶስ አባላት እስካሁን በስብሰባ ላይ የቆዩ ሲሆን በስብሰባቸው ያሳለፉትን ውሳኔዎች ለህዝበ ክርስቲያኑ እንዳያስተላለፉ (ምንም አይነት መግለጫ እንዳይሰጡ) በደህንነት አካላት ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው መሆኑ ታወቀ።
አባቶች በዛሬው ስብሰባቸው ጠንከር ያሉ ውሳኔዎች ያሳልፋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ውሳኔዎቹን ይፋ ከማድረጋቸው በፊት የደህንነት አካላት ነን በሚሉ ግለሰቦች በእጅ ስልካቸው እየተደወለና በአካልም ጠቅላይ ቤተክህነት ድረስ በመምጣት ውሳኔ ለማስቀየር ማስፈራሪያ እያደረሱባቸው መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
 የቋሚ ሲኖዶስ አባላት የ”ኦሮሚያ ቤተ ክህነት ” እንመሰርታለን የሚሉ አካላት ያስቀመጡትን “የ30 ቀን” ቀነ ገደብ ውድቅ አድርገዋል።ጉዳዩም ከስርአተ ቤተ ክርስቲያን አንፃር የቀኖና ጥሰት የተፈፀመበት በመሆኑና ህገ ወጥም ስለሆነ አስቸኳይ ውሳኔ በሲኖዶስ መወሰን እንዳለበትም ተስማምተዋል።
መንግስት ቤተ ክርስቲያኒቷ ለጠየቀችው ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ እየሰጠ አለመሆኑን፣በተለያዩ ጊዜ የመንግስት ሀላፊዎች ወደ ቤተክርስቲያኒቷ መጥተውና ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር ተነጋግረው ከሄዱ በኋላ የተስማሙባቸው ጉዳዮች እንደሚጣሱና እንዳልተፈፀሙ በማንሳት “ከእንግዲህ ከመንግስት ጋር የምናደርገው ግንኙነት ምን መምሰል አለበት?” በሚለው ጉዳይ በሰፊው ተነጋግረዋል።
በተለያዩ ሚዲያዎች አባቶች ከመንግስት ጋር ግንኙነት ለማቋረጥ እንደወሰኑ ተረጋግጧል በሚል እየተለቀቀ ያለውን መረጃ ለማጣራት ባደረግነው ሙከራ ምንጫችን እንደገለፁልን ይህን ውሳኔ መወሰን የሚችለው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በመሆኑ ብፁአን የቋሚ ሲኖዶስ አባላቱ በአጀንዳነት ቢነጋገሩበትም ውሳኔ አልተላለፈበትም። ለሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጉዳዩን እንደሚያቀርቡትም ታውቋል።
አባቶች በስብሰባቸው “ህዝቡ ተቆጥቷል፤በጊዜ እልባት መስጠት ካልቻልን እኛም ሆንን መንግስት ልናቆመው አንችልም። በአስቸኳይ እልባት መስጠት አለብን” ብለዋል።
ከስብሰባው በኋላ የቋሚ ሲኖዶስ አባላቱ በስልክና በአካል ከፍተኛ ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው እንደሆነና ለምእመናንም ሆነ ለሚዲያዎች ምንም አይነት መግለጫ እንዳይሰጡ ተፅእኖ እየደረሰባቸው መሆኑንም ከምንጮቻችን ለማወቅ ችለናል።
ተጨማሪ መረጃ 
የቋሚ ሲኖዶስ አባላት አባቶች በስብሰባቸው የአዲስ አበባ ከንቲባ ለጥያቄያችን ምላሽ እየሰጡ ባለመሆኑ በቅርቡ በአዲስ አበባ በሚካሄደው ብሄራዊ የኩራት ቀን ላይ ቅዱስ ፓትርያርኩ መገኘት የለባቸውም” በሚል ሀሳብ ላይ ጠንካራ ውይይት አድርጓል ይህንን ተከትሎም አመሻሹ ላይ መንግስት አትሌት ሀይሌ ገብረ ስላሴን ጨምሮ አቶ ብርሀን(የሀዋሳ ኦሲስ ሆቴል ባለቤት) እና አቶ አምሀ የተባሉ ባለሀብቶችን በሽምግልና ወደ ቅዱስ ፓትርያርኩ ቢልክም ቀና መልስ አለማግኘታቸውን ለማወቅ ተችሏል።
በቅርቡ የደህንነት ኃላፊ በመሆን በዶክተር አብይ የተሾመው የኦህዴዱ አቶ ደመላሽ ገ/ሚካኤል ለአደገኛ የፖለቲካ ሴራ መሾሙን ብዙዎች ስንናገር እንደነበርን ይታወሳል።
Filed in: Amharic