>

የኦሮሚያ ቤ/ክህነት ጉዳይ ላልገባችሁ!!!  (ጌቱ አያሌው)

የኦሮሚያ ቤ/ክህነት ጉዳይ ላልገባችሁ!!! 
ጌቱ አያሌው
1ኛ- የጥያቄው መነሻ ፦ ከመቆርቆር የመነጨና በቤተክርስቲያን የሚደረገው ስርአተ አምልኮው ፣ ቅዳሴውና ትምህርቱን ዝማሬውን ጨምሮ የኦሮሞው ኦርቶዶክስ ማህበረሰብ በሚሰማውና በሚገባው ቋንቋ በኦሮሚኛ ይሰጥ ከሚል ፣ የአማኞች መመናመንና በቤተክህነት ውስጥ ባለው የተበላሸ ጎጠኛ አሰራር ባዘኑና በተቆጩ የጊቢ ጉባኤ ምሩቃን ወንድሞች የተጀመረ ነበር። በዚህ ጥያቄ ውስጥ ብዙ የምናውቃቸው መምህራኖች ተሳትፈው ነበር። ይሄን ለመፍታት ከማህበረቅዱሳን ጋር የአፋን ኦሮሞ ፕሮጀክት የሚል የጋራ እንቅስቃሴ ጀመሩ ። በማህበረ ቅዱሳን ውስጥም እራሱ የቻለ ክንፍ ሆነ። በዚህም የጸሎት መጽሃፍቶችን፣ የመማሪያ ሞጁሎችን፣ የስርአተ ቅዳሴ እና ሌሎች የስርዓት መጽሃፍቶችን፣ እና ሌሎች እንደ የTv ፕሮግራም፣ በየወሩ የሚወጡ መጽሄቶችን ከማህበረቅዱሳን ጋር ማሰራጨት ተጀመረ። በተጨማሪም በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ባሉ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የጊቢጉባኤ ትምህርት በኦሮሚኛ ለኦሮሞ ተማሪዎች ይሰጥ ጀመር። በተለያዩ አካባቢዎችም ሁሉም ላይ ባይሆን እንኳን በተወሰኑ አካቢዎች በየአቢያተ ክርስቲያናቱ ቅዳሴ በኦሮሚኛ ይቀደስ ጀመረ። በብዙሺ የሚቆጠሩ ተተኪ የኦሮሚኛ መምህራኖችን ከማህበረ ጽራጽዮን እና ማህበረ ቅዱሳን ጋር እያሰለጠኑ ወደ ገጠር ማሰራጨቱን ቀጠሉ። የኦሮሚኛ አብነት ትምህርት የሚሰጥበትም እንዲሁ በማህበረ ቅዱሳን ጋር ኪልጡ ካራ ላይ ተመሰረተ። በርግጥ ገና ብዙ ስራ ቢቀርም ጥሩ እንቅስቃሴ ተጀመረ።
2ኛ- የጥያቄው መጠለፍ፦ ቀድሞ የነበሩት መልካ ሃሳቦችና ኦሮሞ ህዝብ ሃይማኖቱን በራሱ ቋንቋ የመማሩን ነገር በፖለቲከኞችና በጸረ ኦርቶዶክ አቀንቃኞች ቀስ በቀስ ተጠለፈ። ጥያቄውም በቋንቋችን እናገልግል ከሚል ወደ በራሳችን ብሄር ሰዎች እንመራ ፧ ብሄራችንን መሰረት ያደረገ ስትራክቸር እንፍጠር ፧ ከቤተክህነቱም እንገንጠል ወደሚል ተቀየረ። በዚህም አንድ በአንድ ከማህበረቅዱሳን የአፋን ኦሮሞ ፕሮጀክት ስር የነበረቱን ወንድሞች በማሸማቀቅ ከዛም የቻሉትን ወደራሳቸው በመሳብ መውሰድ ጀመሩ። ለምሳሌ እነ ነኸሚያ ፈይሳን፣ አነ አባ ወልደገብርኤልን፣ እነ ዋሲሁን አመኑን …. ወዘተ ከጎን አነ ቀለመወርቅ ሚደቅሳንና ሌሎች ወንድሞችን በቀሲስ በላይ መኮንን አማካኝነት በመሳብ አንድ ቡድን አዋቀሩ።
የዚህ ሃሳብ መስራችና ከቤተክህነቱ ጋር እልህ የተጋቡት ቀሲስ በላይ በይፋ አንዳች ሳይሸማቀቁ ባቀሰሰቻቸው ቤተክርስቲያን ላይ ውርጅብኝ ያወርዱ ጀመረ።
Video ለታሪክ ተቀምጧል በየስብሰባዎች ላይ ፦
 * ኦርቶዶክስ የነፍጠኞች ሃይማኖት ነች
*  ኦርቶዶክስ ኦሮሞን በድላለችና ይቅርታ ትጠይቅ፣ * ኦርቶዶክስ ትግሬና አማራ ብቻ የተሰገሰጉባት እምነት ነች
* ኦርቶዶክስ የኦሮሞን መሬት ወርራለች ይዞታዋን ትቀማ
 * የኦርቶዶክስ ቄሶች ሰፋሪዎች ናቸው ይልቀቁ…. ወዘተ ንግግሮችን ያደርጉ ነበር። በዚህም ብሄርተኞችን የሌላ እምነት ተከታዬችን ሳይቀር ከጎናቸው ማሰለፍ ቻሉ።
3ኛ- ቀሲስ በላይ ማናቸው? ቀሲስ በላይ በህግ ትምህርታቸውን ጨርሰው በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ሲሰሩ የቆዩ ቤተክርስቲያንም ሲያገለግሉ የቆዩ በዃላ የእንባ ጠባቂ ተቋም ዳይረክተርነት የደረሱ ፤ በቤተክህነቱም ቢሆን የአቡነ ጳውሎስ የቅርብ ወዳጅ የነበሩ የአዲስ አበባ አህጉረስብከት ስራስኪያጅ የነበሩ ሰው ናቸው። በሙስና የተጨመላለቀው የአዲስአበባ ሀገረስብከት ዋና ስራስኪያጅ በነበሩበትም ወቅት እንደሌሎቹ የቤተክህነት ሰራተኞች የሰንሰለቱ አካል የነበሩ በዃላም ከሀገረስብከት ስራስኪያጅነታቸው ሲነሱ አኩርፈው ከነ ነሞምሳ ጋር የርቀት የብሄር ቤተክህነታቸውን ውጥናቸውን የጀመሩ። ቀጥሎም በማህበረ ቅዱሳን ውስጥ የነበሩ የኦሮሞ ልጆችን በማፍለስ ማህበረ ነህሚያንም እንዲሁ በማክሰም ” ወልዳ ዱካቦኦታን” የመሰረቱ አስቀጥሎም በየ ዩኒቨርሲቲዎች በዚሁ ማህበር አማካኝነት በኦርቶዶክስ ተማሪዎች መካከል ልዩነት በመንዛት ጊቢ ጉባኤውን ለሁለት በመክፈል ሀ ብለው ስራቸውን ተክለዋል። ቀጥሎም ከለውጥ በዃላ የነጁሃር መሃመድን ወደ አገር ቤት መግባት ተከትሎ አሰላለፋቸውን ከፕሮቴስታንቱ በቀለ ገርባ እንዲሁም የዋቄፈና አማኞች ከሆኑ አባገዳዎች ጋር በነ ድንቁ ፈንድ አድራጊነት የመገንጠሉን ስራ መንግስታዊ ስልጣንንም ጭምር በመጠቀም ኮሚቴ መስርተው መነቀሳቀስ ጀመሩ። ጀምረውም አልቀረ የኦሮሞ ቤተክርስቲያን የሚል የተለየ ተቋም መመስረቱን በመግለጫ ሊያበስሩ በዝግጅት ላይ ናቸው።
4ኛ- የኦሮሞ ቤተክህነት ቢቋቋም ፦ በአጭሩ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት በኦሮሚያ አሁን ያላት ቁጥር ከ20% ያነሰነው ከዛም ጭራሹኑ መደመጥፋት ይደርሳል። ሌሎቹም ብሄሮች እንዲሁ ከዋናዋ ቤተክርስቲያን በመገንጠል የራሳቸውን የብሄር አስተዳደር ይመሰርታሉ። ከዛም እንደ ፖለቲካዎ ሁሉ አንድ በሆነችው ሃይማኖትም ልዩነትን በመፍጠር እምነቱን ከፋፍለው ያዳክሙታል፣ የዶግማ የቀኖና ልዩነቶችን ፈጥረው በአንድ ሀገር የተለያየ የኦርቶዶክስ እምነት እንዲኖር ያደርጋሉ። ከሁሉም በላይ በኦሮሚያ ያሉ ኦርቶዶክሶች በአክራሪ እስላሞች፣ በዋቄፈናዎችና፣ ፕሮቴስታንቶች የተናጥል ጥቃትን ያስተናግዳሉ።
እንኳን ሌላ አዲስ አስተዳደር ተቋቁሞ በእግሩ ቆሞ ሌላ አማኝ ማምጣት አይደለም አሁን ያሉትንም ያስበላል። አሁን ያለው የቤተክህነት ስትራክቸር ያልሞላውን ጎዶሎ ብቻውን ሊሞላ አይችልም። በርግጥ ታርጌት የተደረገው ” በክልላችን ያለችውን ቤተክርስቲያ ነጻ እናወጣለን ቢሊሰ ባስና ” ብሎ ለተነሳ የምዕመናን ጭራሹኑ መጥፋት ያሳስበዋል ብዬ አላስብም።
በአንድም ይሁን በሌላ በዚህ ቤተክርስቲያንን በሚከፍልና በሚያፈርስ እንቅስቃሴ የምትሳተፉ ወንድም እህቶች የእድሜ ዘመን ንስሃ የማይፈታው ሃጥያትና የታሪክም ተወቃሽ እንደምትሆኑ እንዳትዘነጉ።
Filed in: Amharic