>

የኦሮሞን ሕዝብ የሰደበው በቀለ ገርባ ወይስ ህሊና ደሳለኝ (አዳነ ሃይሉ)

የኦሮሞን ሕዝብ የሰደበው በቀለ ገርባ ወይስ ህሊና ደሳለኝ

 

አዳነ ሃይሉ

አቦ በቀለ የወጣቷን ገጣሚ ህሊና ደሳለኝ ግጥም አስመልክቶ የሰጠውን አስተያየት አድምጬ በዝምታ ማለፍ አልቻልኩም፤  እናም ይህቺን አጭር አስተያየት ልጫጭር ተነሳሁ። በቀለ ገርባ ግጥሙን በአጸያፊ ቃላቶች የታጨቀ ሲል አነውሮታል። የህዝብ መብት ደፍጣጭ ሲል ወንጅሎታል። በጸሃፊዋና ግጥሙን ባደመጡት ባለስልጣናት ላይ ሁሉ በርካታ ገራሚ ውንጀላዎች ሰንዝሯል። የግጥሙን ጠቅላላ ይዘት ሂትለራዊ ዘረኝነት ሲልም ገልጾታል።

እኔ አስተያየት ልሰጥበት የፈለኩት ግን ከውንጀላዎቹ አንዱ በሆነው “ውሻ” ተብለናል በሚል እየተንገፈገፈ በሰነዘረው ሃሳብ ላይ ነው።

በቀለ ገርባ ውሻ በሚል ተሰድበናል የሚል ክስና ውንጀላ ያቀረበበትን የግጥሙን ክፍል ቀንጭቤ በማውጣት የውንጀላውን ጭብጥ ለመፈተሽ እሞክራለሁ። ሙሉውን ሃሳብ ለማግኘት ለውንጀላው መሰረት የሆነውን “ውሻ” የሚለውን ቃል ከያዘው ስንኝ በፊት ያሉት ስንኞች የተሸከሙትን ሃሳብ መፈተሽ ግድ ይላልና የሚከተሉትን ስንኞች አብረን እንመልከት …

«…….
ሙያተኛ ሃገሬ ከማጥገብ ጎደለ በረከት ራቀው የገበታሽ ለዛ፤
ተሻምቶ ለመጉረስ ከበላነው ይልቅ የደፋነው በዛ
ሙያሽ ባያስደፍር አጀብ ቢሰኙበት ፤
ማዕዱ ቢሙላላ አይነቱ ቢያምርበት፤
አበዛዙ አይደለም አበላሉ ላይ ነው የገበታሽ ውበት፤
እየተማመንን …!
የፉክክር ቅሚያ በርሃብ እየናጠን፤
ከደፋነው ጠግቦ ውሻችን በለጠን፤
……..»

ከላይ ባሉት ስንኞች የተላለፈው ሃሳብ በአጭሩ ሲቀመጥ

ሃገሬ ሆይ! አጀብ በሚያሰኘው ሙያሽ በየአይነቱ ያዘጋጀሺው ማዕድ ገበታ ቢሞላም ፤ እኛ ልጆችሽ በሥነ ሥራአት መብላት አቅቶን ስንሻማና ስንቃማ፤ አብዛኛው ምግብ መሬት ተደፍቶ ለውሻ ሲሳይ ሆነ። ገበታ ሙሉ ጣፋጭ ምግብ ብታቀርቢልንም ከርሃብ አልወጣንም። ውሻችን ግን ከኛ የወዳደቀውን በልቶ ረሃቡን አስታገሰ። ጠገበ። እናም ዋናው ቁምነገሩ የምግቡ መብዛት ሳይሆን አበላሉን ማወቅ ነው። ” የሚል ነው፡፤

ይሁንና ኦቦ በቀለ ገርባ ይህን ግልጽና የማያሻማ ምክር አዘል መልዕክት በጀዋርኛ አንሸዋሮ በመተርጎም “ገጣሚዋ ውሻ ያለቺው እኛን ነው” በሚል ስሜት የሰነዘረውን አስተያየት አድምጬ አንድም ሳቅኩ ሁለትም ተሳቀኩ።

ኦቦ በቀለ ሆይ! እውነት እውነት እልሃለሁ! ይህ ላሟ ከብት ባልዋለበት ኩበት ለቀማ አይነቱ ትርጉምና አስተያየትህ ከማንም በላይ እራስክን ትዝብት ላይ የጣለና ምሁራዊ እሴቶችህን ጥያቄ ውስጥ የከተተ ሆኖብኛል።የሚያሳቅቀውም እሱ ነው…. እሴት አልቦ ምሁርነት!

ወደ ግጥሙ ልመለስ…

በግጥሙ ውስጥ በገበታው ዙሪያ ከበው የሚናጠቁትና የሚሻሙት በሙሉ “ሃገሬ” በሚል መጠሪያ የተወከለቺው የኢትዮጵያ ልጆች ስለ መሆናቸው ታሳቢ ተደርጓል። ገበታውን ከበው ከተቀመጡት የኢትዮጵያ ልጆች አብዛኛውን ቁጥር የሚሸፍኑት ደግሞ አቶ በቀለ እወክለዋለሁ የሚለው የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች መሆናቸውም ግልጽ ነው። ታዲያ አቶ በቀለ በገበታው ዙሪያ የተሰየመውን የልጅነት ገጸባህሪ ወደ ጎን በመግፋት ውድቅዳቂ የሚለቅመውን የውሻውን ገጸ ባህሪ መወከል የመረጠበት ምክንያት ምን ይሆን ?

ያልተባለ ነገር ተባለ ብሎ መናገር ህዝብን ከህዝብ በማናቆር የማይረባ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል  ?  አቦ በቀለ የዘነጋው ወይም ከታሪክ ሊማር ያልቻለው  ትልቅ ቁምነገር  ህዝብን በህዝብ ላይ በማስነሳት የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ አለመኖሩን ነው። ይብላኝ ለራስህ እንጂ ነፍሱን ይማረውና ሰሎሞን ተከልኝ እንዳለው “የሩዋንዳን ታሪክ አንደግመው እኛ” …..

ብቻ! …አቦ በቀለ ይህን ያለበት ምክንያት ምንም ይሁን የኦሮሞ ህዝብ ከወንድሞቹ ጋር በገበታ ዙሪያ በክብር ከተቀመጠበት አስነስቶ “ውሻ ተባልክ” በሚል የሰደበው እሱ ራሱ እንጂ ወጣቷ ገጣሚ ህሊና ደሳለኝ አለመሆኗን አስምሬበት ማለፍ እሻለሁ ። ገጣሚዋ ግልጽ አድርጋ ያስተላለፈቺው መልዕክት ‘ ሰው ፍቅር ካገኘ ምግብማ ሞልቷል” የሚል ነው። ተስማምተን በፍቅር ከተቋደስን የናታችን ሙያና ጓዳ እንኳን ለኛ ለቤት እንስሳትም ይተርፋል የሚል ምክር ነው።

ደግነቱ የበቀለ ገርባ አስተያየትም ሆነ ጀዋራዊ ትርጉም የሚወክለው እራሱንና እራሱን ብቻ እንጂ ከወንድሞቹ ጋር በገበታው ዙሪያ የተሰየመውን መላውን የኦሮሞ ህዝብ ባለመሆኑ እዳው ገብስ ።

ለነገሩ የኦቦ በቀለ ነገር የበቃን እኮ ራሱ የሥነ-ቋንቋ መምህር ሆኖ ትውልድን ግን ቋንቋ እንዳይለምድ (እንዳይማር) የመከረ ግዜ ነው። …..

በመጨረሻም ከህሊና ደሳለኝ ግጥም ምርጥ ያልኳትን ስንኝ ላካፍላችሁና ልሰናበት

አየህ ሰው ስትሆን ……
የጎጥ አረም ነቅለህ በአንድነት መስክ ላይ ፍቅር ትዘራለህ!
በወረወሩብህ የጥላቻ ድንጋይ ድልድይ ታበጃለህ፤

በነገራችን ላይ ለወጣቷ ገጣሚ ያለኝ ክብርና አድናቆት ቃላት ሊገልጹት ከሚችሉት በላይ ነው። እውነትም ይሄ ትውልድ ፍም እሳት ነው…..!ብያለሁ! ብራቮ ህሊና!!!

ቸር እንሰንብት

አዳነ ኃይሉ

Adanehailu2002@gmail.com

Filed in: Amharic