>

ፈጣሪ ኢትዮጵያን መቼውንም እንደማይረሣት የምናምነው ለዚህ ነው (ነፃነት ዘለቀ) 

ፈጣሪ ኢትዮጵያን መቼውንም እንደማይረሣት የምናምነው ለዚህ ነው

ነፃነት ዘለቀ 

እንኳን ከዘመነ ሉቃስ ወደ ዘመነ ዮሐንስ በ“ሰላምና በፍቅር” አሸጋገረን፡፡ ዕለተ ሰኞ፣ መስከረም 5 ቀን 2012 ዓ.ም፡፡
ተመልከት – ሶማሊያና ሦርያ ከሞላ ጎደል ከምድረ ገጽ ጠፍተዋል፡፡ ምናልባት ፖለቲካዊ ኅልውና እንጂ እውናዊ ኅልውና አላቸው ማለት ያስቸግራል፡፡ የነዚህን ሀገሮች ፈለግ የተከተሉ ብዙ ሀገራትም አሉ፡፡ ኢራቅ፣ ዩጎዝላቪያ፣ የመን፣ አፍጋኒስታን፣ ሊቢያ፣ …. ለይስሙላ አለን ይበሉ እንጂ ብዙዎቹ በመኖርና ባለመኖር መካከል የሚንጠራወዙ ናቸው፡፡ ይህን የምለው በአንድ በኩል የእነዚህ ሀገራት ሕዝቦች በሃይማኖትም፣ በቋንቋም፣ በቀለምም አንድ ሆነው ሲያበቁ በጥቃቅን ልዩነቶች ሰበብ ከመኖር ወደ አለመኖር መለወጣቸውን ለመጠቆም ሲሆን በሌላ በኩል ሃይማኖትንና ጎሣን ጨምሮ በብዙ ነገሮች የምንለያይ እኛ ኢትዮጵያውያን ግን በውስጥና በውጪ ጠላቶቻችን የጥፋት ድግስ ቢደገስልንም እስካሁኒቷ ደቂቃ ድረስ ውድመታችንና መበታተናችን ጠላቶቻችንን በሚያረካ ሁኑታ የሠመረ አለመሆኑን ለማጠየቅ ነው፡፡ በተለይ ግብጽና መሰል የዐረብ ሀገራት ብዙ ቢደክሙም የያዘ ይዟቸው እስካሁን እኛ አብረን አለን፡፡ አሁንም እንደዱሮ እንጋባለን፤ እንዋለዳለን፤ በፍርድ ቤቶችና በባህላዊ የሽምግልና ሂደቶች እንዋዋሳለን፤ በብዙ ነገር አልተለያየንም፡፡ በዕድሩ፣ በፅዋ ማኅበሩ፣ በዕቁቡ፣ በቤት ሥራ ማኅበራቱ፣ በአበልጅነቱ፣ … አንዱ ጎሣ ከሌላው ጎሣ መቆላለፉን ቀጥሏል፡፡ ይህ የሚገርም ትስስራችን የበላዮቻችን (መንግሥቶቻችን) ባይፈልጉትምና በጥይት ሳይቀር ቢዋጉትም እኛ ግን ከነሱ በተቃራኒ እየተጓዝን የልዩነት መርዛቸውን ሁሉ ማክሸፋችንን ቀጥለናል፡፡ ልብ አድርጉ – በቋንቋና በሃይማኖት አንድ የሆኑ ሶማሊያውያንና ሦርያውያን ጃርት እንደበላው ዱባ እዚህም እዚያም ሲዝረከረኩ እኛ ግን እንደምንም ብለን በፈጣሪ ረድዔት አብረን አለን፡፡ ይህም የሚያሳየው ፈጣሪ ከኛ ጋ መሆኑን ነው፡፡ እንጂ እንደኛ ድንቁርናና ፈዛዛነት ቢሆንማ ኖሮ እስካሁን የለንም፡፡ የአዲስ አበባን አሥረሽ ምቺውና የብዙዎችን ራስ ወዳድነት በድራቢውም ገንዘብ ወዳድነትና መከዳዳት ሲታይ ውለን ማደራችን ይገርማል፡፡
ቋንቋን ከተናጋሪ እንለይ!
እንግሊዝኛን በአፍ መፍቻነት የሚናገሩ ሰዎች 60 ሚሊዮን አካባቢ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን እንግሊዝኛ የዓለም ሕዝብ አንዱና ትልቁ የጋራ ሀብት ነው፡፡ እንግሊዞች እንደዜጋ የፈለጉትን ይሁኑ፡፡ ያ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ለዓለም ያበረከቱት ስጦታ ግን ወደር የማይገኝለት ነው፡፡ በዚህም ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ አንድ ቋንቋ በአፍ መፍቻነት ማንም ይናገረው ማን ጠቀሜታው ሁልአቀፍ ከሆነ ብዙ ሳይደክሙ በረከትን ማፈስ ነውና ተጠቃሚዎች ወሮታ ከፋይ ናቸው እንጂ ውለታቢስ ሊሆኑ አይገባም፡፡ ነውር ነው፡፡
አማርኛ መቼና ማን እንደፈጠረው ለዚህ ገጽ አይጠቅመኝምና ይቅር፡፡ ይሁንና ላለፉት በርካታ ምዕተ ዓመታት ኢትዮጵያን አዋህዶ በማስተዳደር ረገድ ያበረከተው አስተዋፅዖ እጅግ የሚደነቅ ነው፡፡ ወደ ሥልጣን የሚመጣው ሽናሻ ይሁን ጠምባሮ፣ ወይጦም ይሁን ኮንሶ፣ አገውም ይሁን ቅማንት… ይህ ቋንቋ በመንግሥት አፍነት እያገለገለ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ኢትዮጵያ ጠላቶቿ እንደሚመኙላትና ሌት ከቀን ተግተው እንደሚዶሉቱባት እንዳትፈራረስ የራሱን ድርሻ ተወጥቷል፡፡ ይህም ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡
መብቱ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ውኃን አልጠጣም ብሎ አንድ ሰው ቢያምጽ የሚጎዳው ራሱ ነው፡፡ እህል አልቀምስም ብሎ አንድ ሰው በራሱ ላይ ዐድማ ቢመታ ተጎጂው ራሱ ነው፡፡ ከዚህ መሠረታዊ እሳቤ አንጻር አሁን አሁን የምንሰማቸው አንዳንድ አስቂኝ ነገሮች አሉ፡፡ በተለይ በትግራይና በአንዳንድ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ አካባቢዎች እየተስተዋለ ያለው አማርኛን ያለመገልገል “ዐድማ” የሕጻናት ዓይነት ኩርፊያ እንጂ ወንዝ ቀርቶ ምንጭ የማያሻግር ድርጊት ነው፡፡ አማርኛን አለመናገር አቶ ስንሻውን ወይም እመት ተጓዳን አይጎዳቸውም፡፡ አጎቴ ዳምጠው በረደድ በዚህ የቂሎች ተግባር የሚጎዳ ከሆነ ይገርመኛል፡፡አማርኛ ባለመነገሩ አማሮች የሚባሉ ሰዎች አንድም ጉዳት አይደርስባቸውም፡፡ እንዲያውም በጊዜ ሂደት አትራፊ ይሆናሉ፡፡ ማንም እየተነሣ “አማራ አማራ” በሚል ያልተገራ መረን አፉን አይከፍትባቸውምና በሂደት የራሳቸውን ሕይወት በሰላም ይመራሉ፡፡ አሁን እየሆነ ያለው ግን ወርቅ ላበደረ ጠጠር እንደመመለስ ዓይነት ነው፡፡ በእግሊዝኛ ወሬ እየጠረቁ በወል ቤት ያሳደገንን ቋንቋ መጥላት ከዕብደት አንድ ነው፡፡
ለማንኛውም ነገሩ እንዲህ እንደምናወራው ቀላል አይደለም፡፡ አንድን ቋንቋ ለማውረድ የሚደረገው ጥረት ለመስቀል ከሚደረገው ጥረት ቢብስ እንጂ አይተናነስም፡፡ እንደዚያ ቢሆን ኖሮ በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ የጋራ ቋንቋ ግዕዝ በሆነ ነበር፡፡ በመቀጠልም “ምድርን ቀርቶ መንግሥተ ሰማይን የመቆጣጠር አቅምና ችሎታ አለን” እስከማለት የደረሱት ሕወሓቶች አማርኛን በትግርኛ ለውጠው ይሄኔ ምድረ አበሻ አብዚሎ ቀብዚሎ ባለች ነበር፡፡ ጉልበትና ቋንቋ ለየቅል ናቸው፡፡ ሞኞች ግን ይህን አይረዱም፡፡ ገና ለገና አንዲት ደቃቅ ዕድል ደጃቸው ላይ ስላረፈች ብቻ ሁሉንም ነገር ማድረግ እንችላለን ከሚል ዕብሪታዊ ዕብደት እያደረጉ ያሉትን ሲያደርጉ ለመታዘብ ታሪክ ንግርታዊ ዕዳውን ከነኮተቱ አሸክሞናል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥና በዙሪያዋ የሚደረገውን የአክራሪ ኦሮሞዎች አጉል ጀብደኝነት ብትመለከቱ ትገረማላችሁ፡፡ እነሁሉ አማረሽ ገበያ ወጥተው ሀገር ምድሩን እያመሰቃቀሉት ይገኛሉ፡፡ ሥልጣን ሁሉ የነሱ ነው፤ መሬቱ ሁሉ የነሱ ነው፤ ቀበሌና ክፍለ ከተማው የነሱ ነው፤ የአነጋገር ለከት የለሽ ጉራው ከነእንቶኔ በኮፒፔስት እንዳለ ተኮርጆ ከባለጊዜ ተብዬዎቹ ከእነሱው ጋር ነው፡፡ … ያዝልቅላቸው ከማለት ውጭ ምን ይባላል? ግና “ለኃጥኣን የመጣ ለጻድቃን ይተርፋል” እንዲሉ ነውና ለነሱ የሚመዘዝ ሠይፍ ሀገራችን ላይ በቀላሉ የማይጠፋ ጠባሳ ትቶ እንዳያልፍ እፈራለሁ፡፡ ከአንጀት በጣም እፈራለሁ፡፡ እናንተም ይህንን ፍሩልኝ፡፡ ፍሩናም በቻላችሁት መንገድ ሁሉ ምከሯቸው፡፡ መጥፎነቱ ጆሮ የላቸውም፡፡ ደራሽ ጎርፍ የሚያመጣው ወርቃማ ዕድል ዐይነ-ኅሊናን ያሣውራል፤ ዕዝነ-ልቦናን ያደነቁራል፡፡ አይጣል ነው!
ኢትዮጵያ ውስጥ ከ80 በላይ ቋንቋዎችና ከ200 በላይ ዘዬዎች እንዳሉ ይነገራል፡፡ አንድ ቋንቋ ደግሞ መቶ ሚሊዮንም ይናገረው ሁለት መቶ ሚሊዮን ዋናው “በጎሣዎች መሀል እንደ ድልድይ ሆኖ ብዙኃንን ያገናኛል ወይ?” የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በተናጋሪ ብዛት ቢሆንማ ኖሮ በአሁኑ ወቅት የዓለማችን የጋራ ቋንቋ መንደሪን (የቻይኖቹ ነው) በሆነ ነበር፡፡ እነሱ ራሳቸው በአሁኑ ወቅት በሠሩት የጅል ሥራ እየተቆጩ እንደሆነ እንሰማለን፡፡ ቋንቋ ላይ አነጣጥሮ እኝኝ ማለት የኋላ ኋላ የጎን ጉዳት አለው፡፡ ቻይኖች በራቸውን ዘግተው በቻይንኛ ብቻ ለመራመድ መሞከራቸው አሁን ዋጋ እያስከፈላቸው ነው፡፡ ስለዚህም በአሁኑ ወቅት የዓለምን ኢኮኖሚ ለመቆጣጠርና ሸቀጣቸውንና አገልግሎታቸውን ወደ ሰፊ ገበያ ለማምጣት እንግሊዝኛን እየተማሩ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ የቋንቋ አርበኝነት ዱሮ በየዋሆቹ ዘመን ቀረ ወዳጄ! ግን ግን – እስኪ እናንተም ይታያችሁ – ነገ በሦስት ክንድ መሬትና በሦስት ክንድ እራፊ ጨርቅ(አቡጄዲ) ተጠቅልሎ ያለምንም ቋንቋና ያለ አንዳች ቤሣቤስቲን ጥሪት ጥርኝ አፈር የሚሆን የሰው ልጅ ዛሬ በሕይወት እያለ ለዚህች ለሦስት ቀን የምድር ኑሮው መስማማት ሲገባው እንዲህ በማይረባ የመግባቢያ መሣሪያ ሲነታረክና ጦር ሲማዘዝ ሳይ ግርም ይለኛል፡፡ በእውነቱ በመካከሉ ምን ገብቶበት ይሆን? የባቢሎናውያን መንፈስ እንዴት ሊጋባብን ቻለ? እንጸልይ!
አንድ ቋንቋ ከአንድ ሰው ጋር ያለው ግንኙነት ይቺ የኪስ ቦርሣየ ከኔ ጋር እንዳላት ግንኙነት ነው፡፡ ተፈጥሯዊ ግንኙነት የለንም – እኔና “ቋንቋየ”፡፡ ሸሚዝና ከናቴራ አዲስ እንደሆኑ ሁሉ አርጅተው ይጣላሉ፡፡ ቋንቋም እንደዚሁ ነው፡፡ ይወለዳል፤ ያድጋል፤ ይሞታል፡፡ ባሕርያዊ ያልሆነና በውርስም የማይገኝ ነው፡፡ በተወለዱሽና ባደጉሽ እንጂ የእናት የአባት ቋንቋ ብሎ ነገር የለም፡፡ እናም አንድ ቋን በደም ትስስር ከሚወረስ አንድ ሞሰብ ወይም ሌማት ያነሰ እንጂ እስከዚህ ነጠላ አዘቅዝቀው ሙሾ የሚወርዱለት ነገር አይደለም፡፡ ስለዚህም ኦሮሚፋ ትግሪፋ አማሪፋ የምትሉ ሞኛ ሞኞች ከሥነ ልሣን ዕውቀትና ግንዛቤ አኳያ ጥርስን አስወቅሮ ከሚያስቅ ከዚህ ውዝግብ በቶሎ ውጡ፡፡ መውጣት ያለባችሁ ስለማይጠቅማችሁ ብቻ ሣይሆን እውነቱ እናንተ ከምታውቁት የተለዬ ስለሆነም ነው፡፡ የዓለም ቋንቋዎች ሁሉ የዓለም ሕዝብ የእኩል ንብረቶች ናቸው፡፡ ትግርኛ የአማራውም ነው፤ ኦሮምኛ የትግሬውም ነው፤ ጉራግኛ የአማራውም ነው፤ ልዩነቱ – የፍላጎት ነገር ታሳቢ ሆኖ – ቋንቋን ለመማር ወይም ለመልመድ ያለን ሰፊ ወይም ጠባብ ዕድል ነው፡፡ ብልኆች ብዙ ቋንቋዎችን ይማራሉ፤ ሞኞች አንድ ብቻ የሚበቃቸው ይመስላቸዋል፡፡ አንድ ሰው አንድ ቋንቋ በጨመረ ቁጥር አንድ የምሥጢር መፍቻ ቁልፍ እንደጨመረ ይቆጠራል – ይላሉ የዘርፉ ምሁራን፡፡ ትክክልም ነው፡፡ ስለዚህ አንድን ቋንቋ ማወቅም ሆነ አለማወቅ የሚጎዳው ግለሰቡን ነው፡፡ አንድ ሰው ቋንቋ እንዳያውቅ በተፅዕኖ መገደብ ደግሞ ከወንጀል አይተናነስም፡፡
ይቺ የመን አልለቀቀችንም!
ሰሞኑን ያ ቆፍጣና ኢትዮጵያዊ መምህር ታዬ ቦጋለ እንዳወጣው ምሥጢር ከሆነ ጃዋር መሀመድ ኦሮሞ አይደለም፡፡ እናቱ ኢትዮጵያዊ (አማራ) አባቱ ደግሞ የመናዊ ናቸው ተብሏል፡፡ ኦሮሞነቱ በዕድገቱ እንጂ የኦሮሞ ተወላጅ አይደለም፡፡ በርግጥም ከመልኩም መረዳት እንደሚቻለው ወደ ነጭነት የሚያደላ እንደመሆኑ የውጭ ደም እንዳለው መገመት አይከብድም፡፡ ይህ ጉዲፈቻ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ከተላኩ ብዔል ዘቡላውያን አንዱ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ባልተወለደበት የኦሮሞ ማኅበረሰብ ውስጥ ተወሽቆ ያን ሕዝብ እንደሚወክልም ተቆጥሮ በሕዝቡ ስም ይህን ሁሉ ግፍና በደል ሊያደርስ ባልተገባ ነበር፡፡ ሃይ መባል ነበረበት፡፡ ካልመሸ አሁንም የሚመለከተው አካል ጥግ ያሲዝልን፡፡ ሳቢውን መግረፍ ሳይሆን ዳተኛን መገሰጽ ሀገርን ከውድመት ሕዝብንም ከዕልቂት ይታደጋልና ይህ ጉዳይ ቸል ባይባል ደግ ነው፡፡
እናም ከዚህ እውነት የምንረዳው ሌላ እውነት የመኖች እጃቸውን ያላነሱልን መሆናቸውን ነው፡፡ በራሱ አንደበት በግማሽ የመናዊነቱን የተናገረው ትልቁ የመናዊ መለስ ዜናዊ ሲሞት ትንሹ የመናዊ ጃዋር መሀመድ ተተክቶ አሣራችንን እያስቆጠረን ነውና ፈጣሪ ይህን ጎልማሣ የመናዊ አንድ እንዲለው በጋራ ወደርሱ እንቅረብና በምህላና በሱባኤ እንጠይቀው፡፡ ፍርጃ ከሆነ ከቅርባችን ከየመን ቀርቶ ከሩቆቹ ከአላስካና ሣይቤሪያም ቢሆን የአጋንንት ውላጆችን ፈጣሪ አምጥቶ አበሳን ማሳየት አይሳነውምና አንድዬ ከልብ እንዲታረቀን እንለምነው፡፡

በተረፈ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡ 2012 የሀገራችን ትንሣኤ የሚበሠርበት ዓመት ይሁንልን፡፡

(netsanetz28@gmail.com)

Filed in: Amharic