>
10:31 am - Wednesday December 7, 2022

ለኦዴፓ ፦ ከጃዋር እና ከኢትዮጵያ አንዱን ምረጡ!!! (ስዩም ተሾመ)

ለኦዴፓ ፦ ከጃዋር እና ከኢትዮጵያ አንዱን ምረጡ!!!
ስዩም ተሾመ
የእነ ጃዋር መሠረታዊ ዓላማ ምንድነው? በእርግጥ ብዙዎች በዚህ ጉዳይ ላይ የተለያየ ሃሳብ እና አስተያየት ይሰጣሉ። ነገር ግን ነገሩን በግልጽ ለመረዳት የእነ ጃዋርን አካሄድ ከመሠረታዊ የሀገር አመሠራረት ፅንሰ-ሃሳብ አንፃር ማየት ተገቢ ነዉ። በመጀመሪያ ደረጃ የትኛውም ሀገር የሚመሰረተው የተሳሰረ ህልውና፣ የጋራ ታሪክ እና የወደፊት አብሮነት አለን ብለው በሚያምኑ ህዝቦች መካከል ነው። ከዚህ ውጪ የተመሠረተ ሀገር ቢያንስ ከአንድ ቢበዛ ደግሞ ከሁለት ትውልድ በኋላ ይፈርሳል። ከላይ በተጠቀሱት ሦስት የማዕዘን ድንጋዮች ላይ ያልቆመ ሀገር ያለ ምንም ጥርጥር ይፈርሳል። የአሁኗ ኢትዮጵያ የተመሠረችው አደዋ ላይ ነው ማለት ይቻላል። የኢትዮጵያ ብሔሮች እና ብሔረሰቦች በጋራ በህልውናቸው ላይ የተጋረጠውን ቀጥተኛ አደጋ በትብብር መግታት ችለዋል። በዚህም የጋራ ታሪክ መስራትና ለወደፊት በአብሮነት በመስማማት ሀገር መስርተዋል። እነ ጃዋር መሃመድ እየሄዱበት ያለው መንገድ እነዚህ ሀገሪቷ የቆመችባቸውን ሦስት መሠረቶች ለመናድ ዓላማ ያደረገ ነው።
የአብዛኛው የኦሮሞ ልሂቃን ዓላማ በኢትዮጵያ ስር የህዝባቸው እኩልነትና ተጠቃሚነት እንዲከበር ማስቻል ነው። እንደ ኦቦ ሌንጮ ለታ እና ሌንጮ ባቲ ያሉ የቀድሞ የኦነግ አመራሮች አቋማቸውን ከተገንጣይነት ወደ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነት ሲቀይሩ ትላንት የመጡት እነ ጃዋር ደግሞ ኢትዮጵያን አፍርሶ ነፃ ኦሮሚያን መመስረት ዓላማ አድርገው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ። ከእኛ ውጪ ያለው ህዝብ አያሳስበንም የሚለው የኦሮሞ ህዝብ ከተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር የተሳሰረ ህልውና የለውም ማለት ነው። የኦሮሞ ህዝብ በአደዋ ድል ላይ ያለውን ድርሻ የሚያንኳስሱት በሀገር ምስረታ ታሪክ ውስጥ የነበረውን ሚና ለማጥፋት ነው። የተሳሰረ ህልውና እና የጋራ ታሪክ የሌለው ህዝብ የወደፊት አብሮነት አይኖረውም። በዚህ መልኩ እነ ጃዋር ኢትዮጵያን የማፍረስ ዓላማና ግብ ይዘው በመስራት ላይ ይገኛሉ። እነሱ ይህን አምነው በግልጽ ባይናገሩትም መሠረታዊ ዓላማቸው ኢትዮጵያን ማፍረስ እንደሆነ መገንዘብ ቀላል ነው። ስለዚህ ይህን ተጨባጭ እውነታ አውቆና ተገንዝቦ በዚህ ላይ የተመሠረተ የመፍትሔ አቅጣጫ መንደፍ ያስፈልጋል።
በመጀመሪያ ደረጃ ኢትዮጵያን ለማፍረስ አስቦና አቅዶ እየሰራ ካለ ሃይል ጋር ስለ አንድነትና አብሮነት በማውራት ችግሩን መፍታት አይቻልም። እዚህ’ጋ ከግንዛቤ መግባት ያለበት የመጀመሪያው ነገር፣ ማንም ቢሆን ከሌላው ኢትዮጵያዊ የበለጠ የሀገሪቱን አንድነት የመታደግ ዕዳና ግዴታ የለበትም። ሁሉም ዜጋ የኢትዮጵያን አንድነት የመታደግ ግዴታና ሃላፊነት አለበት። ይህን የጋራ ግዴታ በመወጣት ረገድ ሁሉም የሚጠበቅበትን መወጣት ከተሳነው የኢትዮጵያ መፍረስ የሚያስከትለውን ጉዳት እኩል መጋራት አለበት። ከዚህ በተጨማሪ እያንዳንዱ ብሔር ራሱን ከኢትዮጵያ ውጪ አድርጎ ለማሰብና ራሱን ችሎ ለመኖር ማዘጋጀት አለበት። ይህ ካልሆነ ደግሞ የኦሮሞና አማራ የሃይል ፍጥጫ በሚያስከትለው ለመቀራመት ራሱን መስዕዋት ለማድረግ ቀድሞ መዘጋጀት አለበት። ሌላው የኦሮሞ ህዝብ ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ወይም ላለመገንጠል ቅድመ-ዝግጅት ማድረግ አለበት። ኦሮሞ ከኢትዮጵያ መገንጠል የሚሻ ከሆነ ዓላማውን ይፋ አድርጎ ከእነ ጃዋር ጎን መቆሙን አለበት። መብትና ነፃነቱ ተከብሮለት በኢትዮጵያ ስር መኖር የሚሻ ከሆነ ደግሞ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር በአብሮነት እንዳይኖር እስከ መጨረሻው እያቃቃሩት ያሉትን ሰዎች ከጉያው ስር አውጥቶ መጣል አለበት። ሌላው ኦዴፓን ጨምሮ ሌሎች የኦሮሞ ፖለቲካ ቡድኖች ከኢትዮጵያ እና ከእነ ጃዋር አንዱን መምረጥ አለባቸው። በአንድ በኩል ኢትዮጵያን የማስተዳደር ስልጣንና ሃላፊነት ይዘው፣ በሌላ በኩል ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚተጋው ቡድን ጋር አብሮ እየሰሩ መቀጠል አይቻልም። በዚህ ረገድ ከኦሮሚያ ክልል መስተዳደር ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ያሉ የኦዴፓ አባላትና አመራሮች ከጃዋር እና ከኢትዮጵያ አንዱን መምረጥ ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም በጓሮ በር ሀገር ለማፍረስ ከሚተጋው ጋር እየተሞዳሞዱ በፊት ለፊት በር ኢትዮጵያን ማስተዳደር አይቻልም።
Filed in: Amharic