>
5:16 pm - Wednesday May 23, 8204

''የዒድ ተቃውሞ ተሰርዟል! የመንግስት የሽብር ዕቅድ እንዲሳካ አንፈቅድም!'' ድምጻችን ይሰማ!

እሁድ ሐምሌ 20/2006

Today Ethiopian Muslim Demo in Addis Abebaበሃምሌ 11 ‹‹የጥቁር ሽብር›› ቀን የሙስሊሙ ማህበረሰብ ትግል ፍጹም ሰላማዊነት ሰላም የነሳው መንግስት አሳፋሪና ታሪክ የማይረሳው የሃይል እርምጃ ወስዷል፡፡ ይህንኑ እብሪቱን በመቀጠል አሁንም በተመሳሳይ መልኩ የኢድ ቀን ተቃውሞ ላይ ከፍተኛ ብጥብጥና ሽብር አስነስቶ የሰው ህይወት በማጥፋት እንቅስቃሴያችንን ለማጠልሽት በከፍተኛ ዝግጅት ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ዒድ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲኖር ታቅዶ የነበረውን ተቃውሞ በሚከተሉት ዋና ዋና ምክንያቶች መሰረዝ አስፈላጊ ሆኗል፡፡
1. በመጀመርያ ደረጃ እንቅስቃሴያችንን ምንጊዜም ሰላማዊና የሰላም ወዳዱ ህዝባችንን ባህልና ክብር የጠበቀ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ስለዚህ ከህዝባችን ባህል እና ክብር ተፃራሪ የሆነ ተግባር ለመፈፀም እየተንቀሳቀሰ ካለው መንግስት ጋር በእኩል ደረጃ መገመት ለህዝባችንም ለእንቅስቃሴያችንም የማይመጥን በመሆኑና ለመንግስትም ያሰበውን እንዲያሳካ እድል መስጠት አስፈላጊ ባለመሆኑ፤
2. ‹‹ጥቂቶች›› እያለ ራሱን የሚያታልለው መንግስት በዒድ የሚኖረውን ግዙፍ ህዝባዊ ተቃውሞ በከፍተኛ ሁኔታ በመስጋት ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ በጣም አስተማማኝ መረጃ በመገኘቱ፤ በአሁኑ ወቅትም በመንግስት አካላት እየተካሄደ ያለው ውይይት ‹‹የምንወስደው እርምጃ በዱላ ይሁን ወይንስ በጥይት?›› የሚለው እንጂ የሃይል እርምጃ መውሰዱ አማራጭ የሌለው እንደሆነ ከውሳኔ መድረሱን በማረጋገጣችን፤
3. በመቀጠልም መንግስት ለራሱ የከሰረ የፖለቲካ ጥቅም ለመገብየት ደፋ ቀና የሚልበትን እኩይ እቅዱን ለማክሸፍና ይህንን ለማድረግ ያበቃውን ግዙፍ እንቅስቃሴ በመንግስት እርምጃ እና ማዋከብ ተቻኩሎ ረጅሙን ጉዟችንን በአጭር ትንፋሽ እንድንጨርስ የሚያደርጉ ማናቸውንም በሮች መዝጋት በማስፈለጉ፤
4. መንግስት በሙስሊሙ ላይ ከፍተኛ ግፍ የፈፀመ ቢሆንም ሃገር ለማስተዳደር ኃላፊነት ወስጃለሁ ብሎ የሚያስብ ከሆነ ከተግባሩ እንዲታቀብና አሁንም የሚመለከታቸው አካላት ቆም ብለው እንዲያስቡበት ለማድረግ፤
5. ላለፉት 3 አመታት ብዙ ችግሮችን ተቋቁመን ሰላማዊነታችንን ያስመሰከርን በመሆኑና አሁንም በዚሁ መርሃችን በመፅናት ሌሎች ዘርፈ ብዙና እስካሁን ድረስ ያልተሞከሩ ስልቶችን ደረጃ በደረጃ መተግበር የበለጠ ውጤታማ ያደርገናል ብለን በማመናችን፡፡
ስለሆነም ህብረተሰቡ የኢድ ቀን ምንም ተቃውሞ እንደሌለ በመገንዘብ ከዘመድ አዝማድ ጥየቃ በተጨማሪ በ‹‹ጥቁሩ ሽብር›› የተጎዱ ሰዎችን በመዘየርና እገዛ የሚፈልጉትንም በመርዳት እንዲያሳልፈው ጥሪ እናቀርባለን፡፡ ወደ ሰላት በምንሄድበትም ሆነ በምንመለስበት ወቅት ከመንግስት አካላት ሊደርስ የሚችልን ማንኛውም ትንኮሳ በትዕግስት በማሳለፍ ብስለታችንን እናሳይ፤ የመንግስትን አላማም እናክሽፍ! በተጨማሪም እኛን መስለው በየአካባቢያችን ባሉ መስጊዶች በመግባት ሙስሊሙን ማህበረሰብ ለአደጋ ለማጋለጥና ለመከፋፈል ከሚሞክሩ የመንግስት ሀይሎች ራሳችንን እንጠብቅ!
በዒድ ቀን በጋራ አንድነታችንን፤ ሰላም ወዳድነታችንን፤ ለእንቅስቃሴው ያለንን ክብርና ታዛዥነታችንን በማሳየት ለቀጣዩ ዘርፈ ብዙ ትግል እንዘጋጅ!
ትግላችን በአላህ ፈቃድ እስከ ድል ደጃፎች ድረስ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማ!

Filed in: Amharic