>

ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ በለውጥ ጎዳና (ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ - ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ)

ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ በለውጥ ጎዳና

 

ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ

ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ

 

ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ ብቁ መምህራንን በማፍራት በአገራችን በመምህራን ስልጠና እና በስፖርት ዘርፍ እድሜ ጠገብ የሆነ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ነበር፡፡ ተቋሙ ከዚህ በፊት በሚታወቅበት በመምህራን ትምህርትና በስፖርት ዘርፉ ያለውን ዕውቅና አጠናክሮ መቀጠል ሲገባው በዘመኑ በነበሩ የፖለቲካ ሊሂቃን ውሳኔ ወደ አዲስ አበባ ት/ቢሮ ከዛም ወደ አዲስ አበባ መስተዳድር ሲሽከረከር ቆይቶ በ2012 ብሩህ ተስፋ የፈነጠቀለት ይመስላል፡፡ አሁን ከበርካታ አመታት የእስር ጉዞው ተፈቶ ተጠሪነቱ ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሁኖዓል፡፡ ይህ የተቋሙን ዕድገት ለሚመኙ ሁሉ መልካም ዜና ነው፡፡

ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የአምስት ዓመቱን ስትራቴጅክ ዕቅድ ግንቦት ሰባት፣ 2011 ዓ.ም. በደብረ ዘይት/ቢሾፊቱ ላይ ለማስገምገም ባካሄደው የውይይት መድረክ ላይ “ተቋሙ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ስር እስካልሆነ ድረስ በአዲስ አበባ መስተዳድር ስር ሁኖ ሊያድግ እንደማይችል በነበረው ስብሰባ ተናግሬ ነበር፡፡” ለዚህም እንደ አስረጅነት አድርጌ ያነሳሁት የሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ተቋምን ተሞክሮ ነበር፡፡ ይህ ተቋም ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ምንም ዕድገት ያላሳየበት ምክንያት ተቋሙ ከመሰል ተቋማት ውጭ ርቆ ስለተገኘ ነው፡፡ በነበረው ስብሰባ ሰብሳቢው ክቡር ኢ/ር እንዳወቅ አብጤ የሚችሉትን እንደሚሞክሩ እና ካልተቻለ ግን ወደ ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተጠሪነቱን እንደሚያደርጉ ቃል ገብተው ነበር፡፡ የቦርድ ሰብሳቢው ክቡር ኢ/ር እንዳወቅ አብጤ በተናገሩት ቃል መሰረት የተቋሙ ዕድገት አሳስቧቸው አስፈላጊውን እርምት እርምጃ ስለወሰዱ አድናቆቴን እየገለፅሁ በዚሁ ሂደት ለተሳተፉ እና ቀና አመለካከት ለነበራቸው እና ተቋሙን ወደ ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲዛውር ጥረት ላደረጉ አካላት በሙሉ አድናቆቴ የላቀ ነው፡፡ በተለይ ግን ለኢ/ር እንዳወቅ አብጤ፣ ለፕሮፌሰር ሂሩት ወ/ማርያም፣ ለዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ፤ ለአዲስ አበባ መስተዳድር፣ ለፕሮፌሰር ባዬ ገላው፣ ለዶ/ር መላኩ መንግስቴ፣ ለዶ/ር ፈቃዱ መገርሳ፣ ለዶ/ር አካሉ ዳፊሳ፣ እና ለኮሚቴው አባላት ምስጋናችን የላቀ ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ ሙሉ በሙሉ ወደ ቀደምት ክብሩ እና ዝናው ይመለስ ዘንድ የመዋቅር እና የአስተዳደር ለውጥ ያስፈልገዋል፡፡ ምንም እንኳን ፕረዘዳንቱ ቀና፣ ገራገር እና ተቋሙን ለመለወጥ ደፋ ቀና ቢልም ተቋሙ ግን በርካታ ችግሮች አሉበት፡፡ ዋናው ተገዳሮቶች የመዋቅር እና የአመራር ችግሮች ናቸው፡፡

በፕረዘዳንቱ ስር የተሰገሰጉት አብዛኛዎቹ ዳይሬክቶሬቶች የቢሮ ፖለቲክስ የሚያውቁ፣ ብልጣብልጥ፣ አፈ- ጮሌ፣ ስለ ራሳቸው የተዛባ እይታ ያላቸው ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ ም/ፕረዘዳንቶች የአካዳሚክ ብቃት ወስንነት ባይታይባቸውም ዘመናዊነትን የተላበሰ የመሪነት ሰብዕና ግን የላቸውም፡፡ አብዛኛዎቹ ም/ፕረዘዳንቶች የአካዳሚክ ስልጣን ማንኛውም አካዳሚክ ስታፍ እንደ-ዱላ ቅብብሎሽ ሊቀያየርበት እንደሚችል ያልተረዱ፣ ኃላፊነትን የሚሸሹ፣ ውሳኔ የማይወሰኑ፣ በዳይሬክቶሬቶች እና በዲኖች ስራ ላይ ጥልቃ የሚገቡ፣ ያለ እነርሱ ቡራኬ ለጉዳዬች እውቅና የማይሰጡ፣ ያለ እነርሱ ተቆርቋሪ ያለ የማይመስላቸው፣ አቋም የሌላቸው፣ በውይይት ጉዳዬችን መፍታት የማይሞክሩ፤ ከአካዳሚክ ብቃት ይልቅ ቡድንተኝነት የሚያጠቃቸው ናቸው፡፡ ዳሩ ግን አብዛኛዎቹ ዲኖች ሚዛናዊነትን ያነገቡ፣ አካዳሚክ ብቃት ያላቸው፣ ለስራቸው የሚተጉ ቢሆኑም ሊሰሩ የሚችሉበት ዕድል ግን አልተሰጣቸውም፡፡

ስለዚህ እነዚህ አመራሮች ከተቋሙ የመተዳደሪያ ደንቦች ጋር በሙሉ ተቀይረው ሁሉም ቦታዎች በትክክለኛ መስፈርት በውድድር መያዝ ይገባቸዋል፡፡ ይህ እስካልሆነ ድረስ ግን ኮተቤን ወደ ተፈለገው የእውቀት ተቋም ማማ ማድረስ አይቻልም፡፡ ይህንን ደግሞ ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በተሎ ይፈፅመዋል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

Filed in: Amharic