>

ጎሠኝነት ይሉኝታና ሀፍረት (ግርማ በላይ)

ጎሠኝነት ይሉኝታና ሀፍረት

ግርማ በላይ

እኔንስ ኅሊና ደሳለኝን መሆን አያምረውም ያለው ማን ነው ?
ባልቻና ደቻሣ – ሐጎስና ማንጁስ እየተባባሉ፤
ከአጥናፍ እስካጥናፍ መላ ኢትዮጵያን ሲግጧት አደሩ፡፡
እኔ ምን ቸገረኝ ግጥሙ ቢያምር ባያምር፤
ለግጥምማ ማማር አዝማሪ አለ አይደለምወይ፡፡ (ብለዋል የፍቅር እስከ መቃብሩ ፊታውራሪ መሸሻ)

ያዝ እንግዲህ!

ሞኙ አበበ፣ ደርግ ባስታቀፈው በሶ ላይ እንደተጎለተ ጩቤ የጨበጠው ጫላ ድንገት ባነነና በያዘው ጩቤ በተለዬ ግብዝነትና ጭካኔ እንዲሁም ስግብግበነት አገር ምድሩን ይበጣጥሰው ገባ፡፡ ጩቤውን ከመጨበጡ ሁለት ዓመት እንኳን ሣይሞላው ገና ከጅምሩ አንስቶ እነሐጎስ 27 ዓመታት የፈጀባቸውን ሀገርን ለብቻ የመቆጣጠር ታላቅ ክፍለ ዘመናዊ ልክፍት በተግባር አሳዬ፡፡ ሞኝ ሲያጨበጭቡለት ይብስበታል መሰለኝ የላኩት የውጭና የውስጥ ምንደኞች የሞራል ድጋፋቸውን ሲሰጡት ጊዜ በሞቅታና በስካር መናፈሉን ተያያዘው፤ የገዛ መቀበሪያ ጉድጓዱንም እያራቀ መቆፈሩን በስፋትና በጥልቀት ተያያዘው፡፡ “ጅል አይሙት እንዲያጫውት”፡፡ በዚህ የቴክኖሎጂና የዕውቀት ዘመን ይህን መሰል ሞኝነት አስገራሚ ነው፡፡

ዘረኝነት መባሉ ካልቀረ በዚያው ልግፋበት – እኔ ግን በዚህ ቃል አላምንበትም፡፡ ምክንያቱም የአዳም ዘር አንድ ነው፡፡ በቀለምና በሃይማኖት ቢለያይም ዘሩ ግን ያው የሰው ዘር ነውና ልዩነቱ የጎሣና የነገድ እንጂ የዘር ሊሆን አይገባም እላለሁ፡፡ ለማንኛውም አሁንን ጨምሮ ባሣለፍናቸው ሃያና ሠላሣ ዓመታት ውስጥ ዘረኝነትን እስከጥጉ አየን፡፡ የመጀመሪያው ከአሁኑ መባሱንም ታዘብን፡፡ እኔን ጨምሮ በአንዳንድ ጉዳዮች የአሁኑ ከመጀመሪያው ቀለል ያለ ቢመስልም በመሠረተ ሃሳቡና በትርጓሜው ግን ዘረኝነት መገለጫዎቹና ገጽታዎቹ ሁሉ አንድና አንድ መሆናቸውን እንደመጀመሪያው ሁሉ በሁለተኛውም አረጋገጥን፡፡ ከሁሉም በባሰ ግን ማንኛውም ዘረኝነት ይሉኝታቢስነትና ሀፍረተቢስት ዋና መገለጫው መሆኑ ነው፡፡

ወደየትም ጥቅስና ምሁራዊ ትንተና ወይም ብያኔ (ድንፈያ) ሳንገባ ዘረኞች በሙሉ ልበ ሥውራን መሆናቸውን መረዳት ይገባናል፡፡ አንድ ሰው ዘረኛ ሆነ ማለት ከሰውነት ተራ ወጣ ማለት ነው፡፡ በቃ ያ “ሰው” ሰው አይደለም፡፡ ካለርሱ ዘር ሌላው ሰው ሣይሆን ከእንስሳም ያነሰ ፍጡር ነው፡፡ አንድ ምሣሌ እንይ – ጽዮናውያን የተቀረጹት በጽዮናውያን ዘር የበላይነት እሳቤ ነው፡፡ ለነሱ ሌላው እንስሳ ነው፡፡ እኛ እንስሳትን በምናይበት ዐይንና በምናስተዳድርበት መንገድ ጽዮናውያንም የነሱ ዘር ያልሆነን ሰው ያስተዳድራሉ – እንደነሱ አገላለጽ “ሰው”፡፡ ዘረኛ ተማረ አልተማረ ያው ነው፡፡ ዋናው እምነቱ ነው፡፡ ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል እኮ የተማረ ነው፤ መለስም እኮ የተማረና “ልዑሉ”ን(ዘ ፕሪንስን) ጨምሮ ብዙ የክፋት መጻሕፍትን ያነበበ ነው፡፡ በነገራችን ላይ አልተመዘገበ ይሆናል እንጂ ዘረኝነት ሃይማኖት ነው – የራስን ዘር እንደፈጣሪ የመመልከት(የማመን) ኃያል እምነት፡፡ ለአንድ ወያኔ “ቋንቋየ ነሽ ድንግል”ን ከምትከፍትለት ይልቅ “እምበር ተጋዳላይ”ንና “ትግራይ አደይ”ን ብትከፍትለት እንትኑ ብቻ ሣይሆን ሁለመናው ይስቃል፡፡ ለአንድ ኦነግ “ሾሌ ያ ነጭ ጠላ”ን ከምትከፍትለት “ኡመታቶታ ኦሮሚያ…” የምትለዋን የሀጫሉ ትሁን የጫልቱን ዘፈን ብትከፍትለት በደስታ ፈንጥዞ ገደል ሊገባ ይችላል፡፡ ዘረኝነት እስከዚህን ከአልጋ ወደ መንጋ ማነው ወደ ዐመድና አፈር አውርዶ ይፈጠፍጣል፡፡ ታዲያ በዚህ ይተከዛል ይጸለያልም እንጂ ይሳቃል? በምትገርም ዓለም ውስጥ እንደምትኖር ተገነዘብክልኝ?

በኛም ሀገር ሕወሓታውያንና ኦነግ/ኦህዲዳውያን (በሚሊዮኖች ይቆጠራሉ!) ሌሎቻችንን በተለይም አማራ የሚባሉትነን እንደ አህያ ያዩናል – እንዳታዝኑባቸው እንዳታሾፉባቸውም፡፡ ይህ ጠባይ መጥፎ በሽታ ነው፡፡ በሽታው ደግሞ መድኃኒት የለውም፡፡ መድኃኒቱ የአመለካከት ለውጥ ነው፤ የአስተሳሰብ ዕድገት ነው፡፡ ሂትለር ራሱ በብዙ መቶኛ ይሁዲ ሆኖ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ማይምነቱ አሣውሮት ባልሆነው የአርያን ዘር ፍቅር ተለክፎ ስንት ሚሊዮን የራሱን ሕዝብ እንዳጠፋ እናስታውስ፡፡ መለስ ዜናዊ በተለዬ ሰይጣናዊ የዘረኝነት መንፈስ ተሞልቶና በጥላቻና በበቀል ታውሮ ስንት ሚሊዮን ዜጎችን በተለይም አማሮችን እንዳጠፋ እናስብ፡፡ በአርመኖች ላይ፣ በኮሶቮ ሙስሊሞች፣ በኩርዶች፣ በግብጽ ክርስቲያኖች፣ በኢራቅ ሱኒዎች፣ በአፍጋኒስታን፣ በሦርያ፣ በየመን፣ …. የደረሰውንና እየደረሰም ያለውን ዘርና ሃይማኖት ላይ የተንተራሰ ዕልቂት እናስተውል፡፡…

የኞች ቂሎች አሁን እየሠሩት የሚገኙትን ወደጠቃቀስኳቸው የሞት ድግሶች የሚያመሩንን ነገሮች ደግሞ አንዘንጋ፡፡ አቢይ አህመድ ለሚዲያ ቅርብ ይመስለኛል፡፡ ምን እንደምንል ብቻ ሣይሆን ምን እንደሚሉንም ያውቃል፡፡ ማወቅ ብቻውን ግን በቂ አይደለም፡፡ ዕውቀትን ወደ ጥበብ መለወጥ ነው የሰው ልጅነት ዋና መለኪያና ተግዳሮት፡፡ የንግግር ማማርም አይደለም፡፡ የሥልጣን ቦታን መቆጣጠርም አይደለም፡፡ እነዚህ ነገሮች ዐይንን የሚያጥበረብሩ አወስላች ነገሮች ናቸው፡፡ ቃልን የሚያሳጥፉ መጥፎ አማላዮች ናቸው፡፡ ግን ግን ሁሉም ይከዳሉ፡፡ ሲከዱ ደግሞ ክፉኛ አዋርደው ነው፡፡ አቢይ ይህን ቀላል ሎጂክ አያውቅም አልልም፡፡ ግን ሥልጣን መጥፎ ነው፤ ሣጥናኤልንም ከክብሩ ያዋረደው ይሄው ልክፍት ነው፡፡

እናም “በኢትዮጵያ ዘረኝነት እየከፋ መጥቷል፤ ኦሮሞው ሁሉንም በግልጽ እየተቆጣጠረ ነው፤ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ፖለቲካውን በግልጽና በግላጭ እየተቆጣጠሩ እነሱ የማይወዷቸውን የእምነት ቤቶችና ምዕመናንን ለአደጋ እየጋበዙ ነው፣ ወዘተ.” የሚሉ አስተያየቶች ከወዲያ ወዲህ ሲሰነዘሩ አቢይና መንግሥቱ አያውቁም አይባልም፡፡ በደምብ ያውቃሉ፡፡ “ተጨፈኑ ላሞኛችሁ” የምትል በተለይ ኢሕአፓ አዘውትራ የምትጠቀምባት አባባል አለች፡፡ አቢይም በዚህች አባባል የተማረከ ይመስለኛል፡፡ እየሣቀና እያሣሣቀ ሰውን እያባበለ ወደ ገደል ይዞን እንዳይነጉድ እሰጋለሁ፡፡ ንግግሩና ተግባሩ ዐይንና ናጫ ሆነውበታል፡፡ ከሚሾማቸው ሰዎች ከጴንጤ ውጪ አንድ ሰው አላውቅም፤ ከሚሾማቸው ውስጥ ዕድሜያቸው በአማካይ ከአርባ አምስት ዓመት ውጭ አንድም ሰው አላውቅም፡፡ ስለዚህ – ሒሳባዊ ድምዳሜ ነው – ስለዚህ አቢይ አህመድ ከጴንጤና ከሚታዘዙለት ወጣቶች ውጪ አይሾምም ማለት ነው – በቃ፡፡ በመረጃ ያሳምነኝ – ማለቴ አንባቢን ያሳምን፡፡ እኔ በባዳ አልቆጣም፤ በጨለማም አላፈጥም፡፡ “የኔ ባልሆነ ሀገር”ና የኔ ባልሆነ ምድራዊ ዓለም ይህ ቀረኝ የምል ገልቱ አይደለሁም፡፡ በዜግነቴ ከሁሉም አንዱን የመሆን መብት ቢኖረኝም የምመኘው አንድ ነገር ብቻ ነው – አምላኬ የሀገሬን ትንሣኤ አሳይቶ በማግሥቱም ቢሆን እንዲወስደኝ፡፡ ወደመነሻየ ልሂድና ነገሬን ልቋጭ፡፡

…. በዚህ የሕይወት ውጣ ውረድ መሀል ነው እንግዲህ በሣቅ ያፈገገችኝን የትናንት ሹመት እንደዘበት የተመለከትኳት፡፡

ሹመቱ በብቃትና በችሎታ ሊሆን ይችላል፡፡ የአሹዋሹዋሙ ዓላማ (ኢንቴንሽን) እንጂ ማን የት ላይ ተሾመ እኔን ብዙ አያስጨንቀኝም – ሲፈልግ ዝንጀሮም ይጎልትበት፡፡ ግን “በብቃትስ ቢሆን ሁሉንም ቦታዎች ኦሮሞ መያዝ አለበት ወይ? ከሌሎች ጎሣዎች ሰው ጠፋ ወይ? አሁን ማ ይሙት ቴሌን ሊመራ የሚችል ትግሬ ወይም ወላይታ ወይም ጉራጌ ወይም ሶማሌ ጠፍቶ ነው? ምን እያደረጉ ነው?” ብሎ የሚጠይቅ ጀግና ቢነሳ እነ አቢይ መልስ የሚኖራቸው አይመስለኝምና ለዚህ ዓይነቱ የሚጠበቅ ጥያቄም መልስ እንዲያዘጋጁ ለመጠቆም ነው አነሳሴ፡፡ “የበላችው ያስገሳታል በላይ በላዩ ያጎርሳታል” እንዲሉ የሰው ሃሜት የማይሞቃቸው የማይበርዳቸው ሰገጤዎቹ ኦህዲዶች ከናካቴው ምን ይሉኝን አሽቀንጥረው ጥለው የሚሠሩትን ያጡ ይመስሉኛል፡፡ በአንድ በኩል ከፍ ሲል እንዳልኩት እነሱም በተያዙበት ህመም ሳቢያ በሚሠሩት መጥፎ ሥራ ያሳዝናሉ፡፡

አሁን ጭንቀቴ ለነሱም ነው፡፡ የጅል ሰው መጥፎ የሥራ ውጤት ደግሞ ለራሱ ብቻ አይደለም፡፡ ለንጹሓንም ይተርፋል፡፡ ተሹዋሚው ባልቻ ሬባ የተባለው ኦነግ/ኦህዲድ የመጀመሪያ ዲግሪ አለው፡፡ 15 ዓመታትን በሥራ ላይ ኖሯል፡፡ ወጣት ቢጤ ነው፡፡ ሃይማኖቱ ርግጠኛ ነኝ ጴንጤ ነው፡፡ አቢቹ ሥልጣን ላይ እያለ መቼም ካለ ጴንጤ ሌላ አይሾምም ብዬ ነው፡፡ በግል የማውቃቸው ሦስት ያህል ሹመኞች ለምሣሌ በስማምን የማያውቁ ፕሮቴስታንት ናቸው፡፡ … (በነገራችን ላይ ሁሉም ተሸዋሚ ኦርቶዶክስ ይሁን ወይም በኮታ ይሾ እያል አይደለም – በጭራሽ፡፡ አካሄዱና የሥራ አፈጻጸማቸው ሸርና ተንኮል እንዲሁሙ ዓለም አቀፉ የኢሉሚናቲዎች ሤራ የሚንጸባረቅበት በመሆኑ ብቻ ነው ይህን ሹት እየተቃወምኩት ያለሁት፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ነው – ኪስን ማለትም አእምሮን ይቀዳል፡፡)
አቢያቸው አሁን አሁን ወጥ እየረገጠች መጣች፡፡ ወጥ መርገጥ ጥሩ ነው፡፡ የራስን መስቀያ ገመድ በራስ መጎንጎንም ጥሩ ነው፤ የሀገርንና የሕዝብን የስቃይ ዘመን ያሳጥራልና፡፡ ፍየል ስትቀብጥ ሾል ማሽተት ትጀምራለች አሉ፡፡ መልካም ዕድል ዶክተር አቢይ አህመድ፡፡ ቻው፡፡

ግርማ በላይ (gb5214@gmail.com)

Filed in: Amharic