>
5:13 pm - Friday April 19, 2718

የጎሰኝነት ምሶሶ መወዛወዝ ጀምሯል (ቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ)

የጎሰኝነት ምሶሶ መወዛወዝ ጀምሯል
ቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ
“ካህያ ቆዳ የተሠራ ቤት፣
ናድ ናድ ይላል ጅብ የጮኸለት።” ብዬ ልጀምር። 
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ያዘጋጀው አጭር ዶኩመንታሪ ቅንብር በሀገሪቱ በሙሉ ባሉ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ከታየ በኋላ «ጎሰኝነት እና ኢትዮጵያዊነት» የገቡበት ጦርነት ድጋሚ ተሟሙቆ ቀጥሏል። ዶ/ር ዐቢይ ተዋናይ የሆኑበት የ44 ደቂቃ ዝግጅት አንድ አጭር ዶኩመንተሪ መሆኑ ቀርቶ የሀገራችን ፖለቲካዊ፣ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ጥያቄዎች ሁሉ ተቀንብበው የቀረቡበት የተዳፈነ እሳት ሆኖ ብቅ ብሏል።
እኔን የደነቀኝ ኢትዮጵያዊነትን እንደ አንድ ታላቅ ማንነት የተገለጸ ሲመስላቸው የጎሰኛው ቡድን ሁሉ መግቢያ ሲጠፋው ማየት ነው። ትናንት ታላቅ ነበርን ማለት እንቅልፍ የሚነሣቸው አያሌ ናቸው። ላለፉት 27 ዓመታት በመንግሥትነት ተንሰራፍቶ የነበረ የጎሰኝነት አይዲዎሎጂ አሁንም ራሱን ችሎ መቆም እንዳልቻለ ስለሚያሳየኝ ልቤ ይደሰታል። ኢትዮጵያዊነትን ለማብሰል ማገዶ አይፈጅም። ትንሽ ይበቃዋል። ዶ/ር ዐቢይ ጨከን አድርገው ኢትዮጵያዊው ብሔርተኛ ላይ ተማምነው መቆም ቢጀምሩ በርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ብዙ ደጋፊ አላቸው። የOMN anchors  እንደሚናገሩት ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅነው ወገን «ቤት አልባ» ሳይሆን «ሁሉም ሀገሩ ሁሉም ቤቱ» (ሁሉ ሀገርሽ) ነው። በአንድ አንዲት የ17 ዓመት ወጣት ልጅ ግጥም “መንጋ” ተባልን በሚል የተነጋነገው የጎሰኝነት ግምብ ፣ «የንጉሠ ነገሥቱ ካዲላክ መኪናዎች» ማንም ሊጎበኛቸው የሚፈልጋቸው መሆኑ በተዋበ አማርኛ መገለፁ ጭራሽ መንግሎ ሊጥለው ምንም አልቀረው።
 ምንም ሥራ ሳይሠራ አንድ ግጥም እና አንድ ቪዲዮ ካርበደበደው ጎሰኝነትን አንፈልግም የምንል ዜጎች በሙሉ ሆ ብለን ብንነሣ ምን ይውጠው ይሆን? ይህ ነገር ለራሳቸው ለጠ/ሚኒስትሩ ጥሩ አስተማሪ ይመስለኛል። ኢትዮጵያዊነት ከአንድ ምርጫ ዘመን በላይም መከታ መሆን የሚችል አይዲዎሎጂ ነው።
መልካም ሰንበተ ጢና (ትንሿ ሰንበት ይላታል ቀዳሚትን የሸዋ ኦሮሞ)
Filed in: Amharic