>

“መንግስት ለፈሰሰው ደም ይጠየቃል!” (ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ)

“መንግስት ለፈሰሰው ደም ይጠየቃል!”
ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ
*  “ኢሕአዲግ ግብሩን እና አሰተሳሰቡን ሳይቀየር ስሙን በመቀየር ብቻ ኢትዮጵያዊያንን ማታለል አይችልም!!!” 
ዛሬ በግሸን ደብረ ከርቤ እየተከበረ ባለው የእመቤታችን አመታዊ ክብረ በዓል ላይ ከ3000የሚበልጡ አውቶብሶሽ በሚሊዮን የሚቆጠር ኦርቶዶክሳዊያንን  ወደ አምባሰል ተራራ ሲያመላልሱ ሰንብተዋል። በስፍራው ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የተሰባሰቡ 3ሚሊዮን ገደማ ኦርቶዶክሳዊያን የተገኙ ሲሆን የሰሜን ወሎ ሃገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የሆኑን ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ ለህዝቡ እና ለመንግስት መልዕክት አስተላልፈዋል። ህዝቡ በእምነቱ እንዲጸና እና ቤተክርስቲያኑን ከጥቃት እንዲጠብቅ ያሳሰቡት አቡነ ኤርሚያስ መንስግት ስብከቱን አቁሞ የመንስግስትነት ስራውን እንዲሰራ አሳስበዋል።
ይሄ መንግስት አሉ ብጹዕ አባታችን እንዲያውም በስሙ ልጥራው ብለው “ኢሕአዲግ ስሙን ሳይሆን ግብሩን ቢቀይር ይሻለዋል።” ብለዋል። ብጹእነታቸው “ኢሕአዲግ ግብሩን እና አሰተሳሰቡን ሳይቀየር ስሙን በመቀየር ብቻ ኢትዮጵያዊያንን ማታለል አይችልም።” በማለት የተሻለ ለመስራት ስራውን እና አስተሳሰቡን በተሻለ መቀየር እንጅ ስም መቀየር ፋይዳ እንደሌለው ተናግረዋል።
ይህን ማድረግ ካልቻለ ሃገር ማስተዳዳር አልቻልኩም ብሎ ቦታውን ለሚችል ይልቀቅ ያሉት ብጹዕነታቸው “መንግስት ህዝቡን የመጠበቅ ግዴታ አለበት። ስራው ነው። ይህን አላውቅም ማለት አይችልም።”ብለዋል።  የሰሜን ወሎ ሃገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ ይቀጥላሉ። “ኢህአዴግ ስም በመቀየር አገር አያቀናም። ነውሩን ማረም እና ስራውን ማቃናት አለበት። ቤተክርስቲያናችን ያለፈው ጥቃት እና መከራ ይበቃታል።” በማለት አሳስበዋል።
ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ “መንግስት በጀት መድቦ፣ስትራቴጅ ቀይሶ፣ እና ቤተክርስቲያንን የሚያቃጥሉ አሰልጥኖ ምዕመናንን እያሳረደ ነው። ሱማሌ ላይ እና ሲዳማ ላይ ለፈሰሰው የኦርቶዶክሳዊያን ደም መንግስት ተጠያቂ ነው። ከዚህ ተጠያቂነት አያመልጥም። እግዚአብሄር ለፈሰሰው ደም ዋጋ ያስከፍላል።” በማለት መንግስት ስብከቱን አቁሞ ስራውን ብቻ እንዲሰራ እና ከተዋህዶ ላይ የጥፋት እጁን እንዲያነሳ ጥሪ አስተላልፈዋል።
Filed in: Amharic