>

ፖለቲካዊ ሃይማኖት/ዋቄፈታ እና ኢሬቻ!!! (ቀሲስ ደጀኔ ሽፈራው)

ፖለቲካዊ ሃይማኖት/ዋቄፈታ እና ኢሬቻ!!!
ቀሲስ ደጀኔ ሽፈራው
የማናውቀው ዋቄፈታ ክርስቶስን ሊረታ የእርሱም የፖለቲካ ሐዋርያት የክርስቶስን ሐዋርያት ድል ሊያደርጉ አይችሉም!!! ልክ እንደ አክአብ ዘመን ለጊዜው ክርስትናን ቢረብሹትም የኋላ የኋላ ልክ እንደዚያን ጊዜው እግዚአብሔር ሲዞርባቸው የሚታደግ አይኖርም!!!
በመጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸው ከምናገኛቸው ታሪኮች መካከል አንዱ ፖለቲካዊ ሃይማኖትን የሚመለከተው ታሪክ ነው።
አሥራ ሁለቱ ነገደ እሥራኤል ከሁለት ከተከፈሉ በኋላ ኢየሩሳሌም የደቡብ እሥራኤል መንግሥት መቀመጫ ስትሆን ሰማርያ ደግሞ የሰሜን እሥራኤል መንግሥት መቀመጫ ሆነች። ስያሜያቸውም የደቡቡ የይሁዳ መንግሥት ሲባል የሰሜኑ ደግሞ የእሥራኤል መንግሥት ተባለ። መጽሐፍ ቅዱሱ የእሥራኤል ንጉሥ የይሁዳ ንጉሥ እያለ በሰፊው የሚናገረው ይህንኑ ሁለትነት ነው።
ከልዩነት በኋላ ለእሥራኤል መንግሥት ትልቅ ሥጋት ታየው። ይኸውም ሁሉም ሕዝብ እግዚአብሔርን ስለሚያመልክ በፖለቲካ የለዩት ሕዝብ በቤተ መቅደስ ይገናኛል። ይህ ደግሞ ውሎ አድሮም ቢሆን አንድ መንግሥት የመሆን እድል እንደሚያመጣ ታያቸው። አንድ መንግሥት የሚሆኑ ከሆነ ደግሞ የይሁዳው መንግሥት ሊጠቀልል ይችላል ብለው ይሰጉ ነበር። በዚህ ሥጋታቸው ምክንያት ሕዝቡን ለዘላለም ለያይተው ሥልጣናቸውን ለማደላደል ሲሉ ብቻ ሰማርያን ማዕከል ያደረገውና ከዐሥራ ሁለቱ ነገድ መካከል ዐሥሩን ነገድ የያዘው የሰሜን እሥራኤል መንግሥት አዲስ ለፖለቲካው የሚመችና ከወገኖቻቸው ከሁለቱ ነገድ የሚለይ የጣዖት አምልኮን ማስፋፋት ተያያዙት።
ጣዖት የሚያመልኩ ከሆነ እግዚአብሔርን ከሚያመልኩ ከሁለቱ ነገድ ጋር የሚያገናኘው የኢየሩሳሌም ጉዞም ይሠረዛልና።
አብዛኛዎቹ የእሥራኤል (የዐሥሩ ነገድ) ነገሥታት ይህን ፖለቲካዊ ሃይማኖት ብዙ ደክመውበታል።
በርግጥ በዚህ ተግባሩ በጣም ጎልቶ የሚታወቀው የኤልዛቤል ባል አክአብ ነው። የእርሱ ለየት የሚያደርገው ሀሳቡን በቀላሉ ለማሳካት ነቢያተ እግዚአብሔርን በሙሉ አስገድሎ የጣዖት ካህናትንና ነቢያትን አስፋፍቶ አዲሱን ፓለቲካዊ ሃይማኖቱን መሠረት አስይዞ ሥልጣኑን ለማደላደል ነበር።
 መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ግን እነዚያ ሁሉ ደከሙ እንጂ አልተሳካላቸውም።
ዛሬ በኢትዮጵያም ያለው ልክ የአክአብን ዘመን ይመስላል። የመስቀል በዐልን በመንግሥታዊ ሥልጣን አዳክሞ ኢሬቻን በመንግሥታዊ ጉልበት መተካት። መስቀል አደባባይን የኢሬቻ አደባባይ ለማድረግ መሯሯጥ። ኦሮሞን ከሌላው አንድ የሚያድረገውን ክርስትናን እያዳከሙ የሚለያየውን ዋቄ ፈታ የተባለ እምነት ማስፋፋት። ይህ ሁሉ ከብዙ ምክር ጋር በመንግሥት ጉልበት (በጀትና ሥልጣን) ሲደከምለት ሳይ በእጅጉ ይገርመኛል።
ነገር ግን ይህም እንደ ጥንቱ አይሳካም። የማናውቀው ዋቄፈታ ክርስቶስን ሊረታ የእርሱም የፖለቲካ ሐዋርያት የክርስቶስን ሐዋርያት ድል ሊያደርጉ አይችሉም። ልክ እንደ አክአብ ዘመን ለጊዜው ክርስትናን ቢረብሹትም የኋላ የኋላ ልክ እንደዚያን ጊዜው እግዚአብሔር ሲዞርባቸው የሚታደግ አይኖርም። ሕዝቡም ተለያይቶ አይለያይም። ትርፉ ትዝብት ብቻ ነው።
ፓለቲካዊ ሃይማኖት ዋቄፈታን በማስፋፋት የምትደክም ኦርቶዶክስ የለችም። ጥንቱንም ኦርቶዶክስ እንደ ፓርቲ በፖለቲከኞች አልተገነባችምና አያሳስበንም። የሚያሳስበን ነገር ቢኖር የእናንተ መጨረሻ ብቻ ነው። እንደ አክአብ ዘመን ካለ መቅሰፍት ጠብቆ ለንስሐ ያብቃችሁ።
አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው።
Filed in: Amharic