>

የተሰባሪ ሰባሪ ልብ የሚሰብር ትርክት!!! (በፍቃዱ ዘ ሀይሉ)

የተሰባሪ ሰባሪ ልብ የሚሰብር ትርክት!!!
በፍቃዱ ዘ ሀይሉ
በ2009 – አስፈሪውና አሰቃቂው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲወጣ በተገኘው መንገድ ሁሉ በአደባባይ ከተቃወሙት ሰዎች አንዱ ነበርኩ። በዚህም ሳቢያ ታስሬ ነበር። ታዲያ ከሌሎች 200 በላይ ከሆኑ የአዲስ አበባ እስረኞች ጋር ወደ አዋሽ ሰባት ወታደራዊ ካምፕ ተጉዤ ነበር። እዚያም ከአንድ ሺሕ በላይ ከኦሮሚያ የታፈሱ ወጣቶች ጋር ተደመርን።
አዋሽ ሰባት ካምፕ ውስጥ ያገኘኋቸው ወጣቶች ላይ ያየሁት የስቃይ እና የተስፋ ማጣት ምሥል ዛሬም ድረስ ከሕሊናዬ አልጠፋም። እንደተፈታሁ አዲስ ስታንዳርድ ላይ በጻፍኩት ጽሑፍ አንድ አብሮን የነበረ እስረኛ “የኩንታ ኩንቴ ፊልም ነው የመሰለኝ” ማለቱን መጻፌ ይታወሳል። እነዚያ ወጣቶች የግፍ በትር እየተቀበሉ በነበረበት በዚያ አሳዛኝ ወቅት የዛሬው የኦሮሚያ [ምክትል] ፕሬዚደንት ሽመልስ አብዲሳ የትሕነግ በትር የነበረው የኦሕዴድ ባለሥልጣን ነበሩ።
ነገሮች ተገላብጠው ዛሬ የትሕነግን ቦታ ኦሕዴድ/ኦዴፓ ተረክቧል። እሽቅድምድሙም ትሕነግን ለመተካት እንጂ ዜጎችን በነጻነት እና በክብር እንዲኖሩ ለማድረግ አይመስልም፤ ይልቁንም የበቀል እና የበላይነትን የማረጋገጥ “ጊዜው አሁን ነው” የተባለ ይመስላል። ለሌሎች ጥላቻን መግለጽ የሚያኮራ አርበኝነት ሆኗል። ስለዚህ የበለጠ ጠዪ ለመምሰል ፉክክር አለ። ለዚህ ጽሑፍ መነሻዬ የኦሮሚያ ምክትል ፕሬዚደንት የኢሬቻን አከባበር አስመልክተው ያደረጉት ንግግር ቢሆንም፥ ብሶቱ ግን የተጠራቀመ ነው። የፖለቲካ ሒደቱ ለእበላባዮች ያጋደለ መሆኑን ፍንትው አድርጎ በሚያሳይ ሁኔታ፥ ዜጎች በግፍ ሲሰቃዩ አንድ ቃል ተናግረው የማያውቁት ሽመልስ አብዲሳ፣ በዜጎች ትግል የተገኘ ድል እና ዕድል ላይ የበቀል መፈክር ማሰማታቸው በጣም ‘ገዳይም እኛ፣ ሟቾችም እኛ’ ነገር ነው።
በአዋሽ ሰባት ያገኘኋቸው ወጣቶች ባብዛኛው በቂ የትምህርት ዕድል ያላገኙ፣ ሥራ የሌላቸው እና ስለፖለቲካውም ጥልቅ ዕውቀት የሌላቸው ነበሩ። እንዲሁ እንደማንኛውም ሰብኣዊ ነጻነቱን እና ክብሩን እንደሚሻ፣ በፖለቲካ ስርዓቱ እንደተማረረ ሰው ነው አደባባይ ወጥተው የፖሊስ ራት የሆኑት። የነርሱ ስብራት የሚጠገነው “እንደሰበሩን ሰብረናቸዋል” በሚል ፉከራ ሳይሆን በተግባር የጠቀስኳቸውን ችግሮቻቸውን ለመቅረፍ ርብርብ ለማድረግ በመሞከር ነበር። በተደጋጋሚ “ጭቆናን መቃወም እና ተረኛ ጨቋኝ” ለመሆን መመኘት/መታገል ለየቅል ናቸው ሲባል የነበረው ይኸው ነው። ኢሬቻ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ አካል የሆነው የኦሮሞ ሕዝብ የሚያከብረው በዓል ነው። በአዲስ አበባ መከበሩ ቢያስደስት እንጂ የሚያስከፋ አንዳችም ነገር የለውም። ነገር ግን የኀይል ሚዛን ማሳያ እና ሌሎች ላይ የተሸናፊነት ስሜት ለመፍጠር መሸለያ ሲደረግ ግን እምነትም፣ ባሕልም መሆኑ ቀርቶ፥ የእበላባይ ፖለቲከኞች መጠቀሚያም ያደርገዋል፤ በዓሉን የማያከብሩትም ባሕላዊ እና እምነታዊ እሴቱን ሳይሆን ፖለቲካዊ ይዘቱን ብቻ ተመልክተው እንዲጠሉት ያደርጋል።
የብሔርተኞች “የኀይል ሚዛን” ማሳየት እና ትከሻ መለካካት እውነተኛውን መስዋዕትነት ለከፈሉት እንዲሁም በየዋሕነት እና በስሜት እጃቸውን አጣምረው አደባባይ ለሚወጡት ወጣቶች አንድም የሚያፈራላቸው ፍሬ የለም። ባሳለፍነው ሁለት ዓመት የእከሌ ብሔርተኞች የእከሌን ክልል መንግሥት፣ የእከሌዎቹ ደግሞ የእከሌን ክልል መንግሥት በጫጫታቸው ብዛት እያስገበሩ በፉክክር ብዛት ኢትዮጵያን ሊያፈርስ እና አልፎ ተርፎም ሁሉንም ክልሎች እና ቢያንስ አንድ ትውልድ ለዕልቂት ሊዳርግ በሚችል ድራማቸው የሚጫወቱት ምስኪኑን ወጣት ተማምነው ነው። ድራማው ሲያልቅ ከሞት የተረፉት ወጣቶች የሚያተርፉት ነገር ቢኖር ፀፀት ብቻ ነው። ልኂቃኑ ወይ ይሸሹና ወደሚመቻቸው ከተማ ይሔዳሉ/ይመለሳሉ አልያም ያተረፉትን ሥልጣናቸውን መከታ አድርገው ይኖራሉ።
ክልሎች “የሌሎች” ብሔረሰቦች እስር ቤት
ኢትዮጵያ በብሔርም ይሁን ብሔር ዘለል ማንነቶች (ለምሳሌ ፆታ) በርካታ ግፎችና መድልዖዎች ሲፈፀሙባት የኖረች እና ያለች አገር ነች። ሆኖም ብሔርተኝነት ላንዳቸውም መልስ አያስገኝላቸውም። ለዚህም አሁን እያየነው ካለነው የፖለቲካ ጫወታ የበለጠ ምስክር የለም። የብሔር ማንነት ጥያቄዎች በቋንቋ የመማር፣ የመሥራት እና አገልግሎት የማግኘት፤ ባሕልን የመተግበር እና የማሳደግ፤ እምነትን በነጻነት መከተል እና ማስፋፋትን የሚያካትት ነገር ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ማንነት ጭቆናዎች ነበሩ ሊያስብሉ የሚያስችሉ ብዙ ታሪካዊ እና ነባራዊ ምክንያቶች አሉ። ነገር ግን ተበዳይነቱን ወይም በዳይነቱን ለአንድ ብሔር ብቻ ጠቅልሎ መስጠት አግባብ አይደለም። ብሔርተኝነት መፍትሔ የማይሆንበትም ምክንያት ይህ ነው። አሁን የተዘረጋው የፌዴራል ስርዓትም ቢሆን በሒደት ያፈራው ብሔርተኝነት የማንነት ጭቆና ለመቅረፍ ተብሎ ቢደረግም አሁን የተሸጋገርነው ከኢትዮጵያ ጭቆና ወደ ክልሎች ጭቆና ነው። ዛሬ ክልሎች በዚያ ክልል ውስጥ ብዙኀን ከሆኑት ብሔረሰቦች ውጪ ላሉ ሰዎች እስር ቤት ናቸው።
የክልሎቹ መሪዎችም በእኩልነት መርሕ ሳይሆን በበላይነት ቅዠት የሚነዱ፣ የዜጎችን ሕጋዊ እና ሰብኣዊ መብቶች እና ክብሮች ከልባቸው የማይቀበሉ፣ የአመራር ድክመታቸውን በብሔርተኝነት የሚሸፍኑ እና ለመጪው ትውልድ ቂምና በቀል የሚያወርሱ ናቸው።
Tyranny of the Nationalists (የብሔርተኞች ጨቋኝነት)
ከሁለት ዓመት በፊት ጨቋኝ መንግሥት ነበር። አሁንም መንግሥታዊ ጭቆና ሙሉ ለሙሉ አልቀረም። እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ግን፣ በተለይ ከአዲስ አበባ ውጪ (95% ኢትዮጵያውያን የሚኖሩበት ማለት ነው) ያሉት ትልልቅ ጨቋኝ አካላት ብሔርተኞች ናቸው። መደራጀትን፣ ሕዝባዊ ስብሰባን እና ግላዊ ነጻነትን ሳይቀር የሚገፍፉት፣ አንዳንዴ ፈራጅ እና ቀጪዎች ብሔርተኞች ናቸው። የመንግሥትን ጭቆና ተደራጅተው ይታገሉታል፤ ሕዝብ ውስጥ ተሸሽገው ያመልጡታል። ሕዝብን እንደ አርማ ለብሰው “ሌሎችን” የሚረግጡ ብሔርተኞችን ግን እንዴት እንደሚታገሏቸው፣ የት ተሸሽገው እንደሚያመልጧቸው ግራ ይገባል። የበለጠ የሚያሳዝነው ደግሞ እነዚህ ብሔርተኞች የየክልል መንግሥታቱን እጅ መጠምዘዝ መቻላቸው ነው። መንግሥት ነው እንዳይባል ሕዝብ ውስጥ የተሸሸጉ እና የብሔር ጥያቄን የለበሱ አታላዮች ናቸው፤ ግለሰቦች ናቸው እንዳይባል የመንግሥት መዋቅርን የመጠቀም አቅም አላቸው። የብሔርተኞች ጭቆና ከመንግሥትም ጭቆና የባሰ ሆኗል።
መውጫ የሚፈልግ ካለ!
በርግጥ ጥላቻ፣ ጥርጣሬ እና እበላባይነት በገነነበት የፖለቲካ ሒደት ውስጥ መፍትሔው ቢታወቅም ፈላጊ የለውም። ለዓመታት ሰብኣዊ ነጻነትም ይሁን ክብር ለአንድ ወገን ተሰጥቶ ለሌላው አይነፈግም። ወይ አብረን ነጻ እንሆናለን፣ አልያም አብረን እንሰቃያለን ሲባል ተኑሯል። ነገር ግን ይህ ለጆሮ አይጥምም፤ ጥላቻ ከፍቅር የተሻለ እየማረከ ነው። ከሁሉም ሰው ባለድልነት ይልቅ በአንዱ ሽንፈት ሌላኛው ይለፍለት የሚለው መርሕ ነው ብዙዎችን የሚያፋጀው። ተወደደም ተጠላም መፍትሔው ትብብር ነው። “ከኛ ወዲያ” የሚሉ ብሔርተኞች ጦርነት ይደግሱ ይሆናል እንጂ የሚመኙትን በዚህ ጊዜ አያገኙትም። ስለዚህ ዜጎች በዜግነታቸው ነጻነታቸው የሚከበርበት፣ ሰላማቸው የሚጠበቅበት የጋራ አገር ውስጥ ተቻችሎ መኖር ይሻላል። ከዚህ ውጪ ሁሉ ያለው መፍጨርጨር አብሮ ለመጥፋት ብቻ ነው።
Filed in: Amharic